አገሪቱ ኢኮኖሚዋን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር እያከናወነች ባለችው ተግባር በተለይ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ሰፊ ትኩረት ሰጥታለች። በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ የተገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮችም ለዚህ አንድ ማሳያ ተደርገው ይወሰዳሉ። አሁን ደግሞ የኢንዱስትሪ ፓርኮቹን ቁጥር ለማሳደግ ጥልቅ ዕቅድ መነደፉን እየሰማን ነው።
መንግሥት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ይበልጥ እንዲጎለብት በዘርፉ የሚሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ቦታ በማግኘት፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ በመፈለግ ወዘተ ዙሪያ ይገጥማቸው የነበረውን ችግር ለመፍታት ሰፋፊ ተግባሮችን አከናውኗል። እነዚህ ተግባሮችም በእርግጥም ዘርፉ በተለይ በውጭ ባለሀብቶች በከፍተኛ ደረጃ ተፋላጊ እንዲሆን አስችለዋል።
ይህ የአገሪቱ ዝግጁነትም አገሪቱን ከአፍሪካ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መዳረሻነት ከሚጠቀሱ አገሮች መካከል እንድትገኝ ከአስቻሏት መካክል ይጠቀሳል። በርካታ የውጭ ባለሀብቶችም በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ እየገቡ ማምረት ጀምረዋል።
ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተውም በአሁኑ ወቅት ሰባት የግል እና አስራ አንድ የመንግሥት ኢንዱስትሪ ፓርኮች በአገሪቱ ይገኛሉ። የሁሉም ፓርኮች የማምረቻ ሼዶች ሙሉ በሙሉ በባለሀብቶች ተይዘው ወደ ማምረት ከመሸጋገራቸውም በተጨማሪ ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ እያስገኙም ናቸው።
የኢንዱስትሪው ዘርፍ አገሪቱ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ በምታደርገው ሽግግር ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣የውጭ ምንዛሬን ለማስገኘት፣የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር ለማድረግ እንደሚያስችሉ ታምኖባቸዋል።የውጭ ባለሀብቶች ሲመጡ ካፒታል ጭምር ይዘው የሚመጡ እንደመሆናቸው ኢንዱስትሪው የሚያስፈልገውን ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ ችግር በመፍታት በኩል አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።
ፓርኮቹ የተቋቋሙባቸውን አካባቢዎች የንግድ እንቅስቃሴ በማነቃቃት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ከተቋቁሙባቸው አላማዎች አንዱ በሆነው የሥራ ዕድል ፈጠራ አስተዋጽኦ ማበርከት ውስጥ ገብተዋል። በአሁኑ ወቅትም ከ70 ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ይጠቁማል።የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው መካከልም ወደ 80 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸው ደግሞ ጅምሩ መልካም እንደሆነ ያሳያል።
ፓርኮቹ ከ70 ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎቻችን የሥራ ዕድል መፍጠር መቻላቸው የጥንካሬያቸው መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል። ይህ አሀዝ ብዙ ወይም ኢምንት ነው ብሎ ለመናገር ግን በየፓርኮቹ ምን ያህል የሥራ ዕድል መቼ ለመፍጠር ታቅዶ ነበር የሚለውን መመልከት ያስፈልጋል።
እንደሚታወቀው የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ ለ60 ሺ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር ይጠበቃል። ሌሎች ፓርኮችም እንዲሁ የተቀመጠላቸው አሀዝ አለ።
በዚህ መሠረት ሁሉም ፓርኮች የሚጠበቀውን የሥራ ዕድል በማስገኘት በኩል እያከናወኑ ያሉት ተግባር መፈተሸ ይኖርበታል። ይህ መደረግ ያለበት ደግሞ መፍጠር ያለባቸው የሥራ ዕድል ወሬ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር በሚል ብቻ አይደለም። በቀጣይ በሚሊዮኖች የሚቀጠር የሥራ ዕድል ለመፍጠር የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት እያንዳንዱ ተቋም የሚጠበቅበትን ያህል እየተጓዘ ስለመሆኑ ለማረጋገጥም ስለሚጠቅም ነው።
የየትኛውም ኢንቨስትመንት ሥራ ስኬት መለኪያ የሚያስገኘው የሥራ ዕድል መሆን እንደሚኖርበት መንግሥት አቅጣጫ አስቀምጧል። ከዚህ አንፃር ሲታይም የፓርኮቹ የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅምና የፈጠሩት የሥራ ዕድል ሁሌም መገምገም ይኖርበታል።
መንግሥት በቀጣይ የኢንዱስትሪ ፓርኮቹን ቁጥር ወደ 30 ለማሳደግ ለሚያከናው ተግባርም በሥራ ላይ ያሉት ፓርኮች አፈፃፀም መገምገሙ ፋይዳው ከፍተኛ ነው። በቀጣይ የሚገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ ሲገቡ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ለተያዘው ዕቅድ ስኬትም በሥራ ላይ ያሉት ፓርኮች ተሞክሮ መታወቁ ይጠቅማል።
እንደሚታወቀው አገሪቱ በዚህ የበጀት ዓመት ብቻ ለ3 ሚሊየን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅዳለች። የሥራ ዕድል ፈላጊው በየዓመቱ በሁለት ሚሊየን እንደሚያድግም ይጠበቃል።
የሥራ ዕድል በማስገኘት በኩል እንደ ግብርናው ዘርፍ ያሉ ሌሎች በርካታ ዘርፎች ቢኖሩም በርካታ ዜጎችን በመቅጠር ለዕቅዱ ስኬት አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቀው የኢንዱስትሪው ዘርፍ ነው። በተለይም ደግሞ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው።
ይህን ለማሳካትም አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን ከመገንባት በተጓዳኝ ወደ ሥራ የገቡት ኢንዱስትሪዎች በሥራ ዕድል ፈጠራ እንደሚያስገኙ የሚጠበቀውና ያስገኙትን በሚገባ በመገምገም የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህም በቀጣይ የሚገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሥራ ዕድል በመፍጠር በኩል አተኩረው ሊሰሩባቸው የሚገባቸውን አቅጣጫ ለማሳየትም ይጠቅማል።
ኮሚሽነር አበበ፡- እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የወጣት አገር ናት። በዓለም ባንክ ጥናት መሰረት በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በሥራ ሊሰማሩ የሚችሉ ዜጎች ከሀገሪቱ ጠቅላላ ህዝብ ቁጥር ወደ 60 በመቶ ገደማ የሚሆን ሲሆን፣ በየዓመቱ በሁለት ሚሊዮን እያደገ ይገኛል።
በመሆኑም በፍጥነት እየጨመረ የሚገኘውን የሠራተኛ ቁጥር ከኢንዱስትሪያላዜሽን፣ ኢንቨስትመንት ፍሰት እና ኢኮኖሚ ልማት ጋር በማጣመር ለሥራ ፈላጊዎች በቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድል መፍጠር ከመቼውም በላይ የመንግሥት መሰረታዊ የፖሊሲ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቷ የብሔራዊ ህልውና መለኪያ እንዲሆን ያደርገዋል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 21/2011