አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የጸጥታው ምክር ቤት አባል ከሆነች በዓለም መድረክ የአፍሪካውያንን ጥቅም የማስጠበቅ አቅሟ ከፍተኛ መሆኑን በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ሙሉጌታ ደበበ (ዶ/ር) አስታወቁ::
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ሙሉጌታ ደበበ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቱ እ.ኤ.አ በ1945 ሲቋቋም ብዙ ሀገራትን ያካተተ አልነበረም:: ኢትዮጵያን ጨምሮ ግብፅ፣ ላይቤሪያ እና ደቡብ አፍሪካ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥራች ቢሆኑም በጸጥታው ምክር ቤት አባል የሆነ አንድም አፍሪካዊ ሀገር የለም:: ድርጅቱም ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላም ሳይሻሻል ሲቋቋም በነበረበት አቋም ላይ ይገኛል ብለዋል::
እንደ ዶክተሩ ገለጻ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ድርጅቱ እንዲሻሻልና የአፍሪካ ሀገራትም የጸጥታው ምክር ቤት አባል እንዲሆኑ እየጠየቁ ነው:: ኢትዮጵያ በተለያዩ የዓለም መድረኮች ላይ ለአፍሪካ ሀገራት ድምጽ መሆኗን አሳይታለች:: በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮችም አፍሪካውያን በተመድ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት እንዲኖራቸው ጥያቄ እያቀረበች ነው:: ኢትዮጵያ የጸጥታው ምክር ቤት አባል ከሆነች ካላት ተሞክሮ አንጻር ለአፍሪካውያን ድምጽ መሆንና ጥቅማቸውን ማስጠበቅ እንደምትችል ገልጸዋል::
ኢትዮጵያ ከዓድዋ ጦርነት ጀምሮ ገናና ነጻ ሀገር ናት ያሉት ዶክተር ሙሉጌታ፤ ወራሪዎችን በማሸነፍ ነጻነቷን ያስከበረች ብቸኛ አፍሪካዊት ሀገር ናት:: ኢኮኖሚዋ በሚፈለገው ልክ ባያድግም በዓለም መድረክ ከፍተኛ ተሰሚነትና ድምጽ አላት:: ከዚህ አኳያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አባል ለመሆን አስፈላጊውን መስፈርት እንደምታሟላ ተናግረዋል::
በዓለም መድረክ የአፍሪካን ሀገራት ጥቅም ለማስጠበቅ በአፍሪካ ያላትን ተቀባይነት ማጠናከርና የምትከተለውን የገለልተኛ መርኋን ማጠናከር እንዳለባት አብራርተዋል::
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል ለመሆን በቂ ታሪክ አላት የሚሉት መምህሩ፤ ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን ለነጻነት የተመረጠች ቦታ ናት:: ለአፍሪካ ነጻነት ከፍተኛ ዋጋ ከፍላለች፤ አፍሪካውያንን በማስተባበርም የአፍሪካ ሕብረትን መሥርታለች:: በዚህም የአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያን እንደ አዳኝ ይመለከቷታል ነው ያሉት::
በርግጥ የጥቅም ፍላት ያላት ግብጽ የኢትዮጵያ ገናናነት ለማኮሰስ ብዙ እንደምትሠራ ገልጸዋል:: አሁን ኢትዮጵያ ወደ ጥሩ መስመር እየገባች በመሆኑ በጸጥታው ምክር ቤት መሻሻል ላይ የምታነሳው ጥያቄ እውን ይሆናል:: የዓለም ሥርዓት መለወጥ አለበት፤ ለዚህም ኢትዮጵያ ጥያቄዋን በማቅረብ አጀንዳ ማድረግ ችላለች ብለዋል::
በሊግ ኦፍኔሽን፤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በአፍሪካ ሕብረት ምስረታ ላይ ኢትዮጵያ ትልቅ ሚና ነበራት:: እንዲሁም በቅኝ አገዛዝ ውስጥ የነበሩ ሀገሮችን ነጻ ከማውጣት አንጻር በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት አበርክቶ ከሃያላን ሀገራት ተርታ ያሰልፋታል:: ለዓለም ሰላም መስፈን ከማንኛውም ሀገር በላይ የጎላ ሚና እንዳላትም ገልጸዋል::
ተመድ አሠራሩን እንዲያሻሽልና አፍሪካም እንድትወከል የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት ዶክተር ሙሉጌታ ገልጸዋል::
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 8/2017 ዓ.ም