የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባን አዲስ አበባ ለማስተናገድ ደፋ ቀና በምትልበት አንድ ጀምበር እንዲህ ሆነ። በአዲስ አበባ ስታዲየም አካባቢ የሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪዎች ተለቅመው የቀድሞ ታጠቅ ጦር ሰፈር ተወሰዱ። እዚያም ተረጋግተው እንዲቀመጡ ተነገራቸው። ብዙ ቃልም ተገባላቸው። ልጆቹ ግን ድርጊቱ አስቆጥቷቸው ስለነበር የተባለውን አልተቀበሉትም። ሰዎቹ ዞር ሲሉላቸው ጠብቀው ለሊቱን በእግር ተጉዘው ሊነጋጋ ሲል ስታዲየም የተለመደ ቦታቸውጋ ተገኙ። ይህን አሳዛኝ ክስተት ልጆቹን አናግራ የዘገበችው በአንድ ወቅት የቢቢሲ የአዲስ አበባ ወኪል የነበረች ጋዜጠኛ ነበረች።
አዎ!.. መሰል ሙከራዎች ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ ተደርገዋል። ጨቋኙ ደርግ ሳይቀር የጎዳና ተዳዳሪዎችን፣ ሴተኛ አዳሪዎችን እየለቀመ ጥጥ ለቀማ ይልካቸው ነበር። ይህ እርምጃ ያው በጨዋ ደንብ ሲነገር “እዚህ ሆናችሁ ገጽታችንን አታበላሹ፣ ሰርታችሁ ብሉ” ዓይነት ውስጠ ወይራ መልዕክት ያዘለ ነው። በአንድ ወቅትም በአዲስ አበባ ሳሪስ አካባቢ የሚገኘው አደይ አበባ ፋብሪካ ውስጥ ሴተኛ አዳሪ ሴቶች እንዲቀጠሩ ሁኔታዎችን አመቻችቶም ነበር። በዚህ ሒደት የተጠቀሙ ጥቂት ወገኖች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገመታል። ግን ለጎዳና ተዳዳሪነትና ለሴተኛ አዳሪነት የሚያበቃው ማህበራዊ ችግር ከመሠረቱ አልተፈታምና እርምጃው የሚታይ የሚዳሰስ ሰፊ ውጤት ሳያመጣ ከሽፏል።
ባለፈው ወር ማጠናቀቂያ ሳምንት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ባካሄደው ስብሰባ በከተማዋ ያለውን የጎዳና ላይ ልመናና የወሲብ ንግድን በዘላቂነት ለመከላከል በተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት አድርጓል። ካቢኔው በቀረበው ረቂቅ ላይ ውይይት አድርጎ በአጀንዳው ላይ የተሻለ ግብዓት ለማግኘት ሲባል በጉዳዩ ላይ የሃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሰፊ ውይይት እንዲያደርጉበት መወሰኑ ተሰምቷል።
ይህን ተከትሎ የከንቲባው ጽ/ቤት ቃል አቀባይ የሆኑት ወ/ት ፌቨን ተሾመ ከፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ጋር አድርገውታል የተባለው ቃለ ምልልስ አነጋጋሪ ነበር። እርሳቸው እንዲህ ማለታቸው ተሰምቷል።
በአዲስ አበባ ከተማ በውስጧ የያዘቻቸው የእኔ ቢጤዎችን በሚመጸውቱና በሴተኛ አዳሪዎች ደንበኞች ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል የህግ ረቂቅ እየተዘጋጀ መሆኑን የሚጠቁም ይዘት ያለው ነው። አስተዳደሩ እንግዲህ ዓሳውን ለመያዝ ባህሩን የማድረቅ እርምጃ ስለማሰቡ ዕቅዱ ፍንጭ ይሰጣል።
በአስተዳደሩ የከንቲባው ጽ/ቤት ቃል አቀባይ በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው የአገሪቱንና የከተማዋን መልካም ገጽታን የሚያበላሹት ከ50 ሺህ በላይ የእኔ ቢጤዎችና 10 ሺህ የሚገመቱ ሴተኛ አዳሪዎች ከከተማው ጎዳናዎች የማንሳት እርምጃ ሊተገበር መቃረቡን ጠቁመዋል።
ረቂቅ ህጉ ሲጸድቅና ተግባራዊ ሲሆን “በ ጎዳና ላይ ሴተኛ አዳሪነት ስራ የተሰማሩ እህቶች ሆኑ ደንበኞቻቸውም በገንዘብ እና በእስራት ይቀጣሉ፣ በልመና ስራ ላይ ለተሰማሩት የእኔ ቢጤዎች እጆቻቸውን የሚዘረጉ መጽዋቾችም እንዲሁ ቅጣት ይፈጸምባቸዋል” ሲሉ አስታውቀዋል። ቃል አቀባይዋ የቅጣቱ መጠንና የእስራቱ እርዝማኔ ምን ያህል እንደሚሆን ለጊዜው አልገለጹም።
ለእነዚህ ጎስቋላ የመዲናይቷ ነዋሪዎች ለሆኑት የጎዳና ላይ ሴተኛ አዳሪዎችና የእኔ ቢጤዎች ተመጣጣኝ የስራ እድል ለመፍጠር ጥረት እንደሚደረግ ወ/ት ፌቨን ተሾመ ጨምረው ገልጸዋል። አብዛኞቹ የኔብጤዎች ከተሰማሩበት የልመና ስራ በወር በአማካኝ ሰባት ሺህ ብር ወይም ሁለት መቶ ዶላር ስለሚያገኙ፣ ሴተኛ አዳሪዎቹም እንዲሁ ሞቅ ያለ ገንዘብ ስለሚያገኙ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከመዲናይቱ ጎዳናዎች ላይ ሙሉ በሙሉ ማስወገድ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል። ከተማው ውስጥ ከሚገኙት የጎዳና ላይ ሴተኛ አዳሪዎችና የጎዳና ተዳዳሪዎች ውስጥ 92 በመቶ ከሌላ ክልሎችና ከተሞች የመጡ መሆናቸውን የከንቲባው ጽ/ቤት ያስጠናው መረጃ ያስረዳል።
የጎዳና ልጆችን የማቋቋሙ ሙከራ
በአዲስ አበባ የጎዳና ላይ ነዋሪዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የማህበራዊ ትረስት ፈንድ ተቋቁሟል። ፈንዱ እስከ አሁን ከሦስት ሺ 147 በላይ ነዋሪዎች ከጎዳና ላይ በማንሳትና ሕይወታቸውን መቀየር፣ ፍላጎቱ ያላቸውን ከቤተሰቦቻቸው ጋር የማገናኘት ሥራዎችን እንዳከናወነ ይነገርለታል።
የሥራ አጥነት ማህበራዊ ችግርንም ከመሠረቱ ለመፍታት የከተማው አስተዳደር የሁለት ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ እንዲመደብና ወደሥራ እንዲገባ ሆኗል።
የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከከተሞች የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ጋር በመተባበር እ.ኤ.አ በ2018 ጀምሮ በ11 ከተሞች ባስጠናው ጥናት በአስከፊ የኑሮ ሁኔታ በጎዳና ላይ ህይወታቸውን የሚመሩ 88 ሺህ 960 ዜጎች እንዳሉ የሚያሳይ ጥናት በቅርቡ ይፋ አድርጓል። ከዚህ ውስጥ 50 ሺህ 820 ያህሉ በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
እነዚህም በጎዳና ላይ በወሲብ ንግድ ህይወታቸውን የሚመሩ፣ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው አረጋዊያን፣ አካል ጉዳተኞችና ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው።
የጎዳና ተዳዳሪዎችን ከመንገድ ለማንሳትና ሴተኛ አዳሪ ወገኖችን ለመደገፍ ራሱን የቻለ የድጋፍ ማሰባሰብ ፕሮግራም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየተከናወነ ይገኛል። በቅርቡም ከሦስት ሺ በላይ የጎዳና ተዳዳሪዎች ወደ ማገገሚያ ማዕከላት ገብተዋል።
በሌላ በኩልም በአዲስ አበባ ከተማ በሺዎች የሚቆጠሩ ጎዳና ተዳዳሪዎች የህክምና ሽፋን እንዲገኙም ተደርጓል። ልጆቹ ሕክምና ባለማግኘታቸው ምክንያት በቀላሉ ሊታከሙ ለሚችሉና ለከባድ በሽታዎች ሲጋለጡ ይስተዋላል።
ይህን ችግር ለመቅረፍም እንደሌሎች ታካሚዎች መታወቂያና የቤት ቁጥር ሳይጠየቁ የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበት ፕሮጀክት መጀመሩን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የህክምና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የአዲስ አበባ ሆስፒታሎች ድጋፍ ኬዝቲም አስተባባሪ አቶ ያዕቆብ ሰማን ተናግረዋል።
አገልግሎቱ በአዲስ አበባ በአስሩም ክፍለ ከተሞች በሚገኙና ጎዳና ተዳዳሪዎች በሚዘዋወሩባቸው አካባቢ ባሉ በተመረጡ ጤና ጣቢያዎች ይሰጣል።
የጎዳና ተዳዳሪዎች ሕይወት ከጊዜ ወደ ጊዜ መፍትሄ ያልተገኘለት ችግር ሆኗል። ሥራዎች ቢሰሩም ዛሬም ስር ነቀል እልባት ላይ አልተደረሰም እየተባለ ነው። በኢትዮጵያ አስራ አንድ ከተሞች ካሉት ከ88 ሺ በላይ ጎዳና ተዳዳሪዎች ውስጥ 50 ሺ ያህሉ በዋና ከተማዋ መዲና ጎዳናዎች ይኖራሉ። ብሔራዊ ቴአትር፣ ሜክሲኮ፣ ኮሜርስ፣ መስቀል አደባባይ፣ ፒያሳ አካባቢ ከሌላው በተለየ በጎዳና የእለት ክስተት መኪኖች የትራፊክ መብራት በያዛቸው ዘንድ ልመና አልያም መስታወት ጠርገው ብር የሚጠይቁ የጎዳና ልጆችን ይመለክታሉ። እነዚህን አዳጊዎች ከጎዳና ህይወት ለማውጣት ስራዎች ቢሰሩም ውሀ ቅዳ ውሀ መልስ ሆኖብናል ሲሉ በስራው የተሰማሩ አካላት ይናገራሉ። ወደ ጎዳና ህይወት መልሶ መግባታቸው “ችግሩ ከስሩ ባለመቀረፉ ምክንያት ነው”ይላሉ። ለጎዳና ህይወት ተጋላጭ ከሆኑት የህብረተሰብ ክፍል ወጣቶች ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዙ አቶ እንደሻው አበራ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማህበራዊ ችግር ተረጂዎች መልሶ ማቋቋም ዳይሬክተር ይገልጻሉ። “ለጎዳና ህይወት ተጋላጭ የሆኑት የህብረተሰብ አምራቹ ክፍል በተለይም እድሜያቸው ከ15 እስከ 29 ክልል ያሉት ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ። “
ተግዳሮቶች
የአዲስ አበባ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በመልሶ ማቋቋም ካሰለጠናቸው የጎዳና ተዳዳሪዎች ውስጥ ከ500 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች ወደ ሥራ ለመግባት የቀረበልን ደመወዝ ዝቅተኛ ነው በማለት ያለሥራ በካምፕ ውስጥ መቀመጣቸውን በቅርቡ ማስታወቁ የሚታወስ ነው።
ተማሪዎቹ ሰልጥነው ወደ ሥራ ሲገቡ በዝቅተኛው ደሞዝ ማለትም በአንድ ሺሕ 700 ብር የሚቀጠሩ ከሆነ በኮካ ኮላ የመጠጥ ፋብሪካ የሚከፈል ሰባት መቶ ብር የቤት ኪራይ ለሰባት ወር ቢዘጋጅም ፈቃደኛ ያለመሆናቸው ተገልጿል።
ዳይሬይክተሩ እንደሻው አበራ በመልሶ ማቋቋም ከሰለጠኑ 966 ተማሪዎች ውስጥ 225ቱ በሥራ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል። በተለያዩ የሥራ መስኮች ከተቀጠሩት ሠልጣኞች ውስጥም ከአንድ ሺሕ 700 ብር እስከ 11 ሺሕ ብር ደሞዝ በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ ያስቀጠረ ሲሆን፤ ሥራ ካላገኙ ተማሪዎች በተጨማሪ በዝቅተኛ ደሞዝ ሥራ መጀመር አንችልም ብለው ያለ ሥራ የተቀመጡ ተማሪዎችም እንዳሉ አስታውቀዋል።
የተቀሩት ተማሪዎችም የሥራ ዕድል እስከሚገኝላቸው ድረስ ሙሉ ወጪያቸው እየተሸፈነላቸው መሆኑን የገለፁት ኃላፊው “አንዳንድ ተማሪዎች በዝቅተኛ ደሞዝ ሥራ መጀመር አንችልም በማለት ውዝግብ ቢፈጥሩም ምንም ዓይነት የተለየ ድጋፍ ሊደረግላቸው አይችልም” ብለዋል።
በቆዳ ሥራ፣ በብረታ ብረትና በእንጨት ሥራ ላይ ከሚሰለጥኑ ተማሪዎች ውጪ በልብስ ስፌት፣ በቆዳ ሥራ፣ በወለል ንጣፍ፣ በጂፕሰም ሥራ፣ በቀለም ቅብ፣ በብረታ ብረት ሥራ፣ በእንጨት ሥራና መንጃ ፍቃድ በማውጣት ለሥራ የሰለጠኑ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አጠናቅቀዋል።
የጎዳና ልጆችን ወደ ሥራ በማስገባት እንቅስቃሴ ውስጥ ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ጋር በመተባበር በልዩ ድጋፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ውስጥ ሥልጠናውን ጨርሰው የሥራ ዕድል የተመቻቸላቸው ወጣቶቹ፣ በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን፣ አዲስ አበባ ቄራ ሥራዎች ድርጅት፣ ኮካ ኮላ ኢስት አፍሪካ ግሩፕና አጋር የጥበቃ ሥራዎች ድርጅት ውስጥ እንዲቀጠሩ መደረጉን ጨምረው ገልጸዋል።
ልጆቹ በአስከፊው የጎዳና ሕይወታቸው ሰርተው ወይንም በወሲብ ንግድ ከሚገኙት ገቢ ጋር ፈጽሞ የማይቀራረብ ክፍያ በስመ ማቋቋም መስጠቱ ላለመግባባቱ አንድ መነሻ ተደርጎ ይወሰዳል። የተሻለና ሊያኖር የሚያስችል ገቢ በሌለበት ሁኔታ ከጎዳና ሕይወት ለማላቀቅ ሲባል ብቻ ስልጠና መስጠቱና በአነስተኛ ክፍያ ስራ ማመቻቸቱ ወጣቶቹ ሕይወታቸውን እንዲቀይሩ የሚያደፋፍር አለመሆኑ እየታየ ነው።
እንደማሳረጊያ
የጎዳና ሕይወትና የሴተኛ አዳሪነት ሕይወት አስከፊነቱ በቃላት ብቻ የሚገለጽ አይደለም። አንዳንድ ወገኖች ሁለቱ የአንድ ሳንቲም ግልባጮች መሆናቸውን ያስረዳሉ። በአብዛኛው በድህነትና በማህበራዊ ችግሮች መክፋት ጋር ተያይዞ ወጣቶችና ሕጻናት የጎዳና ሕይወትን ተገደው ይቀበላሉ። አንዳንዶች የዋጋ ንረት እየገፋ ሲመጣ ገቢና ወጪያቸው አልጣጣም ሲል የዕለት ወጪያቸውን መሸፈን የማይችሉበት የከፋ ደረጃ ያደርሳቸዋል። በዚህም ጎዳናን እንደመጨረሻ አማራጭ እንዲያዩ የሚገደዱ ቤተሰቦች ብዙ ናቸው። ለዚህም ነው አንዳንድ ጊዜ ለልመና ጭምር ባል፣ ሚስትና ልጆች ጎዳና ወጥተው የምናየው። ከእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል በተለይ ጥቂት የማይባሉት ሴቶች ከመጥፎ የተሻለውን መጥፎ ወደመምረጥ ይገባሉ። ጎዳና ላይ ከማደርና የከፋ ሕይወት ከመግፋት ይሻላል በሚል የሴተኛ አዳሪነት ሕይወትን የሚመርጡ አሉ።
በጎዳና ላይ የቀሩትም ቢሆን ወደውም ይሁን ተገድደው ይህንኑ የሴተኛ አዳሪነት ሕይወት ይጋፈጣሉ። ሴቶች የመደፈር አደጋ ስለሚገጥማቸው ላልተፈለገ እርግዝና ጭምር ተጋልጠው በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ለተደራራቢ ማህበራዊ ቀውስ ይዳረጋሉ። እዚህ ላይ በቀላሉ የሚዛቅ ገንዘብ በመሸታ ቤቶች አካባቢ መኖር በራሱ ወጣቶችን ወደሴተኛ አዳሪነት እንዲገፋፉ በር ይከፍታል። ይህ በቀላሉ የሚገኝ ገንዘብ ምንጩ በአመዛኙ ከሙስናና አላግባብ በሥልጣን የመጠቀምና የመበልጸግ የሥነምግባር ዝቅጠት ውጤት ጋር የተያያዘ መሆኑ ደግሞ ሲታሰብ የፖለቲካ ሙስናው የዜጎችን ማህበራዊ ሕይወትን ጭምር ሊጠገን በማይችል መልኩ እየበከለ መሆኑን ለመረዳት ያስችላል።
ይህ ማህበራዊ ቀውስ የማንሸሽገው ቁስላችን ነው። ከምንም በላይ የሚያሳዝነው ችግሩ ዕለት በዕለት እየሰፋና ወደጎዳና የሚወጣውም ሰው ቁጥር እየጨመረ የመምጣቱ ነገር ነው። ይህን ግዙፍ ማህበራዊ ቀውስ ለመግታት ሰጪን መቅጣትና የጎዳና ተዳዳሪዎችን ከጎዳና ላይ ማንሳት ብቻውን መፍትሔ አይሆንም። ይህ እርምጃ ችግሩን የማስታገስ አቅም እንኳን ይኑረው ወይም አይኑረው በውል የሚታወቅ ነገርም የለም። ከዚህ ይልቅ ተመራጩ የዜጎችን ማህበራዊ ሕይወት የሚለውጡ ፕሮጀክቶች በስፋት መጀመርና የልመናን፣ የሴተኛ አዳሪነትን ሕይወት አስከፊነት ቀጣይነት ባለው መልኩ ማስተማር ይሆናል።
ለራበው ሰው ምግብ ማቅረብ ሳይቻል በደፈናው “አትለምን፣ ሴተኛ አዳሪነትን ተጠየፍ..”ማለቱና ይህንንም በህግ ለማሰር ማቀዱ ከፈረሱ ጋሪውን ማስቀደም እንዳይሆን መጠንቀቅ ይበጃል። እናም ከሁሉ በፊት ስለተከማቹት ማህበራዊ ችግሮቻችን በዘላቂነት ስለሚፈቱበት መንገድ ማሰብ፣ ማቀድና መጨነቅ ብልህነት ይሆናል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሀሴ 15/2011
ፍሬው አበበ