ይህንን ጽሑፍ የሚመለከት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወጣት ቀጣዩን ሃሳብ በአዕ ምሮው እንዲያሰላስል እፈልጋለሁ። ለመሆኑ ተሰጥኦውን፣ ድምጹን፣ ልዩ የሆነ ኢትዮጵያዊ ችሎታውን፣ የፈጠራ ሃሳቡን፣ ንግዱን እና መፍትሔ አመላካች ሃሳቦቹን ከአካባቢው፣ ከሰፈሩ፣ ከከተማው አሊያም ከሀገሩ አልፎ ውቅያኖሶችን እና አህጉራትን ተሻግሮ ተፅዕኖ እንዲያሳድር የማይፈልግ ወጣት ይኖራል? ይህ ዓይነት እድል ለተመረጡት ጥቂት ሰዎች የተተወ ሕልም ብቻ ይሆን? ለመሆኑ ስንቶቻችን ነን ይህንን ሃሳብ ለራሳችን ጠይቀን የምናውቀው? መሰል ጥያቄዎች በብዙ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች እንደሚነሳ እገምታለሁ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዓለም ከመቼውም ጊዜ በላይ እርስ በርስ የተቆራኘች ሆናለች። በእዚህ መድረክ ላይ ደግሞ ሁሉም የራሱን ተፅዕኖ መፍጠር ይፈልጋል። የኢትዮጵያ ወጣቶች ወደ ዓለም አቀፋዊ መድረክ የመውጣት አስደናቂ አቅም አላቸው ብዬ አስባለሁ። ብሩህ አዕምሮ፣ አስደናቂ ባሕላዊ እሴት የፈጠራ ሃሳብ እንዳላቸውም ይሰማኛል። ነገር ግን አብዛኛዎቹ አቅም ያላቸው ወጣቶች ዓለም አቀፍ መድረኮችን በብዛት ሲቆጣጠሩ ማየት የተለመደ አይደለም። ይህ እውነታ ሊቀየር ይገባል።
ለመሆኑ በምን መልኩ ይሆን የፈጠራ ሃሳቦቻችንን፣ የንግድ ክህሎታችንን፣ ሳይንሳዊ እውቀታችንን እና የትኛውንም ዓይነት ለምድ ራችን ጠቃሚ የሆኑ ሃሳቦችን በዓለም መድረኮች ላይ በማውጣት ተፅዕኖና ድጋፍ ማግኘት የምንችለው? ይህ ጥያቄ ቀላል መልስ ነው ያለው። የመጀመሪያው ርምጃችንንም ሆነ ሥራችንን በማህበረሰባችን ውስጥ መጀመር ነው።
በአካባቢያችን መሠረት እንጣል
ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖን መፍጠር የሚፈልግ አንድ ወጣት የመጀመሪያው የጉዞው ርምጃ መሆን ያለበት አካባቢው ነው። ዓለም አቀፋዊ ጉዞ የሚጀምረው ካለንበት ማህበረሰብ እና መንደር ውስጥ ነው። የአካባቢያችንን ማህበረሰብ እንደ ጥሩ ልምድ ማግኛ ቦታ መውሰድ አለብን። በአንድ ጊዜ የዓለምን ችግር ልንፈታ፣ የምድራችንን አሳሳቢ ጉዳይ እልባት ልንሰጥ አንችልም። በመሆኑም በዙሪያችን ባለው ማህበረሰብ ውስጥ ምን ችግሮች ይታየናል? ምን የመፍትሔ ሃሳቦችስ አሉን? ዓለም የሚፈልጋቸው ልዩ ችሎታዎችስ የትኞቹ ናቸው? የሚሉ ጥያቄዎችን ለራሳችን እያነሳን ያለንን አቅም መለካት ይኖርብናል።
ለምሳሌ፡- የቡና ማሳ ያለው ገበሬ ልጅ ምርትን ለማሻሻል የሚያስችል አዲስ ቴክኖሎጂን ሊፈጥር ይችላል፤ ወይንም የአካባቢ ብክለትን የሚከላከል እና ኃይል ቆጣቢ መሣሪያን መፍጠር ሊሆን ይችላል። ይህንን መሰል የምንኖርበትን ማህበረሰብ እና የቤተሰቦቻችንን ችግር መፍታት የሚችሉ እውነተኛ ሃሳቦችና ፈጠራዎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን የሚያሰጡ እና ትኩረትን በቀላሉ መያዝ የሚችሉ ናቸው።
ዲጂታል ፓስፖርት
ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነት አሊያም እውቅናን ለማግኘት የግዴታ ወደ ተለያዩ ሀገሮች መጓዝን፣ በትላልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት መሥራትን አይጠይቅም። በአጭሩ ተፅዕኖ ፈጣሪነት የሚገኘው በአውሮፕላን ትኬት አይደለም። ከእዚያ ይልቅ በዲጂታሉ ዓለም ላይ የሚኖረን የአጠቃቀም እውቀትና ራስን የማስተዋወቅ ደረጃ ወሳኝ ነው። ብዙውን ጊዜ የበይነ መረብ ግንኙነት መፍጠር እና በጥበብ የመጠቀም ችሎታዎች ማዳበር አንድ ኢትዮጵያዊ ወጣት ሊማረው የሚገባው ትርጉም ያለው ክህሎት ነው። ይህ ክህሎት የወጣቶች ዲጂታል ፓስፖርት ነው።
ወጣቶች ችሎታቸውን፣ የፈጠራና የንግድ ሃሳባቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ እና ተቀባይነት ለማግኘት ዲጂታል አማራጭን መጠቀም ይገባቸዋል። በዲጂታል አማራጭ ውስጥ ራሳችንን ዓለም አቀፋዊ ለማድረግና ስኬታማ ለመሆን በርካታ መንገዶች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ነፃ የትምህርት እድል መጠቀም ነው። በምድራችን ላይ ከመቼውም ጊዜ በላይ ይህን ያህል እውቀት በነፃነት ተደራሽ ሆኖ አያውቅም። እንደ “Coursera፣ edX፣ Khan Academy እና YouTube” ያሉ መድረኮች በሁሉም ነገር ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ትምህርቶች ተደራሽ ያደርጋሉ። ከላቀ የኮምፒውተር ሳይንስ (ኮድ እና ዳታ ሳይንስ) እስከ ዲጂታል ግብይት፣ ግራፊክ ዲዛይን፣ የፈጠራ ጽሑፍ እና የዓለም አቀፍ የንግድ ልምዶችን በእውቀት የሚያስጨብጡ ትምህርቶችን ማግኘት ይቻላል። ይህንን እድል ማግኘት ደግሞ በቀላሉ በዓለም ዙሪያ ካሉ ወጣቶች ጋር ለመወዳደር ይጠቅማል። በአካባቢያችን ያሉ ውስን የትምህርት አማራጮች እና እድሎች አንቀው እንዲያስቀሩን እና እንዲይዙን አንፍቀድ። ለከፍተኛ ችሎታ እና ቀጣይነት ላለው ትምህርት ጊዜያችንን ያለማቋረጥ (በቀን አንድ ሰዓትም ቢሆን) እንስጥ።
ወጣቶች ዓለም አቀፍ በጎ እውቅናን ለማካበት ሊጠቀሙበት ከሚገባው መንገዶች ውስጥ አንደ ኛው ማህበራዊ ሚዲያ ነው። ይህንን አማራጭ ጓደኞቻችንን ከማውራት የዘለለ ትርጉም ላለው ነገር መጠቀም ያስፈልጋል። እንደ ሊንክድን (LinkedIn) ያሉ መድረኮችን ሙያዊ አቅማችንን ለመላው ዓለም ተደራሽ ለማድረግና መልካም የሥራ ግንኙነት ለመፍጠር ልንጠቀምባቸው ይገባል። ችሎታችንን ለሰው ልጆች ሕይወት መሻሻል የሚጠቅሙ የፈጠራ ሥራዎቻችንን የሚያጎሉ ጠንካራ ግለ ታሪክን በእነዚህ ማህበራዊ መድረኮች በመገንባትና በመረጃ በማያያዝ አቅማችንን ማሳየት ያስፈልጋል።
ችሎታችንንና የማድረግ አቅማችንን በማስ ተዋወቅ ከአካባቢያችን እንዲሁም ከሀገራችን በተሻገረ መልኩ ተፅዕኖ ማድረግ ያስፈልጋል። ለእዚህም ምሳሌ የሚሆኑ ከተለያዩ ሀገራት የወጡ ታዋቂ ግለሰቦች ይኖራሉ። ከእነሱ ጋር ግንኙነት መፍጠር እና መማርም ያስፈልጋል። ማህበራዊ ሚዲያ ለእዚህ ጥረታችን ትልቁን እድል ይሰጠናል። በቀላሉ ከሰዎች ጋር ያለ ገደብ ወዳጅነት መፍጠር እንድንችል አማራጭ ይሰጠናል።
በሥራዎቻችን ተፅዕኖ ፈጣሪ ለመሆንና ዓለም አቀፍ እውቅናን ለማግኘት ብዙ መረዳት ያሉብን ጉዳዮች አሉ። ከእነዚህ ጉዳዮች መካከል ዓለም አቀፋዊ ግንዛቤን ማዳበር ነው። ይህ ማለት እኛ ከሚኖረን እውቀት እና ችሎታ ጋር የሚገናኝ እውቀት፣ አስተሳሰብ እንዲሁም ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ራሳችንን ልናግባባ ይገባል። በተለይ ዓለማችን ላይ አጀንዳ የሆኑ እና የእኛን ጥረት፣ የፈጠራ ውጤት እና አቅም የሚጠይቁ አጀንዳዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ሰዎች “በቴክኖሎጂ፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በሥነ ጥበብ ወይም በቢዝነስ በዓለም ዙሪያ የሚያወሩት ምንድን ነው? የእኔ ችሎታ እና አቅምስ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?” በማለት መጠየቅ ያስፈልጋል። ይህን መመለስ ከቻልን እና ዓለም አቀፍ መረጃዎችን በቀላሉ ካገኘን ራሳችንን ከሁኔታዎች ጋር ለማግባባት እና የራሳችንን አሻራ ለማሳረፍ አይከብደንም።
ሌላው የሚያስፈልገን አቅም በራስ መተማመን በእውነተኛነት ላይ የተመሠረተ ጥረት ነው። ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ መፍጠር የሚያስችል ስብዕናን ለመገንባት ሌሎችን መምሰል አያስፈልግም። ኢትዮጵያዊ ማንነትህ፣ የራሳችንን አቅም፣ በአካባቢያችን ያገኘነው ግንዛቤና ጥንካሬዎች በቂ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪ ስኬታማና ተፅዕኖ ፈጣሪ ለመሆን በምናደርገው ጉዞ ላይ ጽናትና ትዕግስት ከምንም ነገር በላይ አስፈላጊ ነው።
ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነት እና አቅምን መገንባት ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። ብዙ ጊዜ ሥራዎቻችንን ለማስተዋወቅ፣ አቅማችንን ለማሳየት፣ ንግዳችንን ስኬታማ ለማድረግ ሞክረን ላይሳካልን ይችላል። ከእነዚህ አጋጣሚዎች ጋር ስንጋፈጥ ወፍራም ቆዳ ሊኖረን ይገባል። በተለይ ትችትን ገንቢ በሆነ መንገድ መቀበል መማር አለብን።
እዚህ ጋር ራሳችንን አንድ ነገር መጠየቅ ይኖርብናል። “እኔ መፍታት የምችለው የማህ በረሰብ ችግር ምንድነው” የሚል ነው። በማህበረሰብዎ ውስጥ ያለውን ልዩ ፈተና መለየት ይኖርብናል። ለእዚያ ደግሞ አቅምና ችሎታችንን ተጠቅመን እውነተኛ መፍትሔ ልናዘጋጅ ይገባል። ምናልባት አንድ ውስብስብ መንገድን የሚያስቀር የሞባይል መተግበሪያ ሊሆን ይችላል፤ ለኅብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጥ የግብርና ቴክኖሎጂም ሊሆን ይችላል፤ አሊያም ደግሞ ለታዳጊዎች የሚረዳ የትምህርት መሣሪያ መፍጠርም ይሆናል። እነዚህን እውነተኛ መፍትሔዎች ስናመጣ የራሳችንን የማህበረሰብ ችግር ከመፍታት ይሻገራል።
ተመሳሳይ የሆነ ችግሮች በሌሎችም የዓለ ማችን ክፍሎች ይኖራሉ፤ በእዚህ ወቅት የእኛ የመፍትሔ ሃሳብና የፈጠራ ሥራ ዓለም አቀፋዊ በሆነ መንገድ ተፅዕኖ ያሳድራል። ተፈላጊነታችንም በእዚያው ልክ ያድጋል። ለእዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን ዓለም ላይ ቢሊዮኖች የሚጠቀሙት በርካታ የፈጠራ ሥራዎች በአንድ መንደር፣ በአንዲት ቤት ውስጥ ራዕይ እና ጽናት ባላቸው ጥቂት ግለሰቦች ነው።
በሌላ መልኩ ዓለም አቀፍ እውቅናን ወይም ተፅዕኖ ፈጣሪነት የምናገኝበት አንዱ መንገድ ለራሳችን ባሕል፣ ማንነት እንዲሁም ኢትዮጵያዊ እሴት ድልድይ ስንሆን ነው። ኢትዮጵያዊ ታሪካችንን፣ የኪነጥበብ ሀብታችንን፣ ሙዚቃዎቻችንን፣ አመለካከቶቻችንን ለዓለም አቀፍ ተመልካቾች ተደራሽ እና ማራኪ በሆነ መልኩ ማካፈለ አለበን። ይህ በሥራችን የባሕል አምባሳደር እንድንሆን ከማድረጉም ባሻገር ተፅዕኖ ፈጣሪነታችን እንዲጨምር ያደርጋል።
ከአካባቢያችን፣ ከከተማችን ማህበረሰብ አልፈን ወደ ዓለም አቀፋዊ መድረኮች የምናደርገው ጉዞ ማንነታችንን የሚያዘናጋን ኢትዮጵያን ወደ ኋላ የሚያስተወን መሆን የለበትም። ኢትዮጵያን ከእያንዳንዱ ስኬታችን ጋር ልናዋህዳት ይገባል። ሁሌም በመማር ውስጥ፣ ከአዳዲስ ሰዎች ጋር በመተዋወቅ እና ለማህበረሰባችን በመቆርቆር ሂደት ማለፍ ይኖርብናል። ለመማር ደግሞ ራሳችን ላይ ኢንቨስት ማድረግ አለብን፤ ዲጂታል መሣሪያዎችን የመጠቀም ልምድ ልናካብት ያስፈልጋል። ችግሮችን የመቋቋም አቅም መገንባት ይኖርብናል።
በመጨረሻም ይህንን ለማለት እወዳለሁ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት መጀመሪያ ካለህበት ጀምር። በሀገር ውስጥ ትርጉም ያለው ነገር ሥራ፣ ይህ ጉዞህ በእር ግጠኝነት ወደ ዓለም አቀፋዊ ማንነትና ስብእና ግንባታ ይወስድሀል። ለእዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴ ነው። ከትንሹ መንደር የጀመረው ጥረቱና ልፋቱ ቀስ በቀስ እያደገ ዓለም አቀፋዊ እውቅናን፣ ድልን እና የንግድ ስኬቶችን አስገኝቶለታል።
አንተም ዝም ብለህ አትመልከት፤ ሕል ምህን እውን ለማድረግ ከመንደርህ ጀምር። ትኩረትህ አይበተን በዓላማህ ውስጥ ጽናትን እና አይበገሬነትን ገንባ። ችሎታህን አሳድግ፣ አስተሳሰብሀን አሳድግ፣ ብልጥ እና አቅሙን አሟጦ የሚጠቀም ሰው ሁን። ዛሬ የተከልከው ችግኝ ነገ ዛፍ እንደሚሆነው ሁሉ፤ አካባቢህ ላይ የጀመርከው ጥረት እና ችግር ፈቺ ፣ መፍትሔ ሰጪ ለነገ የሰው ልጆች ተግዳሮት፣ መከራ የሚያቀል የአንተንም ተፅዕኖ ፈጣሪነት የሚያጎላ ይሆናል። አትጠራጠር!!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም