የሀገራችን የሃይማኖት ብዝሀነት በርካታ እሴቶችን ገምዶ የያዘ ለመሆኑ ዜጎቿ እየኖሩበት ያለውን የአብሮነት ባህል ማስተዋል ብቻውን በቂና ጠንካራ ምስክር ነው። ሃይማኖታዊ በዓላት ለኢትዮጵያውያን በፍቅር የሚጠበቅና ያለህን እያካፈልክበት ዘመን የምትሻገርበት እውነተኛ እሴት ነው። በእነዚህና በርካታ ምክንያቶች ህዝቡ ያለው መስተጋብር ከሚከተላቸው ሃይማኖታዊ አስተምህሮቶች የሚመነጭ በመሆኑ ሃይማኖቶቹ ለህዝቡ የአብሮ መኖር ባህሉ አቅም እንጂ ፈተና ሆነው አያውቁም።
በመሆኑም የሃይማኖት ተቋማት በሃይማኖት ብዝሀነቱ መልካም እድሎች ተገንብቶ የዘለቀውን በመተባበር እና በሰላም አብሮ የመኖር እሴት ተጠብቆ እንዲቀጥልና ወደላቀ ደረጃ እንዲደርስ ደግሞ የሃይማኖት ተቋማትና አባቶች የአንበሳውን ድርሻ ሊይዙ ይገባል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሆነው በአገሪቱ ያሉ ሃይማኖቶች በጋራ የሚመክሩበትና ሌላው የአብሮነት መገለጫ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ነው።
ጉባኤው ከዚህ ምሳሌነቱ ባለፈ በሃይማኖት ተቋማት መካከል ለዘመናት ተጠብቆ የዘለቀውን የመከባበርና በሰላም አብሮ የመኖር አኩሪ እሴቶችን ዛሬም ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ ያነገበው ዓላማ ስኬታማ ይሆን ዘንድ የተቋሙ የበላይ ጠባቂዎች ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ መናገር ‹‹እናት ለልጇ ምጥ አስተማረች›› እንዳይሆን እንጂ ተገቢ ነው። ይህን በመሰለ የጋራ መድረክ ላይ በመምከር በጋራ እሴቶቻችን ላይ አተኩሮ ሁሉም ቤተ እምነቶችን በማስተባበር እሴቱን ለቀጣይ ትውልድ ማሸጋገር ይገባል። አብሮነት ወይም በሰላም አብሮ መኖር ስንል እነዚህ ብዝሀነቶች በአንድነት የኖሩበትን የማህበራዊ ኑሮ ትስስርና ስነ ልቦናዊ አንድነትና ስርዓት ማለት ነው።
ስለሆነም አብሮነት የብዝሀነትንና የአንድነት ፈርጆችን አካቶ በመያዝ በጋራ ጥቅሞች ዙሪያ በአንድነት መስራት፣በሚያለያይ ጉዳይ ደግሞ መከባበርን፣ መተማመንንና መደማመጥን ማስፈን መቻል ነው።
ከታሪካችን በግልጽ እንደምንረዳው እምነቶቹ ከራሳቸው እምነት ተከታይ አልፈው የሌላውን እምነት ተከታይ በማግለልና በመበደል የፈጸሙት ተግባር ባለመኖሩ በሰላም አብሮ መኖርን አጥብቀው ይዘው የኖሩበት ሁኔታ አጋጣሚ ሳይሆን ጥልቅ የጋራ መስተጋብር ውጤት መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል። ስለሆነም የሀገራችን ሃይማኖቶች ሲፈጠሩም፣ ሲገቡም፣ ሲስፋፉም የሚታወቁት እጅግ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እና የሌላውን ህልውና ለማጥፋት ምንም የተለየ እንቅስቃሴ የላቸውም፤ ወደፊትም አይኖርም።
ህዝበ ክርስቲያኑ ከህዝበ ሙስሊሙ ጋር በሰላም አብሮ የመኖር ተሞክሮ ዘመን መሻገሩ እማኝ አያሻውም። የክርስትና እምነት ተከታዮች የእስልምና እምነት ተከታዮች መስጊድና መድረሳ በሚገነቡበት ወቅት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ያደርጋሉ፣በዓላትንም አብረው ያከብራሉ።
እንዲሁም የሀገራችን እስልምና እምነት ተከታዮች የክርስቲያን ወንድምና እህት ህዝቦችን እምነት እንደራሳቸው አክብረውና ተከባብረው እየኖሩ ናቸው። በአብሮነት ማህበራዊ መስተጋብሮች ማለትም በእቁብ፣ በእድር፣ በሰርግ፣ በሀዘን በተለያዩ ማህበራዊ ግንኙነቶች ላይ ዘር ሃይማኖት ሳይለይ በጋራ ሲከናወኑ የኖሩ ናቸው።
የሃይማኖት ልዩነት ሳይገድበን የሀገራችንን ሉዓላዊነት የደፈሩ ጠላቶችን በጋራ የመመከት ታሪክ ባለቤት መሆናችን ደግሞ ትልቁ የአብሮነት መገለጫችን ያደርገዋል።እነዚህ እሴቶቻችን የሃገራችን ህዝቦች ለዘመናት በሰላምና መከባበር ለመኖር አስችሏቸዋል። አሁን ግን አልፎ አልፎ እሴቶቻችን የመሸርሸር አደጋ እያጋጠማቸው በመሆኑ ወደ ቀደመው መመለስ ያስፈልጋል።ምክንያቱም ለዘመናት የዘለቀው በሰላምና አብሮ መኖር እሴት ለትውልድ ቀጣይ ማድረግ ያስችላል።
በሰላም አብሮ መኖር አለመቻል አደጋ አለው። ለእድገትና ለልማት እንቅፋት ነው። የሀገራችንን በጎ ገጽታ ጥላሸት ይቀባል። ስለሆነም ይህ እንዳይከሰት የመንግስትን መዋቅሮችና አደረጃጀቶች ሴኩላሪዝምን ማረጋገጥ፣ መልካም አስተዳደርን ማስፈን፣ በሰላም አብሮ የመኖር ዕሴትን በተለያዩ ተቋማት በተለይም በትምህርት ተቋማት መገንባት አለብን። የሃይማኖት መሪዎች፣ ምሁራንና ተከታዮቻቸው ላይ በሰላም አብሮ የመኖር ፋይዳው ላይ ሰፊ ግንዛቤ መፍጠር ዛሬም በስፋት ሊሰራበት ይገባል።
የሃይማኖት ተቋማቶች በጋራ ጉዳዮች ላይ አብረው በመስራት ተቋማቸውንና ተከታዮቻቸውን ከማንኛውም አደጋ ሊጠብቁ ይገባል። በሃይማኖታዊ እውቀት የታጠቀ፣ በዘመናዊ ትምህርት የታገዘና ከአብሮነት ተጻራሪ ከሆነ አስተምህሮ የተጠበቀ ትውልድ መገንባት ለነገ የማይባል የቤት ስራ ነው።
በአጠቃላይ በሃይማኖት ብዝሀነት ያገኘነውን መልካም እድሎች መጠቀም አብሮ ለመኖር እሴታችን ትልቅ አቅም ነው። በመሆኑም ከግለሰብ እስከ ተቋም፤ ከእምነት ተቋማት እስከ የመንግስት መዋቅር ሳይቀር የአብሮነት እሴታችን በጋራ ማጎልበት ለልማትም ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታውም ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተገንዝቦ መንቀሳቀስ ወሳኝ ሚና አለው።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 23/2011