ዕንባን የተሻገረ ትናንት

በፍቅር እስከመቃብር መጽሐፍ ውስጥ ሰብለ ወንጌልና ሀብትሽ ይመር ጨዋታ ይዘዋል። በዛብህ እጇን ይዞ ሲያስተምራት ይቆነጥጣት እንደሆነ፣ ሰብለን አንቺ በማለቱ ፊታውራሪ መሸሻ ተቆጥተውት አኩርፎ ሲቀር በናፍቆት ሰበብ ሆዷን ባር ባር ይላት እንደሆነ ሀብትሽ ይመር ሰብለን ትጠይቃታለች።

ይህኔ ሰብለ “ጉንዳን ይቆንጥጥሽ፤ አይንሽን ያብረው እቴ” የገል ሰባራና የባሪያ ዕውር ከመጣል በቀር ዋጋ የለውም ትላለች። ወዲያው ሀብትሽ “ዓይኔስ ይቆይልኝ” ትልና የማያዛልቅ ወግ መሆኑን ስትገነዘብ ሰብለ ወንጌል የተቆጣች ስለመሰላት ምላሷን ትውጣለች።

“ሀብትሽ ይመር የተናገረችው ተረት ሥጋ ሠርቶ ነፍስ ዘርቶ የኔን ሕይወት አክብዶት ነበር” አለ የዛሬ እንግዳዬ ዓሊ አሕመድ የታሪኩን ውጥን ከስሩ እያሲያዘኝ። ዓሊ ከአባቱ አቶ አሕመድ የሱፍና ከእናቱ ከወይዘሮ አመቶ ዓሊ በወርሐ ግንቦት 1995 ዓ.ም በሀገረ ጅቡቲ ሀበሻ ወይም ጋላፊ መጋላ ሰፈር ተወለደ። “የሆድሽን ሸክም በጀርባሽ ያውልልሽ” የሚለው ምርቃት ሰምሮ በአንቀልባ ላይ እንዳለ በስድስት ወሩ የፀሐይ ምች አነደደውና ብርሃኑን ነጠቀው። ይህን ጊዜ እናት ከፈጣሪ የመጣ ቁጣ አድርገው በመቁጠር ማህፀናቸውን ረገሙ።

“አካለ ጎዶሎ ልጅ ወለዱ እየተባልንማ የቡና መጠጫ አንሆንም” ብለው ከቀያቸው የሚያርቁበትን መንገድ እያሰቡ ሳለ ወደኢትዮጵያ ትውልድ መንደራቸው አርጎባ የሚመለስ ሁነኛ ሰው አገኙና አያቱ ዘንድ እንዲያደርስላቸው በአደራ አስረከቡት። የዛኔ ገና ጡት ያልጣለ የሁለት ዓመት ሕፃን ነበር።

የባለጸጋ ረሃብተኛ፣ የመሐይም ወገኛ በሞላባት ምድር አመለካከት ይሉት አባባል፣ የኔ ቢጤ ይሉት አሳሳል ከመንጋው ጋር ያግተለተለውንና መሳ ለመሳ የተሰለፈውን የዓሊ አሕመድን የሕይወት ገጽ በሥነ ጽሑፍ ሰፌድ ላንጓልል በብዕር ዓይነ በጎ ወንፊት ላጠል ከጅቡቲ አንስቼ ጋሬጣና እሾሁ ሳይበግረኝ ዱር ገደሉ ሳይመክተኝ አብሬው እየኳተንኩ ነው።

ፀሐፊው ነኝ፤ ክታባቸው ከደበዘዘ የሕይወት ቀለሞችና ወዛቸው ከነጠፈ የገሃዱ ዓለም ሰዎች ጀርባ ትናንትም ነበርኩ፤ ዛሬም አለሁ፤ ነገም እኖራለሁ። ጥረትና ጽናትን እንዲሁም ይቅር ባይነትን ብሎም ተስፋ አለመቁረጥን ትማሩበት ዘንድ የእንግዳዬን የሃያ ሁለት ዓመቱን ወጣት የዓሊ አሕመድን የሕይወት ገጽ አብረን እንድንገልጠው የአክብሮት ግብዣዬ ነው።

ደቡብ ወሎ ዞን አርጎባ ልዩ ወረዳ እንደደረሰ ከወላጆቹ ያጣውን ፍቅር ከአያቱ ፋጡማ ሐሰን መዳፍ ያለ ስስት መዝገን ጀመረ። አካል ጉዳተኛ መሆኑ ትልቅ ሰው ከመሆን የሚያግደው እንደሌለ ሞራልን የሚያበረታ፣ የበታችነትን ስሜት የሚረታ ብሩህ ተስፋ እየተመገበ አደገ።

እድሜው ለትምህርት ሲደርስ በአካባቢው ካለ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአካቶ ትምህርትን ጀመረ። በስፍራው ሌሎች ዓይነስውራንን ማግኘት ባይችሉም ዕድሉ እንዳይባክንበት ያሰቡ ዓሊ አሕመድን ብቻ በመያዝ የብሬል ትምህርቱን ጀመሩለትና የጨለማ ዘመኑን ገፈፉለት። ይህ መደላድል ግን ከአራተኛ ክፍል በላይ አላሻገረውም። የአያቱ ማረፍ ብዙ መከራ አሳየው።

ከአያቱ ሞት በኋላ የትምህርት ጉዞውን ዳገት አድርጎ ሕይወቱን ያከፋበት አጋጣሚ ተፈጠረ። ጓዛቸውን ጠቅልለው ከጅቡቲ አርጎባ የመጡት እናትና አባቱ ልጃቸው መሆኑ እንዳይታወቅ ከቤት እንዳይገባ አገዱት። በከፋ ድብደባም አካባቢውን ለቆ እንዲሄድ ማስመረር ያዙ። ይህ ድርጊት የዕለት ተዕለት ሥራቸው ቢሆን ዓሊ ለትምህርቱ ሲል ብዙ ታገለ። ከዛሬ ነገ ይመለሳሉ በሚል ታገሰ። ኡስታዞችን ሳይቀር የሀገር ሽማግሌ ይዞ የወላጅ ግዴታቸውን እንዲወጡ ተማጸናቸው። ‹‹በጄ›› አላሉም።

ውሎ አድሮ የሸሸጉት ምስጢር ገሐድ ወጥቶ ሀገር ስላወቀው ፀሐይ ስለሞቀው አኮረፉት። ለይስሙላ በይሁንታ ቢያስጠጉትም እህል በመንፈግ ፆሙን አበዙበትና በራሱ ፍቃድ ተነቅሎ እንዲሄድ ማስመረሩን ገፉበት። እንዳሰቡት ሆነላቸው። ውርጩንና ንፋሱን ተቋቁሞ በረንዳ እያደረ ከዳር ለማድረስ የደከመለት ትምህርቱን የሆዱ ነገር አሸነፈው። ሚኒስትሪን ለመቀበል አንድ ሳምንት ሲቀረው ትቶት ወደ ኮምቦልቻ ሄደና እጁን ለምፅዋት ዘረጋ።

በሌሎች ላይ ሲያየው ይጠላው የነበረው የልመና ሕይወት በሱም ዘንድ ተጋርጦ በሰው ፊት ሲያስፈጀው ፈጣሪውን አማረረ። ዕድሉንም ረገመ፤ ወላጆቹን በድርጊታቸው ክፉኛ አዝኖ ከልቡ ጠላቸው። እጅን ከአፍ ለማገናኘትና ቀምሶ በማደር ሆድን ለመሸንገል ርጋፊ ሳንቲሞችን ሲለቃቅም ይውላል። ይህኔ ከሚያንቃጭለው የሳንቲም ድምፅ ጋር ሰው የመሆን ተስፋው የመከራ ወላፈኑን ተጋፍቶ ከጆሮው ይደውላል። እንዲያም ሆኖ አብረውት ፊደል የቆጠሩ የትምህርት ቤት ጓደኞቹ ሲያዩት በሁኔታው እያፈረ እልፍ ቀናትን ተሸማቆ የእግዜር ሰ ላምታ ይነፍጋቸዋል።

ይህ አይነቱ ባሕሪ ከሰው ጋር አያሳድርምና መባልን ሳይሆን መሆንን ፈርቶ ከተዘፈቀበት የልመና ሕይወት ለመውጣት መታገል ያዘ። ከሚያገኘው የቀን ምፅዋት መቶ ብር ማስቀመጥ ቻለና ከስድስት ወራት በኋላ በአምስት ሺህ ብር የንግድ ዓለሙን አሟሸው። በየትራንስፖርቱና በመዝናኛ ስፍራው ሁሉ ማስቲካና ሶፍት እያዞረ በመሸጥ ለምፅዋት ተዘርግቶ የነበረውን እጁን ወደሥራ መራው። ለብዙ አካል ጉዳተኞች ምሳሌ ከመሆን ባሻገር የሱ ዕጣ ፋንታ እንዳይገጥማቸው የኢኮኖሚ ድጋፍ እያደረገ የትምህርት ሕይወታቸውን ከዳር እንዲያደርሱ አቅም ሆናቸው። አሁንም ድረስ ይህ ማንነቱ አብሮት ነው።

በልመና ሕይወቱ የሚያውቁት የአካባቢው ሰዎች ራሱን ለመለወጥ የሚያደርገው ጥረት ደስ አሰኝቷቸው የተሻለ ደረጃ እንዲደርስ በሃሳብና በገንዘብ እገዛ ብርታት ሆነውታል። ዓሊም የጣሉለትን እርሾ ተጠቅሞ የሚይዘውን ሸቀጣሸቀጥ በማሳደግ ለሌሎች አካል ጉዳተኞች ምሳሌ ሆነ። የሰው እጅ ከመጠበቅ ይላቀቁ ዘንድም የሥራ ዕድል ማመቻቸት ያዘ።

የዓሊ መምህራን የእሱ ቀለም ወጊነት ቀልባቸውን ገዝቶ ከአፋቸው ሳይነጥሉ፣ ከፊት የሚያሰልፉትን ብርቱ ትምህርት ማቋረጥ በሰሙ ጊዜ ከዕውቀት እንዳይርቅ በብዙ ሲጥሩ ቆይተዋል። ዓሊ ግን እቅፍ ድግፍ አድርጎ የመከራ ክረምቱን የሚያሳልፍ ሁነኛ ወዳጅ ዘመድ አልነበረውም። “ሥጋዬ” በሚሉት ተስፋ ቆርጦና “ንፋስ ነው ዘመዴ” ብሎ ራሱን በራሱ ለማሳደር ተጣጣረ። አካሉ ሳይጠናና ነፍስ ሳያውቅም ለጉልበት ሥራ ተዳረገ። እሱም ቢሆን አንድም ቀን “ከትምህርት ጎዳና እወጣለሁ” ብሎ አስቦ አያውቅም። እናም ሕይወት ሽፍንፍኗ ብዕሩን ነጥቃ በንግዱ ዓለም አንደረደረችው።

ከአካል ጉዳተኝነት ጋር ተዳምሮ ራስህን በራስህ ለመምራት የጀመርክበት እድሜ ማነስ በንግድ ሥራህ ላይ የፈጠረብህ ፈተና ይኖር ይሆን? ስል ጠየቅሁት። ዓሊም ፈገግታን የሚያጭሩ ገጠመኞቹን ሊያካፍለኝ ወደደ። እኔም የሚተርከውን ወግ ለመከተብ ብዕሬን ከወረቀት አስማማሁ።

ብዙዎች “እድሜ ልክ ከምለምን አንድ ቀን ለምኜ በረጠቡኝ ዳረጎት ራሴን ለመለወጥ ስታትር ሲያዩ ደስታቸው ወደር የለውም። የነሱ ተስፋ በእኔም ተጋብቶ ከሚጠብቁኝና ከሰጡኝ ደረጃ ለመድረስ ሌት ከቀን ሳልታክት እየደከምኩ ነው። ዳሩ ግን ወደኋላ የሚያንደረድሩ እንቅፋቶች የሉም ማለት አይደለም፤ በጽናት ታግዬ እየተሻገርኳቸው እንጂ።

አንድ ቀን ምን ሆነ መሰለህ?” አለ ከማውራቱ በፊት የሚታገለው ሳቅ እየቀደመው። “የጓደኛ ምክር የሚያለማውን ያህል እንደሚያጠፋም ልብ ሳልል ለከፋ አደጋ ደርሼ ነበር” ሲል የነገሩን ታሪክ ከስሩ አሲያዘኝና በትዝታ ፈረስ ጭኖ ሽምጥ አስጋለበኝ።

“ከተልባ ስፍር፣ ከኑሮ ግርግር ፍሬ ነገር አይዘገንም ›› እንዲሉ እኩዮቼን ሰምቼ የጀመርኩት የኮንትሮባንድ ሥራ ራሴንና ሀገሬን ላጭር ጊዜም ቢሆን ጎድቷል”። ቅርታው ከፊቱ እየተነበበ ነው። “አካል ጉዳተኝነቴን ለስህተቴ ምክንያት አደረኩት” አለ። በቁጭት ደገመና። ካለፈው ተምሮ በንፁሕ ልቦና ነገን መሥራት እንጂ መብሰክሰክ መፍትሔ ይሆናል ብለህ ነው? አልኩት የሆነውን ሁሉ ያለመሳቀቅ እንዲያወራኝ ሞራል ልሰጠው እየታገልኩ።

“ነገሩ እንዲህ ነው” ሲል ሃሳቡን በዝርዝር ሊያወራኝ የወግ እንዝርቱን ማሾር ጀመረ። በተመሳሳይ እድሜና ደረጃ የሚገኙ ወጣቶች በሚያዞሩት ሱቅ በደረቴ ሰበብ ሕገወጥ ንግድን ከሚቆጣጠሩ አካላት ጋር ፖሊስና ሌባ መጫወቱ ቢመራቸው ሞያሌና ውጫሌ ድረስ በመሄድ የኮንትሮባንድ ሥራ ሊጀምሩ ተነጋግረው አዲስ አበባ ገቡ። “ይሁን እንጂ የችግሩ ገፈት ቀማሽ እኔ ብቻ ነበርኩ” ሲል ንግግሩን ገታና ጉሮሮውን ለማርጠብ ከያዘው ውሃ ተጎንጭቶ ሃሳቡን ካቆመበት ቀጠለ። “ለሦስት ጊዜ እንዳመጣሁ በትርፉ ለውጥ ሳገኝ ጓደኞቼ ግን በኬላ ጠባቂዎች ተነጥቀው ኪሳራ ውስጥ ወደቁ። ለአራተኛ ዙር ተመልሼ ስሄድ ማነቆ ሃሳብ አመጡና ነፍሴን አስጨነቋት። ‹‹እንቢኝ›› ልል ብሞክርም ማን እየመራ እዚህ አደረሰህና ነው የኛን ሃሳብ ለመቀበል አሻፈረኝ የምትለው? ምነው ብቻዬን ልብላ አልክሳ? ብለው ፊት ነሱኝ። ይህኔ ሜዳ ወድቄ ከመቅረት ስል የነሱንም እቃ በኔ ስም ለማሳለፍ ተስማማሁ።

ቢሆንም ግን ‹‹ፈሪ በሆዱ ጀግና በክንዱ›› ነውና ገና ኬላው ዘንድ ስንደርስ አወቁብኝና የተለየ ፍተሻ አደረጉብኝ። እድሜ ልክህን እየለመንክ ከምትኖር ሠርተህ ብትቀየር ብለን ፈቀድንልህ እንጂ አካል ጉዳተኛነትህን ጭራሽ ለወንጀል ትጠቀምበታለህ? ሲል አንደኛው ኬላ ጠባቂ ሲቆጣኝ መልስ ለመስጠት አልደፈርኩም። የቱንም ያህል ቢቆጡኝ ግን ጨክነው አልገፉኝም። በሕጋዊ መንገድ ሥራውን እንድቀጥል ሞራል ሆኑኝ እንጂ።

ከዚያን እለት ጀምሮ ራሴንና ሀገሬ የሚገባቸውን ሐቅ ላልነጥቅ ቃል ገባሁ። እናም የደከምኩለት የንግድ ዓለም መሻገሪያ ድልድይ ሆኖኝ ለሌሎች ጭምር መትረፍ ቻልኩ” በማለት አጫወተኝ። ፀዳሉ እንደማለዳዋ ጮራ እየፈካ።

ታዲያ ቤተሰቦችህ የተሳሳተ አመለካከት እንደ ያዙ በዛው ቀሩ ወይስ የግንዛቤ ለውጥ አመጡ? የትምህርትህንስ ጉዳይ ከምን አደረስከው? ስል ጥያቄ ደራረብኩለት “ዕድል ደፋሮችን ትመርጣለች” የሚለው የማርከስ ኦሪሊዬስ አባባል እየታወሰኝ።

“በክፉ የመጣብህን በበጎ መልስለት አይደል ቁራኑስ የሚለው? ዓይነስውርነትን ፈቅጄ ያመጣሁት ይመስል ከወጋግራው ጋር አስረው ጀርባዬ እስኪተላ ድረስ በጉማሬ አለንጋ ገርፈውኛል። ‹‹ስትወለድ ያርባ ቀን ዕድልህ ውሃ አድርጎ ባስቀረህ ኖሮ፤ እህል ከመፍጀት ሌላ ምን ትፈይድልናለህ?›› ተብያለሁ። አንተን ከሚሰጠን ማህፀኔን በዘጋው፤ አንተ የሰው ትርፍ እያሉ አካሌንና ሞራሌን ሲሰባብሩት ኖረዋል።

ይህ ሁሉ ሐቅ እንዳልነበር በኃጢያት ያጎደፍኳቸው እልፍ የመከራ ቀናት በፈጣሪ ምሕረትና ቸርነት ተሽረውልኝ ለዛሬ ስኬቴ በቅቻለሁና ሕያው ቃሉ አጽናንቶኝ እኔም ይቅርታ አድርጌላቸዋለሁ። አሁን ላይም ለመጠያየቅ ደርሰናል” ብሎ ሲነግረኝ እንደፀሐይ የሚሞቅ ፈገግታው ተጋባብኝ። ከጥቂት ፋታ በኋላ ትረካውን ቀጠለ። “ወላጆቼ በሚያደርሱብኝ ግፍ አንጀቱ የቆሰለ የሚወደኝ አንድ የጎረቤት ልጅ ነበር፡:፡ ሲቀናው ቤተሰቦቹን እያስፈቀደ አንዳንዴም እየሰረቀ ሆዴን ለመሸንገል ቁራሽ ያቀብለኛል።

ታዲያ በዚህ ሰዓት የችግር ምዕራፍ ተቀይሮ መልካም ሕይወት ሲጎበኘኝ በወዳጄ በኩል ጥቂት ገንዘብ ላኩላቸው። እጅ የነሳኋቸው ወላጆቼ እጃቸውን በአፋቸው ጭነው በመገረም ይቅርታ ሊጠይቁኝ በቁ። እኔም የገፋኝ ልባቸው ስላቀረበኝ ደስ ተሰኝቼ እርቁን ተቀበልኩና የፈጣሪን ፀጋ በመልበስ ያመጡልኝን እጮኛ ለማግባት ሽር ጉድ ላይ እገኛለሁ”ሲል እያንዳንዷን ኹነት አጫወተኝ።

“ይህ ሁሉ ሲሆን የትምህርቴ ነገር በጀርባዬ ዞሮ አያውቅምና ጎጆ ከቀለስኩ በኋላ ያቋረጥኩትን ትምህርት ለመቀጠል ዝግጅት ጨርሻለሁ። በንግድ ሥራዬም ለቤት ባለቤትነት በቅቻለሁ። ከዚህም አልፎ ለእህትና ወንድሞቼ ባጃጅና ሱቅ በመስጠት ከሥራ አጥነት አላቅቄያቸዋለሁ” በማለት ያካፈለኝን የሕይወት ታሪኩን ስመዝነው ዓላማና ግቡ የሰመረለት እንዲሁም ፈተናን ወደቀጣዩ የሕይወት ምዕራፍ መሻገሪያ አድርጎ የቆጠረና ሲቸገር መላ መፍጠርን፣ ሲናደድ ቶሎ መብረድን መርሕ ያደረገ ብርቱ ወጣት በመሆኑ ‹‹እደግ ተመንደግ›› ስል ምኞቴን ቸርኩት።

ሀብታሙ ባንታየሁ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You