
አዲስ አበባ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ ወሳኝና ቁልፍ የሆኑ ተቋማትን ወደ ግሉ ዘርፍ ለማዞር እየተሠራ መሆኑን ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጃፓን እየተካሄደ ባለው የቶኪዮ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ (ቲካድ) ላይ፥ ስለ ግሉ ዘርፍ ተሳትፎ፣ ስለ ቀጠናዊ ውህደት እና በሃገሪቱ እየተካሄዱ ያሉ ማሻሻያዎችን በተመለከተ ንግግር ማድረጋቸውን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከስፍራው ዘግቧል።
በንግግራቸውም በሁሉም ዘርፍ ተከታታይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስመዝገብ ቅድሚያ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቁመው፥ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ለግሉ ዘርፍ ክፍት ማድረጓን ጠቅሰው፥ የግሉ ዘርፍም ምርታማነትን በሚያሳድጉና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ወሳኝ በሆኑ ዘርፎች የሚኖረው ተሳትፎ እንደሚቀጥልም አንስተዋል። በዘርፉ የተደረገው ማሻሻያም ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ኢንቨስትመንቱን ለማሳደግ ይስተዋሉ የነበሩ ተግዳሮቶች መወገዳቸውን ጠቅሰው፥ ለባለሀብቶች ተሳትፎ በሚያመች መልኩ የተንዛዙ አሠራሮችን ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል። መንግሥት የውጭ ኢንቨስትመንትና ባለሀብቶችን መሳብ በሚያስችል መልኩም ወሳኝና ቁልፍ የሆኑ ተቋማትን ወደ ግሉ ዘርፍ ለማዞር እየሠራ ነው። ለዚህም እንደ ቴሌ፣ የኃይል ዘርፍ፣ አቪየሽንና የሎጂስቲክ አቅርቦትን እንደ ማሳያ ጠቅሰው፥ አሁን ላይ በመንግሥትና በግል አጋርነት ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚውን ሚዛን ለመጠበቅና ተከታታይነት ያለው ዕድገት ማስመዝገብ በሚያስችል መልኩም፥ መንግሥት ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች ማድረጉን ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ማሻሻያዎቹ ፈጠራን እና የአፈጻጸም ብቃትን ማሳደግ የሚያስችሉ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
ቀጠናዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውህደት ለዕድገት በተለይም ተከታታይነት ያለውና ዘላቂ ዕድገት ለማስመዝገብ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል። ኢኮኖሚያዊ ውህደት በቀጠናው ለሚኖረው የሰላም ግንባታ ከፍ ያለ ሚና እንዳለው እንረዳለንም ብለዋል፡፡ ከዚህ አንጻርም ኢትዮጵያም የአፍሪካ ነፃ የንግድ ገበያን በመጠቀም ለቀጠናው ብሎም ለአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ውህደት በግንባር ቀደምትነት ትሠራለችም ነው ያሉት።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ እንደተናገሩት፤ ጃፓን ለአፍሪካ ዕድገት የምታደርገውን ድጋፍ ትቀጥላለች፡፡ የትብብሩ ትኩረትም በኢንቨስትመንት እና ፈጠራ ላይ ነው። ባለፉት ሦስት ዓመታት የጃፓን ኢንቨስትመንት
በአፍሪካ ከ20 ቢሊየን ዶላር በላይ ደርሷል ብለዋል፡፡ ቶኪዮ አሁን ላይ በአህጉሪቱ በሠላም ሂደትም እየሠራች ነው።
“የአፍሪካን ልማት በሰው ሀብት፣ በቴክኖሎጂ፣ በፈጠራ ማራመድ” በሚል መሪ ቃል በጃፓኗ ዮኮሃማ መካሄድ የጀመረው ፎረም ፤ ጃፓን-አፍሪካ የልማት ፎረም በአፍሪካ ልማትን ለማምጣት እና አህጉሪቱን ከድህነት ለማላቀቅ የሚያስችሉ ምክረ ሃሳቦች የሚቀርቡበት ሲሆን ጃፓን ለአፍሪካ የምታደርገው አጠቃላይ ድጋፍም የሚወሰንበት ነው ተብሏል።
ኮንፈረንሱ በ3 ቀናት ቆይታው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የተወያዩበትን የዮካሃማ 2019 ስምምነት መሪዎችም ተወያይተው ያጸድቃሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ጉባኤው በህዝብ አስተዳደር፣ በኢኖቬሽን እና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በአፍሪካ ልማት ላይ ሚና እንዲኖራቸው በማድረግ ላይ ትኩረት አድሮጎ የሚወያይ ይሆናል፡፡ በአፍሪካና በጃፓን የንግድ ግንኙነት ላይም ይመክራል ተብሏል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 23/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር