ለዜጎች ህክምና በቴክኖሎጂ ተደራሽ ለማድረግ እየተጋ ያለው ወጣት

የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ለማኅበረሰብ ደህንነት እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት መሠረታዊ አገልግሎቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የጤና አገልግሎት አቅርቦት ሲባል ታዲያ በሽታዎችን የመከላከል፣ የምርመራ፣ እና የክትትል አገልግሎቶችን ያጠቃልላል፡፡

እ.ኤ.አ በ2021 ዓ.ም በተካሄደው የአፍሪካ የጤና አጀንዳ ጉባዔ ላይ በመላው አፍሪካ እስካሁን ድረስ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት መጠን 52 ከመቶ ብቻ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ይኸን ተከትሎም የጤና ባለሞያዎች የህክምና አገልግሎት ለተገልጋዩ ምቹ በሆነ ሁኔታ፣ በተመጣጣኝ ዋጋ ለሁሉም እንዲደርስ መደረግ አለበት ሲሉ ጥሪ ያቀርባሉ፡፡ በተጨማሪም መንግሥታት በትብብር መሥራት እንዳለባቸውም ያሳስባሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ የጤና አገልግሎቱን ለኅብረተሰቡ ለማዳረስ ባለፉት በርካታ ዓመታት የተከናወኑ ተግባራት ከሞላ ጎደል በገጠር አካባቢዎች ሳይቀር የጤና ኬላዎች እንዲኖሩ አስችሏል። ምንም እንኳን የጤና አገልግሎትን ለኅብረተሰቡ በማዳረሱ ሂደት መሻሻሎች መኖራቸው ቢነገርም አሁንም የሚታይ የተደራሽነት ችግሮች እንዳሉ በተደጋጋሚ ይገለጻል። የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ አንዱ መንገድ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መጠቀም ስለመሆኑ ብዙዎች ይናገራሉ።

ዶክተር ሲሳይ አበባ ይባላል። ወጣት የህክምና ባለሙያ ነው። በተለያዩ የመንግሥትና የግል የህክምና ተቋማት በሙያው ተሰማርቶ የቆየ ሲሆን በሥራ ቆይታው ከተመለከተው የህብረተሰብ ችግር በመነሳት በቴክኖሎጂ የተደገፈ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት በማሰብ የቴክኖሎጂ ኩባንያ አቋቁሟል።

ኬ.ኤም.ኤስ.ኢ.ቲ.ኤች ኽልዝ ትሬዲንግ አ.ማ (ጤናዎ ዲጂታል ኽልዝ) የዲጂታል ጤና አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ መሥራች የሆነው ዶክተር ሲሳይ ሲናገር፤ ‘’እንደ ሀገር የዜጎች መሠረታዊ ፍላጐት የጤና አገልግሎትን ማግኘት ነው። ነገር ግን ዜጎች የህክምና አገልግሎት ፈልገው ወደ ጤና ተቋማት ሲመጡ ተገቢውን አገልግሎት ለማግኘት እጅግ ይቸገራሉ፤ በተጨማሪም በሐኪም የታዘዙ መድኃኒቶችን በቀላሉ አያገኙም፡፡ ይህንን ችግር ለማቃለል በማሰብ ነው ወደዚህ ሥራ የገባነው’’ ይላል

በአዲስ አበባ ከተማ ባደረግነው ጥናት 40 ከመቶ የሚሆኑ የህክምና አገልግሎት ፈላጊዎች ሐኪም አግኝተው ማማከር አይችሉም። 60 ከመቶ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ የታዘዘላቸው መድኃኒት በአቅራቢያቸው ስለማይገኝ ሰዓታትን መድኃኒት በመፈለግ ያባክናሉ የሚለው ዶክተር ሲሳይ በተለይ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ማለትም በካንሰር፣ በስኳር፣ ደም ግፊት የሚሰቃዩ ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ ለዚህ ችግር የተጋለጡ ናቸው ይላል።

የሀገራችን የጤና ሥርዓት ባሕላዊ ስለመሆኑ የሚናገረው ዶክተር ሲሳይ፤ በህክምና ተቋማት ከፍተኛ አገልግሎት ፈላጊ ስላለ በወረፋ የተጨናነቀ ነው፣ የመድኃኒት አቅርቦት ደካማ ነው፣ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ መንግሥት ከፍተኛ ወጪ እያወጣ ቢሰራም የሚታየው ለውጥ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ከዚህ አኳያ በሀገሪቱ የተሻለ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ሥራ መሥራት የውዴታ ግዴታ ነው ይላል።

አሁን ባለው ሁኔታ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ አንድን ሐኪም ለማግኘት በትንሹ ከሁለት ሰዓት እስከ ሶስት ይፈጃል፤ ታካሚ ከዶክተሩ ጋር የሚኖረው ጊዜ ግን ቢበዛ ከአስራ አምስት ደቂቃ የማይበልጥ ነው። በዚህ ምክንያት የሚባክነው ጊዜ ከፍተኛ ነው የሚለው ዶክተር ሲሳይ፤ በዚህ ቴክኖሎጂ ግን ህክምና የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በጥቂት ደቂቃ ውስጥ የሚያስፈልገውን የህክምና ባለሙያ ማግኘት እንደሚችል ይናገራል።

የከተማ መስፋፋት እየበዛ በሄደ ቁጥር ሰዎች ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድላቸው እየሰፋ ይሄዳል የሚለው ዶክተር ሲሳይ፤ ተላላፊ ባልሆነ ህመም የተያዙ ሰዎች በየቀኑ ወይም በየሳምንቱ አልያም በየወሩ መድኃኒት ይወስዳሉ፤ እነዚህ ሰዎች በዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው በቤታቸው ሆነው የሚያስፈልጋቸውን የህክምና ዕርዳታ ማግኘት እንደሚችሉ ይናገራል።

ድርጅቱ ይህንን ቴክኖሎጂ በተለያዩ አማራጮች ይዞ መጥቷል የሚለው ሲሳይ፤ የመጀመሪያው በድረገፅ www/ tena .com መጠቀም ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ድምፅን በመጠቀም የሚሰጥ አገልግሎት ነው። ሰዎች የሞባይል ስልካቸውን በመጠቀም በርቀት ካለ የህክምና ባለሙያ ጋር በመነጋገር የመጀመሪያ የህክምና ዕርዳታ ማግኘት እንዲችሉ የሚያደርግ ነው ይላል።

አንድ ሰው ሐኪም ሲፈልግ ወደ ዌብሳይቱ ወይም የሞባይል መተግበሪያ ውስጥ በመግባት በስፔሻሊቲ ስንት ባለሙያ እንዳለ የስንት ዓመት ልምድ እንዳለው አይቶ፣ የክፍያ መጠኑ ምን ያህል እንደሆነ ተመልክቶ፣ መቼ አገልግሎት እንደሚሰጡ አውቆ በፈለገው አማራጭ በድምፅ ሆነ በምስል የማማከርና ህክምና አገልግሎት ማግኘት እንደሚችል ይናገራል።

በሌላ መልኩ በዚህ ቴክኖሎጂ የሚሰጠው አገልግሎት አሁን ያለውን የሰዎች በአካል ተገኝቶ ህክምና የመከታተል ሂደትን የሚከተል ሆኖ ነገር ግን ቴክኖሎጂው አካሄዱን በማዘመን የመጣ ነው’’ ይላል። ‘’ሰዎች የት ጋር ሄደው የሚፈልጉትን ዶክተር ማግኘት እንደሚችሉ አያውቁም በዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ግን የሚፈልጉትን ሐኪም ካገኙ በኋላ ቀጠሮ በመያዝ ሐኪሙ ወዳለበት የጤና ተቋም ሄደው ህክምና ማግኘት እንዲችሉ ያደርጋል’’ ይላል።

በተጨማሪም ህክምና ፈላጊዎች ቤት ለቤት የሚሰጥ የጤና አገልግሎት ከድርጅቱ ያገኛሉ የሚለው ዶክተር ሲሳይ፤ በዘርፉ የበቃ እውቀት ያላቸው ነርሶች በመጠቀም የቤት ውስጥ ህክምና ለሚፈልግ ሰው አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ አንዱ የድርጅቱ ሥራ ነው። በዚህ ሂደት አገልግሎት ፈላጊው በቤቱ ሆኖ ህክምና ማግኘት እንዲችል መንገዱን ቀላል ማድረግ እንደተቻለ ይናገራል።

ይህ ቴክኖሎጂ ህክምናን ተደራሽ በማድረግ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው የሚለው ዶክተር ሲሳይ፤ ማንኛውም የህክምና አገልግሎት ፈላጊ ግለሰብ ወደ 9456 የጥሪ ማዕከል በመደወል የሚፈልገውን አፋጣኝ የህክምና አገልግሎት ማግኘት እንዲችል ታስቦ የተሰራ በመሆኑ በዚህ ረገድ ትልቅ ትርጉም እንደሚኖረው ይናገራል።

ይህ ቴክኖሎጂ ሌላው ፋይዳ ሰዎች አቅማቸውን ባገናዘበ አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻሉ ነው የሚለው ዶክተር ሲሳይ፤ የካርድ እና መሰል ወጪ ሳይኖርበቸው በቀላል ወጪ አንድ ሰው የጤና ሁኔታውን ማወቅ ይችላል፡፡ ከአንድ ዶክተር ጋር ስለጤናው የምክር አገልግሎት የማግኘት ዕድል ያገኛል፡፡ ስለዚህ በትንሽ ወጪ ጤናን ለመጠበቅ የሚያስችል አሰራር እንደሆነ ይናገራል።

‘’አሁን ባለው የሕይወት ልምምድ ሰዎች ሩጫ ላይ ናቸው’’ የሚለው ዶክተር ሲሳይ፤ ብዙ ህመምና የጤና እክል እያለባቸው ከዛሬ ነገ ወደ ህክምና ቦታ እሄዳለሁ እያሉ ጊዜ ይወስዳሉ፡፡ በዚህ ሂደት ድንገት ሕይወታቸው ያልፋል፤ ይህ ቴክኖሎጂ ግን የ24 ሰዓት አገልግሎት ስለሚሰጥ ይህንኑ በመጠቀም ራስን ከከፋ ጉዳት መታደግ እንደሚቻል ይናገራል።

እንደ ዶክተር ሲሳይ ገለፃ፤ ኩባንያው ይዞት የመጣው ሌላው ትልቁ ነገር ሀገሪቱ ብዙ ኢንቨስት አድርጋ ያስተማረቻቸው የህክምና ዶክተሮች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ማስቻሉ ነው ይላል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እነዚህ ባለሙያዎች በተፈለገው ልክ ሥራ እያገኙ አይደለም፤ አሁን ግን አንድ ዶክተር ሥራ ለመሥራት የግድ ክሊኒክ ወይም ሆስፒታል መገንባት ሳይጠበቅበት በዚህ ቴክኖሎጂ አማካኝነት የራሱን አቅም በማስተዋወቅ ሥራ መሥራት እንዲችል በር መክፈት ተችሏል። ከዚህ ባለፈ ባለሙያው በሚኖርበት አካባቢ ለሚገኝ የህክምና ፈላጊ አገልግሎት በመስጠት የሥራ ዕድል በቀላሉ እንዲያገኝ የሚያደርግ ስለመሆኑ ይናገራል።

የጤና ባለሙያ በዚህ የቴክኖሎጂ መስመር እራሱን ስላስመዘገበ ብቻ ሥራ መሥራት አይችልም የሚለው ዶክተር ሲሳይ፤ እያንዳንዱ የትምህርት ማስረጃና የሙያ ማረጋገጫ ፈቃድ ትክክለኛነት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከጤና ሚንስቴር ጋር በመተባበር እንዲረጋገጡ ይደረግና ከዚህ በኋላ ነው ወደ ሥራ የሚገቡት፡፡ ይህም ተገልጋይ ጥራቱን የጠበቀ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኝ በማድረግ ረገድ የሚኖረው ትርጉም ከፍተኛ ነው ይላል።

በአሁኑ ወቅት ከ300 በላይ ዶክተሮች፣ 70 ስፔሻሊስቶች፣ ከ60 በላይ ነርሶች፣ 15 የፋርማሲ እና 4 የላብራቶሪ ባለሙያዎች ብሎም የሥነ ልቦናና የአዕምሮ ጤና አማካሪዎች በሲስተሙ ተመዝግበው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ የሚለው ዶክተር ሲሳይ፤ በተቋም ደረጃ ደግሞ ከ267 በላይ ተቋማት ማለትም 5 ሆስፒታል፣ 61 መድኃኒት አከፋፋዮች፣ ከ150 በላይ የፋርማሲ ባለቤቶች በጋራ እየሰሩ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ትልቅ እመርታ ነው ይላል።

ባለፉት አራት ወራት በዚህ ቴክኖሎጂ የጤና አገልግሎት ለማግኘት የተመዘገቡ 42ሺህ ሰዎች አሉ የሚለው ዶክተር ሲሳይ፤ ከእነዚህ ውስጥ 11ሺህ ሰዎች አገልግሎቱን አግኝተዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም ካለው ፍላጐት አንፃር የተጠቃሚዎችንም ቁጥር አነስተኛ የሚባል ነው፡፡ ይህንን ለማሳደግ ቴክኖሎጂውን የማስተዋወቅ ሥራ በስፋት መሥራት እንደሚገባ ይናገራል።

የዜጎች ዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ከጊዜ ወደጊዜ መሻሻል እያሳየ ቢመጣም አሁንም በሚፈለገው መጠን አላደገም የሚለው ዶክተር ሲሳይ፤ በተለይ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ህክምና ማግኘት እንደሚቻል አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ግንዛቤ የለውም፤ አሁንም አብዛኛው ሰው ባሕላዊ መንገድ ተጠቅሞ ህክምና ማግኘት ነው የሚፈልገው፤ ይህንን ችግር ለመፍታትና አስተማማኝና ተዓማኒነት ያለው ዲጂታላይዝድ የጤና አገልግሎት መስጠት እንደሚያስፈልግ ይናገራል።

የጤና ሚንስቴርን ጨምሮ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እየሰሩ ስለመሆኑ የሚናገረው ዶክተር ሲሳይ፤ በተጨማሪም በተመሳሳይ የዲጂታል ጤና ዘርፍ ከተሰማሩ ድርጅቶች ጋር በየጊዜው የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል በትብብር የተለያዩ ሥራዎችን እየሰሩ ስለመሆናቸው ይናገራል።

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ቴክኖሎጂ መጠቀም ካልቻለች ከመቶ ሃያ ሚሊዮን በላይ ሕዝቧን ማስተማር እንዲሁም በጤናው ዘርፍ ቁጥሩ ከፍተኛ ለሆነ ሕዝብ ህክምና ተደራሽ ማድረግ አትችልም። በግብርናውም ቴክኖሎጂ በመጠቀም መሥራት ካልተቻለ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ መመገብ አይታሰብም፡፡ ትልቅ ቁጥር ያለው ሕዝብ ነው ያለውና ወደ እያንዳንዱ ቤት መድረስ የሚቻለው በቴክኖሎጂ ነው፡፡ ስለዚህ ከምንም በላይ እንደ ሀገር ለዘርፉ ትኩረት መስጠት ግዴታ ነው ይላል።

በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ በባህርዳር፣ መቀሌ፣ አዳማና ሀዋሳ ከተሞች ላይ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የጤና አገልግሎት ለመስጠት እቅድ እንዳለ የሚናገረው ዶክተር ሲሳይ፤ በዚህም ለዜጎች የተቀላጠፈ የህክምና አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር ከ5ሺህ በላይ ለሚሆኑ የህክምና ባለሙያዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚሰራ ይናገራል።

መንግሥት በሁሉም ዘርፍ ለሚተገበሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ያለው አመለካከት አበረታችና ይበል የሚያሰኝ ነው የሚለው ዶክተር ሲሳይ፤ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው። ነገር ግን በታችኛው የመንግሥት መዋቅር ከፍተኛ ችግር አለ፤ ለኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ጀማሪ ድርጅቶች እንደማንኛውም የንግድ ድርጅት ነው አገልግሎት የሚሰጡት፡፡ ነገር ግን ከንግድ ፈቃድና ግብር አኳያ አበረታች የሆኑ አሰራሮች ተግባራዊ መሆን እንደሚገባቸው ተናግሯል።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 8/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You