በመዲናዋ ከ180 ሺህ በላይ እናቶች በቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም ተጠቃሚ ሆነዋል

አዲስ አበባ፦ በመዲዋ ከ180 ሺህ በላይ እናቶችን በቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የቀዳማይ ልጅነት እድገት ፕሮግራም ከፅንስ አስከ 6 ዓመት ያለውን የእድሜ ክልል የሚያካትት ነው። ይህ የእድሜ ክልል በኢትዮጵያ ትኩረት ያልተሠጠው ነገር ግን ለሰው ልጆች እድገት ዋና መሠረት ነው። ከዚህ አኳያም በመዲዋ ከ180 ሺህ በላይ እናቶችን በቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

ፕሮግራሙ ከጽንስ እስከ 6 ዓመት የእድሜ ክልል ላሉት ህፃናት የአልሚ ምግብ መስጠት፣ የህፃናት ማቆያና የህፃናት መጫወቻ ሥፍራዎች ውብና ማራኪ በሆነ መንገድ በመስራት ህፃናቱ በአካባቢያቸው ባሉ ቦታዎች እንዲዝናኑና እንዲጫወቱ ያግዛቸዋል ብለዋል።

ሕፃናት ከተፀነሱበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 6 ዓመት ድረስ አእምሯዊና አካላዊ ጤናቸውና እድገታቸው ተጠብቆ እንዲወለዱ፣ ተደስተው እንዲያድጉ፣ በአካላቸውና በአዕምሯቸው የዳበሩ ዜጋ እንዲሆኑ በተጀመረው ነፍሰ-ጡር እናቶች፣ አጥቢ እናቶችንና ሕፃናት የቀጥታ አልሚ ምግብ ድጋፍ ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውንም አውስተዋል፡፡

የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ልጆቻቸውን በአካል፣ በአዕምሮ እና በሥነ ልቦና የተሟላ ጤንነት እንዲኖራቸው ልዩ ትኩረት የሚሰጥበት ፕሮግራም ነው ያሉት ዶክተር ዮሐንስ፤ ፕሮግራሙ ከተጀመረ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ180 ሺህ በላይ እናቶችን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ፕሮግራሙን መሠረት በማድረግ ከአምሥት ሺህ 300 በላይ የቤት ለቤት የወላጆችና ያሳዳጊዎች የምክር ሰጪ ባለሙያዎችን አስልጥኖ አስመርቋል። በዚህም ከ180 ሺህ በላይ እናቶችን ተደራሽ በማድረግ የእድገት ውስንነት የተገኘባቸውን ህፃናት መጠን ከ13 በመቶ ወደ 11 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

ባለሙያዎቹ የእድገት ውስንነት ያለባቸውን ህፃናት የመለየት፣ የመከታተል እንዲሁም የበለጠ ምርመራና ህክምና የሚያስፈልግ ከሆነ ደግሞ ወደ ሆስፒታል የማስተላለፍ ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸው፤ ይህንንም ቤት ለቤት በመዘዋወር እንደሚያከናውኑ ገልጸዋል።

የቀዳማይ ልጅነት እንክብካቤ በከተማዋ የታቀደውን ሥራ በስኬት ለመፈጸም የሚያስችል መሠረታዊ መንገድ ነው ያሉት ዶክተር ዮሐንስ፤ ፕሮግራሙ የሕፃናትን ቤተሰቦች ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ተወዳዳሪ ዜጋ እንዲሆኑ የሚያስችል ፕሮግራም መሆኑን አስረድተዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት በአዲስ አበባ ሕፃናት ለትምህርት ያላቸውን ዝግጁነትና አጠቃላይ የቀዳማይ ልጅነት እንክብካቤ ያለበትን ደረጃ በጥናት የፈተሸ ሲሆን በጥናቱ ግኝት መሠረት ዕድሜያቸው ከሦስት ዓመት በታች ካሉ ስምንት ሕፃናት አንዱ ወይም 13 በመቶ ያህል በዕድሜያቸው ሊደርሱበት ከሚገባቸው ዕድገት ደረጃ በታች መሆናቸው ተረጋግጧል ብለዋል።

ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው አምስት በመቶ ከፍ ያለ ሲሆን የኢኮኖሚ ችግር ባለባቸው ቤተሰቦች ውስጥ የሚያድጉ ሕፃናት የተሻለ ቤተሰብ ውስጥ ከሚያድጉ እኩዮቻቸው የትምህርት ቅቡልነታቸው አነስተኛ መሆኑንም ይጠቁማል ነው ያሉት፡፡

እ.ኤ.አ. በ2026 በቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም 330 ሺሕ እናቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ጥቅምት 8/2017 ዓ.ም

Recommended For You