መጪው የ2012 ዘመን የእውነት አዲስ ዘመን ሆኖ እንድንቀበለው የሁላችንም መንፈሳዊ ዝግጅት ያስፈልጋል። አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ሁሉም እንደ አቅሙና እንደገቢው መጠን ጎጆውን ያድሳል፤ ጓዳውን ለመሙላት ይጥራል፤ የልጆቹን የዓመት ልብስና የትምህርት ቁሳቁስ ለማሟላት የየራሱን ዝግጅት ያደርጋል። ሁሌም በአዲስ ዓመት እንደዚህ ነው።
ዘንድሮ ግን ለየት ያለ ነገር ይስተዋላል። ተስተውሏልም። በተለይ የአገራችንን የትምህርት አሰጣጥ በሚመለከት ከፍተኛ የሚባል ስራ ተሰርቷል። በአገር ደረጃ በ2007 ጥናቱ የተጀመረው “የትምህርት ፍኖተ ካርታ” በ2012 አዲስ ዓመት መተግበር ይጀምራል። ይህ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚጀምረው መርሀ ግብር እስካሁን የነበረውን የተዛባ የትምህርት አሰጣጥና የመማር ማስተማር ሂደት ላይ የዓይነት ለውጥ ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል። በተለይ በስነምግባር ረገድ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ርቋቸው የከረመውን የታነጸ ዜጋ የማፍራት ችግር ለመቅረፍ “ሀ” ተብሎ ስራ መሰራት ይጀመርበታል ተብሎ ተስፋ ተደርጓል።
የመማር ማስተማሩን ሂደት የበለጠ ሳቢና ማራኪ ከማድረግ ባለፈ እስካሁን የመንግስት ትምህርት ቤቶች ሲተቹባቸው የነበረውን ለትምህርት አመቺ አካባቢ የመፍጠር ችግር የአዲስ አበባ መስተዳድርም የወቅቱ ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ መስራት ከጀመረ ሳምንታት ተቆጥረዋል። የአዲስ አበባ መስተዳድር በምክትል ከንቲባው በሚመራው ግብረ ሀይሉ እያከናወናቸው ካሉ ተግባራት መካከል በከተማዋ የሚገኙትን አራት መቶ ሰማንያ ስምንት የመንግስት ትምህርት ቤቶች የማደስ፤ በአስፈላጊው የመማሪያና የማስተማሪያ ቁሳቁስ የማሟላት፤ ለተማሪዎች ዩኒፎርም፣ የመማሪያ መጻህፍት፤ እንዲሁም ደብተርና እስክሪፕቶ ማሟላት ዓይነተኛዎቹ ናቸው። ከዚህ ጎን ለጎንም የተማሪዎች የትምህርት ቤት የምገባ መርሀ ግብርም ትልቁ የእቅዱ አካል ነው።
በዚህ ረገድ አስተዳደሩ ክረምቱ ከባተ ጀምሮ ፈቃደኛ አካላትን ከጎኑ በማሰለፍ የጀመራቸው የትምህርት ቤቶች እድሳትና የትምህርት መሳሪያ አቅርቦት ተግባራት እየተከናወኑ፤ በአብዛኛውም እየተገባደዱ ይገኛሉ። በተለይ፤ የመንግስት ትምህርት ቤቶችን ከነበረባቸው የገፍታሪነት እይታ በማላቀቅ ለተማሪዎችና ለመምህራን ምቹና ማራኪ ውበት የማላበሱ ስራ የተሳካ ውጤት እንዳመጣ ምልክቶች እየታዩ ነው። ከዚህም ቀደም ሲል በአብዛኛው የከተማዋ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የነበረው የተማሪዎች ቁጥር በመጪው ዓመት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምር በአሁኑ ወቅት ያለው የአዲስ ተማሪዎች የምዝገባ ጥያቄ መጨመርና ከአንዳንዶቹ ትምህርት ቤቶች አቅም በላይ እየሆነ መምጣቱ ዓይነተኛ ማሳያ ነው።
ይህ ሊሆን የቻለው የከተማው አስተዳደር ትምህርትንና ትምህርት ቤቶችን ማዕከል አድርጎ የጀመረው አኩሪ ተግባር በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በኗሪው ዘንድ በፈጠረው ስሜትና በፈነጠቀው ተስፋ መሆኑ የሚጠቀስ ሲሆን፤ ተጠናክሮ ሊቀጥልም ይገባዋል። ይህ በጎ ተግባር በተለይ ኗሪዋ በተለያዩ ሰው ሰራሽ ሰበቦች በተከሰተው የኑሮ ውድነት እግር ተወርች የታሰረባት አዲስ አበባ በየዓመቱ በአልቦ ምክንያት ዋጋ ከሚጨምረው የግል ትምህርት ቤቶች ምሬት እንደሚያላቅቀውና በመጠኑም ቢሆን እፎይ እንደሚያሰኘው ይጠበቃል።
በዚህ ረገድ፤ በዋጋ ጭማሪው መግፍኤነትም ይሁን በለውጡ ሳቢነት ተገፍቶ ልጆቹን ወደመንግስት ትምህርት ቤት ለማዛወርና ለማስተማር የሚሻው የማህበረሰብ ክፍል ቁጥሩ ከመጨመሩ ጋር ተያይዞ በየደረጃው ያሉ የመንግስት ትምህርት ቤቶችም ዝግጅታቸው ይህንን ታሳቢ ሊያደርጉ ይገባል። ምናልባት አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ካላቸው የመማሪያ ክፍል አቅምና ሊመዘገብ ከደጃቸው ከቆመው ትምህርት ፈላጊ ወላጅ ቁጥር አንጻር ለጊዜው አስቸጋሪ የሚመስሉ ጉዳዮች ቢታዩም ይህ ከአስተዳደሩና ከወላጆች አቅም በላይ አይሆንምና ተመካክሮ ችግሩን ለመፍታት መሞከር ተገቢ ነው።
ከዚህ ሌላ የአዲስ አበባም ሆነ የሌሎች ክልሎች የመንግስት ትምህርት ቤቶች የሚታሙባቸው የትምህርትን ጥራት የማስከበር ጉዳይ የጥራቱ መውድቅ ባንድ ጊዜ የተከሰተ ያለመሆኑን ያህል ጥራቱን ማሳደጉም ጊዜ የሚፈጅ ጉዳይ ነው። ይሁንና፤ ከአሁኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። በዚህ በኩል የትምህርትን ጥራት የማስከበር ርምጃ የሚጀመረው ከመምህሩ ነውና ሙያውን ያወቀና ያከበረ፤ የሚሰራው በሰዎች፤ ያውም በልጆች አዕምሮ ላይ መሆኑን አውቆ ግዴታውን የሚወጣ የመምህር ሀይል እንዲኖር በግልም ይሁን በጋራ መከናወን ያለባቸው ዝግጅቶች ሊደረጉ ይገባል።
በተለይ ትምህርትን ማንም የተማረ ሀይል ሁሉ ማስተማር እንደማይችል፤ ይልቁንም ለዚሁ ተብለው የተመረጡ፤ ስለማስተማር ክህሎት የጨበጡና መስጠትን የተካኑ፤ ከሁሉም በላይ ሙያውን የኔ ብለው የሚወዱት ዜጎች ብቻ የሚሰሩት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። በዚህ ረገድ መምህራን በሚያስተምሩት ትምህርት ዙሪያ እውቀት የቀሰሙ ብቻ ሳይሆኑ የቀሰሙትን እውቀት ለሌሎች ማካፈልን፤ በተለይም ለልጆች መጥኖ መስጠትን የተማሩና የሚያውቁ በመሆናቸው ሙያውን አክብረው ራሳቸውንም ሊያስከብሩ ይገባል። የነገዋን አገር የሚረከቡት የነርሱ አሻራ ያረፈባቸው የዛሬዎቹ ህጻናትና ወጣቶች ናቸውና!
ስለዚህ፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተጀመረው የትምህርት ቤቶችን መልክና ገጽታ የመቀየር፤ ለመማር ማስተማሩ ሳቢ አድርጎ የማደስና የመለወጥ ጥረት የትምህርትን ጥራት ለማሳደግም መሰረት መጣያ ጅምር መሆን አለበት። እናም መምህራን ለዚህ ተልዕኮ ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳሉና አዲሱን የትምህርት ዘመን የወደቀውን የትምህርት ጥራት ለማንሳት ቃል ገብተው የሚጀምሩበት ወቅት ሊሆን ይገባል። በየደረጃው ያሉ የትምህርት አስተዳደርና ባለድርሻ አካላትም የተጀመረው ስራ የአንድ ወቅት የዘመቻ ሳይሆን ዘላቂነት ያለው መሆኑን በማረጋገጥ በጠንካራ መሰረት ላይ ሊያስቀምጡት ይገባል። ክትትልና ድጋፉም በዚያው ልክ በተከታታይነት ሊቀጥል ይገባል።
ይህ በአዲስ አበባ አስተዳደር የተጀመረው አኩሪና መልካም ተግባር ወደሌሎች ክልሎችና አካባቢዎችም ሊስፋፋ የሚገባው መልካም ተሞክሮ ነውና ሁሉም የድርሻውን መውሰድና ሀላፊነትም መወጣት ይገባዋል። በአጠቃላይ ትምህርትና የመማር ማስተማር ስራ ወደቀ ሲባል ጠቅላላ አገሪቱን የሚመለከት ጉዳይ ነውና ሌሎችም ክልሎች ከወዲሁ የቤት ስራቸውን ለይተው ሊሰሩ ይገባቸዋል። በተረፈ፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተጀመረው የለውጥ ተግባር ከአሁኑ ግብረ መልሱ እየታየ ነውና፤ የትምህርትን ጥራት ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት በተቀናጀ ስራ መደገፍ ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 17/2011