ለ43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሩጫ አሸናፊዎች በቤተ-መንግሥት በተዘጋጀ 44ኛው (በአንድ ዓመት ውስጥ መሆኑ ነው) የእራት ግብዣ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ አሉ፡-
“አሁን አሁን በአገሪቱ በሚከሰተው የጸጥታና ተያያዥ ችግር ሣምንትን ያለ ክፉ ዜና ማለፍ እየከበደ መጥቷል። ችግሮችን ባሉበት ለማቆምና እንዳይዛመቱ ለማስቻል ቀና ማሰብ ስለሚያስፈልግ በመጪው እሁድ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች የጽዳት ዘመቻ ይደረጋል። ይህም መጥፎ ስሜትን በመልካም ስሜት ለመተካትና መልካም ለማሰብ የሚያስችል ዘመቻ ነው። የጽዳት ዘመቻው ያስፈለገው ቆሻሻን ከአካባቢ መጥረግ እንደሚገባ ሁሉ ከአእምሮም መጥፎና ክፉ ሃሳብን በመጥረግ በመልካም አስተሳሰብ መተካት እንደሚገባ እገረ-መንገዱን ለማስተማር ነው። በተለይም ቋንቋን መሰረት ያደረጉ ልዩነቶች በሕብር ውስጥ ያሉ ጌጦች እንጂ የመለያያ ነጥቦች መሆን የለባቸውም።”
ይህን ንግግር ተከትሎ እሁድ ጠዋት በርካታ ነዋሪዎች በየመንደሩ መጥረጊያ ይዘው ወጡ፡፡ ጥያቄ ላቀረቡላቸው ልማታዊ ሚዲያዎችም እንደ በቀቀን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉትን ሲያስተጋቡ አረፈዱ፡፡ አንዳንዶችም ‹‹ዘረኝነትን እጠየፋለሁ!›› እና ‹‹ከተማዬን አፀዳለሁ!›› የሚሉ መፈክሮችን መሳ ለመሳ አንግበው አየን፡፡
ሁኔታው እንደ እኔ ላለ ሰው ጥያቄ ያጭራል፡፡ ሁለት ግዙፍ ጉዳዮችን አንስቶ አንዱን በሌላኛው ላይ ማስታከክን ምን አመጣው ? አንደኛውን ሌላኛው ላይ መለጠፍ ግድ ቢሆን እንኳን የአገሪቱ ጊዜ አይሰጤ ችግር የቱ ነው ? … ከማስታከክ ልማዳችን ካልተላቀቅን ዕድሜ ልካችንን ስናክ እንደምንኖር የሚነግረን ነብይ አያስፈልገንም፡፡
ዘረኝነትን ከአካባቢ ጽዳት ጋር ማቆራኘት የጉዳዩን ክብደት አለመረዳት አሊያም ሆነ ብሎ ማቅለል ነው፡፡ ለአመታት በተሰራ ስራ ልቦና ውስጥ የከረመን ጥላቻ በአንድ ጀምበር አሽቀንጥሮ መጣል እንደሚለፈፈው ቀላል አይደለም፡፡ እንኳን በብዙዎች አእምሮ ውስጥ የታተመው ዘረኝነት ፣ ማንጸሪያ ሆኖ የቀረበው ቆሻሻ ከነአካቴው እንዲወገድ ከተፈለገ ብቻውን እንደ አንድ ትልቅ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ተቆጥሮ ተቋማዊ የሆነ የማያቋርጥ ስራ ሊሰራበት ይገባል፡፡
እንዲህ ያለ መልዕክት ከሃይማኖት አባት እንጂ አገር የመምራት ዕድል ከገጠመው ፖለቲከኛ አይጠበቅም፡፡ ችግሮችን ባሉበት ለማቆምም ሆነ እንዳይዛመቱ ለማድረግ መፍትሔው የህግ የበላይነትን ማስከበር ነው፡ ፡ በአንድ እጅ ህገ መንግስት በሌላ እጅ ደግሞ የሃይማኖት መጽሐፍ ይዞ አገር ማስተዳደር የሚቻለው ሳታይር ኮመዲ ቲአተር ላይ ነው፡፡ ክላሽ ተሸክመን እንዋጋለን ያለ መሪ መጥረጊያ ይዞ ማውጋት የለበትም፡፡
11 ተጫዋቾችን ይዞ ወደ ሜዳ የገባን ቡድን ማሸነፍ የሚቻለው የተሻለ ብቃት ያላቸው 11 ተጫዋቾችን በማሰለፍ እንጂ ደጋፊዎች ስታዲየሙን እንዲያጸዱ በማድረግ አይደለም፡፡ ጽንፈኝነትን በሜዳው ካልተፋለምን ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ይሆናል ነገሩ፡፡ ለሆድ ህመም እግር አይታሽማ!
እግረ መንገድ በሚሰራ ስራ ትርምስ ለመፍጠር እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩ ኃይሎችን ማቆም አይቻልም፡፡ የጽንፈኞች ፖለቲካ ሌላውን በመጥላትና በማግለል ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ሰልፋቸውን ያልተቀላቀለ “ባንዳ” ላይ እንኳን ለመጨከን አያመነቱም፡፡
መንግስት አገር አርጅቶ ያፈራቸውን ጃርቶች የፈራ ይመስላል፡፡ “ትዕግስት” የተባለ ማደንዘዣ ተወግቶ ስለመደመር እያወራ ፣ በጽንፈኞች ሰይፍ በየዕለቱ የሚቀነሱትን ዜጎች ቸል ብሏል፡፡ ጽንፈኛ ግለሰቦችና ቡድኖችም መንግስት ማስታመም ይሻለኛል ብሎ የሚያዜመውን የእሹሩሩ እንጉርጉሮ እንደ ማጀቢያ ሙዚቃ ተጠቅመው እንደልባቸው ፈንጭተዋል፡፡
የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲባል ትናንሽ መንግስታትን በይፋ ለማውገዝ ባለመድፈር ጽንፈኝነትን ህዝብ እንደሚምገው ከባቢ አየር እየቆጠሩ ባለቤት አልባ ማድረግ ለግዙፉ ችግር የዕድሜ ማራዘሚያ መድኃኒት መስጠት ነው፡፡
የመንግስት “መለኮታዊ” ትዕግስት የልብ ልብ ሰጥቷቸው ራሳቸውን አብዮተኛ ብለው እስከ መጥራት የደረሱ ጽንፈኞች አሉ፡፡ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር አብዮት ሁለት መልኮች አሉት ይላል፡፡ የመጀመሪያው ለአንድ ስርዓት ወይም አገዛዝ እንቢኝ አሻፈረኝ ማለት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ጀርባ የሰጡትን አገዛዝ የሚጻረር አዲስ ስርዓት ማስፈን ነው፡፡ በዚህ መሰረት የመጀመሪያው አብዮተኛ ሰይጣን ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች ከሚፈጽሙት ሰይጣናዊ ድርጊት አንጻር ለራሳቸው የሰጡት ስም አይበዛባቸውም፡፡
አንድ የአገር መሪ ቁልፍ ችግሮችን አሰልፎ ለበጎ ፍቃድ ተግባራት መሰለፍ የለበትም፡፡ መጥረጊያ ቆሻሻን እንጂ ግጭትን፣ የኑሮ ውድነትን ፣ የመኖሪያ ቤት ችግርንና ስራ አጥነትን ጠራርጎ አያስወግድም:: በንግግር ብቻ መራር እውነታዎችን ከማሽሞንሞን ተቆጥቦ ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል፡፡
በሳምንት ውስጥ ያሉት ቀናት ሰባት ቢሆኑም ፎቶ ጄኒኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ከ10 ጊዜ በላይ በቲቪ ከች እያሉ ጊዜን ደጋግመው በመቅደም ሌላ ሽልማት ለማግኘት መንደርደራቸውን ልብ ስል ወርሃዊ የጽዳት ዘመቻውም የዚሁ አካል እየመሰለኝ ለድካማቸው ዕውቅና ለመስጠት አመነታለሁ፡፡
ጠዋት ሱዳኖችን ሲያስታርቁ ፤ ቀትር ላይ እስረኛ ሲያስለቅቁ ፤ ከሰዓት አቅመ ደካሞችን ሲጠይቁ አመሻሹን ደግሞ ለለውጡ እንቅፋት የሆኑ ኃይሎችን ሲያስጠነቅቁ ፣ ቀኑ ማለቁ አዲስ አይደለም፡፡ እንደውም አሁን አሁን አንድ ቀን ድምጻቸው ከጠፋ “ዛሬ በቲቪ አላየኋቸውም… መሪዬ ምን ሆኑ ?” እያለ ጭንቅ ጥብብ ባዩ ጥቂት አይደለም፡፡
አንዳንዴ እንደውም የአሁኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ሁኔታ ሳይ “ታላቁ መሪ” በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ የሚሉት እንደ መስቀል ወፍ በአመት አንድ ጊዜ እንደ ነበር ትዝ እያለኝ … ጡረታ ላይ ነበሩ እንዴ ስል እጠይቃለሁ፡፡
የሰው ልጅ ካሉት የአካል ክፍሎች መካከል አንዱ በስሙ አይጠራም፡፡ ነገር ግን ትውልድ እንዲቀጥል ትልቅ ሚና የሚጫወተው ይሄ የአካል ክፍል ነው፡፡ ታዲያ በስሙ አለመጠራቱ ወሳኝ ሚናውን እንዳይወጣ አላደረገውም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም አገር እየመሩ መሆኑን ለማስረገጥ የግድ ሚዲያውን መውረር የለባቸውም፡፡ ለወራት በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ባይሉም እንኳን መቶ ሚሊየኖችን የሚመሩ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸውን አንዘነጋም፡፡
አዲስ ዘመን ረቡዕ ነሀሴ 15/2011
የትናየት ፈሩ