ይህ ዓምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ አስተያየታቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሑፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
ሰላም ጤና ይስጥልኝ የተወደዳችሁ አንባቢያን። እንደምንከርማችኋል? ዛሬ በዚህ ከኛም ከናንተም በተሰኘ አምድ ላይ ትክክለኛውን የሰው ልጅ ዋጋ እና በነባራዊው ዓለም በተለይም በሀገራችን ያለውን የተሳሳተ እውነታ የሚያሳይ ሁኔታ ዳስሼ የሰነቅሁትን እነሆ ላካፍላችሁ ወደድኩ። ከአፅንዖት ጋር እንድትከታተሉ እየጋበዝኩኝ ወደዕለቱ መሰናዶዬ አመራለሁ።
የግዛት አወቃቀር ምሁራን አንድ ሀገር ሀገር ነው ሊባል የሚችለው አራት አበይት መስፈርቶችን ማለትም ግዛት፣ ሉዓላዊነት፣ ህዝብና መንግስታዊ አወቃቀርን አሟልቶ ሲገኝ እንደሆነ ያስረግጣሉ። በእርግጥ ከእነዚህ አራት ነገሮች አንዱ ከተጓደለ ሀገር ብሎ ነገር እንደሌለ ቢናገሩም የተቀሩት ሶስቱ ነገሮች እንዲኖሩ የማድረጉን መሰረታዊ ተግባር በመፈፀሙ ረገድ ትልቅ ድርሻ ያለው ሰው ልጅ በመሆኑ የሰው የማይተካ ሚና አለው። ምክንያቱም ግዛት ተብሎ የሚታወቀው የሰው ልጅ የኔ ያለውድንበር ውስጥ የሚገኝ ስፍራ ነው። ሉዓላዊነት ደግሞ የሰው ልጅ የኔያለው ድንበር ወይም እሴት ያለመነካት መብት ነው። መንግስትም ቢሆን በጋራ ስምምነት አብሮ ለመተዳደር የሚያቋቁመው አካል ነውና በሀገር ውስጥ ያሉ ነገሮችን መጠንና አቅጣጫ የመወሰን ትልቁ ኃይልና ስልጣን ያለው የሰው ልጅ ከምንም ነገር በላይ ዋጋ ያለው ስለመሆኑ የማያከራክር ነው።
የዚህ እሳቤ የማያሻማ እውነታነት በዘመናት ዑደት ውስጥ አሌ የማይባልና የማይፋለስ ቢሆንም ቅሉ በመላው ዓለምም ሆነ በሀገራችን የምናስተውለው ግን ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ ዓይነት ከሆነ ቢሰነባብትም ቄሱም ዝም መፅሀፉም ዝም ሆነና የተንጋደደው የሰው ልጅ ዋጋ ጉዳይ አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ እንደሆነ ይኸው ዛሬም አለን። በእርግጥ የሰው ልጅ ለሚሰኘው ክቡር ፍጡር የተሰጠውን የማይገባ ዋጋ የሚገልጡ እልፍ ማሳያዎች በየመስኩ ቢኖሩም የዛሬው ዕይታና ትዝብቴን አንድ መስክ ላይ አነጣጥሬ ለማፍታታት እሞክራለሁ።
እርግጥ ነው እንደኛይቱ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያቸው ደከም ያለ ነገር ግን ደግሞ ተፈጥሮ ችሮታዋን አብዝታ የለገሰቻቸው ደሀ ሀገራት ቁልል የተፈጥሮ ሀብታቸውን አፍጠው እያዩ ድንግልናን በስነ-ቃል እያሞጋገሱ ጦም ውሎ ከማደር ውጪ ብዙም አዲስ ነገር ሲፈጥሩ አይታዩም። የሃሳብም የቴክኖሎጂም ድሃ ስለሆኑ ሀብት ካፈሩ ሀገራት ገንዘቡንም ባለሃብቱንም ለመሳብ መሞከራቸው አይወሬ ነው። ይህ በዘመናዊው የኢኮኖሚ መስተጋብር ውስጥ የተለመደ ነው። የሀገሪቱ ድርሻ ምንድነው; ያላችሁ እንደሆነ ከምርት ኤክስፖርት የሚገኘው ምንዛሪ፣ ከባለሀብቱ የሚገኘው የቀረጥ ገቢ እንዲሁም የገበያ ተሳትፎ ቢጠቀሱም ከሁሉ የሚልቀው የዚህ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት ፋይዳ ግን ለዜጎች የሚፈጠረው የስራ ዕድል ነው። ይህም በሀገራችን በተጀመረው የኢንደስትሪፓርክና የግብርና ኢንቨስትመንት ላይ በተጨባጭ የሚታይ ሀቅ ነው።
የሆነው ሆኖ የዛሬ አብይ ጥያቄዬና የሀሳቤ አስኳል ያለው ከዚህ ባሻገር ነው። ከውጭ በመጡ ኢንቨስትመንት ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ዜጎች ክፍያ ስኬል፣ የስራ ሰዓታቸው እንዲሁም ከሰው ልጅነታቸው ባሻገር የሀገሪቱ ዜጎች እንደመሆናቸው የሚሰጣቸው ክብርስ ምን ይመስላል? የሚለውን ስናይ ብዙ አሳሳቢ ነገሮች ይታዩኛል። አንዳንዴም መንግስታችን ትኩረት የሚሰጠው ፈራንካ ላለው ነው ወይስ ለዜጋው? የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ያቃጭልብኛል። በእርግጥ አሁን አሁን ከተለያዩ ሀገር መንግስታት ጋር በመነጋገር በዜጎች ሉዓላዊነትና ክፍያ ዙሪያ በአረብ ሀገር ካሉ ያብዛኛው ሀገር ዜጎች በታች የሆነ ክፍያና ክብር የሚሰጣቸውን የዜጎቻችንን ጉዳይ እልባት ለመስጠት መንግስታችን እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አድንቄ የሀገር ውስጡስ ሁኔታ ምን ያህል ተቃኝቷል? የሚለውን ጥያቄ ለማንሳት ያስገደዱኝን ሁኔታዎች ለመጠቃቀስ እሞክራለሁ።
ምንም እንኳ ኢንቬስተሮችን ወደ ሀገሪቱ የሚስበው አንዱ ነገር ርካሽ የሰው ጉልበት መገኘቱ መሆኑ በየማስታወቂያው የምንሰማውና እኛም የማንክደው ሀቅ ቢሆንም ቅሉ “ርካሽሲ ባልእስ ከምን ድረስ” የሚለው አፅዕኖት ሰጥቶ መመልከቱ ተገቢ ነው። እንደወራጅ ውሃ የማይቆመው የኑሮ ውድነት ፈተና በሆነበት በአሁኑ ወቅት እንኳን ቤት ተከራይቶ ቀርቶ በልቶ ለማደር እንኳን የማይበቃ ደመወዝ መክፈል የበርካታ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መለያ ሆኗል። በእነዚሁ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚሰራ ዜጋም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ መምጣትም ርካሽ ሰው ጉልበት በሚል ብሂል የሚከፈለው ደመወዝ ከስም ያለፈ ፋይዳ ባለማስገኘቱ ነው። ከደመወዙ አናሳነትም ባሻገር እንደ ህዳር አህያ እንዳሻቸው ሲጭኗቸው፣ ሲያመናጭቁና ሲያበሻቅጧቸው ላየ የቱ ዜጋ የቱ ኢንቬስተር የሚለውን ለመለየት መቸገሩ አይቀሬ ነው።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በቅርቡ በሀዋሳ ኢንደስትሪያል ፓርክ ያለው የስራ፣ ክፍያና የዜግነት መብት ጉዳይ አስመርሯቸው አቤቱታ ያቀረቡ ሰራተኞች እንዳመለከቱት አረብ ሀገር ከሄዱ እህቶቻችን በማይተናነስ መልኩ ራስ ምታት ታመው ማረፍ ቢፈልጉ እንኳን ካልፈለግሽ ስራውን ለቀሽ ውጪ የሚባሉ እህቶቻችንን መኖራቸው እውነትም ይህ እዚህ ጉያችን ስር የሚከሰት ስለመሆኑ ለማመን ይከብዳል። እርግጥ ነው በስራ ባህሪያቸው፣ በስነ-ምግባራቸው፣ በተነሳሽነታቸው ችግር ክብራቸውን አሳልፈው ሰጥተው ራሳቸውንና ሀገርን የሚያሰድቡ ይጠፋሉ የሚል እምነት የለኝም።
ነገር ግን ችግሩ እየገዘፈ መጥቶ በሃገር ውስጥ መስራት ፋይዳ የለውምና ስደት ይሻለናል ሚሉ ዜጎችን እንዳናበራክት ስጋቱ ከወዲሁ ስለገባኝ ነው። በተለይም መንግስት የስራ ዕድሎችን ለማበራከት በሚሯሯጥበት በዚህ ሰዓት በእጃችን የገቡ ስራ ዕድሎችን የዜጎችን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ሊቃኙ ይገባል የሚልም እምነት አለኝ።በመጨረሻም የኢንቨስትመንት ድርጅቶች ክፍያ ስኬል፣ የስራ ሁኔታ እንዲሁም የአስተዳደር ማዕቀፉ ዳግም ታይቶ እንደሚቃኝ ተስፋ እያደረግኩ ሀሳቤን በዚሁ እቋጫለሁ። ቸር ያክርመን።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ዛሬ !
በአንዳርጋቸው ምንዳ