ወሩንና ዓመቱን ጠብቀው ቡሄ ለመጨፈር ቤታችን ድረስ ለመጡት ታዳጊ ወንዶች ልጆች ሙልሙል ዳቦ ወይንም የሣንቲም ስጦታ በመሸለም ሳይረሱን ስለጎበኙን “ዓመት ዓመት ያድርስልን” በማለት ረጅም ዕድሜንና ስኬትን እየተመኘን የሸኘናቸው በዚህ በያዝነው የነሐሴ ወር አጋማሽ ነው። ልጆቹም በብላቴና አንደበታቸው “ዓመት አውዳመት ድገሙና ዓመት!” እያሉ መርቀውናል። እኛም የልጆቻችንን ምርቃት በትልቅ ደስታና አሜንታ ተቀብለን ወደ “አዲሱ ዓመት” ስለመሸጋገራችን እርግጠኛ በመሆን እንዳቅማችን የአዲስ ዓመቱን የበዓል ዝግጅት ጀምረናል። ድንቅ ሀገራዊ ባህል። ቀለሙ የማይደበዝዝ የትውልድ ነባር ትውፊት። እንደልጆቻችን ምኞት ከዘመን ዘመን ሳንጎድልና ዘመንም ሳይጎድልብን ከዓመት ዓመት ያሸጋግረን።
ልንሰነባበተው የቀናት ዕድሜ ስለቀሩት ስለ “አሮጌው ዓመታችን” እና ከደጃፋችን ስለደረሰው ስለ “አዲሱ ዓመት” ጥቂት እናሰላስል። ባለፈው የአንድ ዓመት የጊዜ ቀመር ውስጥ ሀገራችን በርካታ ውጣ ውረዶች ማስተናገዷ እውነት ነው። እኛ ዜጎቿ ያነባንባቸው፣ የተከዝንባቸው፣ የተሳቀቅንባቸውና አንገት ያስደፉን በርካታ ክስተቶች ደጃፋችንን አንኳኩተው በመግባት የሐዘን ፍራሽ ላይ እንዳስቀመጡን አንዘነጋም።
የመፈናቀል ክፉ ዕጣ የወደቀባቸው ዜጎቻችን ከፊሎቹ ሕይወታቸውን ሲያጡ አብዛኞቹም አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸውና ንብረታቸው ወድሞባቸው በመጠለያ ፍራሾች ውስጥ ተኮራምተው እንባቸውን ሲያፈሱ አስተውለን አብረን አንብተናል። በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ የደረሰው አሰቃቂ አደጋ የዚህን ፀሐፊ ልጅ ጨምሮ በርካታ ዜጎቻችንንና የዓለም ዕንቁ ልጆችን አሳጥቶን የሐዘን ከልን የለበስነው በዚሁ ዓመት ነበር። እስከ ዛሬ ድረስ የሐዘን ቱቢት ክንብንባችንን ያላወለቅን ዜጎችም በርካቶች ነን።
በጨካኝ እጆች የሞት ጽዋ በተጎነጩት የአማራ ክልል መሪዎችና በተከበሩት ጄኔራል መኮንኖቻችን ላይ የደረሰው ክፉ ሀገራዊ ሀዘንም አቁስሎን ያለፈው ትናንት ነው። የክፉ ቀናት ታዳጊና የፅናት ተምሳሌት አድርገን ያከበርናቸውን አይተኬ መሪዎች ማጣት ከብሔራዊ ልቅሶም የከፋ ስብራት ጥሎብን አልፏል። የእነዚያ ጀግኖች ቤተሰቦች ሀዘን የተቀመጡበት ፍራሽ ገና ተጠቅልሎ ያለመነሳቱን ልብ ይሏል።
ክፉ አድራጊ በቀለኞችን ለመቆጣጠርና አደብ ለማስገዛት የታወጀው ጊዜያዊ አዋጅም በአንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች ዛሬም እንደ ፀና ነው። እብሪተኞች እስኪገሩ፣ ወንጀለኞች ታድነው ሙሉ ለሙሉ በፍትሕ አደባባይ ቆመው እስክንመለከት ድረስ የኮማንድ ፖስቱ ተግቶ መሥራቱ አግባብ እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ ይታመናል። በዚህ የፀጥታ አጠባበቅ መስክ ላይ ተሠማርተው ግዳጃቸውን እየተወጡ ላሉት ጀግኖቻችን “ብሩክ ሁኑልን!” ብለን በሕዝባዊ ምርቃት እንባርካቸዋለን። በመንግሥታዊ ሽልማትና ሹመት ቢደምቁም የብዙዎቻችን ደስታ ነው።
ያለፈው አንድ ዓመት የኢኮኖሚ ሁኔታም ሕዝብን ለመራር እሮሮ ዳርጎ እንደነበርና ዛሬም ድረስ ግርሻቱ ስላልለቀቀን “ሀንግ ኦቨሩ” እንደተጣባን አለ። የዕለት ፍጆታችንን መሸመት ተስኖን በዋጋ ግሽበት ታሽተናል። የውሃና የመብራት ፈረቃው አንገፍግፎን በጧፍና በሻማ ስንጨናበስ በርካታ ወራትን አሳልፈናል። ለቻይና የሶላር ሸቀጥ አምራቾች ምስጋና፣ የፀሐይ ብርሃንን ያለምንም ክፍያ በቸርነቱ ለሚለግሰን ፈጣሪ ክብርና ውዳሴ አይጓደልበት እንጂ እንደ አምና ካቻምና የኩራዝ ተጠቃሚ ብንሆን ኖሮ በነዳጅ ውድነትና አዘውትሮ መጥፋት ይሄኔ አሳራችን በገዘፈ ነበር። የዩኒቨርሲቲ ግቢዎቻችን ሰላም መናጋቱን በተሰማባቸው ቀናት ሁሉ ወላጆች እንቅልፍ አጥተው በፆም በፀሎት እየቃተቱ ያማጡት በዚሁ ዓመት ነበር።
አልሰክን ያለው የፖለቲካችን እሰጥ አገባ በኑሯችን ጣጣ ላይ ተደምሮ ሰላም መንሳቱ፣ ያም አልበቃ ብሎ በማኅበራዊ የትስስር ኔት ወርኮች ላይ ሲዘሩብን የነበሩት እኩይ እንክርዳዶችም አበዛዛቸውና አይነታቸው ይህንን ያህላል ተብሎ የሚገመት አልነበረም፤ አይደለምም። ጋሻና ጦር አንስተን ርዕስ በርዕስ እንድንፋለም፣ ሰይፍና ሻምላ እያወናጨፍን እንድንበላለት ያልተደገሰልን የጥፋት ድግስ አልነበረም። ዕድሜ ለትዕግሥተኛው ሕዝባችን እንጂ ብዙዎች በየመረባቸው ውስጥ የሚያጨራርስ አሽከላ ለመዘርጋት ያልሞከሩት ሙከራ አልነበረም።
የውጭ ምንዛሪ ድርቅ ሀገሪቱን እንደ ክፉ ምች እያማታ የብሔራዊ ገንዘባችን አቅም ተልፈስፍሶ የመግዛት አቅሙ መሽመድመዱ ሳያንስ በኮንትርባንዲስቶች ይከወኑ የነበሩት ሤራዎች በራሳቸው ግርምት የሚፈጥሩ ነበሩ። የውጭ አገራት ገንዘቦች ከዋቤሸበሌ ወንዛችን እኩል ለመፍሰስ ሲሞክሩ ጥቂቶቹ በኬላዎች ላይ የተገደቡበት፣ የወርቅ ጥፍጥፍ ሀገራዊ ሀብት እንደ ጫማ ሶል ተዘጋጅቶ ሀገር ጥሎ ሊኮበልል ሲል እጅ ከፍንጅ እየተያዘ መመለሱን ከመቼውም ዓመታት ይልቅ ደጋግመን የሰማነው ባለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ነበር። በአሥራ ሁለት ወራት ውስጥ የተፈታተኑን ሀገራዊ ችግሮቻችን በጠቃቀስኳቸው አብነቶች ብቻ የሚወሰኑ ሳይሆን ሁሉንም እንዘርዝር ብንል አንድ ግዙፍ ጥራዝ “መዛግብት” ላይበቃው ይችላል።
ቡሄ ጨፋሪ ልጆቻችን “ዓመት አውዳመት ድገሙና” እያሉ የመረቁን ምርቃት እነዚህን መሰል ሀገራዊ ችግሮቻችን በሚቀጥለው ዓመት እንዳይሸጋገሩ ጭምር በመመኘት ነበር። “እንዲሁ እንዳለን አይለየን” ብለው ሲመርቁንም አሜን ብለናል። “ክበሩ በስንዴ ክበሩ በጤፍ” እያሉ በየዋህ አንደበታቸው ስንዴያችንን በሀገር ውስጥ እንድናመርት እንጂ ከውጭ እየሸመትን እንዳንመግባቸው በመልካም ምኞት አሳስበውናል። እኛም አሜን ብለን በረከታቸውን ተቀብለናል።
እነዚህን መሰል ክፉ አበሳዎች በመጭው ዓመት በምድራችን ላይ እንዳይከሰቱ የጥላሁን ገሠሠን ዘመን አይሽሬ የዜማ ግጥም ማስታወሱ ቦታው ይመስለኛል።
‹‹ክረምት አልፎ በጋ መስከረም – ሲጠባ መስከረም ሲጠባ፤
አሮጌ ዓመት አልፎ – አዲሱ ሲገባ፤
በአበቦች መዓዛ እረክቷል ልባችሁ፤
ሰዋች ሁሉ በጣም እንኳን ደስ አላችሁ። ”
የአንጋፋውን የጥበብ ሰው ከላይ የተጠቀሰውን የዜማ ግጥም እንደሚመቸኝ በራሴ ቃላት ተክቼ ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር በማጎዳኘት ጥቂት ስንኞችን ላስነብብ፤
“ዘላለም አይጉዳን ገብቶ በሽውታ፣
ተነቅሎ ይጥፋልን የብሔር በሽታ፣
ዘረኝነትና መከፋፈል ሁሉ፣
ይጥፉ ካገራችን ሕዝቡን አያባሉ፤”
ዓመቱ መልካም ትሩፋቶችንም ያስተናገድንበት ስለመሆኑ አለማስታወሱ ምሥጋና ቢስነት ብቻ ሳይሆን በአንባቢውም ሆነ በፈጣሪ ዘንድ ውለታ በል ያሰኛል። የሞት፣ የመፈናቀልና የንብረት ውድመት የገጠማቸው እጅግ በርካታ ወገኖቻችን ወደ ቀዬአቸው የተመለሱበትና እንደገና አዲስ ሕይወት በመጀመር ነገም አዲስ ቀን ነው ብለው የተጽናኑበት ዓመትም ነበር። አሹ!
የፖለቲካ ትርምሱና የወጣቶቻችን ዓላማ ቢስ የአደባባይ ፉከራ በአንፃራዊ መልኩ አደብ የገዛበት፣ የኢኮኖሚ ችግሩ፣ የኑሮው ውድነትም ሆነ የንግድ መቀዛቀዙን ሕዝባችን በትዕግስት አስተናግዶ፤
“ተው ቻለው ሆዴ፣
ተው ቻለው ሆዴ፣
ሲያልፍ ለሚያልፍ ቀን ምነው መናደዴ”
በሚል እንጉርጉሮ ችግሩን እንደ ዘበት እያለፈ መሆኑም የሚያስመሰግን ነው። ብዙዎቹ ሀገራዊ ችግሮቻችን ሤረኞችና መሰሪዎች እንደተመኙት ሳይሆን በሕዝቡ መልካም እሴቶች ተሸፍነው ታልፈዋል። ይህ ሁኔታ የዜጎቻችንን ታላቅነትና ቻይነት በሚገባ ያመላክታልና እሰይ እንላለን።
አረንጓዴ አሻራ የማሳረፉ ርብርብ ዓለምን ያስደነቀውና ተፈጥሮ ይቅር እንድትለን ችግኞችን በመትከል በካሣ የታረቅነውም ሊሰናበተን ዳር ዳር በሚለው በዚሁ በያዝነው ዓመት ነው። ሀገራዊ ልማቱ የመነቃቃት ምልክት የታየበት፣ የምኒልክ ቤተ መንግሥት እድሳቱና ተጨማሪ ግንባታው ተጠናቆ ሊከፈትና ጎብኝዎችን ሊቀበል ሸብ እረቡ የተጧጧፈበት፣ ለአዲስ አበባ ከተማ የታቀዱት ግዙፍ ፕሮጀክቶች የተጀመሩበት፣ የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎቶች የተነቃቁበት፣ የሀገሪቱ የትምህርት ሥርዓት እንደተመኘነውና እንደተጯጯህንበት ምላሽ አግኝቶ በአብዛኛው እየተሻሻለ መሆኑን የሰማንበት፣ በርካታ የሕግ መሻሻሎች መደረጋቸውን ያደመጥንበት፣ የውጭ ግንኙነታችን ወደተሻለ የከፍታ እመርታ ያደገበት፣ የብዙኃን መገናኛዎቻችን በአንፃራዊ መልኩም ቢሆን ልጓማቸው ከአንደበታቸውና ከብዕራቸው ላይ የተነሳበት ዓመት ነበር።
እንዲያው በጥቅሉ ሁለንተናዊ የሀገሪቱ የነውጥ ወጀብ ጥቂት ቀዝቀዝ ብሎ የለውጥ ተስፋው እውን ወደ መሆን የተቃረበበት ዓመት ነበር ብንል ከእውነታ አያርቀንም። እነዚህን መሰል መልካም ተስፋዎች በማስተዋል ጭምር ነበር በቡሄ ጨፋሪ ብላቴኖቻችን አንደበት “እንዲሁ እንዳለን አይለየን!” ሲሉን አሜን! አሜን! በማለት ከአንደበታቸው ምርቃት የተቀበልነው።
መጭውን አዲስ ዓመትስ እንዴት እንቀበል? “ቀድሞውንስ አዲስ ዓመት የሚባል አለን?” የሚለውን የፈላስፋ ነን ባዮችን ጉንጭ አልፋ መከራከሪያ ወደ ጎን ገፋ አድርጌ ምኞቴንና ምርቃቴን በብዕሬ ውክልና ለአንባቢዎቼ ላስተላልፍ።
ኢኮኖሚያችን ከደዌ ተፈውሶ የሕዝባችን ማዕድ በበረከት ይትረፍረፍ! አሜን። ፖለቲከኞቻችን ቀልብ ገዝተው፣ ተደማምጠው፣ ተቀራርበውና ተዋህደው ለራስ ክብር ማግዘፊያ ሳይሆን ለሕዝብ አገልጋይነት የሚጨክኑበት ዓመት ይሁን! አሜን። ሕዝብ ከሕዝብ ጋር የጎሪጥ እንዲተያይና ሰይፍ እንዲማዘዝ ሤራ ለሚያውጠነጥኑና ምላሳቸውን ለሚያስረዝሙ አክቲቪስት ነን ባይ “የጨለማ አድመኞች” ልብና ህሊና ይስጣቸው! አሜን።
ነጋዴው በቅንነት፣ ተማሪው በትጋት፣ የመንግሥት ሠራተኞች በንፅህና፣ የተራድኦ ሠራተኞች ያለ ስስት፣ የፍትሕ ሥርዓቱ በሐቅና በእውነት፣ ልማቱ በውጤት፣ ሠራዊታችን በንቃት፣ ፖለቲካው በስክነት፣ መንግሥት በጥበብ፣ ሃይማኖተኞች በርህራሄ፣ ተመራማሪዎች በውጤት፣ ሚዲያው በእውነት፣ ተፈጥሮ በለመደችው ቸርነት ለጋስ አገልጋይ ይሁኑልን! አሜን።
እምዬ ኢትዮጵያ የዳቦ መሶብ፣ የውሃ ማማ፣ የብልፅግና ምድር ትሁንልን! አሜን። ሕዝባችን በሰላም ውሎ በሰላም ይደር። ፈጣሪ የገዢዎቻችን አለቃ፣ የዜጎቻችን አባት ይሁን። 2012 ዓ.ም ሰብሉ አምሮ፣ ንግዱ ሰምሮ፣ ስምሪቱ ደምቆ፣ ፍቅር በምድራችን ላይ ሰልጥኖ የተለየ የበረከት ምንጭ የሚፈልቅበት ዓመት ይሁን። “እንዲሁ እንዳለን አይለየን። ” ዓመት ዓመት ያድርሰን። አሜን! አሜን! አሜን! ሰላም ይሁን።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሀሴ 22/2011
በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ