“ግጭት አቁመን ወደሰላም ምዕራፍ እየተራመድን ነው” – ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ዶ/ር

ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ዶ/ር-የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የብሔራዊ ተሀድሶ የቦርድ ሰብሳቢ

የጦርነትን አስከፊነት እንደ ኢትዮጵያውያን ያየና የቀመሰ ሌላ ሕዝብ እና ሀገር ብዙም አለ ብዬ ለመናገር አልደፍርም ፤ አሁን ላይ ግጭት አቁመን ወደ ሰላም ፊታችንን በማዞር ሂደት አንድ ምእራፍ ወደ ፊት እየተራመድን ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የብሔራዊ ተሀድሶ የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ አስታወቁ ።

ሚኒስትሩ በትግራይ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች የተሀድሶና መልሶ ማቋቋም ሥልጠና ይፋዊ የማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ፣ ግጭት አቁመን ወደ ሰላም አንድ ምእራፍ ወደ ፊት እየተራመድን ነው። ይህም ኢትዮጵያ ሰላምን በማጽናት በመተማመን ላይ የተመሠረተ አጋርነትን ለማጠናከር ትልቅ ርምጃ እየወሰደች ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በታሪኳ በርካታ የውስጥ ችግሮች እንዳጋጠሟት ያመለከቱት ዶ/ር ጌዲዮን ፣ በተለይም ከግጭት ጋር በተያያዘ ባጋጠሙ ችግሮች ሀገሪቱ በበርካታ ፈተና ውስጥ እንድታልፍ መገደዷን ገልጸዋል። በዚህም ለበርካታ ሠብዓዊ ጉዳት መዳረጓን ጠቁመዋል።

ግጭት ኪሳራው የበዛ ፤ ጠባሳው በቀላሉ የማይጠፋ መሆኑንም አመልክተዋል ፤ በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ አስከፊውን የግጭት አዙሪት በማቆም ለሰላማዊ አማራጭ ፊቷን በማዞር በመተማመን ላይ የተመሠረተ አጋርነትን ለማጠናከር ትልቅ ርምጃ እየወሰደች መሆኑን አስታውቀዋል።

በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በማቆም ችግሩን በሰላማዊ አማራጭ እልባት እንዲያገኝ እገዛ ያበረከቱ አካላትን አመስግነዋል። በቀጣይም የሂደቱን ውጤታማነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ሁሉም አካል የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው ፤ የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽንና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እየሠሩት የሚገኘው የመልሶ ማቋቋም ሥራ ከጦር መሣሪያ ማስፈታት ባለፈ የትግራይ ክልልን ሰላምና ደህንነት ግምት ውስጥ ባስገባ መንገድ የሚከናወን ነው ብለዋል።

የቀድሞ የትግራይ ክልል ታጣቂዎችን በተሀድሶ ሥልጠና መልሶ ለማቋቋም እየተሠራ የሚገኘው ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው ፤ በቅንጅት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አዎንታዊ ውጤቶች እያመጡ መሆኑን ገልጸዋል። የጊዜያዊ አስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎችም ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመተባበር የክልሉን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በቅርበት እየሠሩ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ 75 ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎችን በተሀድሶ ሥልጠና መልሶ ለማቋቋም እየተደረገ የሚገኘው ጥረት ትልቅ እመርታዊ ውጤት መሆኑን ገልጸው ፤ የሰላምን ትሩፋቶች ማጣጣም በሁሉም ደረጃ ማየት የምንችልበት ሁኔታ እስኪፈጠር ድረስ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

በአሁኑ ሰአት የሚሰጠው ድጋፍ መጨረሻው እንደማይሆን ሙሉ እምት አለኝ ያሉት አቶ ጌታቸው ፤ የሚሰጠው ሥልጠናም ወደ ፊት ወደ ሥራ ሲገባ የተሻለ አቅም መፍጠር የሚያስችል እንደሚሆን አመልክተዋል

በመቐለ ከተማ መቐለ ዩኒቨርሲቲ መለስ ዜናዊ ካምፓስ ቅጥር ጊቢ በተካሄደው ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሌተናል ጄነራል ፃድቃን ገብረ-ትንሳኤና የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁንን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራልና የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You