አዲስ አበባ፡- ‹‹በእቅድ ላይ ያሉት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሲገነቡ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሎ ይገመታል›› ሲሉ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አበበ አበባየሁ ገለጹ፡፡
ኮሚሽነር አበበ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ መንግሥት ከዚህ በኋላ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንደ እስከ አሁኑ በራሱ ወጪ አያለማም፤ ለኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ምቹ የሆነ የለማ መሬትን ለግል አልሚዎች ያዘጋጃል፤ ለእዚህም አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ በቀጣይም እንደሚካሄድ ኮሚሽነሩ ጠቅሰው፣ግንባታዎቹንም ለማካሄድ መንግሥት የአዋጪነት እና የስነ ምህዳር ጥናት አካሂዶ ከለያቸው ስፍራዎች መካከል አሶሳ፣ ሰመራ እና አይሻ እንደሚገኙበት አስታውቀዋል:: እነዚህ በእቅድ ላይ ያሉት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሙሉ በሙሉ ተገንበተውና ለምተው ወደ ማምረት ሲሸጋገሩ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሎ እንደሚገምትም ጠቁመዋል፡፡
ኮሚሽነሩ የዓለም ባንክን ጥናት መሰረት በማድረግ እንደገለጹት፤በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በሥራ ሊሰማሩ የሚችሉ ዜጎች ከሀገሪቱ ጠቅላላ ህዝብ ቁጥር ወደ 60 በመቶ ገደማ ይሆናሉ፡፡ ይህ አሃዝም በየዓመቱ በሁለት ሚሊዮን እያደገ ይገኛል፡፡
በመሆኑም በፍጥነት እየጨመረ የሚገኘውን የሠራተኛ ቁጥር ከኢንዱስትሪያላዜሽን፣ ኢንቨስትመንት ፍሰት እና ኢኮኖሚ ልማት ጋር በማጣመር ለሥራ ፈላጊዎች በቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድል መፍጠር ከመቸውም ጊዜ በላይ የመንግሥት መሰረታዊ የፖሊሲ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቷ የብሔራዊ ህልውና መለኪያ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
ኮሚሽነር አበበ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት ሰባት የግል ኢንዱስትሪ ፓርክ አልሚዎች እና አስራ አንድ የመንግሥት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ተጠናቀው እና የማመረቻ ሼዶች ሙሉ በሙሉ በባለሀብቶች ተይዘው ወደ ምርት በመግባታቸው ምክንያት ለሀገሪቷ ከፍተኛ የሆነ ጥቅሞችን እያስገኙ ነው።
ፓርኮቹ ከ70 ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ጥራት ያለው፣ ዘላቂ እና አመርቂ የሥራ ዕድልን መፍጠር ማስቻላቸውን ጠቅሰው፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ከመቅረፍ አኳያም ያላቸው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል። የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው መካከልም 80 በመቶው ሴቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ከኮሚሽነር አበበ አበባየሁ ጋር ያደረግነውን ሙሉ ቃለ ምልልስ በገፅ 9 በኢኮኖሚ አምድ ያገኙታል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 21/2011
አስቴር ኤልያስ