‹‹ወደ ኮርያ በአምስት ዙር ከዘመቱት 6,037 ኢትዮጵያውያን መካከል 122ቱ በጦርነቱ ሲሰዉ አንድም የተማረከ ኢትዮጵያዊ ወታደር የለም። ግዳጃቸውን ፈጽመው ከተመለሱት ውስጥ የሽምቅና የደፈጣ ውጊያዎችን ተካፍሎ አኩሪ ገድል ፈፅሟል። የሁለቱ አገራት ወዳጅነት በደም የተሳሰረ ነው የምንለው አብረው ስለተሰዉ ነው። የሁለቱ ደም ተቀላቅሏልና በደም የተሳሰረ ወዳጅነት አለን እንላለን።›› በማለት በጀግንነታቸው ኩራት እየተሰማቸው የሚናገሩት በታሪካዊው ጦርነት የተሳተፉት አባቶቻችን ናቸው።
የመጀመሪያው ቃኘው ሻለቃ በ1943 ዓ.ም ሲዘምት አፄ ኃይለሥላሴ ሰንደቅ ዓላማ አስረክበው ‹‹ ይህን ሰንደቅ ዓላማ መመርያ አድርጋችሁ እንድትዘምቱ፣ በተሰማራችሁበት ቦታ ጀግንነት ሠርታችሁ በደረታችሁ ላይ ልዩ ምልክት አድርጋችሁ በኩራት ስትመለሱ በአደራ የሰጠናችሁን ዓርማ መልሳችሁ ታስረክቡናላችሁ›› ማለታቸው ይታወሳል።
አፄ ኃይለሥላሴ “የጦር ሰው ፖለቲካን ሲለምድ ወላዋይነትን ያስከትላል። ሲታዘዝም ለምን ማለትም ሃፍረት ነው” ሲሉ ወታደርና ፖለቲካ ሊለያዩ እንደሚገባ ያሳሰቡበትን ንግግራቸውን በስፍራው የነበሩት ያስታውሳሉ።
አዎ! በሰው አገር የሚጓዝ ባለአደራ የኃላፊነት ሸክሙ ከባድ በመሆኑ አደራውን የተቀበለውም የአገሩን ስም አስጠርቶ በኩራት በመመለሱ ዛሬ በኮሪያና በኢትዮጵያ ሕዝቦችና አገራት መካከል የጠበቀ ወዳጅነትና መከባበርን ለማየት ችለናል። የዚያን የክፉ ቀን የመረዳዳት ወዳጅነት የጊዜ ርዝመት አልሻረውም፤ ዘመን አላደበዘዘውም።
ታላላቆች ያኖሩት የጠበቀ ወዳጅነት ውሉን ሳይስት 68 ዓመታትን አስቆጥሮ ሰሞኑን እንደገና ማበቡን እያየን ነው። በያዝነው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በደቡብ ኮሪያ ያደረጉት ጉብኝት የዚሁ መልካም ግንኙነት ማሳያ ማረጋገጫ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለት ቀናት የደቡብ ኮሪያ ጉብኝታቸው ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሙን ጃ ኢን ጋር በሁለትዮሽና ሌሎች ጉዳዮች ላይ በስፋት መክረዋል። መሪዎቹ በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ መስማማታቸው የአገራቱ ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት እንዲያድግ ፍላጎት መኖሩና አመላካች ነው።
የኮሪያው ፕሬዚዳንት ሙን ጃ ኢን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ እየወሰዱ ያሉትን የማሻሻያ ዕርምጃ አገራቸውና መላው ዓለም በአድናቆት እየተመለከተው መሆኑንም ጠቅሰዋል። በርግጥም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕርምጃ ኢትዮጵያን ወደተሻለ ደረጃ የማሸጋገርና ዲፕሎማሲው የተጠናከረ እንዲሆን ራዕይን የሰነቀ በመሆኑ ስኬታማነቱ ከወዲሁ የሚታይ ሆኗል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደቡብ ኮሪያ ጉብኝት በውጤት የታጀበ ለመሆኑም በአምስት መስኮች የመግባቢያ ስምምነቶችን በመፈራረም የተጀመረ ነው። የአካባቢ ጥበቃ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በደረጃ ብቃት ማረጋገጫ ተስማሚነት ምዘናና የቴክኒክ ቁጥጥር ዙሪያ በትብብር ለመሥራት፤ እንዲሁም በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የልህቀት ማዕከልን ለማቋቋም የብድር ስምምነትም ተፈራርመዋል።
የጋራ ሚኒስትሮች ኮሚሽን ለማቋቋምና በቪዛ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ስምምነት ላይ መደረሱ፣ የኢትዮጵያን ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት የያዙ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ወደ ደቡብ ኮሪያ፤ እንዲሁም የደቡብ ኮሪያን ዲፕሎማቲክ ፓስፖርት የያዙ ደቡብ ኮሪያውያን ወደ ኢትዮጵያ ቪዛ ሳይጠየቁ መግባት የሚችሉበትን አሠራር መተግበር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
እነዚህ ስምምነቶች የሚያሳዩት ትናንት በመስዋእትነት የተሳሰረውንና ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረው ወዳጅነት ወቅቱና ዘመኑ በሚፈልገው ዲፕሎማሲም የላቀ ደረጃ ላይ መድረሱን ነው። መልካም ውጤትም የተመዘገበበት ነው።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 22/2011