ከአደባባይ በዓሎቻችን የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን

የአደባባ በዓሎች የመዝናኛ እድሎች ከመሆናቸውም በላይ አካባቢን ለማስተዋወቅ፣ በሕዝቦች መካከል ታሪካዊና ባህላዊ ትስስር ለመፍጠር ጠቀሜታቸው የጎላ ነው። ለማህበራዊ ገጽታ እና ለቱሪዝም ዘርፍ እድገት የሚኖራቸው ሚና ቀላል አይደለም። አሁን አሁን በዓላቱ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ውስጥ እንደ አንድ ትልቅ አቅምም እየታዩ ነው።

በዓላትን ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ከፍተኛ አቅም አድርጎ በመጠቀም በኩል የእሲያ ሀገራት፣ በተለይም ቬትናም እና ካምቦዲያን የሚያክላቸው አልተገኘም። እነዚህ ሀገራት በዓላቶቻቸውን በዓለም መድረክ በማስተዋወቅ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቱሪስት በአደባባይ በዓሎቻቸው ላይ እንዲገኙ በማስቻል ከፍተኛ ገቢ በማግኘት ላይ ናቸው።

ሀገራችን ኢትዮጵያም የተለያዩ የአደባባይ በዓላት ከሚከበርባቸው ሀገራት አንዷ ናት። በዓላቱ ሃይማኖታዊ ባህላዊ እና ማህበራዊ እሴቶቻቸውን ጠብቀው በመቆየታቸው አሁን ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቱሪስት በመሳብ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው የገቢ ምንጭ እየሆኑ ነው።

በተለይ በመስከረም ወር የሚከበሩ በዓላት በዋናነት የዓደባባይ በዓት ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በአግባቡ ልንጠቀምባቸው ከቻልን ለሀገሪቱ የቱሪስት ኢንዱስትሪ እድገት ትልቅ አቅም ሊሆኑ እንደሚችሉ አያጠራጥርም። ከእነዚህ በዓሎች መካከል በመስቀል ዋዜማ የሚከበረው የደመራ፣ እሬቻ፣ ፊቼ ጨምበላላ እና የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው ።

በዓላቱ በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብ የሚሳተፍባቸው፤ በዓለም አቀፍም ሆነ በሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ሰፊ ሽፋን የሚያገኙ ናቸው። የማህበራዊ የትስስር ገፆችም የበዓሉ አከባበር ዓለም አቀፍ እይታ እንዲኖረው የተሻለ እድል እየፈጠሩ ይገኛሉ። ከኢትዮጵያም አልፎና ተርፎ አንዳንድ በዓሉ የሚከበርባቸውን የሌሎች ኀገራት አካባቢዎች ከማስተዋወቅ ረገድም አበርክቷቸው ሰፊ ነው።

በዓላቱን ለማክበር አደባባይ የሚገኙት ሰዎች፤ አለባበስ፣ አጊያጌያጥ እና በዓሉን የሚያከብሩበት ሥርዓት እና ሁኔታ ለበዓሉ ከፍተኛ ድምቀትን የሚሰጡ ናቸው። ይህን ተከትሎ የበዓሉ ታዳሚዎች አንዱ የሌላውን ባህል እና የበዓል አከባበር ሁኔታ ይመለከታል። እየቆየ ሲሄድ በዓላቱን የራሱ ብቻ ሳይሆን የጋራ ሀብቱ ማድረግ ይጀምራል። ይህ ደግሞ ህብረብሄራዊነትን ከማጠናከር አኳያ የተሻለ እድል ይፈጥራል።

የመስቀል ደመራ በዓል አክባሪዎች ምንም እንኳ ክርስቲያኖች ይሁኑ እንጂ፤ ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጡ ሰዎች የሚሳተፉበት ነው። በዚህ በዓል ላይ በተለያዩ ቋንቋዎች መዝሙሮች ይዘመራሉ። አንዱ ከሌላው ጋር ይተዋወቃል። በኢሬቻም ሆነ በፍቼ ጨምበላላ ያለውም ከዚህ የተለየ አይደለም ።

በዓላቱ ከማህበራዊ ፋይዳቸው ባለፈም ለሀገር ኢኮኖሚ የሚኖራቸው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። የበዓሉ አክባሪዎች በበዓሉ ቀን የሚለብሱትን ልብስም ሆነ የሚጠለቅ ጌጣ ጌጥ ይገዛሉ። ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ ከትራንስፖርት አገልግሎት ጀምሮ የተለያዩ ወጪዎችን ያወጣሉ።

በዓሉን ለማክበር ከቦታ ቦታ ከተንቀሳቀሱ በዓሉ በሚከበርበት አካባቢ የሚቆዩበት ሁኔታ ስለሚፈጠር፤ ከሆቴል ምግብ እና መጠጥን አገልግሎት ከማግኘት ባሻገር እየተዝናኑ እግረ መንገዳቸውን የሚጠቀሙባቸውን ቁሳቁሶችን ይሸምታሉ። ሰፊ ሸመታን ማከናወናቸው ደግሞ በዓሉ በሚከበርበት ቦታ ላይ የሚኖረውን የገበያ እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ ያደርገዋል። “የሀገር ውስጥ ቱሪዝም” ማለትም ይሄው ነው።

የዓደባባይ በዓሎች ከላይ ከዘረዘርናቸው በተጨማሪ የበዓሉ አክባሪዎች በዓሉ ላይ በመሳተፋቸው እንዲዝናኑ ከማስቻል ጎን ለጎን መንፈሳቸውን እንዲያድሱ እና ከበዓሎቹ በኋላ ሥራቸው ላይ ውጤታማ እንዲሆኑ እንደሚረዳቸውም የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ይጠቁማሉ። ከአሰልቺ የሥራ አካባቢዎች ርቀው በዓል እያከበሩ የተለየ ቦታ ከቤተሰብ ጋር ማሳለፍ የሚኖረው ደስታ እና የሚፈጥረው ስሜት የበዓሉ ታዳሚዎች እንዲነቃቁ እና ከመደንዘዝ እንዲላቀቁም እንደሚያስችል ይነገራል።

ምንም እንኳ የአደባባይ በዓሎቹ በተለይም ለሀገር ውስጥ ጎብኚዎች እንዲሁም ለበዓሉ አክባሪዎች ጥቅም እያስገኙ ቢሆንም፤ የተሻለ የቱሪስት መስህብ ሆነው አሁን እንደሀገር ከሚያስገኙት የኢኮኖሚ ጥቅም በላይ ሀገርን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚያስችሉ ይታመናል።

በቱሪዝም ዘርፍ የተሻለ አቅም ለመፍጠር፣ የመንገድ እና የቱሪዝም መሠረተ ልማቶችን ማስፋት፣ የኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂዎችን በጥራት እና በፍጥነት ማግኘት የሚያስችል አቅም መፍጠር፣ የቱሪዝም መዳረሻ ሥፍራዎችን በአግባቡ ማስተዋወቅ · · · ያስፈልጋል ።

አሁን አሁን በአዲስ አበባ በኮሪደር ልማት መንገዶች እና የተለያዩ የመዝናኛ ሥፍራዎች እየተገነቡ ቢሆንም፤ ጊዜውን የሚመጥኑ፣ ጥራት ያላቸው አማራጭ መንገዶችን መገንባት አስፈላጊ ነው። ግንባታው ከአዲስ አበባ አልፎ በክልሎች፤ በተለይም የቱሪዝም መዳረሻ በሆኑ አካባቢዎች አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል።

የአደባባይ በዓላት ሲታሰቡ የመሠረተ ልማት ጉዳይም ስትራተጂክ በሆነ መንገድ ሊታሰብበት የሚገባው መሠረታዊ ጉዳይ ነው።

ከቴክኖሎጂ አገልግሎት፤ በተለይም ከኔትወርክ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶችን በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በክልል ከተሞችም በጥራት እና በፍጥነት ማግኘት የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ ጥራት ያለው አገልግሎት የሚሰጡ የሆቴል እና የጤና ተቋማትን በየቅርብ ርቀቱ እንዲኖር ማስቻልም ያስፈልጋል።

የአደባባይ በዓሎችን በአግባቡ ማስተዋወቅ ከዘርፉ የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን ወሳኝ የሆነ ሀገራዊ የቤት ሥራችን ነው። ለዚህም በዋናነት ከቱሪዝም ጋር ተያይዞ ሃላፊነት የተሰጣቸው የመንግሥት ተቋማት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ። የሆቴል ባለቤቶች፣ አስጎብኚ ድርጅቶች፣ ዘርፉን ማእከል አድርገው ባለሙያዎችን በማፍራት ላይ የሚገኙ የትምህርት ተቋማት እና መላው ሕዝብ/እንግዶችን በሰላም እና ፍቅር በመቀበል የሚጠበቅበትን ሃላፊት መወጣት ይኖርበታል። ሰላም!

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 8/2017 ዓ.ም

Recommended For You