ሰዎች የጥላቻና የሌሎች መጥፎ ምግባሮችን እውነተኛ ውጤት ቢያውቁ፣ የሚያስከትሉትን የመንፈስ ድቀትና ዝቅጠት ቢረዱ ያለምንም ጥርጥር ከእኩይ ድርጊታቸው ይቆጠቡ ነበር” ሲል እውቁ የግሪክ ፈላስፋ ሶቅራጥስ ተናግሮ ነበር።
የዘመናችን የስነልቦና ባለሙያዎችም ይህንን እውነታ ይጋራሉ። ጥላቻ በቅድሚያ የሚጎዳው ራሱን በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ያለውን ሰው እንደሆነም በተለያዩ ጥናቶች ማረጋገጥ ተችሏል።
ሰው የራሱ አእምሮ ውጤት ነው። እያንዳንዱ ሰው የሚለካው በአእምሮው ልክ ነው። በተፈጥሮው የተሰጠውን የማሰብና የማገናዘብ ፀጋ በአግባቡ ተጠቅሞ አእምሮውን የሚያሰራ ሰው የተሻለ ስብእናና ማንነትን ያዳብራል።
ይህ ደግሞ የተሻለ ህይወት እንዲኖረው ያደርገዋል። በአንጻሩ አእምሮአችንን ላልተገባ ድርጊትና ጥላቻ ስንጠቀም በቅድሚያ ራሳችንን እንጎዳለን፤ ከዚያም አልፎ ሌሎችን ብሎም አገርን እናፈርሳለን።
ሰው ምክንያታዊ አስተሳሰብን ካላዳበረ “ሰው” የሚለውን ባህርይ ሊያሟላ አይችልም። ከሰውነት ይልቅ ለእንስሳነት ቅርብ ይሆናል። እንስሳት ደግሞ ከነገ ይልቅ ዛሬን ብቻ የሚኖሩ ናቸው። በአገራችንም አልፎ አልፎ እያየን ያለነው የዚህ ፀጋ መጓደል ነው።
ከምክንያታዊ አስተሳሰብ ይልቅ ስሜታዊነት ጎልቶ የሚንፀባረቅበት ሁኔታ በስፋት ይስተዋላል። ቆም ብሎ ከማሰብ ይልቅ በጅምላ የመነዳት ሁኔታ ይስተዋላል። ከእውቀት ይልቅ ስሜት ሲገዛን እንታያለን። በዚህም የተነሳ በተለያዩ የግለኝነት አስተሳሰቦች ተጠምደን ሰዎችን ለጉዳት ስንዳክር እንታያለን።
ከክርስቶስ ልደት በፊት በጥንታዊቷ ግሪክ እውቀት እንዲህ እንደዛሬ በየቤቱ አንኳኩቶ በማይገባበት ዘመን ፍልስፍናና ጥበብ ከመምህሩ ወደ ደቀመዝሙሩ የሚዋረሰው በቃል ንግግር በማድረግ ነበር።
እውቀትን በመሻት የተጠመዱ ፈላጊዎችም የጥበብ ዳና በሰፈረበት እያነፈነፉ ይከባሉ። በወቅቱ የነበሩ ተራማጅ ግለሰቦች ምቹ አጋጣሚዎች በተፈጠሩ ቁጥር እየተሰባሰቡ እውቀትን ይለዋወጣሉ። ርዕስ ፈጥረው ይወያያሉ። የሚያውቁትን ሰጥተው የማያውቁትን ይቀበላሉ።
ዛሬ ላይ እውቀትን ለመገብየት በርካታ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። ነገር ግን በአግባቡ ልንጠቀምበት አልቻልንም። ከእውቀት ይልቅ በተፈጥሮ ያገኘነው ማንነት መደበቂያ እየሆነ ነው። አንዱ የሌላውን ቁስል ለማከም ከመሄድ ይልቅ በቁስሉ ላይ ሌላ ቁስል ለመጨመር መሄድ፣ ከማስታረቅ ይልቅ ለማጋጨት ጉድጓድ መቆፈር የብዙዎች የቀን ውሎ ሲሆን ይስተዋላል።
ለምሳሌ ለህይወት መሻሻል ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት የሚታመንበት የማህበራዊ ሚዲያ ኢላማውን ስቶ የጦርነት መሳሪያ ሲሆን ይስተዋላል፤ በዚህ መሳሪያ አማካይነት ከአንድነት ይልቅ መለያየት እየሰፈነ ነው። በዴሞክራሲ ስም በተገኙ ሚዲያዎችም
ሰላምና አንድነትን ከመስበክ ይልቅ መለያየትን መስበክ ትልቁ አጀንዳ እየሆነ ይገኛል። ለበጎ ተብሎ የተሰራ ስራ ህፀፅ እየተፈለገለት የህዝቦችን ቁስል ለመደንቆል ሲውል ይታያል። በአጠቃላይ አሁን አሁን እየመጣ ያለው የመለያየት አጀንዳ ሊታሰብበት ይገባል።
ጥንታዊ ግሪኮች “መካከለኛ ህይወትን መምራት” የሚል የኑሮ ዘይቤ ነበራቸው። እኛም ዛሬ ፅንፍ ከወጡት የብሄርተኝነትም ሆነ በሌላው ጫፍ ፅንፍ ካለው የአሃዳዊ አስተሳሰብ ስርአት ተላቀን ሁሉንም በሚዛኑ የምናይበት እድል ለራሳችን ልንሰጥ ይገባል። የከረረ ነገር ሁሉ መጨረሻው መበጠስ ስለሚሆን ከዚህ አስተሳሰብ ወጥተን ሁሉንም ነገር በሚዛን ማየት ላይ ልናተኩር ይገባል።
እኛ ኢትጵያውን ተፈጥሮ ያደለን በርካታ ሃብቶች አሉን። በቀላሉ ሊለማ የሚችል ምድርና የተፈጥሮ ፀጋ፣ ለዘመናት በጠንካራ ማህበራዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች የተገነባ ህዝብ፣ ጠንካራ ባህላዊ እሴቶች ወዘተ ያለን ህዝቦች ነን። እነዚህ የማንነት መቅረጫ እሴቶቻችን ደግሞ ለነገው ትውልድ የተሻለች አገር ለመገንባት ትልቅ ሃብቶች ናቸው።
ይሁን እንጂ እነዚህን ሃብቶች በአግባቡ ለመጠቀም ከመጣር ይልቅ በማንነት ውስጥ ተሸሽገን በአቋራጭ ያለምንም ጥረት በሌላው ሃብት ለመጠቀም ሩጫ ውስጥ ስንገባ እንውላለን። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያለው ሁኔታ የቀደመውን ጠንካራ አንድነት፣ የፍቅር፣ የመቻቻል እና የመልካምነት እሴቶች በመሸርሸር አገርን ወደሚያፈርሱ የግጭትና የመለያየት አዳዲስ ባህሎች እየገባን በመሆኑ ከዚህ ለመላቀቅ ራሳችንን ቆም ብለን እንይ።
“ኢትዮጵያዊነት መልካምነት” የሚለው የቆየ የማንነት ቀስ በቀስ ሲናድ እያስተዋልን ዝም አንበል። ዛሬ ዛሬ ታናናሾች ታላላቆችን የሚያከብሩበት እሴት ተሸርሽሯል፤ አባት የጎረቤት ልጅን ኮትኩቶ ለማሳደግ የሚያደርገው ድጋፍና ሃላፊነት እንደዋዛ ቀርቷል፤ የርስ በርስ ግንኙነታችን በማንነት ላይ የተመሰረተ ሆኗል፤ በአጠቃላይ አንድነታችንን የሚያጠናክሩልን የፍቅር እሴቶቻችን ዛሬ ላይ በጥርጣሬ ወደመተያየት እያስኬዱን ነው።
በጎዳና ላይ የወደቁ ህፃናት ሳይቀር እንደ እንስሳ መንጋ አብረው የሚጓዙት በአንድ የቋንቋ ቤተሰብ ውስጥ ሲሆኑ ብቻ ነው። በመንደርም በተመሳሳይ በማንነት መሳሳብ ቀስ በቀስ እየጨመረ ሲሄድ ይስተዋላል። በርግጥ ይህ በመልካም ጎኑ ብናየው እንደ ችግር ላይታይ ይችላል። ነገር ግን አስተሳሰቡ ሌላውን በማግለል ሲሆን ወደ መራራቅና ብሎም አገርን ወደማፍረስ የማይሄድበት ምክንያት አይኖርምና አጥብቀን ልናስብበት ይገባል። ምክንያታዊ አስተሳሰብ ካልዳበረ የመንጋ አስተሳሰብ አገር ያፈርሳልና ቆም ብለን እናስብ።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 20/2011