እየተነቃቃ የመጣው የትግራይ ክልል የወርቅ ማዕድን ልማት

በኢትዮጵያ በወርቅ ማዕድን እምቅ አቅም ካላቸው ክልሎች መካከል የትግራይ ክልል ይጠቀሳል። በሀገሪቱ ወርቅ በማምረት በኩል ከሚጠቀሱት ክልሎች መካከልም ይጠቀስ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ወርቅ አምርቶ ጥቅም ላይ ከማዋል አንጻር በርካታ ችግሮች እንዳሉበት ይገለጻል። ለዚህም በምክንያትነት የሚነሳው በክልሉ ወርቅ በማምረትና ግብይት ሂደት ሊደረግ የሚገባው ቁጥጥርና ክትትል የላለ መሆኑ ነው። ይህም ማዕድኑን ለሕገ ወጥ ዝውውርና ግብይት ዳርጎት ቆይቷል፡፡

የምርትም ሆነ የግብይት ሥርዓቱን ወደ ሕጋዊነት በማምጣት ከዘርፉ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ብዙ ሲሰራ ቆይቷል። ካለፈው ዓመት ጀምሮ ሕገ ወጥነት በተስፋፋበት የወርቅ ልማትና ግብይት ሥራ ላይ በተደረገው ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም በተሰጠ ድጋፍ አበረታች ለውጦች እየታዩ መሆናቸውን የክልሉ መሬት አጠቃቀም አስተዳደርና ማዕድን ቢሮ መረጃ ያመለክታል፡፡

የቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ፍስሃ ግርማይ በክልሉ የወርቅ ማዕድን ልማትና ግብይት ላይ በተሰራው የክትትል ሥራና በተደረገ ድጋፍ ለውጦች እየታዩ መሆናቸው ይናገራሉ። በወርቅ ማዕድን በሚታወቁ ወረዳዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ በመሥራቱ ለውጦች ማስመዝገብ ተችሏል ይላሉ። በክልሉ በሚገኙ 26 ወረዳዎች ከፍተኛ የወርቅ ክምችት እንዳለ ጠቅሰው፣ የእነዚህ ወረዳዎችና ዞኖች አመራሮች እና ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉን ያስረዳሉ። ይህም በየወረዳው ያሉ የወርቅ አምራቾች ግንዛቤ እንዲያገኙ ማድረግ ማስቻሉን ያመለክታሉ። ከዚህ ጎን ለጎን በማዕድን ላይ የሚፈጸም ሕገ ወጥነትን ለመከላከል ጠንካራ የቁጥጥርና የክትትል ሥራም መከናወኑን ይጠቁማሉ፡፡

በክልሉ በ2016 በጀት ዓመት 50 ኪሎ ግራም ወርቅ ለማምረት ታቅዶ እንደነበር አስታውሰው፣ ይህን እቅድ ማሳካት የተቻለው በዓመቱ መጨረሻ አካባቢ ባሉ ሦስት ወራት በተከናወኑ ተግባሮች መሆኑን ይጠቁማሉ። ‹‹ለስኬቱ የተደረገው ጠንካራ የክትትልና የግምገማ ሥራ እንደሚጠቀስ ተናግረው፣ በተለይ ወርቅ ላይ ትኩረት መሰራቱ በዓመቱ ለመፈጸም የተያዘውን እቅድ በዓመቱ መጨረሻ ማሳካት ተችሏል›› ይላሉ፡፡

በዘንድሮው በጀት ዓመት የአምናውን እቅድ መነሻ ያደረገ እቅድ ተዘጋጅቶ ሲሰሩ መቆየቱን አቶ ፍሰሃ ተናግረው፣ በተያዘው በጀት ዓመት 800 ኪሎ ግራም ወርቅ ገቢ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነ ይገልጻሉ። ከዚህም ውስጥ 700 ኪሎ ግራም ወርቅ በኢዛና ድርጅት አማካኝነት እንደሚመረት ጠቅሰው፣ 100 ኪሎ ግራሙን ደግሞ በባሕላዊ አምራቾች ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ያመላክታሉ፡፡

አቶ ፍሰሃ እንደሚሉት፤ በክልሉ በወርቅ ማውጣት ላይ ለመሰማራት ከማዕድን ሚኒስቴር ፍቃድ የወሰዱ ትላልቅ ወርቅ አምራች ኩባንያዎች አሉ። ይሁንና ኩባንያዎቹ እስካሁንም ወደ ማምረት ሥራ አልገቡም። ኩባንያዎቹ የማምረት ፍቃድ የወሰዱበት የማዕድን አካባቢ በጣም ሰፊ ቦታን ያካለለ ነው። ተንቤንን በመሳሰሉ አካባቢዎች የተሰማሩ ኩባንያዎች አንድ ወረዳ የሚያህል ቦታ ይዘው እስካሁን ሥራ አልጀመሩም። ኩባንያዎቹ ወደ ሥራ ቢገቡ ኖሮ የወርቅ ምርትን ከመጨመር ባሻገር ለብዙ የአካባቢው ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ይችሉ ነበር። አሁን በማዕድን ዘርፉ እየታየ ያለውን ሕገ ወጥ አሰራር ወደ ሕጋዊነት ለማምጣትም በጣም የሰፋ እድል ይኖር ነበር።

በዘርፉ ትልቅ ማነቆ ተብለው ከተለዩት ችግሮች መካከል ዋንኛው የእነዚህ በፌዴራል ደረጃ ፍቃድ የወሰዱ ኩባንያዎች በወቅቱ ወደ ሥራ አለመግባታቸው እንደሆነ ያነሳሉ። በአሁኑ ወቅትም የማዕድን ቦታው ምንም አይነት አገልግሎት ሳይሰጥ ፍቃዱን በወሰዱት ኩባንያዎች ተይዞ ይገኛል ይላሉ። ኩባንያዎቹ የያዙትን የማዕድን ቦታ ለሌሎች ማዕድኑን ማልማት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ለመስጠት አለመቻሉንም ያስረዳሉ። ‹‹የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ባለሀብቶቹ ፈቃዱን የወሰዱ ከማዕድን ሚኒስቴር ሲሆን፣ ይህን ፈቃድ ክልል መስጠት አሰራሩ ስለማይፈቅድ ቦታውን ለሌሎች ኩባንያዎች መስጠት አልተቻልም›› ሲሉም ያብራራሉ። ኩባንያዎቹ በወሰዱት ፍቃድ መሠረት ወደ ሥራ ገብተው ወጣቱ የሥራ እድል መፍጠር ባይችሉም እስካሁን ምንም ዓይነት ርምጃ መውሰድ አለመቻሉንም ያክላሉ፡፡

የተፈጠረውን ችግር የማዕድን ሚኒስቴር በተደጋጋሚ እንዲያውቀው መደረጉን ጠቅሰው፤ ይሁንና ወደ ሥራ የገባ ኩባንያ አለመኖሩን ያመለክታሉ። ይህ አለመሆኑ የማዕድን ሀብቱ በአግባቡ ለምቶ ጥቅም ላይ እንዳይውል ከማድረግ ባሻገር የሀብትና የጊዜ ብክነትን እያስከተለ መሆኑን ያስረዳሉ። ሚኒስቴሩ በጉዳዩ ዙሪያ ጥናት አሰርቶ ያለውን ችግሩ እንዲቃለል ትኩረት ተሰጥቶ መሥራት እንዳለበት ያስገነዝባሉ፡፡

እንደ አቶ ፍስሃ ማብራሪያ፤ ዘንድሮ ወርቅ ለማምረት ሲታቀድ እነዚህን ኩባንያዎች ታሳቢ በማድረግ ነው። ኩባንያዎቹ ወደ ሥራ ካልገቡ በዘርፉ እቅድ ላይ ትልቅ እንቅፋት ይፈጥራል። በባለፈው ዓመት በማዕድን ዘርፉ ለ45 ሺ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ፤ ለ48ሺ 955 ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል። በመሆኑም በዘርፉ በተመሳሳይ መንገድ የሥራ እድል መፍጠር ያስፈልጋል። የሥራ እድል መፍጠር ሲቻል ሕጋዊ አሰራሮች የመከተሉ ሁኔታ እየተሻሻለ ይመጣል፤ ይህ ታሳቢ ተደርጎ በትኩረት በመሥራቱ አፈጻጸሙም ጥሩ መሆን ችሏል፡፡

የቢሮው መረጃ እንደሚያሳየውም፤ ክልሉ ባለፈው በጀት ዓመት በማዕድን ዘርፉ ከአገልግሎት፣ ከመሬት ኪራይ፣ ከሮያሊቲ ክፍያ በክልልና በወረዳ ደረጃ ገቢ የሚያስገኙ ሥራዎችን ለመሥራት ታቅዶ ሲሰራ ቆይቷል። በዚህም በክልል ደረጃ 10 ሚሊዮን ብር፣ በወረዳ ደረጃ ደግሞ 18 ሚሊዮን ብር በአጠቃላይ 28 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ነበር። በዚህም በክልል ደረጃ ከ11 ሚሊዮን በላይ ብር፣ በወረዳ ደግሞ ከ19 ሚሊዮን በላይ ብር በአጠቃላይ ከ31ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት ተችሏል፡፡

የዘንድሮውን እቅድም ለማሳካት ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ሲወጣ የነበረውን ወርቅ ወደ ሕጋዊነት እንዲመጣ ማድረግ ዋንኛው ሥራ ይሆናል። ሕጋዊ የማምረት ፍቃድ የወሰዱትን አምራቾች ሕጋዊ ፍቃድ ከሌላቸው በመለየት ሕጋዊ ፍቃድ ያላቸውና የተፈቀደላቸው እንዲያመርቱና ያልተፈቀደላቸው ደግሞ ከሥራ ውጭ እንዲሆኑ ይደረጋል፤ የክልሉን የማዕድን ክምችት በመለየት በሌሎች ዘርፎች ላይ መሰማራት ለሚሹ ኢንቪስተሮች ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡

‹‹በበጀት ዓመቱ ከማዕድን ዘርፉ 35 ሚሊዮን ገቢ ለማግኘት ታቅዷል›› ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ይህም ካለፈው በጀት ዓመት አፈጻጸም በአራት ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ይገልጻሉ። ከወርቅ በተጨማሪ የከበሩ ማዕድናት በስፋት ለማምረት መታቀዱን ጠቁመው፤ 60 ኪሎ ግራም ሳፋየር ማዕድን በማምረት ለገበያ ለማቅረብ መታቀዱንም ያመለክታሉ። በክልሉ ብዙ የማዕድናት ዓይነቶች ቢኖሩም በዋንኛነት የውጭ ምንዛሪን ከማስገኘት አንጻር በወርቅና በሳፋየር ማዕድናት ማልማት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡

በበጀት ዓመቱ ለ50 ባለሀብቶች የማምረት ፈቃድ እንደሚሰጥና እነዚህ ባለሀብቶች ወደ ማምረት ሥራ ሲገቡም ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ይጠቁማሉ። በማዕድን ዘርፉ በክልል ደረጃ 172 ሄክታር፣ በወረዳ ደረጃ 2 ሺ 300 ሄክታር መሬት ሥራ ላይ በማዋል ልማቱ እንደሚካሄድ ይጠቁማሉ። በክልሉ ባለፈው በጀት ዓመት በማዕድን ዘርፍ ኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ አካላት ፈቃድ መሰጠቱን ጠቁመው፤ ‹‹ማዕድን ለሚያመርቱ 670 አምራቾች፣ የምርመራ ሥራ ለሚያካሂዱ 499 እና በፈለጋው ለሚሰማሩ 412 ባለሀብቶች ፈቃድ ተሰጥቷል›› ይላሉ። ከእነዚህ ውስጥ ከማዕድን ሚኒስቴር ፈቃድ የወሰዱት 35 መሆናቸውን ያነሳሉ፡፡

በማዕድን ዘርፍ ለመሰማራት ፈቃድ ከወሰዱት መካከል ሪፖርት አድርገው ወደ ሥራ የገቡት 127ቱ ወይም 22 በመቶ ያህሉ ብቻ መሆናቸውን አቶ ፍስሃ አስታውቀው፣ ሌሎቹ ምን ዓይነት ደረጃ ላይ እንዳሉ እንደማይታወቅም ይናገራሉ። ከክልል ጀምሮ እስከ ወረዳ ያለው መዋቅር በሰው ኃይልም ሆነ በሌሎች ዘርፉን በሚመጥን መልኩ የተደራጁ አለመሆናቸውን ጠቁመው፤ በወረዳ ውስን የሰው ኃይል ወይም አንድ ሠራተኛ ብቻ ያለበት ሁኔታ እንዳለም ያነሳሉ። በዚህም በዘርፉ የተሰማሩትን ባለሀብቶች ድጋፍና ክትትል ለማድረግ አስቸጋሪ መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት በዘርፉ ያለው የመረጃ አያያዝ በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ይጠቁማሉ። እስካሁን ባለው ሁኔታ የክልሉ መረጃ አያያዝ በዘርፉ የተሰማሩ፣ ፍቃድ የወሰዱ እና ፍቃድ ያልወሰዱ አካላት ያልተለዩበት መሆኑን ያስረዳሉ። በመሆኑም በበጀት ዓመት መረጃዎችን የማደራጀቱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ይናገራሉ። ‹‹መረጃውን በማጥራት በዘመናዊ የዳታ አያያዝ ሥርዓት እንዲያዝ ይደረጋል። ዘመናዊ የመረጃ አደረጃጀት መኖሩ ደግሞ እነዚህ በአግባቡ ለይቶ እና አደራጅቶ ለመያዝ ያስችላል›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡

በክልሉ ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ብዙ የማዕድን ዘርፉ ሀብት መውደሙን ጠቅሰው፤ ይህም ሁኔታ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት በሚፈለገው ልክ አቅማቸውን አጠናክረው እንዳይጠቀሙ እያደረገ መሆኑን ይጠቁማሉ። አሁን በዘርፉ እየሰሩ ያሉት ኢዛናን የመሳሰሉ ድርጅቶችም የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት አቅማቸውን አሟጠው እየተጠቀሙ በኃላፊነት እየሰሩ መሆናቸውን ነው ያስገነዘቡት።

ሌሎች ግን በጦርነቱ ምክንያት በወደመባቸው ከፍተኛ ሀብት የተነሳ አቅማቸው መዳከሙን አስታውቀው፣ እነዚህ ባለሀብቶች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ያመለክታሉ። ክልሉ ባለበት የአቅም ውስንነት ላይ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮች በመደማመራቸው አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ አለመቻሉን ያስረዳሉ። ለእነዚህ ድርጅቶች ድጋፍ በማድረግ አቅማቸውን ማጠናከር ካልተቻለ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት እንደሚያስቸግርም ይናገራሉ፡፡

በሌላ በኩል በአመለካከት ረገድም የግንዛቤ ችግር መኖሩን ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፤ ወጣቱም ሆነ የተቀረው ህብረተሰብ ሕጋዊነት ተከትሎ መሥራት ላይ ያለው ዝግጁነት ማነስ የዘርፉ ሌላኛው ተግዳሮት መሆኑን ያነሳሉ። በዘርፉ በርካታ የሰው ኃይል፣ ቁሳቁስ እና ቴክኖሎጂ እንዲኖሩ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያመለክታሉ። በዚህ ረገድ ክልሉ ያለበት ደረጃ እስከታች ድረስ ወርዶ ክትትል ለማድረግ የሰው ኃይል እጥረት እና የትራንስፖርት ችግር መኖሩንም ያብራራሉ። ይህም ሥራውን ለማከናወን አዳጋች እንዳረገውም ነው ያስገነዘቡት፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ ክልሉ ከማዕድን ዘርፉ ማግኘት ያለበትን ገቢ እንዲያገኝ ሕጋዊ መንገድ የተከተለ ሥራ እንዲሰራ መደረግ አለበት። ይህም ሥራ ከአገልግሎትም ይሁን ከሮያሊቲ የሚገኘውን ገቢ ከፍ እንዲል ማድረግን ይጠይቃል። ክልሉም የማዕድን ዘርፉን የሚመራበት ደንብ ያልነበረው ሲሆን ዘንድሮ ይህ ደንብ ወጥቶ ሥራ ላይ እንዲውል ተደርጓል። ደንቡ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ ከፍ እንዲል፣ ለሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ እድል ለመክፈት የበኩሉን ሚና ሊጫወት ይችላል። በክልሉ በማዕድን ዘርፉ ልማት ላይ ለመሰማራት ፍቃድ የወሰዱ ባለሀብቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ ረገድ የማዕድን ሚኒስቴር ትኩረት ሰጥቶት መሥራት ይጠበቅበታል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 8/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You