ቡሄ ማለት መላጣ (ገላጣ) ማለት ሲሆን፤ ክረምቱ፣ ጭጋጉ፣ ደመናው ተወግዶ የብርሃን ወገግታ ሲታይ የሚከበር በዓል ነው። ሰማይ ከጭጋጋማነት ተላቆ ወደ ብሩህነት ይሸጋገራልና ሳይጠያየቅ የቆየው ዘመድ አዝማድ ወደነበረው ማህበራዊ ህይወቱ የሚመለስበት ጊዜም ነው። በዚህም ሆያ ሆዬ…ሆ… በማለት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን የሚያስተላልፉ ልጆችም ከቤተሰቦቻቸው ፈቃድ አግኝተው በየቤቱ እየተዘዋወሩ ይጨፍራሉ።
በእርግጥ ይህ በዓል ሃይማኖታዊ አንድምታ ያለው ነው። የእኛ ትኩረት የልጆች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት እንዴት ይከወናል ነውና ይህንን ወደጎን ትተን የቡሄ ግጥሞችን ዛሬና ትናንት እያልን የሥነቃልን ተለዋዋጭነት ለማሳየት እንሞክራለን። በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡን በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሥነቃል ልማት ባለሙያ የሆኑትን አቶ ደሳለኝ ከበደን አነጋግረናል። እርሳቸው በነገሩን መሰረትም እንዲህ አቅርበነዋል።
ይህ ሀገረሰባዊ ሥርዓተ ከበራ በእየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን የሚከበር ሲሆን፤ ማህበረሰቡ በየአካባቢያቸው በመሰባሰብ ጥሎሽ (ስጦታ) በማዘጋጀት፣ ጅራፍ በማጮህ፤ ችቦ በማብራት፤ ሙል ሙል ዳቦ በማዘጋጅትና ልጆች እየጨፈሩ በመዞር የሚያከብሩት በዓል ነው። የቡሄ በዓል ከሌሎች በዓላት በፊት የሚከበርና የሌሎች በዓላት መነሻ እንደሆነም ይገልፃሉ። ቀዳሚ በዓል መሆኑንም በስነ ቃል አማካኝነት ሲያስረዱ እንዲህ ብለዋል።
የጎዶ መነሻ ቡሔ ነውና፤
የመስቀል መነሻ ቡሔ ነውና፤
በጋራ እናክብረው ሰብሰብ በሉና። ቀጥለው ደግሞ የበዓሉ አከባበር በአገሪቱ የተለያየ ስያሜ እንዳላቸውም ይገልፃሉ። ለአብነት በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን “ጎቤ” እየተባለ ሲጠራ በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ ደግሞ “ቡሄ” በመባል ይታወቃል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ደግሞ ደብረ ታቦር አልያም የክርስቶስ መገለጥ ቀን ተብሎ እንደሚጠራ ይናገራሉ።
ለመረጃ ስብሰባ የተሰማሩባቸውን አካባቢዎች መሰረት በማድረግ ሀገረሰባዊ ክበራው በምን ሁኔታ እንደሚከወንም ሰነዶችን እያገላበጡ ነግረውናል። እናም በተሰበሰበው መሰረት የቃል ግጥሞቹ በሦስት ተከፍለው ይታያሉ። የመጀመሪያው በሩ እንዲከፈት የሚዘፍኑት ሲሆን፤ ሁለተኛው ቤት ውስጥ ገብተው እመቤቲቱን፣ አባወራውን እያሞገሱ የሚጨፍሩበት የቃል ግጥም ነው።
ሦስተኛው ደግሞ ከተሰጣቸው የሚያመሰግኑበት ካልተሰጣቸው ደግሞ የሚራገሙበት ወይም የሚሳደቡበት እንደሆነ ባለሙያው ይናገራሉ። እናም ለመሆኑ በፊት የቡሄ አከባበር እነዚህን ተግባራት እንዴት ይከውኑ ነበር? በአሁኑስ? በገጠር በከተማስ ምን አይነት መልክ አለው? በማለት እያነፃፀርን ለጥናቱ የተሰበሰበውን መረጃ መነሻ በማድረግ ጥቂት እንበል።
ክፈት በለው በሩን
የጌታየን፤
ክፈት በለው ተነሳ
ያንን አንበሳ፤
መጣና በዓመቱ
ኧረ እንደምን ሰነበቱ … እያሉ በመጨፈር በአቀንቃኙ መሪነት
ወደ ሚለምኑበት ቤት ያመራሉ። ከዚያም የቡሄ ግጥሞችን እየደረደሩና እያዜሙ ወደ ውስጥ ይዘልቃሉ። ስጦታ ጠያቂዎች የተከበሩ እንግዶችና አስተናጋጁ የተሻለ ነገር እንዲያበረክት የሚያደርግ የቃል ግጥሞችን እንዲህ በማለት ይደረድራል።
ዝና ጠይቆ የመጣ እንግዳ
እራቱ ሙክት ምሳው ፍሪዳ፤
ሆያ ሆዬ ጉዴ
ዝና ወዳዴ
ሆያ ሆዬ ዝና
ተ ው ስ ጠኝ ም ዘዝና የሚል ሲያሰማ ተቀባዮችም ይህንን ይደግማሉ። ቀጥለውም
ሆያ ሆዪ፣
ሆያ ሆዪ
ወይ የኔ ጌታ ዋርካ ነህ ዋርካ
ቢጠለሉብህ የማታስነካ
ወይ የኔ ጌታ የሰጠኝ ሙክት
እግንባሩ ላይ አለዉ ምልክት፣
መስከረም ጠባ እሱን ሳነክት፣
የኔማ ጌታ የሰጠኝ ካራ
ከዚህ ብመዘው ጎንደር አበራ፣
የኔማ ጌታ የሰጠኝ ስንዴ
ገና ሳልበላው አበጠ ክንዴ። ሲል ተቀባዮቹ በየስንኙ መሀል አውራጁ ቆም ሲል “ሆ” እያሉ አባወራውን ያሞግሳሉ። በዚያም ሳይበቃቸው ለእማወራዋም እንዲህ ሲሉ ይገጥሙላታል።
የኔማ እመቤት መጣንልሽ
የቤት ባልትና ልናይልሽ።
የኔማ እመቤት ብትሰራ ዶሮ
ሽታው ይጣራል ገመገም ዞሮ ።
የኔ እማ እመቤት የፈተለችው
የሸረሪት ድር አስመሰለችው
ሸማኔ ጠፍቶ ማርያም ሰራችው
ለዝያች ለማርያም እዘኑላት
አመት ከመንፈቅ ወሰደባት።
እያሉ ወይዘሪቷን በሙያዋ በባልትናዋ ያወድሷታል። ውበቷን በማድነቅም እንዲሁ ሌላ የሙገሳ ግጥም ያወርዱላታል።
የኔማ እመቤት፣ እሜት እሜት
ሎሚ ተረከዝ ትርንጎ ባት
ንጉስ ለእቁባት የተመኟት
ተመኟት እንጂ መች አገኟት።
እያሉም። ይሁንና ይህንን ሁሉ ብለው የዳቦ ስጦታው የዘገየ ከሆነ የሚሉት ነገር አይጠፋቸውም። ለምሳሌ፡-
አንዱን አምጭው አታማርጭው
ወደ ጓዳ አታሩጭው ። ይላሉ። ከዚያ የልጆቹ መምጣት የምስራች ማብሰር ሆኖ ስለሚቆጠር ማህበረሰቡ በደስታ ይቀበላቸዋል። መርቆ ሙልሙል ዳቦ ሰጥቶም ይሸኛቸዋል። ወጣቶችም በተራቸው እንዲህ እያሉ ይመር ቋቸዋል።
ክበር በስንዴ ክበር በጤፍ
ምቀኛህ ይርገፍ ፤
የጌታየ ጦር
ይወጋል ጠጠር
የእመቤቴ እንዝርት
ይወጋል እምብርት
እያሉ ይመርቋቸዋል፡፡ ወይም ደግሞ
ዓመት አውድ ዓመት
ድገምና አመት . . ድገምና፣
የእማምዬን ቤት . .
ድገምና አመት. . . ድገምና፣
ወርቅ ይፍሰስበት. .
ድገምና አመት. . . ድገምና፣
እንዲህ እንዳላችሁ አይለያችሁ፣
እንዲሁ እንዳለን አይለየን፡፡ ይሏቸዋል።
ተረኛው ቤት ሄደው በር እንዲከፍትላቸው መጣና መጣና ደጅ ልንጠና… ሲሉ በር ሳይከፈትላቸው ከዘገዩ ደግሞ እንዲህ ይላሉ።
ኧረ በቃ በቃ
ጉሮሮአችን ነቃ
ኧረ በስላሴ
ልትወጣ ነው ነፍሴ
ብትሰጠኝ ስጥኝ ባትሰጠኝ እንዳሻህ
ከነገሌ ሁሉ አነሰ ወይ ጋሻህ
ተው ስጠኝና ልሂድልህ
እንዳሮጌ ጅብ አልጩህብህ፤ ይህንን ብለው ካልተሰጣቸው ደግሞ
ክበር ክበር በቃሪያ፤
አንተ ቆራጣ ባሪያ፡፡
ክበር ክበር በዶሮ
አንተ የሰው ጎደሎ፡፡
አሆ በል እረኛ የጥሬው ደመኛ!
አሆ በል ጎበዙ አሞሌ እስኪመዙ!
እሆዬ እላለሆኝ እርጎ እወዳለሁኝ!
እሆዬ ማለቴ እኔም ልጅነቴ!
ያምናውን ሳይሰጡኝ ዘንድሮ መምጣቴ። በማለትም የስድቡን አረንቋ ያወርዱባቸዋል። ይህ ሁሉ የሚሆነው በከተማውም በገጠሩም ቀደም ሲል የነበረ የቡሄ አከባበርን ይይዛል። አሁን ደግሞስ ከተባለ ገጠሩ ላይ ብዙም ለውጥ አይታይም፤ የቃል ግጥሙ ልዩነት የመጣው ወደ ከተማው ሲገባ ነው። እናም በአንዳንድ ከተሞች ላይ የሚስተዋለውን እንመልከት።
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እየኖሩ ካሉ የተለያየ የእድሜ ደረጃ ካላቸው ግለሰቦች በመጠየቅና በመመልከት በተገኘው መረጃ መሰረት በየዘመኑ የራሳቸው ቅርፅና ይዘት ያላቸው የቡሄ በሉ ቃላዊ ግጥሞችን ማግኘት መቻሉንም ባለሙያው ይናገራሉ። እናም ተገኙ ያሏቸውንም የተጀመረውን ጥናት መነሻ አድርገው እንዲህ ያስረዳሉ። የእንኳን አደረሳችሁ ምኞታቸውን ለማቅረብ ወደሚፈለጉበት ቤት ሲያመሩ ከሚሉት ይጀምራሉ።
አስዮ ቤሌማ ሆሆ አይበል
አስዮ ቤሌማ የቤሌማ እናት
ሆሆ አስር …ጥጃ አላት…
ሆያ ሆየ ሲሉ ሰምቼ
ከጎንደር መጣሁ በሬን ዘግቼ። በማለት ጉዞ ወደ ልመና ቤት ያደርጋሉ። በዚያ እንደደረሱም
መጠለሉንስ ተጠልያለሁ
ያችን ስሙኒ የት አገኛለሁ። እያሉ ያዜማሉ። ቀጥለው ደግሞ ወደሙገሳው ይገባሉ።
እዚያ ማዶ አንድ ሻሽ
እዚህ ማዶ አንድ ሻሽ
የኔማ እገሌ ወርቅ ለባሽ
እዛ ማዶ አንድ ከሰል
የኔማ እገሌ ማይክል ጃክሰን
እዛ ማዶ አንድ ሚሪንዳ
የኔማ እገሊት ልትሄድ ነው ካናዳ፤
እዚያ ማዶ አንድ ጀሪካ
የኔማ ጋሽየ ሊሄድ ነው አሜሪካን። ይሁንና ይህ ግጥም ሁለት አንድምታዎች አሉት ይላሉ ባለሙያው። የመጀመሪያው የቡሄን ባህላዊ ይዘት የለቀቁ ስንኞች አሉበት። ሁለተኛው ደግሞ የማይበረታቱ ነገሮችን ተካተውበታል። ለአብነት ስደት አይበረታታም። በአገራችን ብዙ ዘፋኞች እያሉ ውጭ ናፋቂነትን መውደድም ተገቢ አይደለም። እናም ይህንን በትክክለኛው ባህል መተካትና ማስተካከል ያስፈልጋል ባይ ናቸው። በእርግጥ ነገሩን የፈጠረው የማህበረሰቡን የልብ ትርታና ዘመኑ ነው። ነገር ግን ማህበረሰቡ በራሱ ይህንን ማረም ይኖርበታል ይላሉ።
የሁለቱም ዘመናትና የገጠርና ከተማውን የቃል የቡሄ ግጥሞችን አጠቃለው ሲያነሱም እንዲህ ይላሉ ባለሙያው። የሁለቱም ዘመናት ግጥሞች በዋናነት አንድ የሚያደርጋቸው የሚባሉበት አውድ ነው፡፡ ግጥሞቹ የሚከወኑበት ጊዜና ቦታም ተመሳሳይ ነው፡፡ ማለትም ጊዜው በነሐሴ ወር አጋማሽ እና ቦታው ደግሞ በተለያዩ ቤቶች ውስጥ የሚጨፈሩ ናቸው፡፡ ጭፈራውን የሚያከናውኑት ልጆች የዕድሜ ሁኔታም ቢሆን ተመሳሳይነት አለው። ከዚህ በተጨማሪ በሐረግ ያላቸው የቀለም ምጣኔ ተመሳሳይነትም አንድ ያደርጋቸዋል። ምንም እንኳ የሰንጎ መገን እና የወል ቤት ቅርፅ ያላቸው አንዳንድ ስንኞች ቢኖሩም።
በየዘመናቱ የተጠቀሱ ግጥሞች በቃላት አጠቃቀምና በግጥም አፈጣጠር ደግሞ ልዩነት አላቸው፡፡ የተዘረዘሩት የቡሄ በሉ ግጥሞች ስንኞች ውስጥ የቃላት አጠቃቀም ልዩነት ይታያል። ማለትም በአንደኛው ዘመን የሌሉ የቃላት አጠቃቀሞች በሌላኛው ዘመን ላይ ይስተዋላሉ፡፡ በተለይም በቀደምት የቡሄ በሉ ግጥሞች ውስጥ ያሉ ቃላት በአሁኑ ዘመን ላይ አይታዩም፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አጋፋሪ፣ ጥጃ፣ ገመገም፣ የንብ እንጀራ፣ የሸረሪት ድር የሚሉት ቃላቶች በአሁን ዘመን ላይ ካሉት ግጥሞች ውስጥ አይታዩም። እናም የዘመናት ልዩነት የቡሄ የቃል ግጥሞችንም ለውጥ አምጥተዋል ብሎ ማስቀመጥ እንደሚቻል ይናገራሉ። ግን ልዩነቱ ሲመጣ ባህል፣ ወግንና ማንነትን ባለቀቀ መልኩ ይሁን መልዕክታቸው ነው። እኛም ይህ ይተግበር እያልን ለዛሬ በዚህ አበቃን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ነሃሴ 12/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው