ሲትኮም

ሳቅ መፍጠር ምናልባት ለአንዳንድ ሰዎች ቀላል ነገር ሊሆን ይችላል። አንዳንዴ በአካላዊ እንቅስቃሴ ብቻም ሰዎች እንዲስቁ ማድረግ ይቻላል። ቀልድ እና ቁምነገርን በአንድ ላይ ማቅረብ ደግሞ ሌላ ጉዳይ ነው። ይህም ሰዎች በደረቁ ታግሰው የማይሰሙትን፣ መንግሥት እንዲነሳበት የማይሻውን፣ ተቋማት ሊታሙበት የማይፈልጉትን፣ ማኅበረሰብ ትክክል ነኝ በሚል ካባ ሸፍኖ የሚያሽሞነሙንና እንዲነካበት የማይፈልገውን ጉዳይ እንዲሰሙት አድርጎ በቀልድ አዋዝቶ ማቅረብ እንደማለት ነው። ይህን ማድረግ የቻለ ወይም የሚችለው ሲትኮም የተባለው የተከታታይ ፊልም ዘውግ ነው።

ሲትኮም (Sitcom) ”Situation-Comedy” ከሚለው የእንግሊዝኛ ጥምር ቃል የወጣ ነው። ‘ከሁኔታዎች ውስጥ ወይም በሁኔታዎች የሚፈጠር አስቂኝ ትዕይንት’ የሚለው ሃሳብ ለትርጉም ይቀርበዋል። ለቃሉ ቀጥተኛና አቻ ሀገርኛ ትርጉም የተሰጠው ባይመስልም፤ በኢትዮጵያ የፊልም ዘርፍ ይልቁንም በቴሌቭዥን ተከታታይ ፊልም ዘርፍ ዝነኛ ከሆነ ሰነባብቷል። እንደውም በርካታ ወይም ሁሉም ለማለት በሚቀርብ መጠን የቴሌቭዥን ጣቢያዎች የሲትኮም ቤት ሆነዋል፤ አልፎም የሲትኮም ዘውግ ያላቸው ፊልሞችን ከመሰናዶዎች መካከል አለማካተት የማይቻል አልያም ክልክል የሆነ ይመስላል።

ሲትኮም ከዓለም ጋር እንደ አንድ ዘውግ ተለይቶ የተዋወቀው በሬዲዮን ሥራዎች አማካኝነት እንደሆነ የተለያዩ በትስስር መረብ ኀሰሳ የሚገኙ መዛግብት ያስረዳሉ። ይህም በአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ወደ 1926 የሚመልሰን ነው። በኋላ በዛው የአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር 1946 በእንግሊዝ የመጀመሪያው ሲትኮም ተብሎ የተጠራ ፊልም ለቴሌቭዥን ተመልካቾች ለዕይታ ቀርቧል። በኋላም የተለያዩ ሀገራት የፊልም ኢንዱስትሪዎች ለዘውጉ እውቅና ሰጥተው መሥራት ቀጥለዋል።

በዚህ ዘውግ ዝነኛ ከሆኑት መካከል ‘ፍሬንድስ’ አንዱ ነው። በጓደኝነት የተጣምሩ፣ በአሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ ውስጥ የሚኖሩና እድሜያቸው በሃያዎቹ መጨረሻ አካባቢ የሚገኝ ስድስት ወጣቶችን ታሪክ ያስቃኛል። ይህ ፊልም ከአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር 1994 ጀምሮ እስከ 2004 በዕይታ የቆየ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝናን ያተረፈ ብሎም በትውልድ መካከል ሳይሰለች አሁን ድረስ የሲትኮም ዘውግ ዳርቻ የሆነ ያህል እየተጠቀሰ የቆየ ነው።

የዚህን ሲትኮም ተወዳጅነት እና ዘመን አይሽሬ ሆኖ መቆየቱን በተመለከተ የተጻፉ ዘገባዎች፣ በፊልሙ የተሳሉ ገጸ ባህርያት የተለያዩና ለአብዛኛው/ለሁሉም የቀረቡ መሆናቸውን እንደ ምክንያት ያነሳሉ። ተመልካቾች ራሳቸውን ወይም ከራሳቸው ማንነት ጋር የሚቀራረብ መልክን በቀላሉ በገጸ ባህርያቱ ውስጥ ማግኘት መቻላቸው ተቀባይነት እንዲያገኝ አድርጎታል የሚሉም አሉ። አዲሱ ትውልድ ደግሞ መለስ ብሎ የቀደመውን ትውልድ መልክ የሚያይበት መሆኑና ያም የቀረበበት ለዛ ማራኪ መሆኑ ዘመን እንዲሻገር አስችሎታል ሲሉ ያነሳሉ።

በዚህ ሲትኮም ላይ ሳቅ የሚፈጥሩ ትዕይንቶችና ንግግሮች ላይ የተመልካቾች የሳቅ ድምጽ (Laugh Track) ይሰማል። ይህም በአብዛኛው አሁን ላይ እንደምናየው የሳቅ ድምጽ ተቀድቶ፣ ቅጂው በየትዕይንቱ የሚለቀቅበት ሳይሆን በቀጥታ ተመልካቾች እየተመለከቱ ግብረ መልስ የሚሰጡበት ነበር። እንደውም የሲትኮሙ ዳይሬክተሮች ሳቅ ያልተፈጠረባቸው ትዕይንቶች ላይ በዛው ማስተካከያ አድርገው ሳቅ እንዲፈጥር ያደርጋሉ።

ይህን በኢትዮጵያ ወጣቶች ዘንድም ተወዳጅ የሆነ ሲትኮም ያነሳነው ለማሳያ ነው። ታዲያ የአንዳንድ ሲትኮሞች መቼት እንደ ፍሬንድስ በመድረክ ግንባታ ታግዞ ታዳሚዎች በቀጥታ በተገኙበት ይቀርባል። እንደዛው ሁሉ በታሪኩና በገጸ ባህርያቱ መልክ መሠረት መቼታቸው ይቀረጻል። ካፌ ውስጥ፣ መኖሪያ ቤት፣ ትምህርት ቤት የመሳሰለው ከመቼቶቹ ይገኙበታል።

“ሲትኮም ማለት አንድ የተወሰነ ‘ሁኔታ’ ላይ መሠረት የሚያደርግ ነው። ሲትኮሞች አንድ ጉዳይ/ሁኔታ ያነሱና በዛ ላይ ሳቅ የሚፈጥሩ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ተያያዥ ሆነው የሚቀጥሉ ናቸው።” ሲል የሚያስረዳው የኢትዮጰያ ፊልም አጥኚ እና ተመራማሪ ምኒልክ መርዕድ ነው። ምኒልክ አያይዞም እነዚሁ በአንድ ሁኔታ መነሻነት ሳቅን እየፈጠሩ የሚሄዱ አልያም ተያያዥ ታሪክ ይዘው ሳቅን በመፍጠር የሚቀጥሉ ፊልሞች፣ አንዳንዶቹ የሳቅ ድምጽ (Laugh track) እንደሚጠቀሙ አውስቷል። ይህ የሳቅ ድምጽን የማስገባት ጉዳይ ግን አከራካሪ መሆኑን ይጠቅሳል። ያም ሆነ ይህ ሲትኮም ፊልሞች ተወዳጅ ሆነዋል። እንደ ምኒልክ ገለጻ፣ ከቀሪዎቹ ተከታታይ ፊልሞች (Series) ባልተናነሰ በደንብ መታየት ጀምረዋል።

ሲትኮም በኢትዮጵያ በዚህ ጊዜ ተጀመረ ለማለት ሰፊ ጥናት የሚጠይቅ ጉዳይ ሳይሆን አልቀረም። ምክንያቱ ደግሞ የሲትኮም ዘውግ ጠባይ ያላቸው ‘ጭውውት’ ተብለው በቴሌቭዥን የሚቀርቡ ሥራዎች ነበሩ። በዛው መጠን ከቴሌቭዥን ቀደም ብሎም በሬዲዮም የሚደመጡ ጭውውቶች ይታወቃሉ።

“ሲትኮም የሚል ስም ባይሰጡትም ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ሥራዎች ተሞክረዋል። ቲቪ ላይ በጭውውት መልክ ይቀርቡ የነበሩ የልመንህ፣ አለባቸው እና እንግዳዘር፤ ደረጄ እና ሀብቴ የመሳሰሉት ሊጠቀሱ ይችላሉ። ሳቅ/ኮሜዲ ፈጥረው በጭውውት ያቀርባሉ።” ሲል ያብራራል። እነዚህ ጭውውቶች ታዲያ የእረፍት ቀናትን ማድመቂያ፣ የበዓላት ቀን ማሞቂያና መጨዋወቻ፣ አንዳንዴም ማኅበራዊ ሕይወትን በተመለከተ መልዕክቶች የሚተላለፍባቸው ሆነው ይታዩ ነበር። እነዚህ ሲትኮም ውስጥ ይመደባሉ ወይ የሚለውን በቀጥታ መመለስ ባይቻልም፤ የሲትኮም ባህርያት ግን ያሏቸው ናቸው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሲትኮም የሌለበት የቴሌቭዥን ጣቢያ ቢታሰስ ለማግኘት ያዳግታል። ለምን እንዲህ ተበራክተው ታዩ፣ ለምንስ በመደበኛ ፊልሞች ይሳተፉ የነበሩ ባለሞያዎች ሳይቀር በአብዛኛው ተምመው ወደዚሁ ዘውግ እንዲሄዱ ያደረጋቸው ምን ይሆን የሚለው እንደ ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም።

በዚህ ጉዳይ ላይ ምኒልክ ዕይታውን አካፍሏል። ሲትኮም አይነኬ የተባለንና በዝርው ለመናገር የማይደፈርን በቀልድ አዋዝቶ ለማቅረብ ማገዙ ባለሞያዎች እንዲመርጡት፣ ተመልካችም እንዲመለከተው አድርጓል ይላል። “ፖለቲካውን ቀጥታ መናገር አይቻልም፣ ሊያስጠይቅ ይችላል። ሲትኮም ሆኖ ሲመጣ ግን ማንሳት ወይም መንካት ይቻላል።” ሲል ያብራራል።

እዚህ ላይ እንደ ምሳሌ “ምን ልታዘዝ” የተሰኘውን ሲትኮም ማንሳት ይቻላል። በዚህ ሲትኮም ላይ የ‘ፖለቲካዊ ሳታየር’ ዓይነት ይዘት ከመታየቱ ባለፈ ማኅበረሰብን ጨምሮ ‘አንቂ ነን’ የሚሉ አካላት ላይ ትችቶች ይቀርቡ ነበር። ከሲትኮሙ በአንዱ ክፍል ላይ ‘የሴቶች መብት አቀንቃኝ’ (Feminist) የሆኑ ሰዎችን አካሄድ ያሳያል። በካፌው ውስጥ ሻይ እና ቡናን ሳይቀር በሴት አንቀጽ መጠራት አለበት ብለው ‘ሲሞግቱ’ ያሳያል። በዚህም ሳቅ ፈጥሮ፣ አካሄዱን ይተቻል፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ራሳቸውን እንዲያጤኑ ያመላክታል። በተመሳሳይ በሲትኮሙ የ’ምን ልታዘዝ ካፌ’ ሥራ አስኪያጅ ጋሽ አያልቅበት እና በአስተናጋጆቹ ብሎም በባሬስታው መካከል ባለው ግንኙነት ውስጥ ፖለቲካዊ ትችቶች ሲሰነዘሩ ይታያል።

“ትችት በሲትኮም መቅረቡ ተአማኒነትን እንዲያገኝ ያስችላል። አንዳንዴ አዲስ የሆነ ነገርን ማኅበረሰቡ እንዲቀበል ለማድረግም ሲትኮምን ይጠማሉ። ሲትኮም ማምለጫ ሊሆን ይችላል። በድምሩ እንዲህ አሁን ላይ ሲትኮም በብዛት የሚታየው በቀልድ ሲመጣ መንግሥት እንዳይጠይቅ፣ ማኅበረሰብም ጥያቄ እንዳያነሳ አድርጎ ‘ኮሶን በማር ጠቅልሎ’ ዓይነት አቀራረብ ስላለው እንደሆነ አስባለሁ።” ሲል ምኒልክ ዕይታውን አብራርቷል።

ወደፊት የፖለቲካ ዘውግ ሊመጣ ይችላል የሚል ግምቱን ግን ሳይጠቅስ አልቀረም። “በመንግሥት የሚደገፉ የፖለቲካ ቅላጼ ያላቸው ፊልሞች ሊመጡ ይችላሉ የሚል ግምት አለኝ። አሁንም እንደዛ ዓይነት ፊልሞችን እያየን ነው። ከዛ ደግሞ አሁን ያለውን የፖለቲካ አካሄድ የሚቃወም የፊልም ሠሪ ሊነሳ ይችላል።” በማለትም ወደፊቱ ይዞታል ብሎ ያመነውን አመላክቷል።

የፊልም ዳይሬክተር ብርሃኑ ሽብሩ በዘውጉ የሚታየውን አቀራረብ ይተቻል። የሰዎችን ወይም የተመልካችን ፍላጎት ብቻ ይዘው የሚከተሉም አሉ ባይ ነው። አሁን ላይ በዝቶ መታየቱንም በተመለከተ “ወረት ነው፤ ያልፋል” ሲል ያስቀምጣል። ይህንንም ቀደም ብሎ በነበሩ ዓመታት በፊልሞች ርዕስ ላይ ይስተዋል ከነበረው ተመሳሳይ ይዘት ጋር ያነጻጽረዋል።

“አንድ ወቅት ላይ ሲኒማ ቤት የነበሩ ፊልሞች በሙሉ ርዕሳቸው እንግሊዘኛ ነበር። ልክ እንደዛው ወረትና ሽሚያ ስለሆነ ነው። ግን ያልፋል። ቁጭ ብለውም አይነጋገሩም። አንድ ሲትኮም ተወደደ ከተባለና ያም የሆነው ሳቅ ስለፈጠረ እንደሆነ ከታሰበ ሌላውም ቀጥታ ወደዛው ሥራ ይገባል። ሀገር ነክ የሆነ ነገር ቢሠራ ትልቅ ትርጉም ይሰጥ ነበር። ግን ጫጫታና ሳቅ እየሆነ ነው። እያመመን መሳቅ ሆነ። አንዳንዴም በሰው የሚያሽሟጥጡ ነው የሚመስለኝ።” ሲልም ዕይታውን አካፍሏል።

ነገሩን ከወቅታዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት ጋር፣ ከሰዎች ሥነ ልቦናዊና አእምሯዊ ሁኔታ ጋር የሚያገናኙት አሉ። ከሰላም ማጣትና በተለያየ መልክ እሳት ላይ ከተጣደው ኑሮ ሰዎችን ለማሳረፍ፣ የብሶትና ችግር መተንፈሻም ነው ብለው የሚያምኑ አሉ። ብርሃኑ በበኩሉ በዚህም እንደማያምን ያስረዳል። “እኔ መተንፈሻ ነው ብዬ አላስብም። አዎን! እንደ ሀገር ጭንቀት አለ፣ ግጭት አለ። በየትኛውም ዘውግ ቢሆን ግን ሥራዬን ሳቀርብ ምን መልዕክት አስተላልፋለሁ ነው እንጂ ላስቅ በሚል አይደለም/መሆንም የለበትም። መናገር የምፈለገው ነገር ወይም ምን እናገራለሁ ነው ጥያቄው። ፖለቲካን ፈርተው አሁን አሁን ዝም ብሎ ማሳቅ ላይ አርፏል። ያንንም ሲትኮም ብለው ይጠሩታል። እሳቤው ከማዕበሉ ጋር ሆኖብን ነው።” ብሏል።

ሁሉም ‘ሲትኮም’ በሚል ዘውግ የሚጠሩ ‘ሲትኮሞች’ በተመሳሳይ ጥንቃቄና የባለሞያ ቅኝት የሚሠሩ አይደሉም። ከመብዛታቸው በላይም በጥራት እና በአግባብ የመሠራታቸው ነገርም ወሳኝ ነው። ምኒልክም በዚህ ላይ ሃሳቡን እንዲህ ሲል አካፍሏል።

“ቀልድ ለዛ ይፈልጋል። ለዛ ባለው መልኩ ማቅረብ ያስፈልጋል። አንዳንዴ የዝግጅት ማነስ የሚያመጣው ይመስለኛል። ኮሜዲ የሚባለው ነገር በፊልም ቅርጽ እንዴት መምጣት አለበት የሚለውን በደንብ ባለማሰብ ለዛ ቢስ ሥራ ሊቀርብ ይችላል። ምን እያሉ ነው እስክንል ድረስ አንዳንዴ መስመር መሳት ያጋጥማል።”

ከዚህ በተቃራኒ መቼታቸውን የቤተሰብ ሕይወት ላይ አድርገው የተሠሩትንና ተጨባጭ መልዕክትን ለዛ ባለው ቀልድ እያቀረቡ ነው ያላቸውን ሲትኮሞች እንደማሳያ ያነሳል። ለምሳሌ ‘በስንቱ’ የተሰኘው ሲትኮም አንደኛው ነው። ይህ በኢቢኤስ ቴሌቭዥን የሚቀርብ ሲትኮም፣ ማኅበራዊ ሕይወትን በደንብ ይተቻል፤ በተለይ በስንቱ በተባለው ገጽ ባህሪ በኩል። በዚህ ሲትኮም ባሎች ሚስቶቻቸውን እንዴት ነው የሚያዩት፣ ሚስቶችስ የሚለው ይታያል። ከሰፊው ቤተሰብ (አማት እና አማችን ጨምሮ) ጋር ያለው መስተጋብር ምንድን ነው የሚለውንም በሚገባ ለማየት ይሞክራል። ሰውም/ተመልካቹም እንዴት እናት አና አባት በልጅ መካከል እንዲህ ያለ መስተጋብር ሊኖር ይችላል ብሎ ሊጠይቃቸው ይችላል።

እንዲህ ባለ ዕይታ የሚሠራ ሲትኮም ውስጥ በማኅበሰረቡ እና በፊልም ሠሪው መካከል ቅብብል ይኖራል። ማለትም ፊልም ሠሪዎች ማኅበረሰቡን ሲመረምሩና ሲተቹት፣ አንዳንዴ ማኅበረሰቡም በበኩሉ በደንብ አልተወከልንም ሲል ጥያቄ ያቀርብባቸዋል። ሲትኮም በዚህ ረገድ፣ በተሠራበት ጥንቃቄ መጠን በድምሩ መስተካከል ያለበትን አካል ሂስ ለማድረግ ምቹ ነው።

የሲትኮሞች በብዛት መቅረብ ጥራት ላይ ጥርጣሬን ከመጫሩ በቀር፤ በቀረፃ፣ በታሪክ አወቃቀር፣ በገፀ ባህርያት ግንባታና በአቀራረብ ለየት ብለው ለመምጣት የሞከሩም አሉ። ከእነዚህም በባላገሩ ቴሌቭዥን ይታይ የነበረው ‘ሦስት ሁለት አንድ’ የተሰኘ ሲትኮም እና በቅርቡ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን መታየት ላይ የነበረው ‘ግራ ቀኝ’ ተጠቃሽ ናቸው። በስንቱ፣ አስኳላ፣ ምን ልታዘዝ፣ ቤቶች፣ ዘጠነኛው ሺህ፣ ሲስተርሊ ብራዘርሊ፣ ጎረቤታሞቹ ወዘተ በዕይታ ላይ ካሉና ቀደም ብለው ከቀረቡት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

ርግጥ ነው! ዘውጉ በበርካታ ጠባዮቹ የተነሳ አሁን ላይ ተመራጭ ዘውግ እየሆነ መጥቷል። ተመልካችና ጊዜም ተባብረው እያነጠሩ በጥሩ ሁኔታ የተሠሩትን ተፅዕኖ ፈጣሪ እና ዘመን ተሻጋሪ ያደርጓቸዋል።

ሊዲያ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 23 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You