የፌደራል የሥነምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ከሀብት ምዝገባ ጋር በተያያዘ ባለሥልጣናት ፈቃደኛ አልሆኑልኝም ስለማለቱ ሰሞኑን ተሰምቷል። በዚህ ምክንያት የሀብት ምዝገባ አፈፃፀም ባሳለፍነው በጀት ዓመት ደካማ መሆኑ ተነግሯል። ይህ ማለት ኮሚሽኑ በአዋጅ የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት አስፈፃሚ አካሉ እንቅፋት ሆኖበታል ማለት ነው። ይህ ማለት ኮሚሽኑ ሙስናን ለመዋጋት የተጣለበት ከባድ ኃላፊነት አደጋ ውስጥ ወድቋል ማለት ነው። ይህ ማለት ለሕግና ሥርዓት ተገዥ የማይሆኑ እምቢ ባይ ሹሞች ወይንም ባለሥልጣናት ተፈጥረዋል ማለት ነው።
ዘገባው እንዲህ ይነበባል፡-
“..የፌደራል ሥነምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በ2011 በጀት ዓመት አፈፃፀምና በ2012 ዕቅድ ላይ ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ ላይም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ሀብት ማስመዝገብ ላይ ያለው አፈጻጸም ደካማ መሆኑ በመድረኩ ተነስቶ ተገምግሟል።
ኮሚሽኑ ይህ ሊሆን የቻለውም ከሀብት ምዝገባ ጋር በተያያዘ የባለስልጣናት ፈቃደኛ ካለመሆን ጋር በተያያዘ መሆኑን የገለፀ ሲሆን፤ በዚህም የሀብት ምዝገባ ሥራው ፈታኝ እንደሆነበት አስገንዝቧል።…”
ኮሚሽኑ በያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር የሀብት ምዝገባውን ይፋ ለማድረግ እየተሠራ ስለመሆኑ የሰጡት ተያያዥ መረጃ በመገናኛ ብዙሃን ተዘግቦ ነበር።
እንዲህ ይላል። “…የሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አየልኝ ሙሉዓለም እንዳስታወቁት፤ በአገሪቱ በሚገኙ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ብሎም በምርጫ ሥርዓት ሊወዳደሩ የሚችሉ አካላት ሀብት መጠን ለማሳወቅ እየሠራ ነው።
ይህንንም በጣም ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግለት በኦን ላይን የመረጃ ቋት ይጫናል። በአሁኑ ወቅትም ከአንድ የህንድ ካምፓኒ ጋር የሙከራ ሥራው መጀመሩንና በወራት ውስጥ የሚጠናቀቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ አስፈላጊ በሆነ መንገድም ለህዝብ ይፋ ይደረጋል ብለዋል። የ150ሺ ግለሰቦች መረጃ በኮሚሽኑ መረጃ ቋት ላይ እንደሚቀመጥ ጠቁመው፤ በዚህም ዓመት (2011 ዓ.ም) ወደ ዳታው እንዲገባ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። …”
ሆኖም ይህ ሥራ እስካሁን ተከናውኖ መረጃው ስለመለቀቁ ወይንም አለመለቀቁ ኮሚሽነሩ የተናገሩት ጉዳይ ስለመኖሩ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባ አያሳይም።
በሰሞኑ መድረክ ላይ እንደተገለፀው ሙስናን ለመከላከል ከተቀመጡ ስልቶች መካከል አንዱ ተመራጮች፣ ተሻሚዎች እና የመንግሥት ሠራተኞች ሀብትና ጥቅማቸውን እንዲያሳውቁ እና እንዲያስመዘግቡ ማድረግ ነው። ይህ እንቅፋት ሲገጥመው የሙስና መከላከል አቅም መዳከምን ያስከትላል። ሙስና እንዲስፋፋ በር ይከፍታል። ሙስና ቁንጮ በሆነበት ማህበረሰብ ደግሞ የመንግሥት የአገልጋይነት ሚና ያሽቆለቁላል። ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ማካሄድ ቀርቶ ማሰብ ቅንጦት ይሆናል። ተጠያቂነት ይዳፈናል፤ ፍትሐዊነት የወረቀት ላይ ጌጥ ሆኖ ይቀራል። መንግሥት በሕዝብ ዘንድ ቅቡልነት ስለሚያጣ ሠላምና መረጋጋት ይጠፋል፣ ግጭቶች መበርከታቸው አይቀሬ ይሆናል።
የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 668/2002 ወጥቶ በሥራ ላይ ከዋለ ስምንት ዓመት ገደማ ተቆጥሯል። የአዋጁ መውጣትና መተግበር የመንግሥትን አሠራርን በግልጽነትና በተጠያቂነት ላይ የተመሠረተ ለማድረግ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሎ ይገመታል። ሀብት ማስመዝገብ ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመከላከልና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።
በአሁኑ ሰዓት የተሰማው ደግሞ የአንዳንድ የአስፈፃሚ አካላት (ባለሥልጣናት) ለምዝገባው ተባባሪ አለመሆን ሕግ መጣስ ብቻ ሳይሆን የሀብት ምዝገባና ማሳወቅ ፋይዳው ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንዲገባ የሚያደርግ አደገኛ ስህተት እየፈፀሙ እንደሚገኝ የኮሚሽኑ ሪፖርት ይጠቁማል። ስህተቱ ሆን ተብሎ የሚፈፀም መሆኑ ደግሞ አደገኛ ያደርገዋል።
ኮሚሽነር አየልኝ ሙሉዓለም በያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር ኮሚሽኑ በአዋጁ መሠረት ከምዝገባ ያለፈ ሥራ ማከናወን እንዳልቻለ ለመገናኛ ብዙሃን ጠቁመው ነበር። “…በኢትዮጵያ ከስምንት ዓመታት በፊት ሀብትን ለማስመዝገብና ለማሳወቅ የወጣው አዋጅ እስከ አሁን ድረስ ተግባር ላይ የዋለው ምዝገባ በማካሄድ ብቻ ነው። ኮሚሽኑ አዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት የ150 ሺህ ባለሥልጣናት እና የመንግሥት ሠራተኞችን የሀብት ምዝገባ አከናውኗል።”
የሀብት ምዝገባው ቢካሄድም በአዋጁ መሰረት ሀብትን የማጣራትና ለህዝብ ይፋ የማድረጉ ሥራ እስከ አሁን ድረስ ማከናወን አልተቻለም ብለዋል።
ሀብት ምንድነው?
ሀብት የምንለው በእንግሊዝኛው (asset) የሚባለውን ትርጉም የያዘ ነው። በኢትዮጵያ የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ አዋጅ መሠረት ሀብት ስንል በይዞታነት የሚገኝ ማንኛውም የማይንቀሳቀስና የሚንቀሳቀስ ግዙፍነት ያለው ወይም ግዙፍነት የሌለውን እንዲሁም የመሬት ይዞታንና ዕዳን ይጨምራል።
በተለመደው አጠራር ሀብት/ንብረት የሚገለፀው በገንዘብ፣ በቤት፣ በመኪና እና በመሳሰሉት ሲሆን የሕግ ባለሙያዎች ንብረት የሚለውን አገላለፅ ለሁለት ከፍለው ይመለከቱታል። ይኸውም የሚንቀሳቀስ እና የማይንቀሳቀስ /ቋሚ/ በማለት ነው።
የሚንቀሳቀሱ /ተንቀሳቃሽ/ ንብረቶች በተፈጥሯቸው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ፀባያቸውን ሳይለቁ መንቀሳቀስ የሚችሉ ናቸው። የሚንቀሳቀሱ ንብረቶች እንደገና ግዙፍነት ያላቸውና የሌላቸው በመባል በሁለት ተከፍለው ይታያሉ። ግዙፍነት ያላቸው የሚባሉት የሚታዩ፣ የሚዳሰሱ እና የሚጨበጡ ንብረቶች ሲሆኑ ግዙፍነት የሌላቸው የሚባሉት በተቃራኒው ለመታየትና ለመዳሰስ የማይችሉ ለምሳሌ የአዕምሮ ንብረቶችና የመሳሰሉትን ያጠቃለለ ነው።
የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች በባህሪያቸው መንቀሳቀስ የማይችሉና ቢንቀሳቀሱም እንኳን የመጀመሪያ ፀባያቸውን በማጣት /በመፍረስ ወይም በመበላሸት/ ሊንቀሳቀሱ የሚችሉ ናቸው። መሬትና ቤቶችን በምሳሌነት ማቅረብ ይቻላል።
ሀብትን ማስመዝገብና ማሳወቅ ለምን ያስፈልጋል?
የመጀመሪያውና ዋንኛው ሙስናን አስቀድሞ የመከላከል (Preventive functions) ሲሆን፤ የሙስና ወንጀልን ምርመራ ማቀላጠፍ (investigative function) እንዲሁም የሕዝብ አመኔታን መፍጠርና ማጠናከር ናቸው።
በእነዚህ ዙሪያ ሊታዩ የሚችሉ በርካታና ዝርዝር ጥቅሞችም ሊጠቀሱ ይችላሉ። ለምሳሌ፡- የህዝብ ተመራጮች፣ በመንግሥት የተመደቡ ኃላፊዎች፣ ተሿሚዎችና ሠራተኞች ሀብት አስቀድሞ በመመዝገቡ ምክንያት ግለሰቦቹ በሚገጥማቸው የጥቅም ግጭት ወቅት ትክክለኛ ውሳኔ እንዲኖራቸው ያግዛል። ለምሳሌ ስጦታና ተመሳሳይነት ያላቸው የገንዘብ ጥቅሞች መቀበልን አስመልክቶ ዜጎች ትኩረት ለሰጡአቸው ህዝባዊና መንግሥታዊ ኃላፊዎችና ሠራተኞችን ሀብትና ንብረት በግልፅ በማወቃቸው በህዝባዊና መንግሥታዊ አስተዳደሩ ላይ እምነት ያዳብራሉ።
ዜጎች ትኩረት በሚሰጧቸው ህዝባዊና መንግሥታዊ ኃላፊዎችና ሠራተኞች የሀብትና የንብረት ይዞታ ላይ ሊነሳ የሚችለውን ከመረጃ የራቀ ሀሜትን ይቀንሳል።
ሙስናን ለመከላከልና ለመዋጋት በሚደረገው ርብርብ የማስረጃ ማሰባሰቡን ሂደት ቀላል ለማድረግ ያግዛል።
ከራሱ ከኮሚሽኑ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያስረዱት የሀብት ማስመዝገብ ሥራ፣ ለሕዝብ ከማሳወቅ ጋር ተቆራኝቶ ካልተተገበረ ለመልካም አስተዳደር እውን መሆን የሚኖረው ፋይዳ ዝቅተኛ ነው። ሀብት ተመዝግቦ መረጃው ለሕዝብ ክፍት የሚሆንበት ሁኔታ ከሌለ የሚጠበቀው ግልፅነት በሚፈልገው ደረጃ ካለመፈጠሩም በላይ ተጠያቂነት የሚተገበርበትን መንገድ ያጠበዋል። በዚህም ምክንያት ሕዝብ በመረጣቸው ተመራጮች፤ መንግሥት ኃላፊዎችና ሠራተኞች ላይ የሚኖረውን ቅሬታና ጥርጣሬ እንዲያድግ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። እርግጥ ነው፤ ምዝገባ ብቻውን ሙስናና ብልሹ አሠራሮች እንዲቀረፉ አያግዝም።
ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ በሀብት ማሳወቅና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 668/2002 መሠረት የምዝገባ መረጃው ለሕዝብ በቀላሉ ተደራሽ ሊሆን በሚችል መልክ የተዘጋጀ አለመሆኑ የኮሚሽኑ ቁርጠኝነት ላይ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን እያስነሳበት ይገኛል። መረጃው በይፋ ባለመገለፁ ምክንያትም ባለሥልጣናትና ተሿሚዎች በገቢያቸው ልክ እየኖሩ ስለመሆኑ፣ ትክክለኛ ሀብታቸውን ስለማስመዝገባቸው ሕዝብ እንዳያውቅና አውቆም ተጨማሪ መረጃ እንዳይሰጥ አግዷል።
በአሁኑ ወቅት በተለይ በማህበራዊ ድረገፆች እገሌ ከገቢው በላይ ሀብት አፍርቷል፣ በሙስና ተዘፍቋል እየተባሉ የሚነገሩ ነገሮች አሉ። እነዚህ በአሉባልታ መልክ የሚነገሩ፣ ነገር ግን ሲደጋገሙ በመንግሥትና በህዘብ መካከል ያለውን አመኔታ ሊጎዱ የሚችሉ መረጃዎች ማጥራት የሚቻለው የሀብት ምዝገባ መረጃውን በወቅቱ ይፋ ማድረግ ቢቻል ነበር። ይህ አለመሆኑ ከገቢያቸው በላይ ሀብት የሚያፈሩና ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ይዘው የሚገኙ ግለሰቦች እንዲሁም ሹማምንት እንዲበራከቱ የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል ተብሎ ይገመታል።
ኮሚሽኑ እስካሁን ምን ያህል መዘገበ?
የፌዴራል ሥነምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን ባለፉት ዓመታት በጥቅሉ ከ150 ሺ በላይ፣ ባሳለፍነው የበጀት ዓመት ደግሞ የ21ሺ 363 ሹመኞች፣ ተመራጮችና የመንግሥት ሠራተኞችን ሀብት መዝግቧል፤ ለ256 መረጃ ፈላጊዎች የሀብት ምዝገባ መረጃ ሰጥቷል፤ የ485 ከፍተኛ አመራሮችን የሀብት ምዝገባ እድሳት አድርጓል።
እንደማጠቃለያ
የሀብት ምዝገባና ማሳወቅ ጉዳይ ከሙስና መከላከል ጋር በቅርብ የተቆራኘ ነው። ያው እንደሚታወቀው በተሾሙ ማግስት ከገቢያቸው በላይ መኖር የሚጀምሩ ባለሥልጣናት ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። አንድ ባለሥልጣን ከገቢው በላይ ስለመኖሩ በቂ ምልክቶች እንዳሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። የዚያን ሰው የቀን ገቢ እና የኑሮ ሁኔታ ማስላት ብቻ ሙስና ውስጥ ስለመግባቱና አለመግባቱ በቂ ጠቋሚ ፍንጮችን ያስገኛል። ሹሙ /ባለሥልጣኑ የሚጠቀማቸው አልባሳት፣ የሚኖርበት ቤት፣ ልጆቹን የሚያስተምርበት ት/ቤት፣ የሚበላው፣ የሚጠጣው፣ለሚስቱ፣ ለልጆቹ እና ለቤተሰቡ የሚያወጣቸውን ወጪዎች በቅርብ በመከታተል የዚያን ሰው ማንነት ለመገመት ያስችላል። ከገቢያቸው በላይ ሀብት የሚያፈሩ ባለሥልጣናት፣ ተሿሚዎች፣ ተመራጮች ከየት አመጣችሁት ብሎ ለመጠየቅ እነዚህን ፍንጮች እንደመነሻ መጠቀም እንደሚቻል ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ለዚህ አባባል እንደትንሽ ማሳያ መጠቆም የሚቻለው የራሳቸው የመኖሪያ ቪላ (ከየት አምጥተው እንደሠሩት የማይታወቅ) በውጭ ምንዛሪ ጭምር እያከራዩ በመንግሥት ቤት የሚኖሩ ባለሥልጣናት መኖራቸውን ነው። አንዳንዶች ከባለሀብቶች ጀርባ ሆነው ትልልቅ ንግዶችን የሚያንቀሳቅሱ፣ አንዳንዶችም በጠራራ ፀሐይ ግዙፍ ሕንጻዎችን ጭምር አስገንብተው ኪራይ የሚሰበስቡ፣ አንዳንዶች የመንግሥት ፕሮጀክቶችን ሕግና ሥርዓት ከሚፈቅደው ውጭ ምዝበራና ብልሹ አሠራር እንዲሰፍን የሚተባበሩ፣ አንዳንዶች የመንግሥትን ሥራ ለግል ጥቅማቸው በሚመቻቸው መንገድ የሚመሩ… ዓይን አውጣ ሹመኞችን/ባለሥልጣናትን ፈልጎ ማግኘት ከባድ አለመሆኑ ሲታሰብ የሀብት ምዝገባና ማሳወቅ አዋጁ ፋይዳ ጥያቄ ያስነሳል።
በአጠቃላይ «ሙስናና ብልሹ አሠራር፣ ኪራይ ሰብሳቢነት፣የመልካም አስተዳደር ችግር (አፈፃፀም ችግር)…» የተሰኙ ቃላቶች በተለይ ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ ሰምተናቸዋል፣እየሰማናቸውም ነው። ሥጋቶቹና ችግሮቹ ግን የሚነገረውን ሲሶ ያህል የመቅረፍ ዕድል ያገኙ አይመስሉም። ባለፉት አራት ዓመታት በአንዳንድ ክልሎች የተነሱ ሕዝባዊ ተቃውሞዎችን ተከትሎ «የመንግሥት ሥልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል..» የሚሉ ንግግሮች ከከፍተኛ አመራሩ ሲነሳም እንደነበር የምናስታውሰው ነው።
ያም ሆነ ይህ ሙስናና ብልሹ አሠራር የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ በተለይ በለውጡ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የተረሳ መስሏል። አክራሪ ብሔርተኝነት ዝንባሌዎች፣ ግጭቶች በአጠቃላይ ሠላምና መረጋጋት ጎልቶ መታየቱ ሙስና ምቹ የመሸሸጊያ ጫካ እንዲያገኝ መልካም ዕድል ፈጥሮለታል።
በተለይ ሙስናን ለመከላከል ቁልፍ መንገድ የሆነው የባለሥልጣናት ሀብት ምዝገባና ማሳወቅ ጉዳይ በአንዳንድ ባለሥልጣናት ትብብር እየተነፈገው ነው መባሉ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ሀብትን አለማስመዝገብ ወይንም ለማስመዝገብ በቀጥታና በተዘዋዋሪ እንቅፋት መሆን የሙስና ትግሉን ማደናቀፍም መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። የጠ/ሚ አብይ አስተዳደር በእንዲህ ዓይነት ባለሥልጣናትና ሹመኞች ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ካልቻለ የፀረ ሙስና ትግሉ ከዚህም የከፋ ፈተና ሊገጥመው ይችላል። (የፀሐፊው ማስታወሻ፡- ለዚህ ጽሑፍ ጥንቅር፡- የፌደራል የሥነምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ የሰንደቅ ጋዜጣ፣ የአዲስ ዘመን፣ የፋና፣ የኢዜአ…ዜናና መረጃዎችን መጠቀሜን ከምስጋና ጋር እገልፃለሁ። )
አዲስ ዘመን ነሀሴ 22/2011
(ፍሬው አበበ)