አዲስ አበባ(ኢዜአ)፡- ‹‹ሰላም የሰፈነባት፣ ህዝቦቿ እንደታሪካቸው በመከባበር የሚኖሩባትን ሀገር ለመገንባት ሁላችንም የድርሻችንን ማበርከት ይጠበቅብናል›› ሲሉ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰመስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ገለጹ።
ምክትል ርዕሰመስተዳድሩ ይህን የተናገሩት ‹‹ህገ-መንግሥትና ህብረ-ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓትን ማዳን ለዴሞክራሲያዊ ሀገራዊ አንድነት›› በሚል መሪ ሐሳብ ትናንት በመቀሌ ከተማ የተጀመረውን ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ ሲከፍቱ እንደተናሩት፤ ሰላም የሰፈነባት፣ ህዝቦቿ እንደታሪካቸው በመከባበር የሚኖሩባትን ሀገር ለመገንባት ሁሉም የድርሻውን ማበርከት ይጠበቅበታል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት አንዣቦ በታየው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የዜጎች መብቶች በአደባባይ ሲጣሱ የታየበት፣ ህዝቦች በነፃነት ተንቀሳቅሰው መሥራት የማይችሉበት፣ ሀብት ለማፍራት የተቸገሩበት፣ ለጥቃት የተጋለጡበትና የህግ የበላይነት አደጋ ላይ የወደቀበት መሆኑንም ዶክተር ደብተፅዮን ተናግረዋል።
‹‹ይህ አስከፊና አደገኛ ሁኔታ ለዜጎች ህይወት መጥፋት፣ ጉስቁልናና የወደፊት ተስፋ መታጣት ምክንያት ሆኗል›› ያሉት ዶክተር ደብረፅዮን፣ በዚህ ከቀጠለ በአገሪቱ አንድነትና ህገ-መንግሥታዊ ስርዓት ላይ የከፋ አደጋ እንዳይከሰት ስጋት መፍጠሩንም አስረድተዋል።
‹‹እየታየ ያለውን ከፍተኛ ስጋትም ሁላችንም ተባብረን በመታገል ህዝቦቻችን የሚፈልጉትን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ለማስፈን ችግር የሚፈጥሩ አካላትን በብቃት መመከት አለብን›› ብለዋል። አሁን በአገሪቱ በስፋት እየተከሰቱ ያሉትን ችግሮች ህገ-መንግሥቱን ካለማክበርና የህግ የበላይነትን ካለማረጋገጥ የሚመነጩ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
እየተፈጠሩ ላሉት ችግሮች ምክንያቱ የፌዴራል ስርዓቱ እንደሆነ ለመግለጽ የሚሞክሩ ኃይሎች መኖራቸውን ገልጸው የብሄር ግጭቶች፣ማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች መበራከታቸው በፌዴራል ስርዓት በመመራታችን ሳይሆን ህግና ህገ-መንግሥትን በአግባቡ ማስከበር ባለመቻሉ የመጣ እንደሆነም ተናግረዋል።
‹‹ብዝሃነትን መሰረት ያደረገው ፌዴራላዊ ስርዓት አሉታዊና አወንታዊ ገፅታዎች እንዳሉት የማይካድ ሀቅ ነው›› ያሉት ምክትል ርእሰመስተዳድሩ፣ አወንታዊ ገፅታውን በማጠናከርና አሉታዊ ገፅታውን በማስተካከል ህብረ-ብሄራዊ ፌዴራሊዝምን ማስቀጠል አማራጭ እንደሌለው አስረድተዋል።
‹‹አሁን የገባንበት ፖለቲካዊ ሁኔታ በአግባቡ ተመርቶ በጥበብ ማለፍ ካልቻልን ከባድ ጉዳት ሊያጋጥመን ይችላል›› በማለት ለህገ-መንግሥቱና ለፌዴራላዊ ስርዓቱ መጠናከር ሁሉን አቀፍ ትግል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም አመልክተዋል። ‹‹የውጭ ጠላቶቻችን የሀገራችን መዳከም ብቻ ሳይሆን መበታተን የግድ አስፈላጊ ነው ብለው እየተረባረቡ ይገኛሉም›› ብለዋል።
በመድረኩ ላይ ‹‹ህገ-መንግሥትና ህገ-መንግሥታዊ ስርዓት በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት ዶክተር መንበረጸሐይ ታደሰ በበኩላቸው፤ አራተኛ ህገ-መንግሥት የሆነው የአሁኑ ህገ-መንግሥት የተረቀቀው በኢትዮጵያ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሰፊ ውይይት ተደርጎበት መሆኑን ተናግረዋል።
ህገ-መንግሥቱ ከመጽደቁና ተግባራዊ ከመደረጉ በፊትም በ22 ሺ ቀበሌዎች ውስጥ በህዝብ ሰፊ ውይይት የተደረገበት ከመሆኑም ባለፈ፣በዓለም አቀፍ መስፈርት መሰረት የህገ-መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን ተቋቁሞና በወቅቱ ለነበረው የተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደነበርም አስታውሰዋል።
ህገ-መንግሥቱ በተለይ በብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ውስጥ የነበሩ መሰረታዊ የማንነት፣የሰላም እጦትና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄዎችን የመለሰ መሆኑንም አስረድተዋል።
ለሁለት ቀናት በሚካሔደው መድረክ ላይ ‹‹ህብረ-ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓት በኢትዮጵያ››፣‹‹የህግ የበላይነትና ሰላምና ደህንነት በኢትዮጵያ›› እና ‹‹ምርጫ 2012 በኢትዮጵያ›› በሚሉ-ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በምሁራን ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ይጠበቃል።
በመድረኩ ላይ ክልላዊና ሀገራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ምሁራን እየተሳተፉ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 21/2011