በቴክኖሎጂ በተደገፈ የቢዝነስ ሥራ ላይ ተሰማርቶ ውጤታማ መሆን ችሏል። ኢንተርኔትን ተጠቅሞ በርካቶችን የመኪና እና ንብረት ባለቤት ማድረግ ሲችል ለእራሱ ደግሞ ገቢ በመፍጠር እየሰራበት ይገኛል። ማህበራዊ ኃላፊነትን ባልዘነጋው የማህበራዊ ድረገጽ ሥራዎቹም ቢሆን ሥነምግባርን ባልለቀቀ መልኩ ሰርቶ ማትረፉን ተያይዞታል። በወጣትነት ዕድሜው ለሌሎችም ሥራ ከመፍጠሩ በተጨማሪ ልምዱን በማካፈል ረገድ እንደማይሰስት የሚያውቁት ይመሰክራሉ።
ሁልጊዜም ከተንቀሳቃሽ ስልኩ ወይም ከኮምፒዩተሩ ጋር ሲነጋገር የሚውለው ወጣቱ ከዚያ በተረፈ ደግሞ የተለያዩ ተሽከርካሪዎችን ሙሉ መረጃ በመሰብሰብ እና ለፈላጊዎቹ በማሳየት ሥራውን በየቀኑ ይከውናል። ከሰኞ እስከ ሰኞ ሥራ ላይ የሚሆንበት ጊዜ ይበዛል አንዳንዴም ምሽት ላይ ጭምር በኢንተርኔት ግብይቱን በማቀላጠፍ ሁሉም ሰው ባለበት ሆኖ የሚፈልገውን መረጃ እንዲያገኝ እያገዘ ነው።
ይህ በቴክኖሎጂ የተደገፈው ንግዱ ታዲያ አንድ ቀን ልክእንደ አሊባባ እና አማዞን የተሰኙ ስመጥር የኢንተርኔት ግብይት መከወኛ ድረገጾች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደንበኞችን እንደሚያፈራ እና እንደሚያድግ ሙሉ እምነት አለው። አቶ አሉላ ክብሮም ይባላል ሙሉ ስሙ። በአዲስ አበባ ሳር ቤት አካባቢ ነው ተወልዶ ያደገው። ለቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በልጅነቱ ኃላፊነት ያላቸው ጉዳዮች ላይ እንዲሳተፍ ትኩረት አይደረግበትም። በዚህም ምክንያት ከዕኩዮቹ ጋር ሙሉ ጊዜውን በጨዋታ ያሳልፍ እንደነበር አይረሳውም።
ለአቅመ ትምህርት ሲደርስ ደግሞ አንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመከታተል መቅደላ የተሰኘው ትምህርት ቤት ይገባል። ለትምህርት ቅቡል የሆነው አዕምሮው የተሰጠውን ዕውቀት በቶሎ የሚይዝ በመሆኑ በየክፍሉ አንደኛ ይወጣ ነበር። በትምህርት ቆይታው ግን ጎን ለጎን ወደሰዓሊነቱ ያደላበት ወቅት እንደነበር ይናገራል። በተለይ ወደሰባተኛ ክፍል ሲደርስ ክረምት ወቅት ላይ የስዕል ትምህርት ስልጠና በመውሰድ ፍላጎቱን ማዳበር ጀመረ። ከዚያም ስምንተኛ ክፍል እያለ የሥነጥበብ ፍላጎቱን ያናረ አጋጣሚ ተፈጥሮ ሕይወቱን በሰዓሊነት እንደሚመራ ያሰበበት ወቅት አጋጥሞት ነበር።
በወቅቱ አራት ኪሎ የሕፃናትና ወጣቶች ቴያትር ቤት ውስጥ ለአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የቀረበ የስዕል ውድድር እንዳለ ይሰማል። እናም ጊዜ ሳያባክን የዱር እንስሳት በመኖሪያ አካባቢያቸው በተፈጠረ እሳት ምክንያት ሲሰደዱ የሚያሳይ ስዕል ሰርቶ ያቀርባል። በመልዕክቱ አስተማሪነት እና በስዕል ችሎታው የተደሰቱ አወዳዳሪዎች ታዲያ አሉላን አሸናፊ አደረጉት። አሉላ ወደ9ኛ ክፍል ሲያልፍ ግን ሰዓሊነቱንም ጋብ አደረገው። 9ኛ ክፍል ትምህርቱን የቀጠለው ከፍተኛ 23 የተባለው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። በዚያም የሒሳብ ትምህርት ላይ ያለው ፍላጎት ደግሞ ከፍተኛ ሆኗል።
ትምህርቱም ከበድ እያለ ሲሄድ የስዕሉን ጉዳይ ቀነስ አድርጎ ጥናቱ ላይ ያተኩር እንደጀመር ያስታውሳል። አስርን አልፎ ወደፕሪፓራቶሪ ክፍል ሲሸጋገር ደግሞ የተፈጥሮ ሳይንስን ምርጫው በማድረግ 11ኛ እና 12ኛን ክፍል በብቃት ተምሮ አለፈ። በወቅቱ ለሒሳብ ትምህርት ብቻ ሳይሆን ለቴክኖሎጂም ያለው ዕውቀት ከጊዜው ጋር እየጨመረ በመምጣቱ የኮምፒዩተር ሳይንስን ለማጥናት አቅዷል። እናም አዳማ ዩኒቨርሲቲ ሲመደብ የመጀመሪያ ምርጫው ያደረገው የኮምፒዩተር ሳይንስን ትምህርት ክፍል ለመቀላቀል ነው።
በአዳማ ዩኒቨርሲቲ ቆይታው ስለቴክኖሎጂ ያለውን እውቀት በማዳበር የሶፍትዌር እና ድረገጽ አሠራሮችንም በሚገባ ማወቅ ችሏል። በተለይ የመመረቂያ ሥራውን ሲያዘጋጅ በኢትዮ ቴሌኮም የንብረት አያያዝ ችግሮችን ዘመናዊ የሚያደርግ ሶፍትዌር ነበር ያዘጋጀው። ሶፍትዌሩ የተሟላ ነው ባይባልም በተወሰኑ የተቋሙ ቅርንጫፎች ላይ ተሞክሮ አድናቆትን አትርፎለታል። የመጀመሪያ ዲግሪውን በ1999 ዓ.ም ሲያጠናቅቅም ችሎታውን የተረዱ ሰመራ ዩኒቨርሲቲ በኮምፒዩተር ሳይንስ መምህር እንዲሆን መደቡት።
ሕይወትና ሥራ በሰመራ ዩኒቨርሲቲ ለተወሰኑ ሳምንታት በጥሩ መልኩ ብትጓዝም ቀና ሆና ልትቀጥል ግን አልቻለችም። ከአካባቢው ሙቀት ጋር ተያይዞ የሚጠጣው ውሃ አልስማማ ቢለው አሉላ አንድ ቀን ወደሕክምና ማዕከል ያመራል። እናም ባልገመተው መልኩ የኩላሊት በሽታ እንዳለበት ይረዳና ሥራውንም ከአንድ ንፍቀ ዓመት ትምህርት በኋላ ለማቋረጥ ተገደደ። አዲስ አበባ ተመልሶ ሕክምናውን እየተከታተለ ሻል ሲለው እንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተቋም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ለማስተማር ተቀጠረ።
ለስምንት ወራት እንደሰራ ግን በሶፍትዌር ኢንጂነርነት ሙያ የሚቀጥረው ሌላ የመንግሥት ተቋም በማግኘቱ እንጦጦን ለቆ ወደሌላ መስሪያ ቤት ተሸጋገረ። የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) የተሰኘው ተቋምን በ2000 ዓ.ም መጨረሻ ላይ በሲቪል ሠራተኛነት በመቀላቀል ልምዱን ያካብት ቀጥሏል።
ወጣት አሉላ በኢንሳ በርካታ የኮምፒውተር ሳይንስ ዕውቀት እና ልምድ ያገኘበት ተቋም እንደሆነ ይመሰክራል። በዚያም ሁለትና ሦስት ዓመታትን እንደሰራ በግሉ አንዳንድ የኦንላይን ሥራዎችን መሞካከር ጀመረ። በተለይ ጋራዥ ቤቶችን እና መኪና ሻጮችን እንዲሁም አከራዮችን በማፈላለግ በተለያዩ ማህበራዊ ድረ ገጾች ስለተሽከርካሪዎቹ ሙሉ መረጃዎችን ማስተላለፉን ተያያዘው። ገዥ ሲገኝ ተሽከርካሪዎቹን በአካል እየወሰደ በማሳየት ከሽያጩ ገቢ ኮሚሽን መሰብሰቡን የትርፍ ሰዓት ሥራው አደረገው።
አራት ዓመታትን በኢንሳ እንደሰራ ደግሞ የግሌን ንግድ መጀመር አለብኝ በሚል አቋም ሥራውን በፈቃዱ ለቀቀ። ከዚህ በኋላ ወጣት አሉላ ተቀጥሮ እንደማይሰራ እና የእራሱን ድርጅት ማቋቋም እንዳለበት በመወሰኑ አንድ አጋር ፈልጎ ለቡ አካባቢ ቢሮ ተከራዩ። አጋሩ ደግሞ በኢንሳ እያለ አብሮት የሚሰራ ጓደኛው ነበር። ወጣቶቹ ለቡ አካባቢ በ2300 ብር ቢሮ በተከራዩት ቢሯቸው ሆነው በኢንተርኔት ድረገጽ የታገዘ የተሽከርካሪ ሽያጭ እና ኪራይ ንግዳቸውን አጧጧፉት። አሉላ እና ጓደኛው አንድም ተሽከርካሪ ሳይኖራቸው ፈላጊ እና ሻጭን በቴክኖሎጂ በማገናኘት ገቢያቸውን ይሰበስቡ ነበር።
ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ግን ወጣት አሉላ እና የንግድ አጋሩ አለመግባባት ውስጥ በመግባታቸው ሽርክናቸው መፍረሱን ይናገራል። በወቅቱም የያዛትን ጥሪት በሽርክናው መፍረስ ምክንያት ሲከፋፈሏት በማነሷ ሥራውን ለመቀጠል ያሰበው ወጣት መንቀሳቀሻ እንኳን ገንዘብ አጥቶ የተቸገረበት ወቅት መሆኑን አይዘነጋውም። አላማው ትልቅ በመሆኑ እና ፈተናዎቹን በጥንካሬ ለማለፍ ቁርጠና ከመሆኑ የተነሳ ግን እዛው ለቡ አካባቢ ሥራውን በጥቂት ገንዘብ ቀጠለ።
አሉላ የጀመረውን የመኪና ማከራየት እና ማሻሻጥ ንግድ ብቻ ሳይሆን የሶፍትዌር እና የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያ (አፕሊኬሽን) በመጨመር ለተጠቃሚዎቹ ማቅረቡን ተያያዘው። አልፎ ተርፎም ለተለያዩ ድርጅቶች ድረገጽ በማዘጋጀት የቴክኖሎጂ ሥራውን ደረጃ ከፍ እያደረገው ሄደ። ሁሉካር ዶት ኮም የተሰኘ ድረገጽ ከፍቶም የግብይት ማሳለጫ ንግዱን የተደራጀ ያደረገው አሉላ ከተለያዩ ደላሎች ጋር በአጋርነት በመስራት የደንበኞቹንም ቁጥር አሳድጓል።
ለኢትዮጵያውያን አዲስ በሆነው ሥራ ላይ ተሰማርቶ በድፍረት እራሱን ችሎ በመንቀሳቀሱ አትራፊ እንጂ ከሳሪ አለመሆኑ ያስደስተዋል። በየጊዜውም የተለያዩ ተቋማት እና ግለሰቦች የእርሱን ንግድ ተጠቃሚ በመሆናቸው ገቢውም እያደገ ይገኛል። አንድ መለስተኛ አቅም ያለው ስለአንድ ድርጅት አገልግሎት እና ሥራ የሚያስተዋውቅ ድረገጽ ለማዘጋጀት 20ሺ ብር ያስከፍላል። የተለያዩ የተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያዎች እና የተለያዩ ሶፍትዌሮች ለማዘጋጀት ደግሞ ከ25ሺ ብር እስከ 100 ሺዎች እየጠየቀ ይሰራል። አሁን አሉላ ኑሮው የተመቻቸ ሆኖለታል ትዳር መስርቶም የሞቀ ቤት እየመራ እንደሚገኝ ይገልጻል።
ወጣት አሉላ በጀመረው የቴክኖሎጂ ንግድ ከለቡ መስሪያ ቦታ በተጨማሪ ሜክሲኮ አካባቢ ቢሮ ከፍቶ እየሰራ ይገኛል። በየአካባቢው አብረውት ከሚሰሩት ደላሎች በተጨማሪ አምስት ቋሚ ሠራተኞችን ቀጥሮ በቴክኖሎጂው የግብይት ሥራ ላይ ያለውን ልምድ እያካፈለ ይገኛል። በዓመትም ከ100 የማያንሱ ድረገጾችን እና ሶፍትዌሮችን ከመስራት ባለፈ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች የኢንተርኔት ግብይትን መስመር በማሳየት በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ሀብት እያካበተ ይገኛል።
ወጣት አሉላ ቀጣይ እቅዱ ሁሉካር የተሰኘው ድርጅቱ አድጎ በቀጥታ ኢንተርኔት ላይ ግብይት የሚፈጸምበት የንግድ ማዕከል እንዲሆን ነው። በዚህ ዓይነቱ አሠራር እንደ አማዞን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ደንበኞቻቸው በኢንተርኔት የፈጸሙት ግብይት አማካኝነት የሚፈለጉት ዕቃ ቤታቸው ድረስ ተጓጉዞ እንደሚመጣላቸው ያውቃል። እናም እዚህ ዓይነቱ ደረጃ ለመድረስ ያለመ አሰራርን በማላመድ «ሀ» ብሎ የጀመረው ሥራ የበለጠ ስኬታማ እንደሚሆንለት አይጠራጠርም።
የኢንተርኔት ግብይት ሕግ አለመኖር እና የቀጥታ ግብይቱ መፈጸሚያ የባንክ ሥርዓት በኢትዮጵያ አለመዳበሩ እንደችግር የሚነሳ ቢሆንም በቀጣይ ዘርፉ የሚያድግ እንደመሆኑ ተስፋ ሰንቋል። አሁን ላይ በሥራው አማካኝነት ዘመናዊ የቤት ተሽከርካሪ እና ጠቀም ያለ ገቢ የሚያገኘው አሉላ የቤት ባለቤት ለመሆንም እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። ይህ ሁሉ የተገኘው ግን ያለልፋት እና ጥረት እንዳልሆነ ነው የሚናገረው። እንደ እርሱ ከሆነ ማንኛውም አዲስ ንግድ እና ሥራ ለመጀመር የሚያስብ ሰው በመጀመሪያ ፈተናዎች ቢገጥሙት እንኳን በጥረቱ ማለፍ እንደሚችል አምኖ መግባት አለበት።
ሁሉም ሥራ የሚጀመረው አንድ ተብሎ ነውና ዛሬ የተጓዝነው አንድ እርምጃ ነገ በርካታ ማይሎችን የሚያስጉዘን በመሆኑ ጥንካሬ ዋነኛው ጉዳይ ይሆናል። በተለይ ወጣቶች ንግድን መጀመር ካለባቸው ዛሬ ነገ እያሉ ከማመንታት ይልቅ አቅማቸውን እና ጊዜያቸውን ተጠቅመው ሰርተው ስለማደግ አንድ እርምጃ ዛሬውኑ ስለመጀመር ማሰብ አለባቸው የሚለው ደግሞ ምክሩ ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሀሴ 25/2011
ጌትነት ተስፋማርያም