በአካባቢው ያለው የሚሰነፍጥ ጠረን እንኳንስ በሥፍራው ቆሞ ለመገበያየት በዚያ ለማለፍ እንኳ አስቸጋሪ አድርጎታል። እንግዳ የሆነ ሁሉ ‹‹እንጢስ! እንጢስ!›› እያለ ነው የሚያልፈው። ወዲህ ደግሞ ሻኛቸው ግራ ቀኝ እያለ የሚንጎማለል ድልብ በሬዎች አሉ። ከበሬም ደግሞ የጅሩ፣ የሐረር፣ የጅማ ሠንጋ እየተባለ በየዘረፍና በየአካባቢ ሥያሜ የተሰጣቸው ድልቦችን በቦታው ማየት ደግሞ በራሱ ሌላ ትዕይንት ነው።
ላታቸው ከብዷቸው ሰውነታቸው ግራ ቀኝ የሚወዛወዙ በጎች፣ ፍርንባቸው ከመሬት ሊሳሳም የደረሰ ቀንዳም ፍየሎች በተጓዳኝ ደግሞ በአካባቢው እንጀራ ፈላጊዎች ላይ ታች ይባዝታሉ። ወከባው እና የእንስሳት ዋጋ ጥሪው እንዲሁም የገበያው ድባብ ደግሞ የአካባቢውን መጥፎ ሽታ አስረስቶ በሥፍራው ለመቆየት ከሚያስገድዱ ሁነት ውስጥ አንዱ ነው።
በእርግጥ ሰማይ የነካው የሥጋ ዋጋ እጅ ላጠራቸው ሰዎች የሚቀመስ ባይሆንም በዚህ አካባቢ እያለፉ አድናቆታቸውን ለአድላቢዎች ይገልጹ ይሆናል- በልባቸው። በዚህ አካባቢ ድሆችና ሃብታሞች በእኩል የሚጋሩት አንድ ነገር አላቸው። ድልብ፣ በሬዎችን፣ ፍየሎችና በጎችን ቆሞ የማየት መብትና እንዲሁ በተመሳሳይ ሰዓት በአካባቢው ያለውን መጥፎ ሽታ፣ ሁካታና ግርግር በነፃ የማሽተት እና የመመልከት መብት።
ይህ ወደ ደብረብርሃን መውጫ ስንቃረብ ካራ በሚባለው የቁም እንስሳት መገበያያ ስፍራ የሚታይ እውነታ ነው። ሥፍራው ለአካባቢው ነዋሪዎች ጤና አሳሳቢ ቢሆንም ለበርካቶች የሥራ ዕድል የተፈጠረበት ማዕከል ሆኗል። ሳር ሻጮች፣ ውሃ አቅራቢዎች፣ የሉካንዳ ባለቤቶች፣ አርሶ አደሮች፣ እሳት የላሱ ደላሎች፣ ሊስትሮዎች፣ ቢላዎ ሻጮች፣ ከብት አራጆችና ሌሎችም በዚህ አካባቢ የዕለት ጉርሳቸው መሠረት አድርገዋል።
ታዲያ ስፍራው በበጋ ወቅት አቧራው፤ በክረምት ጭቃው አስቸጋሪ መሆኑን የተረዱ ሰዎች ደግሞ ለአካባቢው የሚመጥን አለባበስና ጭቃውን የሚደፍር ቦቲ ጫማ እያከራዩ አዲስ የሥራ ፈጠራ ዘይቤ ይዘው ብቅ ብለዋል።
ጫማ አከራዮችና ጫማ ጠባቂዎች
ጓደኛሞቹ አለማየሁ ደሳለኝ እና ካስትሮ ኮንቶ ውልደታቸውና ዕድገታቸው ወላይታ ሶዶ አካባቢ ሲሆን በአንድ ወቅት ለሥራ ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውን ያስታውሳሉ። ሥራና ሠራተኛ ይገናኛል እንዲሉ አለማየሁ ደሳለኝ እና ካስትሮ ኮንቶ የኑሮ ፈተናን ለማለፍ ሲሉ ከ10 ዓመት በፊት ነበር ሞክረውት የማያውቁትን ሥራ ‹‹ሀ›› ብለው የጀመሩት።
በርካቶች እኔ ይህን ሥራ አልሠራም፣ አይመለከተኝም፣ አይመጥነኝም በሚሉበት በዚህ ዘመን አለማየሁና ካስትሮ ግን አንድ መላ መቱ። እንስሳት ገበያ በሚደራበት የካራ ገበያ አካባቢ ገበያው በክረምት ወቅት በጭቃ ቡካት፤ በበጋ ወቅት ደግሞ በአቧራ የሚሸፈን
ስፍራ ነው። ታዲያ በዚህ የሚማረሩ በርካቶች መሆናቸውን የተረዱት አለማየሁና ጓደኛው በአካባቢው የጫማ ማፅዳት ሥራ ጀመሩ።
የአካባቢው ነጋዴዎችና ቋሚ ደንበኞች ፍላጎት ግን ጫማ እንዲፀዳላቸውና አቧራው ከልብሳቸው እንዲለቅላቸው ብቻ አልነበረም። በአለማየሁና ጓደኛው አረዳድ እነዚህ ሰዎች ጫማ የሚቀርብላቸው፤ ልብስም የሚዘጋጅላቸው ሰዎችን እንደሆኑ ተገነዘቡ። ከቆይታ በኋላም ከሊስትሮ ሥራቸው ጎን ለጎን ቦት ጫማ ገዝተው ማከራየት ጀመሩ።
ጭቃ እና ዝናብ የሚከላከሉ በተለምዶ ሻማ የሚባሉ ልብሶችንም እንዲሁ ማከራየት ጀመሩ። በሂደት ደግሞ የራሳቸው ቦት ጫማ እና የዝናብ መከላከያ ያላቸው ሰዎች ከተጠቀሙ በኋላ ጫማ እና ልብሳቸውን አጠገባቸው በአደራ መልክ ያስቀምጡ ጀመር። እናም ጫማ ማከራየት ብቻ ሳይሆን ጫማቸውን እየጠበቁ እስከ 20 ብር ይከፍሏቸዋል።
አለማየሁ በዚህ ሥራው በአሁኑ ወቅት ከ30 በላይ ቦቲ ጫማዎችን ባለቤት በመሆኑ ያከራያል። አርብና ዕሮብ የገበያ ቀን በመሆኑ ደግሞ ጭቃ መከላከያ የሚሆነውን ጫማና ልብስ ለደንበኞች በሰዓት አስከፍሎ ያውሳል። በአማካይ ከአንድ ሰው በቀን እስከ 40 ብር ይቀበላሉ። በተቀሩት ቀናት ደግሞ ጥቅም ላይ የዋሉት ልብሶችንና ጫማዎች ወደእጥበት ይገቡና ዳግም ለሥራ ዝግጁ ይሆናሉ። እነዚህ ቦቲ ጫማዎችና ልብሶች ሥራ የፈቱ ቀን ቤት ውስጥ ይከረቸማሉ። በየወሩም ለቦቲ ጫማ ማስቀመጫ 1000 ብር የቤት ኪራይ ይከፍላሉ።
አለማየሁ በዚህ ሥራ ላለፉት 10 ዓመታት የሠራ ሲሆን ኑሮውን በልዩ ሙያ ሲመራ ቆይቷል። የትዳር አጋሩን ጨምሮ አራት የቤተሰቡን አባላት በዚሁ ስራ ይመራል። ካስትሮም ቢሆን በዚሁ ሥራ የሚተዳደር ሲሆን በአሁኑ ወቅት እራሱን ጨምሮ ሦስት ቤተሰቡን እያስተዳደረ ይገኛል፤ ማህበራዊ ሕይወቱን ይደጉማል፤ የቤት ኪራይ ይከፍላል የተቻለ እንደሆነም ቤተሰቡን ያግዛል። በስፍራው በርካታ ደንበኞችን በማፍራታቸውና እምነት በማትረፋቸው ከዚህም ሥራ ጎን ለጎን ቆጭቆጫ እና ቡላ እያመጡ ይሸጡላቸዋል – ለደንበኞቻቸው።
ጭቃ ጠራጊዎችና መንገድ ዘጊዎች
በአካባቢው ያሉ አንዳንድ ሰዎች ‹‹እነዚህ ጭቃ ጠራጊዎች›› ሲሉ አልፎ አልፎ ሥራቸውን ያጣጥሉባቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ደንብ አስከባሪዎችና ፖሊሶች ‹‹መንገድ ዘጊዎች ህገ ወጦች›› ይሏቸዋል። በዚህም የተነሳ ነጋ ጠባ ያስቸግሯቸዋል፤ ያሳድዷቸዋል፣ ያስቀይሟቸዋል።
የአካባቢውን መጥፎ ሽታ ተቋቁመው መሥራታቸው ለሌላም ሰው የሥራ ዕድል መፍጠራቸው አልተዋጠላቸውም። እነርሱ ግን አካባቢው መጥፎ ሽታ ተቋቁመው፤ የሰዎች ግልምጫ ቻል አድርገው፣ የሰዎችን አሽሙር ከቁብ ሳይቆጥሩ፣ የፖሊሶችና ደንብ አስከባሪዎች ማስፈራሪያና ዛቻ ሳያስበረግጋቸው ይኸው እንዳለን አለን፤ ከመስረቅ መስራት ክቡር ነው ብለን ሲሉ ስለነገው ሩቅ አሳቢነታቸው ያወጋሉ፤ ተስፋ ይሰንቃሉ።
ተደራጅተን ብናደራጅ
አለማየሁ ደሳለኝ እና ካስትሮ ኮንቶ እኛ ተደራጅተን ብንሰራ ለሌላ ሰው ተደራጅቶም በአካባቢው ቢሰራ ደስታችን ወደር የለውም ይላሉ። ‹‹ግን ለመደራጀት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች፣ እውቀትና መመሪያዎች የሉንም። ለአብነት እንኳን በካራ የቁም እንስሳት ገበያ በሚከናወንባቸው እሮብና አርብ ቀን በመቶዎች የሚቆጠሩ ተሽከርካሪዎች በአካባቢው የጭነት አገልግሎት ይሰጣሉ። ይሁንና በቂ ፓርኪንግ ስፍራና የፓርኪን አገልግሎት ጥበቃ የለም። እኛ በዚህ ቦታ ተደራጅተን ሌሎችም ቢደራጁ ለአካባቢው መልካም ነው።
እኛ እያልን ያለነው ተደራጅተን ለሥራ የሚመጡትን ብናደራጅ የሚል ሃሳብ ነው። አንድ ሰው ሊሠራ የሚችለው ውስን ሥራ ነው። ስለዚህ ሃሳብና መተባበር ከመንግስት ደግሞ እገዛ ከተደረገ በርካቶች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዕድል መኖሩን ይናገራሉ። ተደራጅተን ብናደራጅ የሚመለከታቸው አካላት ቢያግዙን ክፋቱ ምንድን ነው ሲሉም ህገወጦች ናችሁ ብለው የሚያሳድዷቸውን ሰዎች ይጠይቃሉ።
የሚሸጡ ሐሳቦች
ወጣቶች ለራሳቸው ሠርተው ከመለወጥ በዘለለ ለመንግስት የምንሸጣቸው ውድ ሃሳቦች ስላሉን ወደ እኛ ቢመጡ መልካም ነው ሲሉ ለመንግስት ጥሪ ያቀርባሉ። እኛን ከማሳድድ ሥራ አጦችን እያሳደዱ ወደ እኛ ቢያመጧቸው፣ ከእኛም ተርፎ ለሌሎች የሚሆን የሥራ ዕድል መፍጠር እንችላለን ባይ ናቸው።
እንደወጣቶቹ፤ ለአብነትም በአካባቢው በርካታ ቁም እንስሳት ግብይት የሚከናወኑበት በመሆኑ እበትና ሌሎች ተረፈ ምርቶች አካባቢውን እያቆሸሹ የከተማዋን ውበት እያጎደፉ የአዲስ አበባን ስም እያሳነሱ ነው። ታዲያ እበትና ሌሎች ተረፈ ምርቶችን የሚሰበስቡና በዘመናዊ መንገድ አብላልተው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ቢያዘጋጁ በሚሊዮን የሚቆጠር የከተማው ህዝብ ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል።
በሌላ መንገድ በእንስሳት መሸጫ አካባቢ ነጋዴዎች ለተከታታይ ሦስት እና አራት ቀናት የመዋልና ማደር ባህሪ ስላለው ልብሳቸው እጅጉን ይቆሽሻል። ታዲያ እነዚህ ሰዎች ሁነኛ ሰው ቢያገኙ ልብሳቸውን ማሳጠብ ይፈልጋሉ። በመሆኑም በእንስሳት መሸጫ በረቶች አካባቢ ልብስ አጣቢዎች ቢደራጁ እንዲሁ ሥራ አጥ ዜጎችን ከሥራ ገበታ ላይ እንዲውሉ ማድረግ ይቻላል።
በተጨማሪም በእንስሳት መሸጫ በረቶች አካባቢ በርካታ ጫኝና አውራጅ፣ ሻጭና ገዥ፣ ሃብታምና ድሃ ብቻ አላፊ አግዳሚው ብዙ ነው። ታዲያ በዚህ ድካምና እቅስቃሴ በብዛት አካባቢ የሙቅና ቀዝቃዛ ሻወር ቢኖር መንግስትም ሥራ አጦችም ተጠቃሚ ይሆናሉ። በቀዝቃዛ ሻወር የፀሐይ ግለቷ ሲያስቸግር በረድ ለማለት፣ በሙቅ ሻወር ደግሞ ቅዝቃሴው እንደ በረዶ ሲያጠጥር ሰውነትን ለማፍታታት በእጅጉ የሚመከር በመሆኑ መንግስት በዚህ ላይ ቢያተኩር ብለው ይመክራሉ።
በሌላ ጎን ደግሞ በርካታ ወጣቶችን በሻይና ቡና፣ ለስላሳ መጠጦች ምግብና ተያያዥ ሥራዎች ላይ ቢደራጁ ሥራ አጥነትን የሚቀንስ ሥርዓት አልበኝነትን ደግሞ ፈር የሚያስይዝ ታክቲክ በመሆኑ ትኩረት ቢሰጠው መልካም እንደሆነ ይጠቁማሉ። የቁም እንስሳትን የሚጎትቱ፣ ገመድ የሚሸጡ፣ ከእንስሳት መሸጫ እስከ ማረጃ (ቄራ) ድረስ የሚያስተባብሩና የፀጥታ አካላትን የሚያግዙ አካላት ቢደራጁ ሥራ አጥነትን በመቀነስ፤ ለመንግስትም አመቺ የሥራ ቀመር እንዲዘረጋ በማድረግ ‹‹በአንድ ዘዴ ሁለት ወንበዴ ይሉት›› ብሂል በርካታ ሥራዎችን በአንድ ጊዜ ማከናወን እንደሚቻል ይጠቁማሉ። ወጣቶቹ ከእነዚህም ሐሳቦችና ምክሮችም በተጨማሪ ቀርቦ የሚያናግረን፤ ምክራችንን የሚሰማ የመንግስት አሊያም ደግሞ ባለሀብት ካሉ በውድ የሚሸጡ ጠቃሚ ሐሳቦች አሉን ሲሉ ይናገራሉ።
የሥራ ዕድል ተፈጥሮልናል
አስራት ወልደሚካኤል እና ቴዲ ተስፋ ከወላይታ ሶዶ ኪያ ጆኒ ደግሞ ከሲዳማ ሌኮ ከሚባል አካባቢ ክረምቱን ሥራ እንስራ ብለው ከወራት በፊት ነበር ወደ አዲስ የመጡት። ሦስቱም ተማሪዎች ሲሆኑ ለበጋው የትምህርት ወቅት የሚያስፈልጋቸውን ወጪ ለመሸፈን ሲሉ ቤተሰብ ማስቸገር አልፈለጉም። በክረምቱ ወደ ሸገር የመጡት አንገታቸውን ደፍተው ያገኙትን ሥራ ለመሥራት ወስነው ነበር። አለማየሁን ያውቁት ነበርና ወደ እርሱ ዘንድ ሄዱ። እርሱም አርብ እና ረቡዕ ጥቅም ላይ የዋሉ ቦቲ ጫማዎችን እንዲያፀዱ ያደርጋቸዋል። በቀን ከ100 እስከ 150 ብር ይሰጣቸዋል።
አርብና ረቡዕ ቦቲ ጫማ እና ሻማ ልብሶቹ ስለሚከራዩ ቦቲ ጫማ አያፀዱም። ግን ደግሞ ጫማቸውን አውልቀው ቦቲ የሚያጠልቁ ሰዎች ‹‹ጫማችንን አፅዱልን፤ በደንብ ቦርሹልን›› ብለው ሰጥተዋቸው ይሄዳሉ። በእነዚህ ሁለት ቀናት ታዲያ እያንዳዳቸው በጫማ ማፅዳት ሥራ በአማካይ ከ350 እስከ 400 ብር ያገኛሉ።
እነዚህ ተማሪዎችም የሥራ ዕድል ተፈጥሮልናል ባይ ናቸው። በበጋ ወቅት ወላጆቻቸውን ማስቸገር አይፈልጉም፤ ቢቻላቸውስ ማገዝ እንጂ። በዚህ ክረምት ባጠራቀሙት ገንዘብ የሚያስፈልጋቸውን ቁሳቁስ ገዝተው ለመመለስ ወስነዋል። ከመስቀል ደመራ ጀምሮ ከቤተሰባቸው ጋር አሳልፈው ከመስቀል ማግስት ደግሞ እምር! ቅብርር…! ብለው ወደ ትምህርት ገበታ ሊያመሩ ቋምጠዋል። ላባችንን ጠፍ አድርገን ያጠራቅመነውን፤ በጭቃ ተለውሰን ጭቃ አፅድተን ያገኘናትን ገንዘብ ባርክልን እያሉ – ወደ ፈጣሪ አንጋጠው።
እውነትም እጅ አጣጥፎ ተቀምጦ በባዶ ሆድ ወደ ፈጣሪ ከማመልከት የተቻለን ሰርቶ ወደላይ ማንጋጠጥ! ኩራትም ክብርም ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሐሴ 25/ 2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር