በሀገራችን የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች የኢኮኖሚ ምንጫቸው የተለያየ ነው ። የአንዳንድ ግብርና ፣ የሌላው የከብት እርባታ፤ ንግድ ወዘተ ሊሆን ይችላል። የጋሞ ማህበረሰብ ዋነኛ የኢኮኖሚ ምንጭ ግን በሽመና / በዕደ ጥበብ ሥራ ላይ የተመሠረተ ነው::
የማህበረሰቡ ሴቶች፣ ወንዶች፣ ህጻናት ከሽመና ወይም በቋንቋቸው ከዱንጉዛ ጋር ጥብቅ ትስስር አላቸው:: በጋሞ የሽመና ሥራ ከምስት መቶ 50 አመት በፊት እንደተጀመረ በአካባቢው ያሉ አስጎብኚዎች ይናገራሉ::
በጋሞ ዞን ዶርዜ መንደር እግር ጥሎት ከተገኙ ፣ ሴት፣ ወንድ ፣ ሕጻኑ በስፋት ፣ ከፍ ባለ ሙያዊ መሰጠት በሽመና ሥራ ላይ ተሠማርተው ማየት የተለመደ ነው::
በርግጥ ሽመና ለጋሞ ማህበረሰብ ሁሉ ነገሩ ነው:: የማንነቱ ፣ የባህሉም አንዱ መገለጫ ነው:: በሽመና ጥበብ የባህል አልባሳትን አስውቦ በመሥራት እራሱን ያስውባል፤ ለሀገር ውስጥና ለሀገር ውጭ ገበያ በማቅረብም ኢኮኖሚውን ይደግፋል:: የቱሪስት መስህብ በመሆንም ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ይሆነዋል::
የጋሞ አካባቢ አስጎብኚ የሆነው ወጣት ታረቀኝ ቦጋለ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ መና እና እርሻ ዋንኛ የማህበረሰብ የገቢ ምንጭ ፤ አጠቃላይ የኢኮኖሚ መሠረት ናቸው:: አብዛኛው የጋሞ ማህበረሰብ ሽመና /ዱንጉዛ መሥራት ይችላል:: ሁሉም የማህበረሰቡ አባል ሽመና ለክፉ ቀን ይጠቅማል በሚል ቤተሰብ እንዲማር ይደረጋል::
በሽመና ሥራ የጋሞ ማህበረሰብ በተለይም ፣ የዶርዜ አካባቢ ተዋሪዎች ተጠቃሚ እየሆነ ነው የሚለው ወጣቱ ፤ አካባቢው የቱሪስት መስህብ እየሆነ ነው ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ የጎብኚዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱም ሽመና ለማህበረሰቡ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እየሆነ እንደሚገኝ አመልክቷል::
የሀገር ልብሶቹ በአካባቢው በድምቀት በሚከበረው ለዮ/ መስቀል በዓል በስፋት ይለብሳሉ:: በማኅበረሰቡ ባህል መሠረት በቤተሰቡ ልክ የባህል ልብስ ይኖራል::
የመስቀል በአል ዕለት ሁሉም የቤተሱቡ አባላት በልዩ ሁኔታ የተዘጋጀውን የሀገር ባህል ልብስ ለብሰው በአንድ ላይ ይወጣሉ:: ለልብሱ ክብር ሲባል የባህል ልብሱ ዘወትር እንደማይለበስም ይገልጻል::
የጋሞ ልጆች ሽመና ሥራው የገቢ ምንጭ መሆኑን በመገንዘባቸው ባህሉን በሚገባ እያስቀጠሉ ነው:: የባህል አልባሳቱን በዘመናዊ ዲዛይን እያስዋቡ ወደ ገበያ በማስገባት ፤የተሻለ ገቢ ከማስገባት ባለፈ ፤ የልብሶቹን የገበያ ተወዳዳሪነት እያሳደጉ መሆንን ወጣት ታረቀኝ ይናገራል::
የጋሞ ዞን መንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ሰላማዊት ቦዳ በበኩላቸው ፤ እንዳስታወቁት ፤ የሽመና ሥራ ለጋሞ ሕዝብ የማንነት መገለጫው፣ ለኢኮኖሚው የደም ስሩ ነው:: ማህበረሰብ ለሀገር ሰንደቅ ዓላማ የሚሰጠውን ክብር ያህል ለሽመና ሥራው ልዩ ክብር ይሰጣል::
ሴቶች ጥጥ በመፍተል ኮፍያ፣ ቀሚስ፣ ፎጣ፣ ጋቢና የተለያዩ አልባሳት ይሰራሉ:: የሚመረቱ ምርቶችን በማህበርና በግል በመሆን ለውጭ ሀገር ገበያ ይቀርባል::
የሚገኘውን ትርፍ የማህበሩ አባላት ይካፈላሉ:: ቁጠባም ይቆጥባሉ፤ በዚህም የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እንደሚያጎለብተው አመልክተዋል::
ይህም ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ያረጋግጣል::ሴቶች ከኢኮኖሚ ከጥገኝነት ተላቀው የራሳቸው ገቢ እንዲኖራቸው ያደርጋል ፤ በአሁኑ ወቅት ተፈላጊነታቸው እየጨመረ በመምጣቱም ጥሩ የገቢ ምንጭ እየሆኑ ነው ብለዋል::
የሽመና ሥራ ባህልን ወደ ወጣቱ ለማስተላለፍ የተለያዩ ሥልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን ያመለከቱት የመምሪያ ኃላፊዋ፤ የዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ከሚመለከታቸው ጋር በመተባበር በዩኒስኮ ለማስመስዘገብ እንቅስቃሴ መኖሩን አስታውቀዋል::
እንቅስቃሴው በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል ፤ ይህም ባህሉን ጠብቆ ለትውልዶች ለማስተላለፍ ይረዳል ብለዋል:: ወጣቱ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ይህን ባህሉን የእኔ ነው በሚል ስሜት ማስቀጠል መቻል እንዳለበትም አሳስበዋል::
የዕደ ጥበብ ሥራው በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ባሉ ጎብኚዎች ይጎበኛል ያሉት ወይዘሮ ሰላማዊት፤ የቱሪስት መስህብነቱ እየጨመረ ነው:: አሁን ካለው በተሻለ መንገድ የገቢ ምንጭ እንዲሆን የክልሉ በህልና ቱሪዝም ቢሮ እቅዶ እየሠራ እንደሚገኝ አመልክተዋል ::
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም