ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በአንድ ሀገር ውስጥ የተማረን ዜጋ ከማፍራት ባሻገር የሚፈጠሩ ልዩ ልዩ ችግሮችንና ማነቆዎችን መፍቻ የዕውቀት በሮች ቁልፍ ናቸው። የአንድ ሀገር ጥንካሬም ሆነ ድክመት የሚመሰረተው በእነዚሁ ተቋማት ድክመትና ጥንካሬ ላይ ነው።
ወደ ሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለስ በሀገሪቱ ያሉት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሀገሪቱ ያጋጠሟትን ችግሮች በጥናትና በምርምር አስደግፎ ከመፍታት እና የመፍትሄ አካል ከመሆን ይልቅ ዋነኞቹ የችግር መፍለቂያ ማዕከላት ሲሆኑ ተስተውለዋል። ብጥብጥ ሁከት በብሄርና ሃይማኖት ጎራ ለይቶ መጠዛጠዝ ሙስና እና ብልሹ አሰራር የትምህርት ጥራት ችግር የዩኒቨርሲቲዎቻችን መገለጫዎቻችን ከሆኑ ውለው አድረዋል።
በአጠቃላይ ዓለምአቀፋዊ ተልዕኮ ያለው የከፍተኛ ትምህርት ዛሬ አካባቢያዊነት ወርሶት ተፈጥሯዊ ባህሪውን አጥቷል። አድማሳዊ አስተሳሰብና ዕውቀት ጠፍቶ አካባቢያዊነት ወርሶት ይታያል። ችግሮቹ ጥልቅና ውስብስብ ቢመስሉም ሁሉም አካላት ዩኒቨርሲቲዎቻችንን ከገቡበት አዘቅት ውስጥ ለማውጣት ጥረት ካደረጉ ግን የማይቻል ነገር የለም ብሎ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ያምናል። የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል በተደጋጋሚ በችግሮቹ ዙሪያ ሰፋፊ ዘገባዎችን ሲያቀርብ የቆየና ችግሮቹን በቅርበት የሚያውቃቸው በመሆኑ በግልጽ የሚታዩት የመፍትሄ ሃሳቦችም አሉት።
የመጀመሪያው ጉዳይ በዩኒቨርሲቲዎች የሚታየውን መልካም አስተዳደርና ብልሹ አሰራሮችን ጊዜ ሳይሰጣቸው መፍትሄ ሊበጅላቸው ይገባል። የመልካም አስተዳደርና ብልሹ አሰራር የሰፈነበት ዩኒቨርሲቲ የግጭት ማዕከል መሆኑ አይቀርምና። በሙስናና በብልሹ አሰራር ውስጥ የተዘፈቁ አመራሮች እኩይ ተግባራቸው እንዳይታወቅባቸው በግጭት ውስጥ ተደብቀው መኖርን ስለሚመርጡ ሰላምን ከማስፈን ይልቅ የግጭጥና ሁከት ፈልፋይ ማሽኖች መሆናቸው አይቀሬ ነው። ስለሆነም ዩኒቨርስቲዎቻችን መልካም አስተዳደር የሰፈነባቸው፤ ከብልሹ አሰራርና ሙስና የነጻ ሊሆኑ ይገባል።
ሁለተኛው ጉዳይ የዩኒቨርሲቲዎችን አካዳሚክ ነጻነት ሙሉ ለሙሉ ማረጋገጥ ነው። በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚታየው ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት የመማር ማስተማሩን ሂደት በማወክ ዩኒቨርሲቲዎች ከተሰጣቸው ተልዕኮ ውጭ የፖለቲካ መራኮቻ ማዕከል እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። ለፖለቲካው ቅርበት ያላቸው እንዲሾሙና እንዲሸለሙ ፤ፖለቲካው ውስጥ የሌሉና አካዳሚው ላይ የሚያተኩሩት እንዲረሱና በትምህርት ሥርዓቱም ላይ ተስፋ እንዲቆርጡ ስለሚያደርግ ዩኒቨርሲቲዎች ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት የጸዱ ሊሆኑ ይገባል።
ሶስተኛው ጉዳይ ዩኒቨርሲቲዎች ጥብቅ በሆነ ህግና ደንብ እንዲተዳደሩ ማድረግ ነው። ተማሪዎች በብሄር ተቧድነው ሲገዳደሉ፣ በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ሲያምጹ፤ የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖችን ተልዕኮ ሊያስፈጽሙ ሲሯሯጡ እና በመሰል አስከፊ ተግባራት ውስጥ ገብተው ሲገኙ የሚወሰደው እርምጃ ሌሎች ተማሪዎች ነገ በተመሳሳይ ተግባር ወስጥ እንዳይገቡ ትምህርት የሚሰጥ አይደለም። አስተማሪዎችም ቢሆኑ በጎሳና በብሄር ተቧድነው የእኔ ነው ለሚሉት ያልሰራውን ውጤት ሲያሸክሙ፤ የለፋውን ሲጎዱ፤ በክፍል ውስጥ ከትምህርት ይልቅ ፖለቲካ ሲሰብኩ ሃይ ባይ ያላቸው አይመስልም። ስለዚህም በዩኒቨርሲቲዎቻችን ውስጥ ህግና ደንብ ይከበር።
አራተኛው ጉዳይ ዩኒቨርሲቲዎች ግጭቶች እንዳይከሰቱ ነቅቶ መጠበቅ ከተከሰቱም በኋላ ቶሎ ፈር የማስያዝ ችግር በስፋት ይታያል። አንዱ ዩኒቨርሲቲ ግጭት ሲነሳ ወደ ሌላው እንዳይዛመት ቅድመ ጥንቃቄ የማድረግና የተነሳውንም ግጭት ባለበት መፍትሄ የመስጠት ጉድለቶች ይታያሉ። እነዚህና መሰል ችግሮች በአግባቡ ተለይተው መፍትሄ ከተበጀላቸው የ2012 የትምህርት ዘመን ሰላማዊ እንደሚሆን የዝግጅት ክፍላችን ያምናል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 25/2011