አዲስ አበባ፡- የማህበረሰብ አቀፍ የጤና አገልግሎቱን በመላው ሀገሪቷ በሁሉም የአገልግሎት መስጫ ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ጤና መድህን ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
አገልግሎቱን ያቀላጥፋል በተባለለት ረቂቅ አዋጅ ላይ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ውይይት በአዲስ አበባ ትናንት በተካሄደበት ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሳሙኤል ዘ-መንፈስ ቅዱስ እንዳሉት፤ ኤጀንሲው እስከ አሁን በሚሰጠው አገልግሎት ከአቅሙ በላይ ሆኖ የቆየበትን አገልግሎቱን በየትኛውም የአገልግሎት መስጫ ቦታ መስጠት ያለመቻል ችግር የሚፈታ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ውይይት እንዲካሄድበት እያረገ ነው፡፡
ረቂቅ አዋጁን ለውይይት ያቀረቡት የኢትዮጵያ ጤና መድህን ኤጀንሲ አማካሪ አቶ አብዱልጀሊል ረሻድ የኤጀንሲው አገልግሎት ተገልጋዮች የመድህን መታወቂያ ባወጡበት ወረዳ ደረጃ ብቻ የተገደበ ሆኖ መቆየቱን ጠቅሰው፣ ይህም ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተገልጋዮችን ለማስተናገድ ሳያስችል መቆየቱን አስታውቀዋል፡፡ በሁሉም ክልሎች በረቂቅ አዋጁ ላይ የህዝብ ውይይት በማድረግ ግብአት
ለማሰባሰብ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ረቂቅ አዋጁ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ በቀጣይ ዓመት እስከ 6 ወራት ወደ አፈፃፀም ይገባል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ አብዱልጀሊል ገለጻ፤ የጤና መድህን አገልግሎቱ የቀድሞ አሠራር በወረዳ ላይ የተወሰነ በመሆኑ ህብረተሰቡን በፌዴራል ደረጃ ትልልቅ ሆስፒታሎች መገልገል የማያስችል ነበር፤ ይህንንም ለማስቀረት እንዲሁም ህብረተሰቡ በመላ አገሪቷ በሚገኙ የአገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች ላይ አገልግሎቱን ለመስጠት እየሠራ ነው፡፡
ኤጀንሲው በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ በ509 ወረዳዎች ላይ አገልግሎቱን እየሰጠ መሆኑን የጠቆሙት አማካሪው፣ በሚያዳርሰው ህዝብ ቁጥር ልክ አገልግሎቱን ለማዘመን የአዋጁ መፅደቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ 7 ክፍሎች እንዲሁም 32 አንቀፆች ያሉት ሲሆን፣ አዋጁን በተመለከተ በተካሄደው ውይይት ላይም የጤና አገልግሎቱን የተሻለ ለማድረግ እንዲሁም አገልግሎቱን ለህብረተሰቡ በተገቢው መንገድ ለማዳረስ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ጉልህ ሚና እንዳለው ተጠቅሷል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 21/2011
ዳግማዊት ግርማ