
አዲስ አበባ።- ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል “ጳጉሜንን ለጤና” በሚል መርሀ ግብር ከአዲስ አበባና ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ለተወጣጡ አንድ ሺህ ዜጎች ነጻ የምርመራና የህክምና ድጋፍ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑ ተጠቆመ። ማዕከሉ አስረኛ ዓመቱን ‹‹አስር መልካም ነገሮችን በመስራት›› ሊያከብር ነው።
የውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ኃይሉ የማዕከሉን አስረኛ ዓመት የበጎ አድራጎት መርሀ ግብሮች ዝርዝር አስመልክተው ትናንት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፤ ማዕከሉ በአዲስ አበባና አካባቢዋ ያለውን የጤና ክፍተት ለመሙላት “ጳጉሜንን ለጤና” በሚል መርሃ ግብር ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለተውጣጡ አንድ ሺህ ዜጎች ከጳጉሜን 1 እስከ 6 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ነጻ የምርመራና የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።። ምርመራው አጠቃላይ የውስጥ ደዌን ጨምሮ የአንገት፣ የጉበት፣ የካንሰር፣ የጨጓራ፣ የልብና መሰል የጤና እክሎችን የተመለከተ መሆኑን አስታውቀዋል።።
ማዕከሉ ከተመሰረተ ዘንድሮ አስር ዓመት እንደሞላው የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለተወጣጡ 38 ሺህ ዜጎች ነጻ የምርመራና የህክምና አገልግሎት መስጠቱንም ተናግረዋል።
ዘንድሮም አስረኛ ዓመቱን በማስመልከት ስድስቱን የጳጉሜን ቀናት ለመንግስት ሰራተኞችና ከፍለው መታከም ለማይችሉ አቅመ ደካሞች ነጻ የምርመራና የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።። በመሆኑም፤ “ማንኛውም አገልግሎቱን ማግኘት የሚፈልግ ግለሰብ ከጳጉሜን 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በግንባር በመቅረብ መመዝገብ ይችላል” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዳይሬክተሩ፤ “ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል ምንም እንኳን በህክምናው ዘርፍ ተሰማርቶ ማህበረሰቡን የሚያገለግል የንግድ ድርጅት ቢሆንም፤ በተሰማራባቸው ዘርፎች ላይ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን የመወጣት ሞራላዊ ልዕልናውን እያስመሰከረ የሚገኝ ተቋም ነው” በማለት፤ በተለይ በዘንድሮው ዓመት አስረኛ ዓመቱን በሚያከብርበት ወቅት ከነሐሴ 27 ቀን 2012 ዓ.ም እስከ ጳጉሜን 6 ቀን 2011 ዓ.ም አስር ያህል የበጎ አድራጎት ተግባራትን እንደሚያከናውን ገልጸዋል።። በካንሰር ከተጎዱ ህጻናትና ከጎዳና ተዳዳሪ ህጻናት ጋር ማሳለፍ፣ ነጻ የምርመራ አገልግሎት መስጠት፣ የጽዳት አግልግሎት መስጠትና ‘ንጹህ ንግድ’ በተሰኘ ርዕስ ውይይት ማድረግ ማዕከሉ ሊተገብራቸው ካሰባቸው አስር በጎ ተግባራት ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 24/2011
አዲሱ ገረመው