– 37 ነጥብ ስድስት ሺህ ቶን ዓሣ ተመርቷል
አዲስ አበባ፡- በ2017 በጀት ዓመት አራት ወራት በሌማት ቱርፋት መርሐግብር ሶስት ቢሊዮን 503 ሊትር ወተት መገኘቱም ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። 37 ነጥብ ስድስት ሺህ ቶን የዓሣ ምርት እና 42 ነጥብ 19 ሺህ ቶን የማር ምርት መገኘቱንም አመለከተ፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ዘርፍ የሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ዶ/ር ዮሀንስ ግርማ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የወተት፣ የዶሮ፣ የእንቁላል፣ የማር እና ዓሣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሌማት ትሩፋት መርሐግብር ተቀርጾ እየተተገበረ ይገኛል፡፡
በመርሀ ግብሩ በ በ2017 በጀት ዓመት 12 ቢሊዮን 116 ሊትር ወተት ለማምረት ታቅዶ፤ በአራት ወሩ ሶስት ቢሊዮን 503 ሊትር ወተት መገኘቱን ጠቁመው ፤ የወተት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የወተት ላም ዝርያ ማሻሻል እና የመኖ አቅርቦት ላይ በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የመርሐግብሩ ዋና ዓላማ የእንስሳት ምርትና ምርታማናትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ
መሆኑን ያመለከቱት ዶ/ር ዮሀንስ ፤ በአራት ወሩ 37 ነጥብ ስድስት ሺህ ቶን የዓሳ ምርት እና 42 ነጥብ 19 ሺህ ቶን የማር ምርት መገኘቱን አመላክተዋል፡፡
በተጨማሪም የዶሮ ሥጋና የእንቁላል ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሌማት ትሩፋት መርሐግብር የትኩረት አቅጣጫ ነው ያሉት አማካሪው፤ በአራት ወሩ ሁለት ቢሊዮን 853 እንቁላል እና 56 ሺህ ቶን የዶሮ ስጋ
መመረቱን ተናግረዋል፡፡
መርሐግብሩ አርሶ አደሩን፣ አርብቶ አደሩን እና ሸማቹን የሚያገናኝ ድልድይ በመሆኑ፤ ሀብት ማሰባሰብ፣ ተከታታይነት ያለው የማህበረሰብ ንቅናቄ ማካሄድ፣ የባለሙያ ሥልጠና መስጠት፣ የግብዓት አቅርቦትና ስርጭትን ማጠናከር፣ ጠንካራ የክትትልና ድጋፍ አሠራር ከፌዴራል እስከ ክልል መዘርጋት የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
በየክልሉ የመኖ ማቀነባበርያ ፋብሪካ ለመገንባት የተያዘውን እቅድ ተፈጻሚ ለማድረግ እንዲሁም የምርት ግብይትን እና የዕሴት መጨመር አሠራርን ለመዘርጋት በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ በዘርፉ የግል ባለሀብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እና የብድር
አቅርቦት ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የሌማት ትሩፋት የሥነምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር የወጪ ንግድ ገቢን ለማሳደግ፣ ከውጭ የሚገባ ምርትን በሀገር ውስጥ ለመተካት እና የሥራ ዕድልን በመፍጠር የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለውም አስታውቀዋል።
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም