በአዲስ አመት ዋዜማ ላይ ቆመን በሀገራችን እየነፈሰ ያለው የሰላም እና የፍቅር ንፋስ መልኩ ቀየር ያለ እንደሆነ እናስተውላለን፤ ሁኔታው ከወትሮው ይለያል፡፡ ቀድሞ አንድ የነበሩ ቤተሰቦችን፤ እናትና ልጅን፤ እህትና ወንድምን፤ ለዘመናት ተቀራርበው የኖሩ ህዝቦችን ሆድና ጀርባ ለማድረግ ሰፊ ስራ የተሰራበት ነው፡፡ ሁኔታው በተለይ ላለፉት ሁለት አስርት አመታት የእምነት ተቋማት ሳይቀሩ ሁለት ቦታ ከፍሏቸው የቆየ ቢሆንም በእርቅና በሰላም አሸንፈው አንድ ሆነዋል፡፡ ከእርቅና ከሰላም የሸሹ ግን መድረሻቸው የከፋ እንደሆነ ታሪክ ያስተምረናል፡፡
እርቅና ሰላም ያልተጠጋው በጉልበትና በሃይሉ፤ በሴራና በተንኮሉ የተመካ ሲምስ በዋለው ጉድጓድ ገብቶ እስከወዲያኛው ማለፉን ታሪክ ይነግረናል። በግርማቸው አስፈሪ የነበሩትም ነገሥታት እስከጭፍራ ሠራዊቶቻቸው በውሃ ሙላት ሲወሰዱ፣ እንደ እንስሳ በጫካ ሲቅበዘበዙ፣ እና ከነመታሰቢያቸው ትቢያ ሲሆኑ ዓለም ታዝባለች።
ሃይልን እና እብሪትን በፍቅር እና ርህራሄ፣ በይቅርታ እና ታጋሽነት፣ በትህትና እና ጨዋነት የሚመክቱ ግን በስተመጨረሻ አሸናፊዎች ናቸው፤ ሆነዋልም። እስከመጨረሻዋ አስፈሪ ቅጽበትም ባመኑበት ነገር ፀንተው የሚቆሙ፣ የመጨረሻዋን ጽዋ ለመጐንጨት የታመኑ፣ በህይወታቸውም ባይሆን በህልፈታቸው ዛሬም ፍቅር ህያው እንደሆነ የሚሰብኩ ወገኖች በየዘመኑ መገኘታቸው ደግሞ ለሰው ልጆች ሁሉ ተስፋ ነው፤ በተለይ ደግሞ ለአገራችን ኢትዮጵያ። ፍቅር በሰው ልጅ ላይ ያለንን የመልካምነት እምነትም ያጠናክርልናል።
ዛሬም እንደ ትናንቱ አዲሱን ዓመት በመተዛዘን፣ በመዋደድ፣ በአንተ ትብስ አንቺ መከባበር፣ ራስን አሳልፎ በመስጠት፣ በመረዳዳት፣ ደስታና ሀዘን በመካፈል፣ ያለንን ሁሉ በማካፈል፣ ለወገንና ለእምነታችን በመቆርቆር የወደፊቱን ትውልድ ህይወት የእኛንም ጭምር ብሩህ ማድረግ የምንችልበት ዘመን የምንፈጥርበት ሊሆን ይገባልም፡፡
እኛ ከተዋደድን ልባችን ለእርቀ ሰላም ክፍት ከሆነ ብዙዎቹ የድህነት እና የሰላም ችግሮቻችን እንደ ተራራ ቢገዝፉም በፊታችን ደልዳላ ሜዳ ይሆናሉ። ፍቅር ሃያል ነው፤ ፍቅር ያላቸውም ኃያላን ናቸው። በመሆኑም ፍቅር ያላቸው ሁሉ የኃያላን ተግባራትን ይከውናሉ። በልበ-ሙሉነት እና በፍፁም በራስ-መተማመን ስሜት ሊገላቸው ጭምር ከመጣው ሰው ፊት የፍቅር ምላሽ ይሰጣሉ። ሰይፍን በሰይፍ አይመልሱም፤ ሰይፍን የሚያነሱ በሰይፍ እንደሚጠፉ ያውቃሉና!
ይልቁንም ግራ ጉንጫቸው ሲመታ ቀኙን ለማዞር ይዘጋጃሉ። እኛም ኢትዮጵያውያን ከፊታችን የተደቀኑ ችግሮቻችንን ለማስወገድ ልባችን በፍቅር ሊሞላ ግድ ነው፡፡ ታላላቅ የአገራችን ጀግኖች አሸናፊነታቸው የታየው ሊገላቸው የመጣውን ሰው በክፋት ባለመተባበር ጭምር መሆኑን አንዘንጋ፡፡ የገዳይ ግብረ-አበርም አይሆኑም፤ ለመሞት ይመቻቹለታል እንጂ አይገድሉም። በዚህም ተግባራቸው የፍቅርን ሃያልነትና ረቂቅነት ይገልጣሉ! እየሞቱም ‹‹… የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው!›› እያሉ ስለገዳዮች ይማፀናሉ። እንዲህ ያለ ለፍቅር፣ ለእርቅና ለሰላም ክፍት የሆነ ልብ ይዘን አዲሱን አመት መሻገር አለብን፤ ይህን ማድረግ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን አዲስ አይሆንም፤ ከአባቶቻችን የወረስነው እሴት ይኸው ነው፡፡
ታዲያ ዛሬ አሮጌውን አመት ትተን አዲሱን ልንቀበል እየተዘጋጀን ባለንበት በዚህ ዋዜማ ‹‹እርቅን በልባችን ይዘን እንሻገር›› የሚለው መንግስትን ጨምሮ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚፈትን መሆን አለበት፡፡ ይህን የምንለው ያለምክንያት አይደለም፡፡ ላለፉት አመታት ያሳለፍነውን ሕይወት መለስ ብለን ስንቃኘው፣ ወደውስጣችን ስንመለከት፣ ጓዳችንን ስንመረምረው፣ ልባችንን ስንፈትሸው ፍቅርን እናገኘው ይሆን? ወይስ በቦታው ጥርጣሬ፣ አለመተማመን፣ ፍርሃት፣ ቂም በቀል እና ጥላቻ ነግሶበታል?
ይህ ሁኔታ ከእነ መርዘኛ ሰንኮፉ የምንነቅለውስ በምንድን ነው? ምንም መልካም እንዳንሠራ ብቻ ሳይሆን የምንሠራው ሁሉ ጥፋት እንዲሆን ከሚያንደረድረን ጥላቻስ የምንወጣው በምን መላ ነው? ከራሳችን፣ ከቤተሰባችን፣ ከጐረቤቶቻችን፣ ከአባቶቻችን ጋር ተጣልተንስ የምንኖረው እስከመቼ ነው? መቼስ እርቅ እናወርዳለን? መቼስ የቀደመውን ፍቅር ከወደቀበት እናነሳዋለን? እነዚህን ጥያቄዎች በቅጡ መመለስ የሚገባን ዛሬ በአዲስ አመት ዋዜማ ነው፡፡ ልባችን ለእርቀ ሰላም የተዘጋጀና የተመቸ ማድረግ ለማንም ተብሎ የሚከናወን አይደለም ለራስ ጥቅም- በተለይ ለኢትዮጵያችን እንጂ፡፡
በጥቅሉ ይህ ወቅት ለአገራችን ወሳኝ ነው የሚባለው ለሰላምና ለፍቅር ብሎም ለእርቅ የሚሆን ጊዜ ላይ በመሆናችን ነው፡፡ ‹‹መግደል መሸነፍ ነው፤ ፍቅር ግን አሸናፊ ነው›› የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሀሳብ ማጠንጠኛው ይህ ነው፡፡ በመሆኑም ሁላችንም የምናሸንፈው ፍቅር ሲያሸንፍ ነው። ፍቅር ሲያሸንፍ አባት ያሸንፋል! ፍቅር ሲያሸንፍ እናት ታሸንፋለች! ፍቅር ሲያሸንፍ ልጆች ያሸንፋሉ! ፍቅር ሲያሸንፍ አባቶች ያሸንፋሉ! ፍቅር ሲያሸንፍ ህዝብ ሁሉ ያሸንፋል! ፍቅር ሲያሸንፍ የሰው ልጆች ሁሉ ያሸንፋሉ! ፍቅር ሲያሸንፍ ለሁላችን ሰላምና አንድነት ይሆናል!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 16/2011