መጣና መጣና ደጅ ልንጠና፤
መጣና ባመቱ፣ ኧረ እንደምን ሰነበቱ፤
ክፈት በለው በሩን የጌታዬን፤
ክፈት በለው ተነሳ፣ ያንን አንበሳ፤ ወዘተ…
ከስጦታ በኋላ ደግሞ
እዚህ ቤት፣ እዚህ ቤት ይግባ በረከት፣
የወፋፋ የወፋፋ፣ የወለዱት ይፋፋ ወዘተ።
ይህ የቡሄ ሰሞን የምንሰማው ሃይማኖታዊ መሰረትና ባህላዊ ይዘት ያለው ዜማ ነው። ይህ ዜማ በዋናነት ነሐሴ በገባ ከአንድ ሳምንት ጀምሮ እስከ ቡሄ ድረስ የሚሰማ የልጆች ጭፈራ ሲሆን ልጆችና ወላጆችን በፍቅር የሚያስተሳስር ትልቅ አገራዊ ትርጉም ያለው በአል ነው።
ዛሬ የቡሄ በዓል ነው። ቡሄ ወይም የደብረታቦር በአል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ትርጉም ያለው በአል ሲሆን ከበዓሉም ባሻገር በባህላዊ መልኩ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ይከበራል። በተለይ በልጆች ዘንድ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ይህ በአል ልጆች ገና ከበአሉ አንድ ሳምንት ቀደም ብለው ጅራፍ በማዘጋጀትና በማስጮህ እንዲሁም ሰብሰብ ብለው የቡሄ ጨዋታን በመጨፈር እየዞሩ ከየቤቱ ሙልሙል ዳቦ የሚቀበሉበት፣ እናትና አባትን የሚመርቁበት ልዩ በዓል ነው።
ቡሄ በመጣ ቁጥር የልጆች ዝግጅትና ደስታ ለሁሉም ማህበረሰብ ደስታን ከመፍጠሩም ባሻገር አንድነትን የመፍጠር አቅሙም ከፍተኛ ነው። በቡሄ ጭፈራ ወቅት “ይህ የእከሌ ቤት ነው፤ ይህ ደግሞ የእከሌ” የሚባል አስተሳሰብ ፈጽሞ አይታሰብም። ልጆች ሲጨፍሩም የቤቱን ባለቤት ማንነት መርጠው አይንቀሳቀሱም። በሁሉም ቤት በመዞር መጨፈርና ከሁሉም ቤት ስጦታ መቀበል የቆየ እሴት ነው። ወላጆችም ቢሆኑ እኛ እምነታችን ከዚህ ውጪ ነው፤ ወይም ይህ ጉዳይ እኔን አይመለከተኝም የሚል ማግለል በዚህ በአል ላይ ፈጽሞ አይታሰብም። ይህ ለአመታት የቆየ የኢትዮጵውያን ልዩ መገለጫ እሴት ነው።
ኢትዮጵያን የተለየ ውበት ከሚያላብሷት ገጽታዎቿም ውስጥ አንዱ እንዲህ አይነት ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቿ ናቸው። ከ80 በላይ የሚሆኑት የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች የተለያዩ ባህሎች፣ እምነቶች እና ቋንቋዎች ባለቤቶች ናቸው። እነዚህ የተለያዩ ማንነቶች ደግሞ በአገራቸው ጉዳይ ላይ ባላቸው አንድነትና ህብረት በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ ጭምር ይታወቃሉ።
በተለይ ቀደም ባሉት ዘመናት ከውጭ የመጣ ወራሪ ሃይልን በአንድነት ለመመከትና አገራቸውን ለመጠበቅ ያስቻላቸውም ይኸው ጠንካራ ማንነት እንደሆነ ብዙዎች የሚመሰክሩት ሃቅበህዝቦቻችን ውስጥ ጠንካራ መሰረት የነበራቸው እንዲህ አይነት ባህላዊ እሴቶቻችን ለአገራዊ አንድነትና ሰላም ትልቅ ሚና ነበራቸው።
በዚህም መሰረት በአገራችን ለዘመናት የኖረው ታላላቆችን የማክበርና የማዳመጥ፣ እርስ በርስ የመከባበር፣ አንዱ ሌላውን የመውደድና አብሮ የመብላትና የመኖር ባህል ጠንካራ መሰረት ነበረው። ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላው አካባቢ የሄደ እንግዳ ከማንም በላይ የሚከበርበትና ከቤተሰቡ አባል በላይ እንክብካቤ የሚያገኝበት ጠንካራ ባህል ይዘን ኖረናል።
ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ስፍራ የሚጓዝ መንገደኛ በድንገት ቢመሽበትና በደረሰበት አካባቢ እባካችሁ አሳድሩኝ ቢል ከምንም በላይ ቅድሚያ ተሰጥቶት እግሩን አጥቦና የራስን መኝታ ለቆ እንግዳን ማሳደር የኢትዮጵያውያን መገለጫ ሆኖ እንደኖረ የታሪክ ማህደሮቻችን ያሰፈሩልን ባህላዊ እሴቶቻችን ናቸው።
በሌላ በኩል በአገራችን እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ታላላቆችን በተለይ በእድሜ የገፉ አባቶችና እናቶችን ማክበር የተለመደና በእያንዳንዱ ትውልድ ውስጥም የሰረፀ በመሆኑ ማንም ቢሆን ለዚህ ምክርን የሚሻበት ሁኔታ አልነበረም። በዚህም የተነሳ በአካባቢያችን የሚገኝ አንድ አባት ለሁላችንም የምናከብረው አባት ነው። የአካባቢያችን እናት ለሁላችንም እናት ናት። እናም እነሱን ማክበርና መከተል ግዴታችን እንደሆነ አምነን እንተገብረዋለን።
አሁን አሁን ግን ባህላዊ እሴቶቻችን ቀስ በቀስ እየተሸረሸሩ የመጡበት ሁኔታ ይስተዋላል። ለምሳሌ በቡሄ በአል ላይ ቀደም ሲል የነበረው ባህላዊ ይዘቱ እየተቀየረ በዘመናዊነት የመተካት አዝማሚያ በስፋት ይስተዋላል። ከግጥሞቹ ጀምሮ አሁን አሁን ዘመናዊነትን የመላበስ ሁኔታ በከተሞች አካባቢ ይስተዋላል። ከዚህም አልፎ በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ በዓሉ የሚከበርበት መንገድ ተቀይሮ አልፎ አልፎም እየተረሳ ሲሄድ ይስተዋላል። ይህ ደግሞ የቆየውን ጠንካራ ማንነታችንን እንዳያሳጣን ልናስብበት ይገባል።
አሁን አሁን በህብረተሰባችን ውስጥ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ የማንነት ጥያቄዎች ሲፈጠሩ ማየት የተለመደ ሆኗል። በአንድ በኩል “እኛ ኢትዮጵያውያን ነን” በሚል አንድነትን የምናቀነቅንበት ሁኔታ እያየለ ሲመጣ በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ይህ አካባቢ የኔ ነው፤ አንተ ማንነትህ ከዚህ ስላልሆነ ከዚህ ውጣ፤ ወዘተ ›› እያልን በማንነት ጥያቄዎች ግጭት ስንፈጥር እንውላለን።
በመሆኑም የቀደመውን የአገራችንን ጠንካራ የአንድነትና የመቻቻል እንዲሁም የመከባበር ባህል በመመለስና በማጠናከር አገራችንን ወደ ሰላምና ወደ ብልጽግና ለማምጣት ከቀደመው ማንነታችን በጎ በጎውን ልንወስድና ልንጠቀምበት ይገባል። ዛሬ ላይ አገራችንን ወደ አንድነትና ሰላም ሊያመጣት የሚችለው በጎ በጎውን እየወሰድን፣ የተበላሸውን እያረምን ስንሄድ በመሆኑ እንደዚህ አይነት እሴቶችን ከያሉበት በማውጣት ማደስና ወደ ተግባር መቀየር ከሁላችንም ይጠበቃል።
አዲ ዘመን ነሃሴ 13/2011