ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በአገር ደረጃ ችግር መሆኑ ግንዛቤ ተይዞበት መፍትሄ ለማበጀትና ሰለባዎችን ለመታደግ በመንግሥት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ይገኛል። መንግሥት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትና በሕግ ማዕቀፍ ለማስደገፍ ሲል እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ በተለይ ለቤት ሠራተኝነት ወደ መካከለኛው ምሥራቅና ሌሎች አገራት የሚደረገውን ጉዞ አግዶ መቆየቱ ይታወሳል።
በአሁኑ ወቅትም የታሰበው የውጭ አገር የሥራ ስምሪት ሕግ በተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ወደሥራ ተገብቷል። ወደ ውጭ ሀገር ወጥተው ለመስራት የሚፈልጉ ዜጎች መስፈርቱን አሟልተው፤ ሕጋዊውን መንገድ ተከትለው እንዲሄዱ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል። እናም ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ ከጥቂት አገራት መንግሥታት ጋር ስምምነት ተደርሶ ውል ተፈጽሟል።
ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስም እንዲሁ! ይሁን እንጂ፤ እስካሁን ድረስ ወደተባበሩት አረብ ኤምሬትስ/ዱባይ የሚደረገው የሕገወጥ ዝውውር መልኩን ቀይሮ ተከስቷል። በዚህም ብዙዎች ተጎድተዋል፤ በተለይ ከገጠር የሚመጡ በርካታ እንስት በአዲስ አበባና፤ በውጭ አገር አየር ማረፊያዎች ውስጥ የደም እንባ እያለቀሱ ይገኛሉ።
ይህ ሕገወጥነት ምንም ዓይነት ፈቃድና እውቅና የሌላቸው በሕጋዊ ኤጀንሲዎች ጥላ ስር ተጠልለው የሠራተኛ ኃይል በማቅረብ በተካኑ ደላሎች የሚሰራ ነው። የነዚህ ወገኖች ዓላማ ገንዘብ ማፍራት ብቻ በመሆኑ የቱሪስትና የጉብኝት ቪዛና ቲኬት በማስመጣት በጉጉት ለተሞሉ ልጆች በመስጠት ይከናወናል።
ሕገወጥነቱ የሚጋለጠው አብዛኛውን ጊዜ ተጓዦቹ ከአገር ወጥተው ከመዳረሻቸው አየር ማረፊያ ሲረግጡ ነው። የሄዱት በቱሪስት ቪዛ ቢሆንም፤ ተቀባይና አስጎብኝ የላቸውምና እንግልቱ በዚያ ይጀምራል። በዚህ ረገድ በአሁኑ ወቅት በተለይ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ/ዱባይ ላይ የሚ ታየው ችግርና የሚ ሰማው ሰቆቃ ብዙዎችን ያ ሳዝናል።
መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሕገወጥ መንገድ ከአገር ወጥተው በተለያዩ የአረብ አገራትና በጎረቤቶቻችን ለእስርና ለአደጋ ተዳርገው የነበሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችንን በከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረት ወደአገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉን እንደ ትልቅ ስኬት እናየዋለን።
] ከዚህ በኋላም የዜጎች ወደ ውጭ ሀገር የመውጣት ጉዳይ አንድ ነገር ሆኖ፤ በሚሄዱበት አገር ግን ሰብዐዊና ሕጋዊ መብቶቻቸው ተከብረው እንዲኖሩና እንዲሰሩ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ለማድረግ የሕግ ማዕቀፍ አዘጋጅቶ፤ ከተቀባይ አገራትም ጋር በወል ጥቅም ላይ የተመሰረተ ስምምነት በማድረግ ጥቅማቸውንና ክብራቸውን ለማስጠበቅ ይሰራል።
በአገር አቀፍ ደረጃም ሕገወጥ የሰዎችን ዝውውር የሚከላከል ብሔራዊ ግብረ ኃይል ተቋቁሟል። ግብረ ኃይሉ በእስካሁኑ ሂደት የሰራቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ። በዚያው ልክ ግን ሕገወጡ አሠራር በሕጋዊነት ሽፋን መካሄዱን ቀጥሏል። ዜጎች በውጭ አገር በሕጋዊም ሆነ በሕገወጥ መንገድ ሲንገላቱ በዚያ ወይም በአቅራቢያ ባለው ኤምባሲ ወይም ቆንስላ ጽሕፈት ቤት የመደገፍ መብት አላቸው።
ሕጉም ይደግፋቸዋል። የሚበልጠውና ውጤቱ የሚያምረው ግን ሕጋዊ መሠረት ያለው፤ በውል የታሰረ፤ መብትና ግዴታን ያጣመረ የጉዞ አቅጣጫና አፈጻጸም ሲኖረው ብቻ ነው። ምክንያቱም፤ ሕጋዊው ማዕቀፍ በቀጣሪውም ሆነ በተቀጣሪው ላይ የሚያሳድረው
ለሕግ የማደር ተፅዕኖ አለውና!
የአሁኑ የዜጎች ወደ ውጭ አገር ለሥራ መሄድ ቀደም ሲል እንደነበረው እነርሱን ሥራ የማስያዝ ዕድል ፈጠራ ብቻ ተደርጎ ሊታይ አይገባም። ይልቁንም፤ የተቀባዩ አገር በተለያዩ ሙያዎች ያለበትን የሰው ኃይል እጥረት የመሙላት ጭምር እንጂ፤ ጥቅሙ የጋራ ነው። በዚህ ረገድ ለዜጎች ትምህርት መስጠት፤ አስተሳሰብን መለወጥና «ተፈላጊዎች ነን» የሚል ሥነልቦና አዳብረው በሕጋዊ መንገድ ብቻ እንዲጓዙ ግንዛቤ ማስጨበጥ ያስፈልጋል። ከዚህም መጀመር አለበት እንላለን።
በተለይ ከቤት ሠራተኝነት ጀምሮ በተለያዩ መስኮች ላይ ተቀጥረው እንጀራ ለመብላትና ጥሪት ለማፍራት የሚንቀሳቀሱ ዜጎች በእውቀት ላይ የተመሰረተ ተግባር ማከናወን ይገባቸዋል። የመጀመሪያው የሕጋዊውን መንገድ አካሄድና ጥቅም መረዳት፤ በዚህም ከነጣቂ ሕገወጥ ደላሎች ራሳቸውን መጠበቅ፤ በውጭ አገር ለመኖርና ለመስራት የሚያስፈልጋቸውን ክህሎት መታጠቅ ይኖርባቸዋል።
በዚህ ረገድ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደተቋም ትልቅ ኃላፊነት አለበት። ዜጎችን በማስተማርና ሕጋዊ ከሚመስሉ ሕገወጦች ራሳቸውን እንዲጠብቁ በሰፊው ሊያስተምር ይገባል። አገር አቀፉ ግብረኃይልም መልኩን እየለዋወጠ በሚከሰተው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር አብዛኞቹ ተጎጂዎች የሚወጡባቸው ክልሎችና አካባቢዎች የሚታወቁ በመሆናቸው እስከዚያ ድረስ በመውረድ በተለይ የገጠሩን ማህበረሰብ በማስተማር የባህሪይ ለውጥ እንዲመጣ መስራት ያስፈልገዋል።
በተለይ በአሁኑ ወቅት ወደተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሚደረገው ጉዞ በሕጋዊ የውል ስምምነት የታሰረ በመሆኑ ምቹ ሁኔታ ስለመፈጠሩ ብስራት ነው። በውሉ መሠረትም ከቤት ሠራተኝነት ጀምሮ በተለያዩ ሙያዎች የተማሩ ዜጎችን ለመቀበል፤ የሚደረገው ምዝገባም በቀጥታ በኢንተርኔት ነው።
እናም ይህ መልካም ዕድል በመፈጠሩ ባጠቃላይ ማህበረሰቡ፤ በተለይ ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦችና የእምነት አባቶች፤ ሚኒስቴሩም የማህበረሰቡን አስተሳሰብ ለመለወጥ ግብረኃይሉን ሊያግዙት ይገባል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ቤተሰብ ልጆቹ ተፈላጊው እውቀትና ክህሎት ካላቸውና ሕጋዊውን መስፈርት ካሟሉ ሕጋዊው መንገድ የቪዛም ይሁን የቲኬት ወጪ የሌለው መሆኑን አውቆ ጥሪቱን ከማሟጠጥ ሊጠበቅ ይገባል። ወጣቶችም አቋራጭ መንገድ ከመሻትና ራስን ለኪሳራና ለአደጋ ከማጋለጥ በፊት እንቅስቃሴቸውን ሁሉ በትዕግስት አጅበው በጥሞና አስበው ሕጋዊውን መንገድ ተከትለው ፍላጎታቸውን እንዲያሟሉ ሊመከሩ ይገባል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 24/2011