የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የአፍሪካ የልማት ፎረም (የቲካድ ) ጉባዔ ላይ ለመካፈል ጃፓን ገቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጃፓን ሲገቡ በሀገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን፤ ከጉባዔው ጎን ለጎንም ከጃፓን ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ጋር ተገናኝተው እንደሚወያዩ ይጠበቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጃፓን-አፍሪካ የልማት ፎረም (የቲካድ ) ላይ እንዲሳተፉና ከጉባዔው ቀደም ብሎም በሀገሪቱ ጉብኝት እንዲያደርጉ በጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞአቤ ጥሪ በቀረበላቸው መሰረት በደቡብ ኮሪያ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቅቀው ጃፓን መግባታቸውን የኤፍ.ቢ.ሲ ዘገባ አመልክቷል።
በተያያዘ ዜና የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በጃፓን ከኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት ጋር ተገናኝተው በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
በውይይቱ በጃፓን የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው ለውጥና የተለያዩ አገራዊ ጉዳዮችን አንስተው የሃሳብ ልውውጥ ያካሄዱ ሲሆን፤ ተወያዮቹ ላነሷቸው ጥያቄዎችም ሚኒስትሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በውይይቱ ኢትዮጵያውን በጋራ ሆነው ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በጋራ እየተወጡ በሀገሪቱ የተጀመረው ለውጥ ዳር ለማድረስ ከመቼውም ጊዜ በላይ መተባበርና መተሳሰብ እንደሚያስፈልግ ሚኒስትሩ አሳስበዋል። በጃፓን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ሀገራዊ ለውጡን ለመደገፍ ቃል መግባታቸው ተጠቁሟል።
በጃፓኗ ዮኮሃማ ከተማ የቲካድ ጉባዔ ከዛሬ ከነሐሴ 22 እስከ ነሐሴ 24 ቀን 2011 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 22/2011