አዲስ አበባ፡- የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የ2019 የሄሲያን የሰላም ሽልማት ማሸነፋቸውን የፍራንክፈርት የሰላም ምርምር ማዕከል አስታወቀ፡፡ የሽልማት መርሐ ግብሩ እ.አ.አ መስከረም 23 ቀን 2019 እንደሚካሄድ ማዕከሉ ይፋ አድርጓል፡፡
ማዕከሉ ትናንት በድረገጹ እንዳስነበበው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሽልማቱ አሸናፊ የሆኑት ለሁለት አስርት ዓመታት በባላንጣነት ሲተያዩ የነበሩት ኢትዮጵያና ኤርትራ ታሪካዊውን የሰላም ስምምነት እንዲፈራረሙ ባበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ ነው፡፡ ለ100 ሺ የሚደርሱ ዜጎች ህልፈት ምክንያት የሆነውና እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ በሀገራቱ መካከል በተደጋጋሚ ሲፈነዳ የነበረው ግጭት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አነሳሽነት በተደረሰው ስምምነት እልባት አግኝቷል ሲል አስታውሷል፡፡
የሁለቱ ሀገራት የባላንጣነት ምዕራፍ መዘጋቱ ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦችና ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና አዳዲስ ዕድሎችን ከፍቷል ያለው ማዕከሉ፤ በሁለቱ ሀገራት ብሎም በቀጣናው የታየው ለውጥና የለውጡ ትሩፋቶች ነገን የበለጠ ብሩህ የሚያደርጉ በመሆናቸው ዕውቅና ሊቸራቸው ይገባል ብሏል። የሁለቱ ጎረቤት አገራት የሰላም ስምምነትና እርቅ ለመላው ቀጣና የመረጋጋት ተስፋ የሚፈነጥቅ መሆኑም ተጠቁሟል።
“አብይ አህመድ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ካሉት ትላልቅ ተስፋዎች አንዱ ናቸው:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሰላም ላሳዩት ቁርጠኝነት እና ይህንኑ የሰላም ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የሄሲያን የሰላም ሽልማት ለመሸለም ወስነናል” ያሉት የማዕከሉ ኃላፊና የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ኒኮሌ ድትልሆፍ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአፍሪካዊያን ችግሮች መፍትሔ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መሪነት በኢትዮጵያ ውስጥ የታየው ለውጥ ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ ታይቶ የማይታወቅ ዓይነት ነው ያለው ማዕከሉ፤ አጼ ኃይለ ስላሴ ከስልጣን ከተወገዱበት ከ1966 ዓ.ም ወዲህ በሀገሪቱ ያለ ደም መፋሰስ የስርዓት ለውጥ ተደርጎ እንደማያውቅ አንስቷል። ከ1983 ወዲህ የመንግሥትን ስልጣን ጨብጦ የነበረው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢህአዴግ) የፓርቲና የመንግሥት መዋቅሮችን በማወሃድ ሁሉንም የመንግሥት መዋቅሮችን በመቆጣጠር የከፋ ተግባር መፈፀሙን አስታውሷል።
በዶክተር አብይ የሚመራው መንግሥት በኢህአዴግ የሚደገፍ ቢሆንም ባለፈው አንድ ዓመት ከግንባሩ ባህሪ ወጣ ባለ መልኩ ትርጉም ያለው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ማካሄዱን የገለጸው ተቋሙ፤ የሄሲያን የሰላም ሽልማት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላከናወኗቸው ተግባራት ህዝቡ ትኩረት እንዲሰጥ በማድረግ የጀመሩትን ሰላማዊና ሁሉን አቃፊ የማሻሻያ ተግባራቸውን እንዲቀጥሉበት የሚያበረታታ እንደሆነም አብራርቷል።
እ.አ.አ በ1993 በአልበርት ኦስዋልድ የተመሰረተው የሄሲያን የሰላም ሽልማት፤ ለዓለም አቀፍ ሰላምና መተሳሰብ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱት ግለሰቦች የሚሰጥ ነው። እ.አ.አ ከ1994 ጀምሮ በየዓመቱ የሽልማት አሸናፊ በሄሲያን የሰላም ሽልማት ዳይሬክተሮች ቦርድ የሚመረጥ ሲሆን የፍራንክፈርት የሰላም ምርምር ማዕከል በዕጩዎች አመራረጥና በሰነዶች ዙሪያ ቦርዱን ያማክራል። ከሽልማቱ በተጨማሪ 25 ሺህ ዩሮ ገንዘብ ይበረከትላቸዋል።
በ2018 የቱርክ የሰብዓዊ መብት ተቋም ፕሬዚዳንትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ዶክተር ሴብኔም ኮሩር ፊነካንሲ ለሰብዓዊ መብት መከበር ላበረከቱት አስተዋጽኦ ሽልማቱን መረከባቸው ይታወቃል።
ባለፉት 25 ዓመታት ሦስት አፍሪካዊያን ብቻ ይህን ሽልማት ማሸነፍ ችለዋል። በ2013 ናይጄራዊያን እማም ዶክተር ሙሃመድ አሻፋና ፓስተር ዶክተር ጄምስ ውዬ በጋራ በናይጄሪያና በአካባቢው ሀገራት የሃይማኖት ግጭት ለማስወገድ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ሽልማቱ ተበርክቶላቸዋል። እንዲሁም በ2009 የኬኒያዊው የሰላም አቀንቃኝ ድክሃ ኢብራሂም አብዲ በሃይማኖቶችና በብሄሮች መካከል የተፈጠረውን ግጭት በማሸማገል ላበረከተው አስተዋጽኦ ተሸላሚ ሆነዋል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 23/2011
መላኩ ኤሮሴ