የኢፌዴሪ ህገ መንግስት የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች የቃል ኪዳን ሰነድ መሆኑን በመግቢያው አስፍሯል። ይህ የሚያመለክተው ኢትዮጵያ የብዝህነት ሃገር መሆኗን ነው። የበርካታ ቋንቋ፣ ባህል፣ እምነት ሀገር መሆኗንም በማስረገጥ ለሁሉም እኩል እውቅና ይሠጣል።
ስለሆነም ሁሉም ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቋንቋቸው፣ ባህላቸውና እምነታቸውን በነጻነት የማራመድና የማሳደግ መብት አላቸው ማለት ነው። ይህን መብታቸውን እውን የሚያደርጉት በክልላቸው ብቻ ሳይሆን በሚኖሩበት በየትኛውም አካባቢም ጭምር መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡
በተለይ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ከሁሉም የሀገራችን ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ይገኙበታል። ስለሆነም ሁሉም በቋንቋቸው፣ በባህላቸውና በእምነታቸው የሚኮሩ መሆን አለባቸው። ለዚህ ደግሞ በተለይ ከበዓላት ጋር ተያይዞ አስተዳደሩ ዘንድሮ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑ ይታወቃል። ይህ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው፡፡
ሰሞኑን የሰሜን ኢትዮጵያ ህዝቦች በተለይ በትግራይና አማራ ክልሎች የሚከበረውን የልጃገረዶች በዓል (የአሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድየ፣ ሶለል፣ ዓይኒ ዋሪና ማርያ) ከክልሎቹ ውጪ በአዲስ አበባ እንዲከበሩ መደረጉ እንዲሁም በቀጣይ የኢሬቻ በዓል በከተማዋ ለማክበር መታቀዱ አስተዳደሩ የከተማዋን ብዝሀ ባህል በመገንዘብ የወሰነው በመሆኑ የሚያስመሰግነው ነው፡፡
የእነዚህ በዓላት በከተማዋ መከበር የነዋሪዎቹን አንድነት ከማጠናከር ባለፈ ህገ መንግስታዊ መብታቸውንም ማክበር ነው። ሕዝቦችን በማቀራረብም ለሰላምና ልማት በጋራና በአንድነት እንዲሰለፉም ያስችላል፡፡
ዛሬና ባለፈው ሳምንት በሚሊኒም አዳራሽ የተከበሩት የሰሜን ኢትዮጵያ ልጃገረዶች በዓል ምንም እንኳን መሰረታቸው ሃይማኖታዊ ቢሆንም ባህላዊም በዓላት ናቸው። ልጃገረዶች በአንድነትና በሰላም የሚያከብሯቸው ናቸው። የነጻነት በዓልም ነው። በመሆኑም እነዚህን በዓላት በከተማዋ ማክበር የከተማዋን ነዋሪዎች እርስ በእርስ የባህል ልውውጥ እንዲያደርጉም ያስችላል። አብሮነትንና መከባበርን ያጎለብታል።
ከተማዋም ብዝህነትን በተግባር የምታከብር መሆኗንም ማረጋገጫ ነው። ስለሆነም የከተማዋ ነዋሪዎች አብሮነት በማጎልበት ረገድ የከተማ አስተዳደሩ ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑንም ማረጋገጫ ነው፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መበራከታቸው ግልጽ ነው። ይህ የሆነው ብዝህነትን ማስተናገድ የማይሹ ፖለቲከኞች በፈጠሩት ችግር መሆኑም ይታወቃል። መላው የሀገራችን ህዝቦች በየትኛውም ክልል የመኖር፣ ተንቀሳቅሶ ሀብት የማፍራት መብታቸው ተገፎ ለመፈናቀል መዳረጋቸው ተገቢ አይደለም። አሳፋሪም ነው። እንኳን ሊፈናቀሉ ባህላቸውንም በዓላቸውንም የሚያከብሩበት ሁኔታ ማመቻቸት ይገባ ነበር። ግን አልሆነም። ስለዚህ መወገዝም አለበት፡፡
በሁሉም የሀገራችን ክልሎች ብዝህነት አለ። በየክልሉ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ አመራሮችና የህብረተሰብ ክፍሎች ይህን ብዝህነት ተገንዝበው መስራት አለባቸው። ማክበርና ማስከበርም አለባቸው። ሀገራችን ለሁላችን ትበቃለች። ዋናው ጉዳይ ይህንን አውቆ በጥበብና እውቀት መምራት ነው።
በህዝቦች መካከል መቼም ቢሆን ጠብ የለም። ግጭትም የለም። የግጭት መሰረቱ የፖለቲካ እውቀት አለኝ የሚለው ሃይል ነው። ስለሆነም ይህ አካሄድ ስለማይጠቅም መታረም አለበት። ከአዲስ አበባ አስተዳደር ትምህርት መውሰድ ይገባል፡፡
የአዲስ አበባ አስተዳደር ዘንድሮ የሰራው በዓላትን በከተማዋ የማክበር ስራ ህዝቦች ባህላቸውን እንዲያስተዋውቁ፣ እንዲተዋወቁ የሚያደርግ ነው። አንድነታቸውን ጠንካራ የማድረግ ስራ ነው። ስለዚህ ሌሎች ክልሎችም በተለይ ደግሞ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት የተፈናቀሉባቸው ከዚህ ትምህርት ሊወስዱ ይገባል። ብዝህነት ማስተናገድ አለባቸውና፡፡
የአዲስ አበባ አስተዳደር የሰሜን ኢትዮጵያ ልጃገረዶች ድጋፍ አድርጎ በዓል በከተማዋ እንዲከበር መወሰኑ፣ በቀጣይ የኢሬቻን በዓል ለማክበር ዝግጅት እያደረገ መሆኑ የሚያስመሰግን ነው። እነዚህ በዓላት የከተማዋን ህዝቦች በማቀራረብ አስተዳደሩ ለሚሰራቸው የልማት፣ የሰላምና የመልካም አስተዳደር ስራዎች በአንድነት በአንድ ዓላማ ለማሰለፍ አቅም ይፈጥራል። ህገ መንግስታዊ ድንጋጌም ማክበር ነው፡፡
እንደ ከተማ አስተዳደሩ አዲስ አበባ የብዝሃነት ከተማ መሆኗን ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል። የሁሉም የከተማዋ ነዋሪዎች ባህል ለከተማዋ ጌጥ ነው። ውበት ነው። ድምቀት ነው። ስለዚህ ብዝሃነትን የማክበርና የማስከበር አስተሳሰብ በማጎልበት ረገድ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል። አዲስ አበባ የብዝሃነት ከተማ ናትና፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 26/2011