የበጎ ሰው ሽልማት በ2005 ዓ.ም ነው የተጀመረው። ዘንድሮ 7ኛ ዓመቱ ነው። በኪነ ጥበብ ዘርፍ የነበሩ ተሸላሚዎችን ለማስታወስ መረጃዎችን ስናገላብጥ የኪነ ጥበብ ዘርፍ የተጀመረው በ2006 ዓ.ም ነው። ዘንድሮ 6ኛ ዓመቱ ማለት ነው። ራሱን ችሎ ዘርፍ ባይሆንም ግን በኪነ ጥበብ ውስጥ ያሉ ሰዎች ተሸልመዋል።
እግረ መንገድ ለማስታወስ ያህል፤ የበጎ ሰው ሽልማት በ2005 ዓ.ም ሲጀመር ዘርፎቹም አምስት ነበሩ። «የወጣቱን የንባብ ባህል በማሳደግ» በሚለው ዘርፍ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ተሸላሚ ነበር። እንዳለጌታ ከበደ ደራሲ ነው፤ የንባብ ባህልን ማሳደግም ጥበብ ነው። ስለዚህ የኪነ ጥበብ ዘርፉ በተዘዋዋሪ ነበረበት ማለት ነው። በሚዲያ የሴቶች አስተዋፅዖ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ፣ በማህበራዊ አገልግሎት የመቄዶንያ መሥራች ቢኒያም በለጠ፣ በኢኮኖሚ መስክ ዶክተር እሌኒ ገብረመድኅን፣ በትምህርት መስክ፣ ንቡረ ዕድ ተፈራ መልሴ ተሸላሚዎች ነበሩ።
ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ኪነ ጥበብ ራሱን ችሎ ዘርፍ ሆኗል። ዘንድሮ 6ኛ ዓመቱ ቢሆንም ዛሬ ልናስተዋውቃችሁ የምንችለው አምስቱን ነው። ስድስተኛውን ነገ እናውቀዋለን።
- ተስፋዬ ሳህሉ (አባባ ተስፋዬ)
በ2006 ዓ.ም በተደረገው ሁለተኛው ዙር የበጎ ሰው ሽልማት «አባባ ተስፋዬ» በመባል የሚታወቁት የተረት አባት ተስፋዬ ሳህሉ ተሸላሚ ነበሩ።
አርቲስት ተስፋዬ ሳህሉ በቀድሞው ባሌ ክፍለ ሀገር ልዩ ስሙ ከዱ በተሰኘ ስፍራ ከአባታቸው ኤጀርሳ በዳኔ እና ከእናታቸው ዮንዢ ወርቅ በለጤ ሰኔ 20 ቀን 1916 ዓ.ም ተወለዱ። ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም ጎባ ከተማ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን መከታተል ጀመሩ። ቤተሰባቸው በሥራ ምክንያት ወደ ጊንር በመቀየራቸው ትምህርታቸውን በጊንር ቀጠሉ። በመቀጠል ወደ ሐረር ሄዱ። ሐረር የፈረንሳዮች ትምህርት ቤት ገብተው ተማሩ፣ ለተወሰኑ ዓመታት ሐረር ከኖሩ በኋላ በ14 ዓመታቸው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።
የፋሽስት ጣልያን መንግሥት ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት በርካታ ሰዎችን ረሽኗል። ከረሸናቸው ሰዎች መካከል የእሳቸው እናትና አባት ይገኙበታል።
በጣልያን ወረራ ወቅት በልጅነታቸው ከቤተሰቦቻቸውና ከአካባቢያቸው በቀሰሙት የሽለላ፣ ቀረርቶና መሰል ትውፊታዊ ክዋኔዎች እና በውስጣቸው በነበረው የኪነ ጥበብ ፍቅር እንዲሁም ፍላጎት አማካኝነት ወደ ሙያው ተቀላቀሉ።
ገና በልጅነታቸው እናትና አባታቸውን ያጡት አባባ ተስፋዬ ለከፍተኛ የሕይወት ፈተና የተጋለጡ ቢሆንም ያጋጠማቸውን የሕይወት ፈተና ተቋቁመው በአገራችን አንቱ ለመባል በቅተዋል።
ጥቅምት 23 ቀን 1957 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲቋቋም የልጆች ጊዜ የተሰኝ ፕሮግራም እንዲኖር ሀሳቡን አቅርቦ በማፀደቅ የራሳቸውን የአቀራረብ መንገድና የፈጠራ ችሎታ በመጠቀም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያስተዋወቃቸውን ዝግጅታቸውን ለ42 ዓመታት በአባትነት አገልግለዋል። ፕሮግራማቸውን ሲጀምሩ «ጤና ይስጥልኝ ልጆች! … የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች እንደምናችሁ ልጆች !» እያሉ አቅርበዋል።
አባባ ተስፋዬ ሴት ሆነው ሲጫወቱ ገፀ ቅባቸውን የሚሠሩት እራሣቸው ነበሩ። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ለ36 ዓመታት ያገለገሉት አባባ ተስፋዬ በ1973 ዓ.ም በጡረታ ተገለሉ። ሆኖም በቴአትሩ አይቀጥሉበት እንጂ በልጆች ክፍለ ጊዜ ለረጅም ዓመታት ለአገር እና ለሕዝብ ሠርተዋል።
ደቡብ ኮሪያ በተወረረችበት ወቅት ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል በመሆኗ በቀረበላት ጥሪ ወቅት የክቡር ዘበኛ ቃኘው ሻለቃ አባል በመሆን ከ1944 እስከ 1945 በ2ኛ ቃኘው ሻለቃ ለ2ኛ ጊዜ ከሄደው ሠራዊት ጋር ደግሞ ከ1946 እስከ 1947 በ4ኛ ቃኘው ሻለቃ ለሁለት ጊዜ የወታደራዊ ሳይንስ ተዋናይ በመሆን ሠራዊቱን አገልግለው ለዚሁም የሃምሳ አለቃነት ማዕረግ አግኝተዋል።
ከተሰጣቸው ሜዳልያዎች መካከል ጥቂቶቹ፤ የቅዱስ ጊዮርጊስ የጦር ሜዳ ሜዳሊያ (ባለ አንድ ዘንባባ) ከኢትዮጵያ መንግሥት፣ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የወርቅ ሜዳልያ ከኢትዮጵያ መንግሥት፣ ዩኒየን ሣይቴሽን ከአሜሪካ መንግሥት ተሸልመዋል።
2. ሠዓሊ ታደሰ መስፍን
የ2007 ዓ.ም ሦስተኛው ዙር ተሸላሚ ነው። ሰዓሊ ታደሰ መስፍን በ1945 ዓ.ም በወልዲያ ተወለደ። ከእረኝነቱ ጀምሮ እጅና እግሩ ላይ በእንጨት በመሞንጨር ሥዕልን የጀመረው አዳጊው ምንም እንኳን ዝንባሌው ወደ ሥዕል ማጋደሉን ከልጅነቱ ቢረዳም መደበኛ ትምህርቱን ከመከታተል ወደ ኋላ አላለም። በዚሁ መሠረት በዕቴጌ ጣይቱ ብጡል ት/ቤት መደበኛ ትምህርቱን ጀምሮ ነበር። ይሁን እንጂ የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት ቆይታውን እንዳጠናቀቀ የ6 ዓመቱ ታዳጊ ከአጎቱ ጋር ለመኖር ወደ አዲስ አበባ መጣ።
አዲስ አበባ ከመጣ በኋላም በስዊዲሽ ሚሽን ት/ቤት ገብቶ መደበኛ ትምህርቱን በማጠናቀቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በበዕደ ማርያም ትምህርት ቤት አጠናቀቀ። ከመደበኛ ትምህርቱ ጎን ለጎን ግን በትምህርት ቤቱ ውስጥ ለሚዘጋጀው መጽሔት «ኢሉስትሬሽን» የውጭ ሽፋን የመሳሰሉትን ይሰራ ነበር።
ሰዓሊ የመሆን ጥልቅ ፍላጎትና ችሎታ ስለነበረው በ1960 ዓ.ም ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ገባ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ቆይታው ታዋቂው ሰዓሊ ገብረክርስቶስ ደስታ አስተምሮታል።
ለተጨማሪ ከፍተኛ ትምህርት ወደ ራሽያ ሀገር በማቅናት በሴንት ፒተርስበርግ ከተማ በሚገኘው ሬፒን አካዳሚ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን ለመከታተል የቻለ ሲሆን በዚህ ተቋም በነበረው ቆይታ ከራሽያ ተማሪዎችም ሆነ ከሌላ አገር ከሄዱት ተማሪዎች እጅግ የላቀ ብቃት አሳይቷል። በዚህም ልዩ ብቃቱ በአካዳሚው ታሪክ የመጀመሪያው የውጭ አገር ዜጋ የክብር ተሸላሚ በመሆን ማስተርሱን ይዞ ወደ አገሩ ተመለሰ።
በደርግ ጊዜ በየጊዜው ለብሔራዊ ግዴታ በሚሉ እና በሌሎችም መነሻዎች ምንም ሳይከፈለው በነፃ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ፖስተሮችንና ሥዕሎችን በመስራት፣ የሶሻሊስት ኢትዮጵያ ዓርማን በመቅረፅ፣ ለታላቁ የሕዝብ ለሕዝብ ትዕይንት የሚሆኑ የመድረክ እና የአልባሳት ዲዛይን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በማዘጋጀት፣ እንዲሁም የሀገራችን የመገበያያ ሳንቲሞች (25 ሳንቲም እና 50 ሳንቲም) ላይ የራሱን ሙያዊ አስተዋፅዖ በማድረግ አንጋፋው አስተማሪ እና ሰዓሊ ታደሰ የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ግዴታ ሊወጣ ችሏል።
በተለያዩ ጊዜያት በመንግሥት እና በሌሎችም አካላት ሙያዊ አስተዋጽዖን ሲጠየቅ ወደ ኋላ ብሎ የማያውቀው ሰዓሊው ከደርግ መንግሥት መውደቅ በኋላም በተለያዩ የመታሰቢያ ሥራዎች ላይ ሙያዊ ተሳትፎን አድርጓል። ከቅርብ ጊዜ ሥራዎቹ ውስጥም ትግራይ ላይ ያለውን የሰማዕታት ሐውልት የመጀመሪያውን ንድፍ ያጠናና የፈጠረ እንዲሁም በአማራ የሰማዕታት ሐውልት ሥራ ላይ የበዛ አስተዋፅኦ ያደረገባቸውን መጥቀሱ በቂ ይሆናል።
3.ደራሲ አውግቸው ተረፈ
በ2008 ዓ.ም በተደረገው አራተኛው ዙር የኪነ ጥበብ ዘርፍ ተሸላሚ ደራሲ አውግቸው ተረፈ ናቸው። አውግቸው ተረፈ የኅሩይ ሚናስ የብዕር ስም ነው። በቀድሞው አጠራር ጎጃም ክፍለ ሀገር ቢቸና አውራጃ በ1942 ዓ.ም ተወለዱ። ዋና ትምህርታቸው የቤተ ክህነት ትምህርት ነው። በስማቸው የተጻፉ ጥቂት መጻሕፍት ቢኖሩም በአንባቢያን ዘንድ ጎልተው የወጡት በአውግቸው ተረፈ ስም የተጻፉት ናቸው።
ከፈጠራ ሥራዎቻቸው መካከል፤ «ወይ አዲስ አበባ፣ እብዱ እና የፕሮፌሰሩ ልጆች» የሚሉት ሲሆኑ ከትርጉም ሥራዎቻቸው መካከል ደግሞ፤ «ምስኪኗ ከበርቴ፣ ያንጌት ጌጡ(ከሌሎች ደራሲያን ጋር)፣ ጽኑ ፍቅር፣ ምሥጢራዊቷ ሴት፣ ጩቤው» ሲሆኑ ከኢ ልቦለድ ሥራዎች የትውልድ ዕልቂት ይጠቀሳሉ።
ደራሲ አውግቸው ተረፈ «እብዱ» የሚለው መጽሐፋቸው በአዕምሮ ህክምና ሰጪዎች ስለተወደደ የአማኑኤል ሆስፒታል በስማቸው ሕንፃ ሰይሟል።
4. ተስፋዬ ገሠሠ
በ2009 ዓ.ም የተደረገው አምስተኛው ዙር የኪነ ጥበብ ዘርፍ ተሸላሚ የሆነው ተስፋዬ ገሠሠ የብዙ ጥበብ ባለቤት ነው። ደራሲ፣ ገጣሚ፣ ተርጓሚ፣ መምህርና ጸሐፊ ተውኔት ነው።
ተስፋዬ ገሠሠ መስከረም 17 ቀን 1930 ዓ.ም በሐረር ጉሮ ጉቱ ተወለደ። ቴአትርን የጀመረው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለ ነው። በዚያ እንቅስቃሴውም በስኮላርሺፕ አሜሪካ አገር ሄዷል። ከአሜሪካ ተመልሶ ቴአትርን ከባላባቶች መጫወቻ ወጥቶ እንዲያገለግል አደረገው። በከተማ ሕይወት ላይ ያተኮረውን «የሺ» የተባለውን ቴአትርም አቀረበ። በ1966 ዓ.ም የሀገር ፍቅር ቴአትር ሥራ አስኪያጅ ሆነ። ዳሩ ግን በ1967 ዓ.ም ደርግ ወደ ወህኒ ቤት አስገባው።
የታሰረበት ምክንያትም «ዕቃው» በተሰኘው ቴአትር መንግሥታዊ ሽብርን በመተቸቱ ነው። በ1968 ዓ.ም የብሔራዊ ቴአትር ሠራተኞች ባደረጉት ሰልፍ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመኅን ከብሔራዊ ቴአትር ሥራ አስኪያጅነት ሲነሳ ተስፋዬ ሥራ አስኪያጅ ተደረገ። ከዚያ በኋላም በሚሰራቸው ቴአትሮች እስራት አጋጥሞታል።
በቴአትር ሙያው ከቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ የእጅ ሰዓት ተሸልሟል። በ«ሐምሌት» እና ከ20 በላይ ተውኔቶች ላይ ተጫውቷል። የተለያዩ መጻሕፍትን ጽፏል፤ ተርጉሟል። ከእነዚህም «መተከዣ» የተሰኘው ይጠቀሳል።
5. አበበ ብርሃኔ
ባለፈው ዓመት 2010 ዓ.ም በስድስተኛው ዙር የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚው አበበ ብርሃኔ ነው። አበበ ብርሃኔ የዜማና ግጥም ደራሲ ነው። አበበ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ከታዳጊ ሕፃናት እስከ ከፍተኛ የኪነት ቡድን የሰራ ነው። በትምህርት ቤትም መዝሙር ይደርስ ነበር።
አበበ በ1975 ዓ.ም የሰባተኛ ክፍል ተማሪ እያለ ጎንደር ከተማ ውስጥ የተቋቋመው ፋሲለደስ የኪነት ቡድን ተቀላቀለ። እዚያው ፋሲለደስ የኪነት ቡድን እያለ ለአሰፉ ደባልቄ እና ሰላማዊት ነጋ ዜማና ግጥም ደርሷል።
አበበ አዲስ አበባ በመምጣትም ከሶል ኩኩ የሙዚቃ ባለቤት ከአቶ ሣህለ ጋር በመተዋወቁ፤ በ1980 ዓ.ም የጸጋዬ እሸቱን የመጀመሪያ አልበም «ተከለከለ አሉ» እና «ያየ አለ» ደርሷል። አሰፉ ደባልቄን ከጎንደር በማስመጣትም «ተው ተው የእኔ አካላት» አልበም ላይ ያሉትን ዘፈኖች በሙሉ የደረሳቸው አበበ ብርሃኔ ነው። በዚሁ ዓመትም የየሺመቤት ዱባለን እና የብርቱካን ዱባለን ሥራዎች ሰርቷል።
አበበ ብርሃኔ የበርካታ ድምጻውያን ዜማ ደራሲ ነው። ሁሉንም ከነሥራዎቻቸው መዘርዘር ባይቻልም የጥቂቶችን እንንገራችሁ።
ኬኔዲ መንገሻ፣ ቴዎድሮስ ታደሰ፣ ንጋቱ ዱባለ፣ አበበ ተካ፣ ተፈራ ነጋሽ፣ ወረታው ውበት፣ ገነት ማስረሻ፣ አስናቀ ገብረየስ፣ ፍቅርአዲስ ነቃዓጥበብ፣ ሀብተሚካኤል ደምሴ፣ ማሪቱ ለገሠ፣ ይሁኔ በላይ፣ ማርታ አሻጋሪ፣ ኩኩ ሰብስቤ፣ ውብሸት ፍስሐ፣ ጌታቸው ካሣ፣ ነፃነት መለሰ፣ ሒሩት በቀለ፣ መሀሙድ አህመድ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ ጥላሁን ገሠሠ፣ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ማለፊያ ተካ፣ አዳነ ተካ፣ ጋሻው አዳል፣ ኤፍሬም ታምሩ፣ አለማየሁ እሸቴ፣ ማዲንጎ አፈወርቅ፣ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ አቦነሽ አድነው፣ ፋሲል ደሞዝ፣ ደረጀ ደገፋው፣ በዕውቀቱ ሰውመሆን፣ ተመስገን ታፈሰ፣ ዳዊት ጽጌ፣ ማስተዋል እያዩ ይጠቀሳሉ።
አዘጋጆቹ እንደሚሉት፤ የበጎ ሰው ሽልማት ዋና ዓላማው በጎዎችን በማስተዋወቅ ሌሎች በጎ ሰዎችን መፍጠር ነው። የሰሩትን ሥራ ለሕዝብ ማስተዋወቅ ነው። ለአዘጋጆቹም ለበጎዎቹም በርቱ እንላለን!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሀሴ 25/2011
ዋለልኝ አየለ