ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች ነው

ቢሾፍቱ፡- ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምን ለማስከበር እየተጫወተች ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ:: በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የነበረው የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ ተጠናቀቀ::

የዩጋንዳ መከላከያ ሚኒስትር ጃኮብ ኦቦት ሰሞኑን በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ ጎን ለጎን የኢፌዴሪ አየር ኃይልን በጎበኙበት ወቅት ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የኢፌዴሪ አየር ኃይል ታሪኩና ያለበት ቁመና የሚደነቅ ነው ብለዋል:: ኢትዮጵያ በታሪክ በሰላም ማስከበር ሥራዎች ለቀጣናው ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቷንም ገልጸዋል::

ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ታሪካዊ ሚና ያላት ሀገር ናት ያሉት ሚኒስትሩ፤ ይህ እንቅስቃሴዋ ፓን አፍሪካኒዝምን እስከማምጣት የደረሰ መሆኑን ጠቅሰዋል::

ኢትዮጵያ የሌሎችን ሀገራት ችግርን እንደ ራሷ ችግር አድርጋ በመቀበል በእኔነት ስሜት ችግሮችን ለመፍታት በቁርጠኝነት የምትሰራ ሀገር መሆኗንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል:: ይህም በአፍሪካ በሰላም ማስከበር ሥራ ከፍተኛ ድርሻ ያበረከተች ሀገር አድርጓታል ነው ያሉት::

ዩጋንዳ ከኢትዮጵያ ጋር የረጅም ጊዜ ወታደራዊ ግንኙት ያላት ሀገር ናት በማለት፤ በተለይም በሥልጠና፣ በደህንነትና ሌሎች መስኮች ላይ በጋራ እንደምትሠራም ገልጸዋል::

የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች ጉባኤ”አፍሪካ በጠንካራ አንድነት፣ ለሁለንተናዊ ፀጥታና ሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ሲካሄድ የነበረው ጉባዔ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ የጉባዔው ተሳታፊዎች የአፍሪካ ሀገራት መከላከያ ሚኒስትሮች እና ወታደራዊ አታሼዎች ቢሾፍቱ የሚገኘውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ አየር ኃይል በመገኘት የሥልጠና እና የጥገና ማእከላትን እንዲሁም የበረራ ትምህርት ቤትን ጎብኝተዋል:: ከዚህም ባሻገር በትናትናው ዕለትም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርንና ሌሎች ተቋማትን ጎብኝተዋል::

የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በተለይም ትናንት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርንና የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጄንስ ኢንስቲትዩትን በተጎበኘበት ወቅት እንደገለጹት፤ ተቋማቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም መሥራት እንደሚችሉ ተናግረዋል። ሁለቱ ተቋማት ያላቸውን ልምድና እውቀት ማከፈላቸውም የዚሁ ማሳያ እንደሆነ አንስተዋል።

እንደ አህጉር ችግሮችን ለመፍታትም በጋራ መቆም ይግባናል በማለት፤ እንዲህ አይነት ተቋማትን መመስረት የሚፈልጉ ሀገራትን ለማገዝ ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗንም ገልጸዋል::

ተሳታፊዎች በጉብኝታቸው ወቅት፤ ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ሥራ ላይ ብቻ ሳትሆን ለሌሎች ሀገራት ጭምር በማሠልጠን ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ትልቅ ሚናን እየተጫወተች እንዳለ ገልጸዋል:: ይህ የመሪነት ሚና የአፍሪካ ሀገራትን የጋራ ደህንነት አቅም ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑንም ነው ያመላከቱት:: ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም እያበረከተች ካለው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ባሻገር የደህንነት ተቋማቶቿ ለሌሎችም አስተማሪ መሆናቸውን ገልጸዋል::

ጉባዔው የአፍሪካ ህብረትን “አፍሪካዊ ለአፍሪካ ችግሮች መፍትሄ” የሚለውን መርህ በማንፀባረቅ በሰላም ማስከበር ተልእኮዎች ውስጥ አንድነትን እና በራስ መተማመንን የማጎልበት ሰፊ የአፍሪካ አጀንዳን ያረጋግጣል የተባለ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ለሰላም ማስከበር የምታበረክተው አስተዋፅኦ ለዚህ ራዕይ ወሳኝ ሆኖ በመታየት ሀገሪቷን በአህጉሪቱ ዘላቂ ሰላም በማስፈን ረገድ ቁልፍ ተዋናይ አድርጓታል ሲሉ የጉባዔው ተሳታፊዎች ምስክርነት ሰጥተዋል።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 8/2017 ዓ.ም

Recommended For You