ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ “በሥልጣን አለአግባብ መገልገል፤ ምንጩ ያልታወቀ ንብረት ወይም ገንዘብ መያዝ፤ የመንግሥት ሥራን በማያመች አኳኋን መምራት” ወዘተ የሚሉ ቃላትን በተለይም ከፍርድ ቤቶች የችሎት ውሎ ዘገባዎች ደጋግመን ስናደምጥና ስናነብ ነው የከረምነው።ጥቂት የማይባሉ የመንግሥትና የህዝባዊ ድርጅት ሠራተኞችና ሹማምንት በተለይም ሥልጣናቸውን ባልተገባ መልኩ ተገልግለውበታል በሚል ተጠርጥረው ምርመራ ሲደረግባቸውና ክስም ተመስርቶባቸው በፍርድ ሂደት ላይ መሆናቸውንም ስንሰማ ሰነባብተናል።በዛሬው ጽሁፋችን ታዲያ ለግንዛቤም፣ ለጥንቃቄም እንዲሆን በማሰብ በሥልጣን አለአግባብ የመገልገል ወንጀልን በተመለከተ ማብራሪያ አቅርቤላችኋለሁ።
በሥልጣን ያለአግባብ መገልገል በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት የሙስና ወንጀሎች ውስጥ አንዱ ነው።እናም በሥልጣን ያለአግባብ ስለመገልገል ወንጀል በዝርዝር ከማየታችን በፊት ስለሙስና ወንጀሎች ምንነትና ባህርያት በጥቅሉ መቃኘቱ በጉዳዩ ላይ ደህና የሆነ ግንዛቤ እንድንጨብጥ ያስችለናል።
የሙስና ወንጀሎች
ሙስና የሚለው ቃል በህጋችን አልተተረጎመም። ያም ሆኖ ሙስና በሥልጣን ላይ ባሉ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች የሚፈጸም ያለመታመንን እና በስልጣን መባለግን የሚገልጽ ሰፊ መገለጫዎች ያሉት ከባድ የወንጀል ዓይነት መሆኑን የተለያዩ ጽሁፎች ተርጉመውታል።ወንጀል የሚለውም ቃል እንዲሁ በወንጀል ሕጉ “ሕገወጥነቱና አስቀጭነቱ በሕግ የተደነገገውን ድርጊት መፈጸም ወንጀል ነው” በሚል ከመገለጹ ውጭ በሕጋችን በአግባቡ አልተተረጎመም።እናም ከሕጉ አነጋገርና በጉዳዩ ዙሪያ ትንታኔን ካቀረቡ ጽሁፎች ቃርመን የወንጀልን ትርጓሜ በጥቅሉ ስናስቀምጥ “ወንጀል ማለት በሕግ አድርጉ በሚል የተቀመጠውን ድርጊት ባለማድረግ ወይም አታድርጉ የተባለውን በማድረግ በራስ አልያም በሌሎች ሰዎች ወይም በሕዝብና በአገር ላይ የሕይወት፣ የአካል፣ የሥነ ልቡና፣ የነጻነት ወይም የሃብት ጉዳት የሚያደርስ የሚያስቀጣ አድራጎት ነው” የሚል አንድምታን እናገኛለን።
በተመሳሳይ የሙስና ወንጀል የሚለውም ሐረግ በሕጋችን ትርጉም ያልተሰጠው ነው።በመሆኑም የሙስና ወንጀል ጉቦን፣ በስልጣን ያለአግባብ መገልገልን፣ አታላይነትን እና ሌሎችንም በሙስና ወንጀል ድንጋጌዎች ውስጥ የተዘረዘሩትን ወንጀሎች የሚያጠቃልል ነው ማለት ነው።
በኢትዮጵያ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ ራሱን የቻለ ሕግ የወጣው በ2007 ዓ.ም. ነው – በአዋጅ ቁጥር 881/2007።ከዚህ አዋጅ አስቀድሞ የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግም የሙስና ወንጀል ድንጋጌዎችን በውስጡ አካትቷል።ይሁንና የወንጀል ሕጉ በሥራ ላይ ከዋለበት ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ በአፈጻጸም ወቅት በውስጡ ተካትተው የነበሩት የሙስና ወንጀል ድንጋጌዎች ግልጽነት የጎደላቸው ሆነው ተገኝተዋል።ከሁሉም በላይ የወንጀል ሕጉ የሙስና ድንጋጌዎች በመንግሥት ሥራና በመንግሥት ሠራተኞች ወይም ሹማምንት የተፈጸሙ ወንጀሎችን ብቻ ነበር የሚያጠቃልሉት።ድንጋጌዎቹ በተለይም ከሕዝብ የተሰበሰበ ወይም ለሕዝብ ተብሎ የተሰበሰበ ሃብት በሚያስተዳድሩ የግል ዘርፍ አካላት ላይም ጭምር የሚፈጸሙ ድርጊቶችን የሚያካትቱ አልነበሩም።
በዚህ መነሻ ኢትዮጵያ ተቀብላ በመፈረም የሕጎቿ አካል ባደረገቻቸው ዓለም አቀፍና አህጉራዊ የሙስና መከላከያና መዋጊያ ስምምነቶች ውስጥ አገራት በግሉ ዘርፍም የሚፈጸሙ የጉቦኝነት እና የምዝበራ ተግባራትን በሙስና ወንጀልነት እንዲፈርጁ ግዳጅ የተጣለ በመሆኑ አዋጁ ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ሊጸድቅ ችሏል።
በዚሁ መሰረት አዋጁ በመንግሥት መስሪያ ቤቶች (በሙሉ ወይም በከፊል በመንግሥት በጀት የሚተዳደሩ ወይም ሙሉ ወይም ከፊል የመንግሥት የባለቤትነት ድርሻ ያለባቸው የልማት ድርጅቶች) ውስጥ ከሚፈጸሙት በተጨማሪ በማንኛውም አግባብ ከአባላት ወይም ከሕዝብ የተሰበሰበ ወይም ለሕዝብ አገልግሎት ታስቦ የተሰበሰበ ገንዘብ ወይም ንብረት ወይም ሌላ ሃብት በሚያስተዳድሩ የግል ዘርፍ አካላት (ሕዝባዊ ድርጅቶች) በበጎ አድራጎት ማህበራትም ውስጥ የሚፈጸሙ የሙስና ተግባራትንም ጭምር በሙስና ወንጀልነት ደንግጓል።
እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ዋነኛው ነጥብ ታዲያ የሃይማኖት ተቋማት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች (ፓርቲዎች)፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ እድርና ተመሳሳይ ባህላዊ ወይም ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ማህበራት ሕዝባዊ ድርጅቶች ከሚለው የሕጉ ትርጓሜ ውጭ መደረጋቸው ነው።እነዚህ ድርጅቶች ምንም እንኳን የሕዝብ ወይም ለሕዝብ ተብሎ የተሰበሰበ ሃብት የሚያስተዳድሩ ቢሆንም ሕግ አውጭው ባስቀመጣቸው የተለያዩ ምክንያቶች (በተለይም ከእምነት ነጻነት፣ የመንግሥትን እጅ ከፖለቲካ ፓርቲዎች አካባቢ ከማራቅና በሌሎችም ምክንያቶች) በተቋማቱ ውስጥ የሚፈጸሙ የሙስና ተግባራት በሙስና አዋጁ አያስጠይቁም።
ከአዋጁ እንደምንገነዘበው የሙስና ወንጀል በሶስት ዓበይት ዘውጎች የሚመደቡ ወንጀሎችን ያጠቃልላል።የመጀመሪያው የመንግሥት ወይም የህዝባዊ ድርጅት ሠራተኞች በመንግሥት ሥራ ላይ የሚፈጽሟቸውን ወንጀሎች ያካትታል።የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሠራተኛ ማለት በመንግሥት መስሪያ ቤት ወይም በሕዝባዊ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ፣ ተሹሞ፣ ተመድቦ፣ በሕዝብ ወይም በአባላት ተመርጦ በቋሚነት ወይም በጊዜያዊነት የሚሰራ ሰው ሲሆን፤ የቦርድ አባልን፣ የድርጅት መሪን፣ የአክስዮን ማሕበር ወይም የበጎ አድራጎት ድርጅት የሚያደራጅ ሰውን ወይም ኮሚቴን ሁሉ ያካትታል።
በሥልጣን ያለአግባብ መገልገል፤ ጉቦ ወይም የማይገባ ጥቅም መቀበል፣ ሥራን በማያመች አኳኋን መምራት፣ አደራ በተሰጠው ዕቃ ያለአግባብ ማዘዝ፤ ንብረት ወይም ሰነድ የመውሰድና የመሰወር ተግባር፤ በሥልጣን ወይም በኃላፊነት መንገድ፣ በሕገ ወጥ መንገድ ገንዘብ ወይም እቃ መሰብሰብ ወይም ማስረከብ፤ ያለአግባብ ጉዳይን ማጓተት፤ ያለአግባብ ፈቃድ መስጠት ወይም ማጽደቅ፤ ምንጩ ያልታወቀ ንብረት ወይም ገንዘብ መያዝ፤ የሥራ ምስጢርን መግለጽ፤ ከባድ የዕምነት ማጉደልና ከባድ አታላይነት ወንጀሎች የመንግሥት ወይም የህዝባዊ ድርጅት ሠራተኞች በመንግሥት ሥራ ላይ የሚፈጽሟቸው የሙስና ወንጀሎች ናቸው።
ሁለተኛው የሙስና ወንጀሎች ዘውግ የመንግ ሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሠራተኛ ያልሆነ ማንኛውም ሰው በመንግሥት ወይም በሕዝባዊ ድርጅት ሥራ ላይ የሚፈጽማቸውን ወንጀሎች ያጠቃልላል።እነዚህ ወንጀሎች ማንኛውም ሰው የሌላን ሰው መብት ወይም ጥቅም ለመጉዳት ወይም ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ተገቢ ያልሆነ ማናቸውንም መብት ወይም ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት በማሰብ በመንግሥት ሥራ ላይ የሚፈጽሟቸው የሙስና ወንጀሎች ናቸው።
የመንግሥት (የሕዝባዊ ድርጅት) ሰነዶችን አስመስሎ ማዘጋጀት፤ ወደ ሐሰተኛነት መለወጥ፤ ወይም በሐሰተኛ ሰነዶቹ እያወቀ መገልገል፤ ሰነዶችን ማጥፋት ወይም ጉዳት እንዲደርስባቸው ማድረግ፤ ጉቦ ወይም ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለመንግሥት (ለሕዝባዊ ድርጅት) ሠራተኛ መስጠት፤ ጉቦ ወይም ሌላ ጥቅምና አገልግሎትን ማቀባበል፤ በሌለው ሥልጣን መጠቀም፤ የመንግሥት (የሕዝባዊ ድርጅት) ሠራተኛ በመምሰል ያለውን ወይም እንዳለው ያስመሰለውን የግል ተሰሚነት በመጠቀም አንድ የመንግሥት (የሕዝባዊ ድርጅት) ሠራተኛ ብቻ ሊሰጥ የሚችለውን መብት ወይም ጥቅም ለሌላው ሰው እንደሚያስገኝ አድርጎ መነገድ እንዲሁም በምርጫ ላይ መደለያ የመስጠት ድርጊቶች ማንኛውም ሰው በመንግሥት (በሕዝባዊ ድርጅት) ሥራ ላይ የሚፈጽሟቸው ወንጀሎች ናቸው።
በሶስተኛው የሙስና ወንጀሎች ዘውግ ውስጥ የሚመደበው አስታራቂ ሽማግሌዎችና ሌሎች ሰዎች የሚፈጽሙት ጉቦ የመቀበል ወንጀል ነው።አስታራቂ ሽማግሌ፣ የግልግል ዳኛ፣ ንብረት ጠባቂ ወይም ንብረት አጣሪ፤ ተርጓሚ፣ አስተርጓሚ፣ በዳኝነት ነክ በሚታይ ጉዳይ ላይ በሙያው ረገድ አስተያየቱን ወይም የምስክር ቃሉን የሚሰጥ ልዩ አዋቂ፣ ኦዲተር፣ አንድ ግንባታ በውል መሰረት መከናወኑን የሚያረጋግጥ መሐንዲስ ማድረግ የሚገባውን ላለማድረግ ወይም ማድረግ የማይገባውን ለማድረግ በሚል ወይም በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት ማድረግ የሚገባውን ተግባር ለማከናወን ሲል ከማከናወኑ በፊት ወይም ከፈጸመ በኋላ ጥቅም እንዲሰጠው የጠየቀ ወይም የተቀበለ ከሆነ በዚህ የሙስና ወንጀል ዘውግ ውስጥ ይመደባል።
በሥልጣን ያለአግባብ መገልገል ወንጀል
ከላይ ስለሙስና ወንጀሎች በተሰጠው ማብራሪያ እንደተገለጸው በሥልጣን ያለአግባብ መገልገል ወንጀል የመንግሥት ወይም የህዝባዊ ድርጅት ሠራተኞች በመንግሥት ሥራ ላይ በሚፈጽሟቸው የሙስና ወንጀሎች ሥር የሚመደብ ነው።የሙስና ወንጀሎች አዋጅ አንቀጽ 9 በሥልጣን ያለአግባብ መገልገል ወንጀልን በዝርዝር ደንግጓል።ከድንጋጌው ለመረዳት እንደሚቻለው ታዲያ በሥልጣን ያለአግባብ መገልገል ወንጀል በሶስት መልኩ የሚገለጹ አድራጎቶችን ያጠቃልላል።
ማንኛውም የመንግሥት (የሕዝባዊ ድርጅት) ሠራተኛ የማይገባ ጥቅም ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት ወይም በሌላ ሰው ጥቅም ወይም መብት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ለማድረግ በማሰብ፡- አንደኛ የተሰጠውን ሹመት፣ ሥልጣን ወይም ኃላፊነት በግልጽ ተግባር ወይም በግድፈት ያለአግባብ የተገለገለበት እንደሆነ፤ ሁለተኛ በግልጽ ከተሰጠው ሥልጣን ወይም ኃላፊነት አሳልፎ የሰራ እንደሆነ፤ ሶስተኛ ሥልጣኑ ወይም ኃላፊነቱ የማይፈቅድለትን ጉዳይ በተለይም ሥልጣን ወይም ኃላፊነት ሳይኖረው ወይም ከሥራው ከታገደ፣ ከተዛወረ፣ ከተሻረ ወይም ሥልጣኑን ወይም ኃላፊነቱን ከተወ በኋላ የሰራበት እንደሆነ በሥልጣን አለአግባብ መገልገል ወንጀል ይጠየቃል።
ከዚህ ድንጋጌ የተለያዩ ጉዳዮችን በዝርዝር መመልከት ተገቢ ነው።የመጀመሪያው “ሥልጣን” ሲባል ሹመት ወይም ከፍተኛ የኃላፊነት ወይም የመሪነት እርከን የሚል አንድምታ ብቻ የያዘ አለመሆኑን ነው።ከላይ የመንግሥት (የሕዝባዊ ድርጅት) ሠራተኛ የሚለውን ስናብራራ በመንግሥት መስሪያ ቤት (በሕዝባዊ ድርጅት) ውስጥ ተቀጥሮ፣ ተሹሞ፣ ተመድቦ፣በሕዝብ ወይም በአባላት ተመርጦ በቋሚነት ወይም በጊዜያዊነት የሚሰራ ሰው እንዲሁም የቦርድ አባል፣ የድርጅት መሪ፣የአክስዮን ማሕበር ወይም የበጎ አድራጎት ድርጅት የሚያደራጅ ሰው ወይም ኮሚቴ ሁሉ የመንግሥት ሠራተኛ እንደሚባል ተገንዝበናል።
ስለሆነም ሥልጣን የሚለው አገላለጽ ለሙስና ወንጀሎች አዋጅ አፈጻጸም ሲባል ሰፊ አንድምታ ያለው በመሆኑ በሥልጣን ያለአግባብ መገልገልም እንዲሁ የመንግሥት (የሕዝባዊ ድርጅት) ሠራተኛ በሚለው ማዕቀፍ ውስጥ የተጠቃለለ ሰው ሁሉ የሚፈጽመው በስልጣን የመባለግ አድራጎት ነው ማለት ነው።ዋና ዓላማውም የመንግሥት (የሕዝባዊ ድርጅት) ሠራተኞች ሕዝብና መንግሥት አምነው የሰጧቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም ማዋል ሲገባቸው ይህንን ወደ ጎን በማለት ሥልጣናቸውን አለአግባብ መጠቀሚያ፣ መጥቀሚያ እና መጉጃ መሳሪያ ሲያደርጉት ድርጊታቸውን ለማስቆምና በጥፋታቸው ለመቆንጠጥም ጭምር ነው።
በሥልጣን ያለአግባብ የመገልገል ወንጀል የሚፈጸመው የማይገባ ጥቅም ለራስ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት ወይም በሌላ ሰው ጥቅም ወይም መብት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ለማድረግ በማሰብ በመሆኑ “ጥቅም ወይም መብት” በሚል የተገለጸው ጉዳይ ሌላው መሰረታዊ ነጥብ ነው።አዋጁ “ጥቅም” የሚለው አገላለጽ የሚያካትታቸውን ነገሮች በዝርዝር አስቀምጧል።
ጥቅም ሲባል በገንዘብ ወይም በማናቸውም ዋጋ ባለው መያዣ ወይም በሌላ ንብረት ወይም በንብረት ላይ ያለን መብት ያጠቃልላል።ከዚህ ሌላ ጥቅም ማንኛውንም ሹመት፣ ቅጥር ወይም ውል፤ ብድር፣ ግዴታን ወይም ማናቸውንም ዕዳ በሙሉም ሆነ በከፊል መክፈልን፣ ማስቀረትን፣ ማወራረድን ወይም ነጻ ማድረግንም ያካትታል።በተጨማሪም ከተመሰረተ የአስተዳደር፣ የፍትሐብሔር ወይም የወንጀል ክስ ወይም ቅጣት በማዳን የሚደረግ አገልግሎት ወይም ውለታ እንዲሁም ማናቸውንም መብት ወይም ግዴታ መፈጸም ወይም ከመፈጸም መታቀብም ጥቅም ነው።በገንዘብ የማይተመን ማናቸውም ሌላ ጥቅም ወይም አገልግሎት እንዲሁም ጥቅሞቹ የሚገኙበትን መንገድ ማመቻቸት፣ የተስፋ ቃል መግባት ወይም መቀበል ሁሉ ጥቅም ተደርጎ እንደሚወሰድም ነው ሕጉ የሚያስቀምጠው።
በሕጉ ውስጥ “መብት” የሚለው ጉዳይ በግልጽ ትርጓሜ አልተሰጠውም።በተለይም ድንጋ ጌው በሥልጣን ያለአግባብ የመገልገል ወንጀል የሚፈጸመው በሌላ ሰው ጥቅም ወይም መብት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ለማድረግ በማሰብ በመሆኑና በአዋጁ ውስጥ ደግሞ “ጥቅም” የሚለው ቃል በዝርዝር ትርጓሜ ተሰጥቶት ሳለ “መብት” የሚለው ግን ለአዋጁ አፈጻጸም ሲባል ትርጓሜ ያልተሰጠው መሆኑ የሕጉ ዓይነተኛ ክፍተት ነው።በዚህ መነሻ አንድ የመንግሥት (የሕዝባዊ ድርጅት) ሰራተኛ በሌላ ሰው መብት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ለማድረግ በማሰብ ሥልጣኑን ባልተገባ መልኩ ተገልግሎ የመብት ጉዳት አድርሷል በሚል በሥልጣን ያለአግባብ መገልገል ወንጀል ተጠያቂ ለማድረግ “መብት” የሚለውን በአግባቡ መተርጎም ያስፈልጋል ማለት ነው።
ከድንጋጌው መረዳት እንደሚቻለው ሥልጣንን ያለአግባብ የመገልገል ወንጀል የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት (“… with intent to obtain for himself or to procure for another an undue advantage…”) ብቻ ሳይሆን በሌላ ሰው መብት ላይም ጉዳት ለማድረስ በማሰብም ጭምር (“… (with intent) to injure the right of another”) ሊፈጸም እንደሚችል ነው።ለዚህም ነው ድንጋጌው የሃሳብ ክፍል ማቋቋሚያውን “ወይም” በሚለው አያያዥ በመጠቀም ሥልጣንን ያለአግባብ መገልገል ወንጀል የሚፈጸመው ጥቅም ማግኘት ወይም ማስገኘት ወይም በሌላ ሰው መብት ላይ ጉዳት ማድረስን በማሰብ እንደሆነ በግልጽ ያመለከተው።
ስለሆነም መብት ማለት ምንድን ነው የሚለውን ማየት ጉዳዩን በግልጽ ለመረዳት ይጠቅማል።የህግ ቃላትን ለመተርጎም የዓለም ቁጥር አንድ መዝገብ ቃላት የሆነው ብላክስ ሎው መዝገበ ቃላት መብት (right)ን ሲተረጉም (a recognized and protected interest the violation of which is a wrong) በሚል አስቀምጦታል።ከሰብዓዊ መብቶች ዓለም ዓቀፍ ድንጋጌ፣ ከሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን እና ከኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና የባህል መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን ድንጋጌዎች መረዳት እንደሚቻለው ደግሞ መብት ሲባል ሰብዓዊ መብትንም እንደሚያጠቃልል እንዲሁም ሰብዓዊ መብት ሲባል ሰዎች ሰው ሆነው በመፈጠራቸው ከተጎናጸፉትና አብሯቸው ከተፈጠረ ክብር የሚመነጭ የተፈጥሮ ጸጋ መሆኑን ነው።በመሆኑም ልክ እንደ ጥቅም ሁሉ መብትን ለመጉዳት በማሰብም ጭምር ሥልጣንን ያለአግባብ መገልገል ወንጀል ይፈጸማል ማለት ነው።
ድንጋጌው ቀላል፣ ከባድና በጣም ከባድ ቅጣቶችን የሚያስከትል ሆኖ ነው የተቀረጸው።በአንቀጽ 9 (1) እንደተመለከተው በሥልጣን ያለአግባብ የመገልገል አድራጎቱ የተፈጸመው ወይም ኃላፊነቱ እንዲጣስ የተፈለገበት ዓላማ፤ የተገኘው ጥቅም፤ የጥፋተኛው የኃላፊነት ወይም የሥልጣን ደረጃ፤ በግለሰብ፣ በመንግሥት ወይም በሕዝባዊ ድርጅት ጥቅም ወይም በሕዝብ ላይ የደረሰው ጉዳት ሲመዘን የተፈጸመውን ወንጀል ቀላል አድርጎት ከሆነ የሚያስከትለውም ቅጣት በአንጻራዊነት ቀላል ይሆናል።
ይኸውም ቅጣቱ ከአንድ ዓመት የማያንስ ቀላል እስራት እና ከሶስት ሺ ብር የማይበልጥ መቀጮ ወይም እንደነገሩ ሁኔታ ከአሥር ዓመት የማይበልጥ ጽኑ እስራት እና ከአስር ሺ ብር የማይበልጥ መቀጮ ይሆናል ማለት ነው።በዚህ ንዑስ አንቀጽ የተከሰሰ ሰው ታዲያ በተሻሻለው የጸረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ አዋጅ መሰረት ከአሥር ዓመት በታች በሚያስቀጣ ወንጀል የተከሰሰ በመሆኑ የዋስትና መብቱ ይከበርለታል።
የሙስና ወንጀሎች አዋጁ አንቀጽ 9 (2) ደግሞ በሥልጣን ያለአግባብ የመገልገል ወንጀሉ ከ7 እስከ 15 ዓመት ጽኑ እስራት እና ከአስር ሺ እስከ መቶ ሺ ብር በሚደርስ መቀጮ የሚያስቀጣበትን ከባድ ሁኔታ አስቀምጧል።በዚሁ መሰረት ኃላፊነቱ ወይም ግዴታው እንዲጣስ የተፈለገበት ዓላማ ከባድነት፤ የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት፤ የጥፋተኛው የኃላፊነት ወይም የሥልጣን ደረጃ፤ በግለሰብ፣ በመንግሥት ወይም በሕዝባዊ ድርጅት ጥቅም ወይም በሕዝብ ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛነት የተፈጸመውን ወንጀል ከባድ አድርጎት ከሆነ ቅጣቱ በተገለጸው መልኩ ከባድ ይሆናል ማለት ነው።
እዚህ ላይ ግንዛቤ ሊያዝበት የሚገባው ነጥብ አንድ ሰው በዚህ ንዑስ አንቀጽ ሊከሰስ የሚችለው የወንጀሉን ሁኔታ ለመመዘን ከተዘረዘሩት ከእነዚህ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ተሟልቶ ከተገኘ ነው።ለምሳሌ በየትኛውም የኃላፊነት እርከን ላይ የሚገኝ ሠራተኛ በሥልጣኑ ያለአግባብ ተገልግሎ በፈጸመው ድርጊት በሚሊዮኖች የሚቆጠር የሕዝብና የመንግሥት ሃብት ጠፍቶ ወይም ባክኖ ከሆነ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ በዚህ ንዑስ አንቀጽ ስር ይከሰሳል ማለት ነው።የዋስትና መብቱም ይነፈጋል።(ቀላልነት እና ከባድነት የሚለው በምን ይለካል የሚለው ጉዳይ ግን በሕጉ ያልተቀመጠ በመሆኑ ዓቃቤ ሕግ እና ፍርድ ቤቶች ከተለያዩ ሁኔታዎች አንጻር በመመዘን ክብደትና ቅለቱን ይወስናሉ)
የመጨረሻውና ከባድ ቅጣትን የሚያስከትለው በሥልጣን ያለአግባብ የመገልገል ወንጀል ደግሞ በአዋጁ አንቀጽ 9 (3) የተመለከተው ነው።በዚሁ መሰረት ከላይ የወንጀሉን ሁኔታ ለመመዘን ከተዘረዘሩት ምክንያቶች ውስጥ ሁለቱ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑት ተሟልተው ከተገኙ ሠራተኛው ከባድ ቅጣት በሚያስከትለው በዚሁ ንዑስ አንቀጽ ይከሰሳል።ቅጣቱም ከ10 እስከ 25 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራትና ከ20ሺ ብር እስከ 200 ሺ ብር የሚደርስ መቀጮ ይሆናል ማለት ነው።ለምሳሌ የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ሌሎች ሚኒስትሮች፣ ኮሚሽነሮች፣ ሥራ አስፈጻሚዎች/ሥራ አስኪያጆች፣ የፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶችና ዳኞች ወዘተ ከፍተኛ መጠን ያለው ሃብት ቢመዘብሩ ወይም ከፍተኛ ጉዳት ቢያደርሱ፤ ሥልጣናቸውን ያለአግባብ የተገለገሉት በሕዝብ ጤና፣ ሰላምና ደህንነት ላይ ጉዳት የማድረስ ዓላማን ይዘው ከሆነ በዚህ ንዑስ አንቀጽ ሥር ይጠየቃሉ።የዋስትና መብታቸውንም ይነፈጋሉ።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሀሴ 15/2011
ከገብረክርስቶስ