
“ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለት ስለሚያሳቅቀኝ ኤርትራዊ ወይም የሶማሌ ተወላጅ ነኝ እላለሁ” የምትለዋ ወጣት መሰለች ወርቁ፤ በተደጋጋሚ ወደ ዱባይ ስትመላለስ የኢትዮጵያውያንን ስቃይ ማየት እንዳንገፈገፋት ትናገራለች።
እንደመሰለች ገለፃ፤ የዜጎችን ሰቆቃ ማየቱ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞች ተርሚናል ይጀምራል። ከኦሮሚያ ክልል ከጅማ፤ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከሃዋሳና ከወላይታ፣ ከአማራ እና ከሌሎችም ክልሎች፤ በተለይ ከከሚሴ አካባቢ በደላሎች የተጭበረበሩ ሴቶች አዲስ አበባ ደርሰው ወደ ዱባይ እስኪሳፈሩ ያለበቂ ምግብና ውሃ እየተሰቃዩ ይጠብቃሉ።
በአንድ ክፍል ታጉረው ለቀናት ይቆያሉ። ፅዳታቸው ሳይጠበቅ የተቀቡትን ቅቤ ሳይታጠቡ፤ ደላላው የጉብኝት ቪዛ እና የመሄጃ ትኬት ብቻ ሰጥቷቸው ቦሌ አየር ማረፊያ ጥሏቸው ይሄዳል። እንደሌላው ሰው ለመሳፈር ሲጠጉ መጓዝ እንደማይችሉ ሲነገራቸው እንባቸውን ማፍሰስ ይጀምራሉ።
ከአገራቸው ወደዱባይ ለመሄድ መውጣታቸ ውን፤ ቤተሰብ መተዳደሪያ በሬውን እና መሬቱን ሸጦ እንደላከላቸው ይገልፃሉ። የሚሰማ ቸው የለም። የፀጥታ ሃይል “ለጉብኝት ከሆነ ትኬቱ የደርሶ መልስ መሆን አለበት::” እያለ እንዲመለሱ ሲያስገድዳቸው፤ መሬት ላይ እየተጎተቱ “አልወጣም፤ ብትፈልጉ ግደሉኝ” በማለት ያለቅሳሉ። በዚያ ያሉት የፀጥታ ሃይሎቹ “ያመጣችሁ ደላላ ማን ነው?” ብሎ ሴቶቹን አረጋግቶ ከመጠየቅ ይልቅ አመናጭቆ ማስወጣትን ይመርጣሉ።
ያንን አምቧጓሮ መሰል ትዕይንት ሲያዩ ቆይተው የተሳፈሩት እነመሰለች፤ ዱባይ ሲደርሱ የደርሶ መልስ ትኬት ተቆርጦላቸው አብረዋቸው የተሳፈሩት ሴቶች ደግሞ ዱባይ ሲደርሱ ተቀባይ አጥተው የዱባይ ፖሊሶች ሲያዋክቧቸው ይመለከታሉ።
ሌሎች ግራ የተጋቡ ርዳታ ያጡ ኢትዮጵያዊያን ሴቶችም ያገኛሉ። አንዳንዶቹ በዚያው በዱባይ አየር መንገድ የሚቀበላቸው አጥተው የሚጠጣ ውሃና የሚመገቡት ምግብ ለማግኘት አይናቸውን እያንከባለሉ ሲለማ መጧቸው ለመርዳት ቢመኙም የሌላ አገር ሰው መስለው ያልፋሉ።
እንደመሰለች ገለፃ፤ እነርሱን ለመርዳት ካነጋገሯቸው “ያመጣሻቸው ደላላዋ አንቺ ነሽ” በሚል ወደ እስር ቤት እስከመወሰድ ይደር ሳሉ። ኢትዮጵያውያኑም ልርዳችሁ በማለት ሲጠጓቸው “አልለቅሽም፤ ቤትሽ ውሰጂኝ፤ አኑሪኝ እና አስቀጥሪኝ” በማለት ከአቅም በላይ የሆኑ ጥያቄዎችን ያቀርባሉ። ይህንን በመፍራት እነመሰለች መተኛ አጥተው በቀዝቃዛ ሴራሚክ ላይ እያደሩ የሚንገላቱትን ኢትዮጵያውያን ነጋቸውን የሚያጨልም በሽታ እንደሚይዛቸው ቢያውቁም፤ አይናቸው እያየ እንዳለዩ ሆነው እያዘኑ አልፈው ይሄዳሉ።
ተጓዦቹ ወደ አየር መንገዱ የሚሄዱት “ዱባይ ደርሰን፤ በቤት ሰራተኝነት ሰርተን፤ ቤተሰባችንን እና ራሳችንን እንለውጣለን” ብለው ነው። ደላሎቹ የሚነግሯቸው ይህንን ቢሆንም የሚሄዱት በጉብኝት ቪዛ ሲሆን፤ እዚያ ሲደርሱ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለው ሁሉ የቤት ሰራተኛ በደላላ መቅጠር የሚፈልግ ሰው እየመረጠ ይወስዳቸዋል።
የቪዛ ጊዜያቸው እስከሚያልቅ ወሳጅ ያጡት፤ አንዳንዶቹ ሴቶች የጉበት በሽታ አለብሽ፤ ነፍሰጡር ነሽ እና የተለያዩ ምክንያቶች እየተሰጣቸው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ይደረጋል። ጥቂት የማይባሉት ትልቅ ተስፋ አድርገው ወጥተው፤ ዱባይ የሚያገኙት ያልጠበቁት ሲሆንባቸው አዕምሯቸው መቀበል አቅቶት እስከማበድ ይደርሳሉ። በደህና ከቤት የወጡት ልጆች በሽተኛ ሆነው ሲመለሱም እነመሰለች አይተዋል።
“ይህንን ለማረጋገጥ የዱባይ በረራ ሲኖር በየቀኑ ከሰኞ እስከ ሰኞ ቦሌ አየር ማረፊያ ሄዶ ማየት ይቻለል። ኤሜግሬሽን “መሄድ አትችሉም” ከማለት ውጪ የሚሰራው ነገር የለም። ፖሊሶችም መርምረው ሴቶቹን ከአገራቸው ያስመጧቸውን ደላሎች ከመያዝ ይልቅ ሴቶቹን “ህጋዊ አይደለሽም” ብሎ ከማባረር ውጪ ምንጩን ማድረቅ አልቻሉም።
ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ “ወደዚህ አገር ለሥራ መሄድ አይቻልም፤ መሄድ ያለባችሁ ስልጠና ወስዳችሁ በህጋዊ መንገድ መሆን አለበት።” ከማለት ባሻገር ለስራ ብለው ስለሚንከራተቱት ዜጎች የሚጨነቅ አይመስልም። ኤንባሲዎችና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ከውጪ የታሰሩትን ሰዎች ከማስመጣት እና አትሂዱ ብሎ ትምህርት ከመስጠት በዘለለ፤ ዜጎች ወደውጪ እንዳይሄዱ ደላሎችን በማስቆም በኩል ሚናቸውን እየተወጡ አይደሉም፤” ትላለች ወጣት መሰለች።
በሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በውጪ አገር ሥራ ስምሪት የትምህርት እና ሥልጠና ክትትልና ድጋፍ ቡድን መሪ አቶ ወንድሙ ሃይሉ እንደሚገልፁት፤ አሁን ለስራ መሄድ የሚቻለው ወደ ሳውዲ አረቢያ፣ ኳታር እና ጆርዳን ብቻ ነው። ሆኖም፤ ህጋዊ ጉብኝት በሚል ስም ለቤት ሰራተኝነት ወደ ዱባይ የሚሄዱ መኖራቸው ይታወቃል። ያንን ለመከላከል ከኤሜግሬሽን ጋር በመተባበር ከአገር እንዳይወጡ ይከለከላሉ። ያም ሆኖ አታልለው የሚያልፉ ያጋጥማሉ። ነገር ግን ተቋሙ በህጋዊ መንገድ ወደተፈቀደበት አገር ብቻ እንዲሄዱ በማስተማር ላይ ይገኛል።
“ለቤት ሰራተኝነት የሚሄዱ ዜጎች ስልጠና ወስደው፤ ተፈትነው፤ ተመልምለው ዝግጁ መሆናቸ ውን የሚያረጋግጥ ቢጫ ወረቀት ካገኙ በኋላ አሰሪውን ወክለው ከሚፈራረሙ ህጋዊ ኤጀንሲዎች ጋር ውል ገብተው መሆን አለበት። በሰው አገር ሄደው ለሚያጋጥማቸው ሁሉ ኤጀንሲው ተጠያቂ ይሆናል። ከዚህ ውጪ በህገወጥ መንገድ የሚሄዱትን ቢቻል ከኤርፖርት እንዲመለሱ ይደረጋል። ከአገር ከወጡ ግን ማንም ሊያውቃቸው አይችልም፤” ይላሉ።
ህገወጥ የሰዎችን ዝውውር ለመከላከል በክልልና በወረዳ ደረጃ ትምህርት እየተሰጠ ነው። በአገር አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ ህገወጥ የሰዎችን ዝውውር የሚከላከል ግብረሃይል ተቋቁሟል። የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርም ህገወጥ የሰዎችን ዝውውር ለመከላከል ይሰራል። በርካታ ህገወጥ ደላሎች ተይዘዋል። ርምጃ እየተወሰደ ነው። ያም ሆኖ ማስቆም አለመቻሉን ነው አቶ ወንድሙ የሚገልፁት፤
በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የዜጎች መብት ማስከበር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አምባሳደር መሃመድ ሰዒድ፤ “ማንኛውም ዜጋ በህጋዊም ሆነ በህገወጥ መንገድ ከአገር ወጥቶ ሲንገላታ የማገዝና የመደገፍ ሃላፊነት የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው። ይህንን ከኤንባሲ ጋር በጋራ እየሰራን ነው።
ማንኛውም ሰው ፓስፖርት አውጥቶ ከአገር አገር መንቀሳቀስ ይችላል። አትሂድ በሚል መከልከል አይቻልም። ዱባይ ያለው ኤንባሲ የተቸገሩ ሰዎችን ለመርዳት ከአቅሙ በላይ ቀንና ሌሊት በመስራት ላይ ነው። ነገር ግን ከእርሱም አቅም በላይ የሚሆን ብዙ ነገር አለ። የታሰሩ፤ የታመሙ እና የጠፉ ሰዎች ይኖራሉ። እነዚያን ሁሉ የማፈላለግና ወደ አገር የማምጣት ሥራ ይሰራል። ችግሩን ሙሉ ለሙሉ መፍታት በጣም አስቸጋሪ ነው። ብዙ መሥራት ይጠይቃል።
“ህዝቡ አገሩ ውስጥ እንዲሰራ፤ ደላሎች እንዲታቀቡ፤ ህብረተሰቡ ህጋዊውን መንገድ እንዲመርጥና ህገወጥ ዝውውር ከምንጩ እንዲደረቅ የማድረጉ ሥራ በቂ አይደለም። ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ቢሰራም ሰዎች እያወቁም ጭምር በህገወጥ መንገድ ይሄዳሉ። ሥራ አጥነት ራሱ ታሳቢ መደረግ አለበት። በጉዳዩ ግዝፈት ልክ መፍትሄ እየተገኘለት አለመሆኑን መተማመን ይቻላል” ይላሉ።
የፌዴራል ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶጄይላን አብዲ በበኩላቸው፤ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር እጅግ ከባድ እና የተወሳሰበ ዓለም አቀፋዊ ችግር መሆኑን ይገልፃሉ። “ደላሎቹ ዱባይና ሳውዲ አረቢያ ተቀምጠው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የመንደር ደላላ ‘ሴቶችን ላኩ’ እያሉ ዜጎችን ይወስዳሉ። ይህን ለመከላከል ፖሊስ ብቻውን የሚችለው አይደለም። የተቀናጀ ሥራ ያስፈልጋል።
“ተጓዦቹ ኤሜግሬሽን ‘ለምን ትሄዳላችሁ?’ ሲላቸው ‘ለጉብኝት’ ይላል። ማንም ሰው መዘዋወር መብቱ በመሆኑ መከልከል አይችልም፤ ይላካል። ፖሊስም የሚሄደውን በሙሉ መመርመር አይችልም። ዜጎች በተለያየ መልኩ ከአገር ይወጣሉ። ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ ክልሎች እና ወረዳዎች፤ ኤንባሲዎችና የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ የፌዴራል ፖሊስ እና ሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሌሎች አካሎችንም ርብርብ ይጠይቃል። ይላሉ።
አቶ ጀይላን፤ “በአውሮፕላን ከሚሄደው ባሻገር በአይሱዚ ተጭኖ፤ በእግሩ የሚሄደው ሰው ቁጥር ቀለላ አይደለም።” ካሉ በኋላ፤ “ፖሊስ አንድ ደላላ ለመያዝ ብዙ ደክሞ፤ ምናልባትም ዓመት ፈጅቶበት ሊይዝና ለህግ ሊያቀርብ ይችላል። ሆኖም ሥራው ከከፍተኛ ብር እና ከብዙ ሰዎች ጋር የተያያዘ በመሆኑ አንዱ ሲያዝ ሌላ አዲስ አዘዋዋሪ ደላላ ይተካል።
የፖለቲካ እና የመንግስት አመራሮች፣ የክልል፣ የወረዳ እና የፌዴራል አመራሮች ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው። ፖሊስ የሚችለውን እየሰራ ቢሆንም አባይን በጭልፋ ያህል ነው። ፖሊስ ቢያስቀጣ የተወሰኑ ሰዎችን ነው።” በማለት ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ ፖሊስ ሃላፊነቱን በመወጣት ላይ ቢሆንም የሁሉንም አካላት ተሳትፎ እንደሚጠይቅም ነው የተናገሩት፤
አዲስ ዘመን ነሃሴ 24/2011
ምህረት ሞገስ