ባለፉት ዓመታት ፈጣን ዕድገት ካስመዘገቡት ሀገራት ኢትዮጵያ አንዷና ዋነኛዋ ብትሆንም ዕድገቷ ተመስርቶ የቆየው በውጭ ብድር ላይ በመሆኑ ዕድገቱ ዘላቂ መሆን ተስኖት ሀገሪቱን አጣብቂኝ ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል።ሀገሪቱን ያለማቋረጥ ከአበዳሪ ሀገራትና ከዓለም አቀፍ ተቋማት የወሰደቻቸውን ብድሮች በወቅቱ መመለስ ባለመችሏም የሀገሪቱ የብድር ክምችትም 1.5 ትሪሊዎን ዶላር ሊደርስ ችሏል። ከሀገሪቱ ዓመታዊ ገቢም 20 ቢሊዮን ብር ያህሉን ይህንኑ ዕዳ ለመክፈል እየዋለ መሆኑን መንግሥት በቅርቡ ይፋ አድርጓል።
ከብደር ክምችቱ በተጨማሪም የአገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት (ጂዲፒ) ውጣ ውረድን፣ የውጭ ምንዛሪ ችግሮችን ወይም የገቢና ወጪ ንግድ ሚዛንን እንዲሁም የተባባሰ የዋጋ ግሽበት ከሥራ አጥነትና ከተቀዛቀዘ ኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ሲደመር የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ቅርቃር ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። ይህንኑ በመረዳትም ኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን ሲጠቀምበት የቆየውን በብድር ላይ የተመሰረተውን የፋይናንስ ሞዴል ለመቀየር ተገዷል።
በብድር ላይ የተመሰረተውን የፋይናንስ ሞዴል በመቀየርም ትላልቅ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በከፊል ወደ ግሉ ዘርፍ በማዘዋወር ፤የውጭ ንግድን በማበረታታትና የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚፈስባቸውን ልዩ ልዩ ስልቶች በመንደፍ ኢኮኖሚው ከተቀዛቀዘበት ቆፈን ውስጥ እንዲወጣ ጅምር ጥረቶች እየተስተዋሉ ነው። የዚህ ጅምር ጥረት አንድ አካል የሆነውና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዕረፍት ከተበተነበት ለአስቸኳይ ስብሰባ ተጠርቶ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከል የውጭ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን አክሲዮን መግዛት ብቻም ሳይሆን፣ ባንክ ማቋቋም እንደሚችሉ የሚፈቅዱ አንቀጾች የተካተቱበት የባንክ ሥራ አዋጅን በማሻሻል ማፅደቁ ይታወሳል። እንዲህ ያሉት ለውጦች በውጭ ሀገራት ያለውን ፋይናንስ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ በማድረግ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ለመቅረፍ የሚጫወተው ሚና የጎላ ነው።
መንግሥት እያደረጋቸው ያሉ መዋቅራዊ ለውጦች በቀጣይ የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ እንደሚያነቃቁት እምነት ቢጣልባቸውም አሁን የሚታየውን እና ጊዜ የማይሰጠውን የዋጋ ሽበትና የሥራ አጥነት ችግር ቅጽበታዊ መፍትሄ ይሰጣል ተብሎ ስለማይታሰብ ዋጋ ግሽበትና ሥራ አጥነትን አፋጣኝ በሆነ ሁኔታ መልክ ማስያዙ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም።በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ወደ 20 ሚሊዮን ዜጎች ሥራ አጥ እንደሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ። በየጊዜው እያሻቀበ የመጣውን የሥራ አጥ ቁጥር ለማቃለል በርካታ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑና ለዚህም ማሳያነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙ መልካም ቢሆንም የተጀመሩትን መሰል እንቅስቃሴዎች በሚታይና በሚዳሰስ መልኩ መሬት ማውረዱ ላይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል እንላለን።
ከመንግሥት ባሻገር መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና የግል ኩባንያዎችም የድርሻቸውን እንደሚያበረክቱ ይጠበቃል።በጅምር ደረጃም ቢሆን ሰሞኑን መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከግል ኩባንያዎችና ከመንግሥት ጋር በመተባበር የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማገዝ እንደሚፈልጉ አመላካች ስምምነት ማድረጋቸውም ይበል የሚያሰኝ ሲሆን፡ አሥር ሺህ የሚደርሱ ወጣቶችን ሥራ ለማስያዝ የሚያስችል ጥናት በማስጠናት ከግል ኩባንያዎች ጋር ለመሥራት ፕሮጀክት የቀረፀው የስዊድኑ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (SNV) ተጠቃሽነው። በሌላም በኩል የተባበሩት መንግሥታት የተለያዩ ድርጅቶች ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል የሚያገኙባቸውን ዕድሎችና ስልቶች ላይ ገለጻ ማድረጉ ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ ሁሉን አቀፍ ጥረት መደረግ መጀመሩን የሚያሳይ በመሆኑ ሁሉም በተመሳሳይ መልኩ የዚሁ ጥረት አካል እንዲሆን ምቹ መደላድል መፍጠር ይገባል።
ከሥራ አጥነት ችግሩ ጎን ለጎንም በየጊዜው እየናረ የመጣውን የኑሮ ውድነት የመታደጉ ጉዳይ በተመሳሳይ መልኩ በይደር የሚታለፍ አይደለም።ከቀናትም አልፎ በሰዓታት ውስጥ ዋጋቸው እየጨመረ የመጡት መሰረታዊ ፍጆታዎች የድሃውን ኑሮ እየተፈታተኑት ከመምጣታቸውም በላይ በልቶ የማደር ስጋት ውስጥ ከተውታል።በእርግጥ ችግሩን ለመቅረፍ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሞ የመፍትሄ ሃሳቦችን እያፈላለገ እንደሚገኝ የተገለጸ ቢሆንም ችግሩ ውሎ የማያሳድር በመሆኑ ችግሩን የሚመጥን መፍትሄ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር ሊሸጋገር ይገባል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ነሀሴ 18/2011