የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ የናይል ወንዝን የቅኝ ግዛት ስምምነቶችና ውሎች በተግባር የሻረ ማርሽ ቀያሪ የ21ኛው መክዘ ክስተት ከመሆኑ ባሻገር ከቡድ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው። የናይል ወንዝ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት ወደ ሥራ መግባት በቅኝ ግዛት ውሎች የሬሳ ሳጥን ላይ ለመጨረሻ ጊዜ የተመታ 12 ቁጥር ምስማር ነው። ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ “የናይል ወንዝ የትብብር ማሕቀፍ ስምምነት ወደ ተፈጻሚነት መግባት የዓባይን ውሃ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም የተደረገው ረጅም ጉዞ ፍጻሜ ነው።” ያሉት።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በበኩላቸው እንዳስታወቁት ፤ የናይል ወንዝ ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ በናይል ወንዝ ተፋሰስ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በጣም ብዙ ሀገራትን ያሳተፈ የሕግ ማሕቀፍ መፈረሙ ደስታው ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የተፋሰሱ አባል ሀገራት ነው። የስምምነት ማሕቀፉ ላለፉት አስርት አመታት በርካታ ሂደቶችን አልፎ ነው ከጥቅምት 3/2017 ዓ.ም ጀምሮ ሕጋዊ ማሕቀፍ ሆኖ የሚተገበረው። ማሕቀፍ የሁሉንም የተፋሰሱ ሀገራት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ቢሆንም ኢትዮጵያ ደግሞ ለናይል ወንዝ እያበረከተችው ባለው አስተዋጽኦ ልክ ተጠቃሚነቷን ያረጋግጣል፡፡
የሕግ ማሕቀፍ ስምምነቱ በ45 አንቀጾች የተደገፉ አስራ አምስት ዋና ዋና መርሆዎች ያሉት ሲሆን፤ ከመጠቀም መብት ጋር የተገናኙ፣ የውሃ ሀብት ጥበቃን፣ ተፋሰሱን በመንከባከብና በማልማት ዘላቂነት ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ የማድረግ ኃላፊነትንና አስገዳጅነትን ለሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት የሚሰጥ ሥርዓትን፤ እንዲሁም የተፋሰሱ አባል ሀገራት በተፋሰሱ ላይ ያሉ ማንኛውንም መረጃዎች በመለዋወጥ እንዲሰሩ የሚደነግጉ አንቀጾችን የያዘ ነው፡፡
ነባር የቅኝ ግዛት ስምምነቶች ፍትሐዊ ያልነበሩና የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት ማለትም የሱዳንና ግብፅን ተጠቃሚነት ብቻ የሚያረጋግጡ ከመሆናቸው ባሻገር፤ በተለይም ኢትዮጵያ ለናይል ወንዝ ከ85 በመቶ በላይ አበርክቶ እያደረገች የቅኝ ግዛት ውሎች ግን እሷን ያገለሉ ብቻ ሳይሆን እፍኝ ውሃ እንዳትጠቀም የሚደነግጉ ነበሩ። የትብብር ማሕቀፉ ግን ይሄን አድሎአዊ አሰራር በመሻር ፍትሐዊ አጠቃቀምን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
የናይል ተፋሰስ የትብብር ማሕቀፍ ከጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በይፋ ወደ ተግባር ገብቷል። ማሕቀፉ፣ የናይል ኮሚሽንን በማቋቋም የናይል ወንዝ አጠቃቀምና አስተዳደር በሕጋዊና ተቋማዊ ማሕቀፍ እንዲመራ የሚያስችል ነው። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፣ ማሕቀፉን ያልፈረሙ ሀገራት እንዲፈርሙ ጥሪ አድርገዋል። የማሕቀፍ ፈራሚዎች ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛኒያና ቡሩንዲ ናቸው። አበው ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ ስለ ታላቁ ወንዞችን ዓባይ አንዳንድ ነጥቦችን እናነሳሳ።
የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ የአፍሪካን አህጉር አንድ አስረኛ ይሸፍናል። በዓለማችን ከምንጩ እስከ ሜዲትራኒያን ባህር ድረስ 6ሺህ 700 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ረዥሙ ወንዝ ነው። የዓባይ ወንዝ ሁለት ታላላቅ ገባሮች አሉት። ከቪክቶሪያ ሀይቅ ተፋሰስ የሚነሳው ነጭ ዓባይና ከኢትዮጵያ ተራራማ ቦታዎች የሚመነጨው ጥቁር ዓባይ ነው። ለዓባይ ወንዝ 77 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ ማለትም 86 በመቶ ከእነለም አፈሩ በመገበር ጥቁር ዓባይ እንደ ስሙ ታላቅ ወንዝ ነው። ለራሱ ለጥቁር ዓባይ ደግሞ 49 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በመገበር ዓባይ ትልቁን ድርሻ ሲወስድ፤ ባሮ አኮቦ ወንዝ 17 ቢሊዮን ሜትር ኩብ እና የተከዜ ወንዝ 11 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በዓመት ይገብራሉ። የጥቁር ዓባይ የፍሰት መጠን ከሀገሪቱ አጠቃላይ ፍሰት ግማሽ ከመሆኑ ባሻገር በጠቃሚ ማዕድናትም የበለጸገ ነው። ጥቁርና ነጭ ዓባይ ሱዳን ካርቱም ላይ ይገናኙና ዓባይ /ናይል/ ይሆናሉ።
ዳሩ ግን የናይል ወንዝ የስምንት የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት ሀብት ጭምር ቢሆንም እስከ ዛሬ በብቸኝነት እየተጠቀሙ ያሉት ግን የግርጌ ተፋሰስ ሀገራት የሆኑት ሱዳንና ግብፅ ነበሩ። የጋራ የውሃ ሀብት ቢሆንም የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት እኤአ በ1929 በሱዳንና በግብፅ በቅኝ ግዛት ዘመን በተፈረመ አግላይ ስምምነት የተነሳ መጠቀም አልቻሉም። በእንግሊዝ አይዟችሁ ባይነት በተፈረመው ኢፍትሐዊ ውል መሰረት ለሱዳን 4 ቢሊዮን ሜትር ኩብ፤ የተቀረውን ማለትም 48 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ለግብፅ ጀባ ብሏል።
ይህ የቅኝ ግዛት ዘመን ውርዴ የሆነ ስምምነት ሱዳንና ግብፅ የራስጌ የተፋሰሱ ሀገራትን በድጋሚ በማግለል በራቸውን ዘግተው እኤአ እስከ ተፈራረሙበት 1959 ድረስ የቀጠለ ሲሆን፤ በእብሪት የተወጠረው ይህ ስምምነት፣ “ከግብፅ መንግሥት ፈቃድ ውጭ የውሃ መጠኑን ሊቀንስ የሚችል የመስኖም ሆነ የኃይል ማመንጫ ሥራዎችን በዓባይ ገባሮችና ሀይቆች ላይ መገንባት አይቻልም። “ይህ ግብዝነትንና እብሪትን የሚያሳይ ስምምነት ታዋቂው የግሪክ የታሪክ ሊቅ ሔሮዶተስ “ግብፅ የዓባይ ስጦታ ናት።” የሚለውን ይትበሀል የዘነጋ ነው። እኔ ግን ግብፅ የዓባይ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ስጦታ ናት ብዬ ነው የማምነው።
ጥንታዊ ስልጣኔዋም ሆነ የዛሬ ህልውናዋ ከዓባይ ጋር የተቆራኘ ሆኖ ሳለ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከራስጌ የተፋሰስ ሀገራት ጋር ተቀራርቦና ተባብሮ መሥራቱ ይቅርና የምታሳየን ንቀት ያበግናል። ከግርጌዋ ተፋሰስ ሀገራት ለዛውም ከሱዳን ጋር ስለ ዳግም የውሃ ክፍፍሉ ምክክር ካደረገች ከ15 አመታት በላይ እንደሆናት መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ ፈርኦኖችም ሆኑ የዛሬዎቹ ገዥዎች ምን ያህል ከዘመኑ ጋር የመሄድና መሬት ላይ ያሉ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ለመቀበል ፍላጎቱ እንደሌላቸው ያስረዳል። ሆኖም ውሎ አድሮ ሱዳን የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ማንሳቷ አልቀረም።
የ1929ኙ ስምምነት ላይ እንደገና መደራደር እንደምትፈልግ ግብፅን መወትወት ጀመረች። የ1959ኙ የውሃ ክፍፍል ላይም ጥያቄ ማቅረብ ቀጠለች። የተፋሰሱን ራስጌ ሀገራት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋገጥ አዲስ ስምምነት መፈራረም ካልተቻለ፤ ሱዳንና ግብፅ በአንድ በኩል፤ ኢትዮጵያና ሰባቱ የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት በሌላ በኩል ለግጭት የመዳረግ እምቅ አቅም እንዳለው ቀጣናዊ የውሃ ፖለቲካ ልሒቃን ያስጠነቅቃሉ።
የጋራ የሆነውን የውሃ ሀብት በጋራ መጠቀም ሲገባ፤ ግብፅ ግን ከማንኛውም ድርድር በፊት የግርጌም ሆነ የራስጌ ሀገራት የ1959ኙ ስምምነት እንዲቀበሉ ቅድመ ሁኔታ ታስቀምጣለች። ሆኖም ይህ የግብፅ ቁሞ ቀር ቅድመ ሁኔታ በተፋሰሱ ሀገራት ተቀባይነት አላገኘም። ምክንያቱም ስምምነቶቹ የተፋሰስ ሀገራትን በተለይ ሀገራችንን ያላሳተፉ ከመሆኑ ባሻገር ስምምነቶቹ የመንግሥታቱ ድርጅት እኤአ በ1997 ይፋ ካደረገው የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ድንጋጌ ጋር ይጣረሳሉ። ሆኖም የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ የሆነውን የዓባይ የውሃ ሀብት ለማልማት የግብፅ ፍቃድ አያስፈልጋቸውም።
ሱዳንና ግብፅ ዓባይን ለትላልቅ መስኖዎችና የኃይል ማመንጫነት ሲጠቀሙበት በአንጻሩ ሌሎች የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት ወንዙን የሚጠቀሙበት ለአነስተኛ ኃይል ማመንጫነት ብቻ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት የጋራ የሆነውን ሀብት በስፋት አልምተው የመጠቀም ፍላጎት ስለሌላቸው ሳይሆን ዓለማቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በግብፅ ተፅዕኖ የተነሳ ብደር የመስጠት ፍላጎት ስለሌላቸው ነው። የተፋሰሱ ሀገራት የሕዝብ ብዛት በከፍተኛ ፍጥነት በመጨመር ላይ መሆኑን ተከትሎ የውሃ ፣ የምግብና የኃይል ፍላጎታቸው በእጅጉ እያሻቀበ ነው።
የሚያሳዝነው እነዚህ ፍትሐዊ ያልሆኑ የፋይናንስ ተቋማት ለግብፅ ሲሆን እጃቸው ይፈታል። በዚህም ጭው ባለ በርሀ ግዙፍ መስኖዎችን ፣ ሀገሪቱን ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ያደረጉ ትላልቅ የውሃ ኃይል ማመንጫዎችን ገንብተዋል። በስተሰሜን የሱዳንና ግብፅ ድንበር ላይ ግብፅ በዓለማችን ረጅሙን የዓባይ ወንዝ በመገደብ በግዙፍነቱ ከዓለም 3ተኛ የሆነውን የአስዋን ግድብ ገንብተዋል። የአስዋን ግድብ 10 ዓመት ከፈጀ ግንባታ በኋላ እአአ በ1970 ተጠናቋል።
በ1954 ግብፅ ከዓለም ባንክ ብድር፣ ከአሜሪካ ደግሞ እርዳታ ለማግኘት ጠይቃ ተስፋ ተሰጧት የነበር ቢሆንም ከእስራኤል ጋር በገባችበት ውዝግብ የተነሳ ሳይሳካ ቀርቷል። በዚህ የተከፋችው ግብፅ ወዲያው ፊቷን ወደ ሶቪየት ሕብረት በማዞር ባገኘችው ብድር ግንባታውን ማካሄድ ችላለች ። ግድቡ 90ሺህ ሱዳናውያን ከማፈናቀሉ ባሻገር በቅርስነት ተከልለው የነበሩ ቦታዎችም በውሃ ተውጠዋል።
እነዚህ ተፈናቃዮች ከቀዬአቸው 600 ኪሎ ሜትር ርቀው እንዲሰፍሩ ሲደረግ ፤ በግድቡ የተነሳ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ግብጻውያን ግን 40 ኪሎ ሜትር ብቻ እርቀው እንዲሰፍሩ ተደርጓል። ግብፅ ይህን ግዙፍ ግድብ ስትገነባ ከሱዳን ውጭ ሌሎች ሀገራትን ማማከር አይደለም እወቁልኝ እንኳ አላለችም። ሱዳንንም ያማከረቻት አስባላት ሳይሆን በዜጎቿ ላይ የምትፈፅመውን ግፍ እንድታውቀው ይመስላል።
የአስዋን ግድብ 2ሺህ 100 ሜጋ ዋት በማመንጨት ማለትም ግማሹን የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ያሟላ ሲሆን ለከፍተኛ መስኖ ልማትም ውሏል። ግብፅ እምቅ የኃይል አማራጭ ቢኖራትም ከውኃ የኃይል ማመንጫዎች ውጭ የመጠቀም ፍላጎት የላትም። አንዳንድ ምንጮች እንደሚጠቁሙት 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን በርሜል የነዳጅ ድፍድፍ ክምችት በምድሯ ቢኖርም በቀን እያመረተች ያለው ከ640ሺህ በርሜል በታች ነው።
የተፈጥሮ ጋዝ ክምችቷ ወደ 2 ነጥብ 2 ትሪሊዮ የሚጠጋ ኩም የሚጠጋ ሲሆን እያመረተች ያለው ግን ወደ 60 ቢሊዮን ኩም የሚጠጋ ብቻ ነው። እንዲሁም 547ሺህ 500 በርሜል በቀን የተጣራ ነዳጅ ታመርታለች። ሰፊ የከርሰ ምድር ውሃ እንዳላትም ጥናቶች ያመለክታሉ። ይህ ሁሉ አማራጭ የኃይልም ሆነ የመስኖ ሀብት እያላት መላው ስስቷና ቀልቧ ዓባይ ላይ ነው። እሷ የተሻለ አማራጭ ያላት መሆኑን ዓይኔን ግንባር ያርገው ብላ በየአደባባዩ እየማለች፣ እየተገዘተችና እየካደች ፤ ኢትዮጵያ ዝናብን ጨምሮ በርካታ አማራጭ የውሃ ሀብት እያላት ጥቁር ዓባይ ላይ ግድብ የምትገነባው ግብፅን ለማንበርከክና ጂኦ ፖለቲካዊ ሚዛኗን ለመጨመር ነው ስትል በየመድረኩ የአዞ እንባዋን እየረጨች ነው።
ግብፅ የዓባይን የተፈጥሮ ፍሰት በመቀየር በረሀውን ለማልማት 30ሺህ 300 ኪሎ ሜትር የመስኖ ቦዮችን ገንብታለች። ከአስዋን ግድብ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ያህል ውሃ በመሳብ ቶሽካ የተባለውን ሰው ሠራሽ ሀይቅ በመገንባት በረሀውን እያለማች ትገኛለች። በአሁኑ ሰዓት ግብፅ 3 ነጥብ 76 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ ታለማለች። ከአስዋን ግድብና ከዓባይ ወንዝ ያልተገባ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሚነሱ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ሆኖ። በትነትና በስርገት የተነሳ በየዓመቱ ከ12 እስከ 14 በመቶ የሚደርስ ውሃ ከግድቡና ከመስኖ ቦዮች ይባክናል። ለመስኖ ከሚያስፈልገው ውሃ በላይ በመጠቀም ማባከንና ጥራት የሌለው የፍሳሽ መውረጃ በግድቡ ላይ ከሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች ይጠቀሳሉ።
ከአሜሪካው የካምፕ ዴቪድ ስምምነት በኋላ የግብፅና የእስራኤል ግንኙነት በመሻሻሉ ፤ የወቅቱ የግብፅ ፕሬዝዳንት አንዋር ሳዳት የፍልስጤምና የእየሩሳሌም ችግር የሚፈታ ከሆነ ከዓባይ ወንዝ 365 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ በየዓመቱ ለእስራኤል ለመስጠት ቃል ገብተው ነበር። ይህ የጂኦ ፖለቲካ የአሰላለፍ ለውጥ በራስጌ የተፋሰስ ሀገራት ላይ ውስብስብ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ አልቀረም።
ሌላዋ የግርጌ ተፋሰስና ጎረቤት ሀገር ሱዳን ግድቦችን ገንብታለች። እአአ በ1926 ሴናርን ለመስኖ፣ በ1936 ጀበል አውሊያ ለኃይል ማመንጫና ለመስኖ ገንብታለች። በ1950 3ኛውንና 420ሺህ ሄክታር መሬት መስኖ የማልማት አቅም ያለው የሮሴሪስ ግድብን እንዲሁም ከእዚህ በተጨማሪ ሌሎች ግድቦችን ገንብታለች። በዚህም በመስኖ መልማት ከሚችለው 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬቷ 1ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታሩን ማልማት ችላለች። በግብፅና በሱዳን በመስኖ እየለማ ያለ መሬት የዓባይን 86 በመቶ ከምታበረክተው ሀገራችን ጋር ስናስተያየው እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑ ሊያስቆጨን ይገባል።
ሻሎም ! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥቅምት 8/2017 ዓ.ም