ለሕዝብ የሰላም ጩኸት መልስ አለመስጠት በታሪክ ተወቃሽ የሚያደርግ ከፍ ያለ የልብ ድንዳኔ ነው

ሰላምን በድርድር ለማምጣት፣ ለማስቀጠል እና ለማጽናት የሚደረግ የትኛውም ዓይነት ጥረት የሰላምን ዋጋ በአግባቡ ከመረዳት ፣ ሰላም ማጣት ሊያስከትል የሚችለውን ሁለንተናዊ ጥፋት በሰከነ መንፈስ ከማስተዋል ፤ የየትኛውንም ማህበረሰብ በሰላም የመኖር መሻት በተጨባጭ ከመረዳት የሚመነጭ ከፍ ያለ የዓላማ ጽናት የሚጠይቅ የአስተሳሰብ ከፍታ ነው።

በሰው ልጅ ካለው ግለሰባዊ ማንነት /ሥብእና አኳያ እለት ተእለት ባለው መስተጋብር ውስጥ ከፍጥረታዊ ማንነቱ በመነጨ ልዩነቶች መፈጠራቸው የተለመደ እና ተጋማች እውነታ ነው። የታሪክ መዛግብት አብዝተው እንደሚያመላክቱት ይህ ልዩነት በዘመናት ለመጣባቸው የለውጥ መንገዶች መሠረት ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

እነዚህ ልዩነቶቹ የአስተሳሰብ ብዛህነትን በመፍጠር በመላው ዓለም ለሚገኙ የተለያዩ ወግ ባህሎች መፈጠር ዋነኛ ምክንያት ተደርገው ይወሰዳሉ። የሰው ልጅ አሁን ላይ ፍጥረታዊ ውበቱ አድርጎ ለተቀበለው እና ለሚንከባከበው ህብረብሄራዊነቱ ምንጭ ፤ በማህበረሰብ መካከል ለሚፈጠሩ መስተጋብሮች አቅም እንደሆነ ይታመናል።

በ21ኛው ክፍለ ዘመን እነዚህን የአስተሳሰብ ልዩነቶች በአንድም ይሁን በሌላ ፍጥረታዊ በረከት አድርጎ መቀበል የግድ የሆነበት ዘመን ነው ፤ ዘመኑን መዋጀት የሚቻለውም ከትናንት ስህተቶች ተምሮ የተለያዩ አስተሳሰቦችን አቻችሎ የተሻለ ዓለም መፍጠር የሚያስችል ዓለም አቀፋዊ ሥርዓት በመፍጠር ነው ።

ከዚህ ውጪ ልዩነቶችን በሃይል ለመደፍጠጥ የሚደረጉ ጥረቶች በቀደሙት ዘመናት ዓለምን ካስከፈሏት ያልተገባ ዋጋ አኳያ አሁን ላይ የጥፋት ሁሉ ምንጭ ፤ በየትኛውም መንገድ የሚወገዝ ፤ የኋላ ቀርነት ከዛም ባለፈ የቆመ ቀርነት መገለጫ የሆነ የአስተሳሰብ ስንኩልነት ነው።

ልዩነቶችን በሃይል ከመደፍጠጥ ይልቅ በልዩነቶች ዙሪያ ቁጭ ብሎ መነጋገር የተሻለች ዓለም ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ አትራፊ እንደሆነ ዓለም ከመቼውም ጊዜ በላይ የተረዳበት እና ለተግባራዊነቱም እየተጋ ያለበት ዘመን ነው። በተለይም የፖለቲካ ልዩነቶችን በድርድር የመፍታት አመራጭ ሰላማዊ ዓለም ለመፍጠር መተኪያ የሌለው አማራጭ ስለመሆኑ ዓለም አሁን ላይ ተጨማሪ አስረጅ የሚፈልግበት ወቅት አይደለም።

የትኛውም ማህበረሰብ በሰላም ለመኖር ካለው ፍላጎት አኳያ የትኛውንም ወደግጭት የሚወስድ ልዩነት በሰላማዊ መንገድ በድርድር ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ይደግፋል። ይህ ፍላጎቱ በአጋጣሚ የተገኘ ሳይሆን ከሳለፋቸው ሰላም አልባ ዓመታት እና ከከፈለችው ያልተገ ዋጋዎች የተነሳ ነው።

ኢትዮጵያውያንም ከሰላም ጋር በተያያዘ ከተቀረው ዓለም የተለየ ፍላጎት የላቸውም ፤ ለሰላም ካለን ቀናኢነት አኳያ ሰላም የእለት ተእለት የሕይወት መስተጋብራቸው ዋነኝ አጀንዳ ነው። ለዘመናት ከሰላም እጦት ጋር በተያያዘ ከከፈሉት ያልተገባ ብዙ ዋጋ አኳያም አበክረው የሚሹት ጉዳይ ነው።

በተለይም ከሰላም እጦት ጋር በየዘመኑ ብዙ ዋጋ ለመክፈል የተገደደው የሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ሕዝባችን ፤ ጦርነት እና የጦርነት ከበሮ አይፈልግም ፤ ግጭት እና የግጭት ዲስኩሮችን የሚሰማ የተከፈተ ጆሮ የለውም። ከቀደሙት የእርስ በርእስ ጦርነቶች /ግጭቶች ያተረፈው ነገር የለም ፤ወደፊትም ከግጭት እና ከጦርነት ሊያተርፍ የሚችለው አንዳች ነገር አይኖርም።

ትናንት በግጭት እና በጦርነት እራሱን ፤ ልጆቹን እና በልጆቹ ተስፋ ያደረጋቸውን ትናንቶቹን ተነጥቋል። ሀብት ንብረቱ ፤ በብዙ ጣር የገነባቸው መሠረተ ልማቶቹ ወድመዋል። በብዙ የሚመካባቸውን ሀገራዊ እሴቶቹ ደብዝዘዋል፤ የጠላቶቹ ፍላጎት አውቆትም ሆነ ሳያውቀው በላዩ ላይ ተጭኖበታል። በዚህም በድህነት እና ኋላቀርነት ውስጥ ተመጽዋች ሆኖ አንገቱን ደፍቶ እንዲኖር ሆኗል ።

ከዚህ እንደጥላ ከሚከተለው ችግር ለመውጣት ልዩነቶችን አቻችሎ የሚቀበል ሀገራዊ የፖለቲካ ሥርዓት መፍጠር ያስፈልጋል ። ይህ ደግሞ ከዓለም አቀፉ የፖለቲካ ሥርዓት ጋር መቀላቀል ፤ እራስን በዘመኑ እውቀት መዋጀት እንጂ ማነስ አይደለም። የመዘመን ሀሁ እንጂ ፤ጥራዝ ነጠቅነት አይደለም።

ይህንን እውነታ ከሁሉም በላይ ፖለቲከኞቻችን በአግባቡ ሊያጤኑት ይገባል ፤ በትንሹም በትልቁም፤ ጠበንጃ አንግቦ በሕዝብ የሰላም ፍላጎት ላይ በተቃርኖ ከመቆም በፊት ፤ ደግሞ ደጋግሞ ማሰብ በሚያስፈልግበት ዘመን ላይ እንዳሉ፤ ችግሮችን በድርድር ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች የማነስ ምልክቶች ሳይሆኑ የመዘመን መገለጫዎች መሆናቸውን ሊያስተውሉ ይገባል።

የሰላማዊ ድርድር ጥሪዎችን ተቀብሎ መቆም በራሱ ጀግና የሚፈልግ ፤ የዘመኑ የሕዝብ ወገንተኝነት መገለጫ መሆኑን በተለይም ጠበንጃ አንስተው በየጫካው በገዛ ወገናቸው ላይ የሚተኩሱ ሃይሎች ሊያጤኑት ይገባል ። ወንድምች እየገደሉ፤ እያገቱ ፤ በብዙ ጣር የተገነቡ መሠረተ ልማቶች እያወደሙ ፤ የሕዝብን የሰላም ፍላጎት የሚንጥ የግጭት ምንጭ እየሆኑ ስለ ሕዝባዊነት ሆነ ወገንተኝነት መናገር አይቻልም። ትልቅ አለማስተዋል፤ መታወር ነው።

ሰላም በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ያለ ሕዝባችን ትልቁ ጥያቄ ነው። ከሰላም እጦት ጋር በተያያዘ እየከፈለ ያለው ዋጋ፤ የግጭትን /የጦርነትን አስከፊነትን ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲያውቅ ፤ ስለሰላም የበለጠ እንዲጮህ እያደረገው ነው ፤ ለዚህ ጩኸት መልስ መሆን አለመቻል በታሪክ ተወቃሽ የሚያደርግ ከፍ ያለ የልብ ድንዳኔ ነው።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 8/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You