ኦሊምፒክ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለቶኪዮ ኦሊምፒክ ለማለፍ ከካሜሮን ሴት ብሄራዊ ቡድን ጋር ያደረገውን የቅድመ ማጣሪያ የሁለተኛ ዙር ጨዋታ በአቻ ውጤት ነበር ያጠናቀቀው። በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ነሃሴ 20 ቀን 2011 ዓ.ም የተካሄደው ጨዋታው 1 ለ1 በሆነ ውጤት መጠናቀቁ የቡድኑን ቀጣይ እጣ ፈንታ የሚወስን አለመሆኑን የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ ገልጻለች።
በአቻ ውጤት የተጠናቀቀውንና በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ የሚከናወነውን የመልስ ጨዋታ በማስመልከት አስልጣኟ በሰጠችው አስተያየት፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በመጀሪያው የጨዋታ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥርና የግብ እድሎችን በመፍጠር ከተጋጣሚው የተሻለ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ የካሜሮን ብሔራዊ ቡድን የተሻለ እንቅስቃሴ ማሳየት ችሏል። ‹‹ከካሜሮን ሴት ብሄራዊ ቡድን ጋር የነበረን ጨዋታ ምንም እንኳን በሜዳችን የነበረ ቢሆንም ከባድና አስቸጋሪ ነበር›› ብላለች።
እንደ አሰልጣኟ ገለጻ፣ በመጀመሪያው አጋማሽ ቡድኑን አክብዶ ከማየት አንጻር በእንቅስቃሴ ውስጥ በራስ መተማመን ሲያጡ ተስተውለዋል። ሁለተኛው አጋማሽ ላይ በካሜሮኖች በኩል ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ መኖርን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ቅርፁን የማጣት ሁኔታዎች ተስተውለውበት ነበር። የቡድኑ መረጋጋት ማጣት ግብ እንዲቆጠር ምክንያት የሆነም ነበር።
‹‹በቡድናችን ላይ በተለይ የአካል ብቃት ችግር ጎልቶ ይታይ ነበር። ለጨዋታው ያደረግነው ዝግጅት ወደ 17 ቀናት አካባቢ ሲሆን፤የዝግጅቱ ሁኔታ በቂ ነው ለማለት አዳጋች ነው። ተጫዋቾቹ ከሁለት ወራት በላይ እረፍት ላይ ስለነበሩ ተጽዕኖ ፈጥሯል›› ብላለች።
በጨዋታው የካሜሮን ብሄራዊ ቡድንን ማሸነፍ ባይቻልም እንኳ ውጤቱ ጥሩ የሚባል እንደሆነ የገለጸችው አሰልጣኟ፤ የካሜሮን ቡድን የሚናቅ እንዳልሆነና ቡድኑ አሁን በሚያሳየው እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን ትልቅ እና የሚከበር ቡድን መሆኑንም ተናግራለች። በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በኩል የልምድ ማነስና በራስ የመተማመን ችግር ባይስተዋል ማሸነፍ ይቻል እንደነበርም ጠቁማለች።
«ጨዋታው አልቋል ብዬ አላስብም። በባህር ዳር የነበረው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ እንጂ ጨዋታው ሙሉ ለሙሉ አልቋል ብለን አናምንም። የጨዋታው 90 ደቂቃ አልቋል፤ቀሪውና ወሳኙ 90 ደቂቃ ይቀራል» በማለት ተናግራለች።
የባህር ዳሩ ጨዋታ በዚህ መልኩ ቢጠናቀቅም ለመልሱ ጨዋታ ጊዜ ሳያጠፉ ወደ ዝግጅት እንደሚገቡ የገለጸችው አሰልጣኝ ሰላም፤ ነሐሴ 26 ቀን 2011 ዓ.ም በካሜሮን ዋና ከተማ ያውንዴ ለሚጠብቃቸው የመልስ ጨዋታ በቀሩት ጊዜያት ተዘጋጅተው ድክመታቸው አሻሽለው ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሞክሩ ገልፃለች።
በባህር ዳር ዓለም ዓቀፍ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ለስፔኑ ክለብ ሪያል ቤቲስ የሴት ቡድን የምትጫወተው የአጥቂ መስመር ተጫዋቿ ሚካኤላ አባም በ50ኛው ደቂቃ ባስቆጠረችው ግብ ካሜሮንን ቀዳሚ ማድረግ ችላ ነበር። ከእረፍት መልስ ተቀይራ የገባቸው የአዳማ ከተማዋ ተጫዋች ሰናይት ቦጋለ፣ የካሜሮን የተከላካይ ክፍል የሰራውን ስህተት ተጠቅማ በ82ኛው ደቂቃ ያስቆጠረችው ግብ ሉሲዎችን አቻ ማድረግ ችሏል። በጨዋታው ኬንያዊቷ ኢንተርናሽናል ዳኛ ናፓኞር አኜታ የካሜሮኗን የተካላካይ መስመር ተጫዋች ሌዩኮ ዩቬኔ በቀይ ካርድ ያሰናበተች ሲሆን ለሁለት የካሜሮን ተጫዋቾችም የቢጫ ካርድ አሳይታለች።
የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች የመልስ ጨዋታ ነሐሴ 26 ቀን 2011 ዓ.ም በካሜሮን ዋና ከተማ ያውንዴ ይሄዳል። የኢትዮጵያ ሴቶች ኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድን በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈ በሶስተኛ ዙር ማጣሪያ በመስከረም 2012 ዓ.ም ከዴሞክራቲክ ኮንጎ እና ከኢኳቶሪያል ጊኒ አሸናፊ ጋር የሚጫወት ይሆናል። ብሔራዊ ቡድኑ በመጋቢት 2011 ዓ.ም የመጀመሪያ ዙር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎን ከዩጋንዳ ጋር አድርጎ በድምር ውጤት 4 ለ 2 ማሸነፉ ይታወሳል።
እ.አ.አ በ2020 በጃፓን ቶኪዮ በሚካሄደው 32ኛው የኦሊምፒክ ውድድር የአፍሪካ ዞን የእግር ኳስ የማጣሪያ ውድድር ከመጋቢት 2011 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሀሴ 22/2011
ዳንኤል ዘነበ