በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተለያየ ጊዜ ለሚሰማው የሰላም መደፍረስ አንዱ ምክንያት ተማሪው ከታች ጀምሮ በስነ ምግባር የታነጸና በምክንያት የሚያምን ካለመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው። ተማሪውን በስነምግባርና በስነዜጋ ትምህርት ለመቅረጽ ከታች ጀምሮ ትምህርቱን ቀደም ሲል እንዲማሩ ቢደረግም፦ አንደኛ በሙያው በቂ ዕውቀት እና ስልጠና ያላቸውን መምህራን በፍላጎት ከመመደብ እና ከማፍራት እንዲሁም ይህንን ይወጣል ተብሎ የታሰበው መምህር ጋር ያለው ክፍተት ሳይለይ ወደ ሥራ የተገባ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የታሰበውን ያህል ለውጥና ውጤት ማምጣት አልተቻለም።
ይህም በተማሪው ስነ አዕምሮ ላይ የተዘበራረቀ ሥዕል እንዲሳልበት አድርጓል። በዚህም ምክንያት ተማሪው መብቱን አውቆ ጠያቂ እንጂ ከእሱ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እና ግዴታውን በተገቢው መንገድ መወጣት እንዲችል አላደረገውም። እንዲሁም ተማሪው በምክንያት የሚያምንና የሚቃወም የበሰለ አስተሳሰብ ያለው እንዲሆን ሳይሆን በስሜት ብቻ የሚነዳ ሆኖ ቆይቷል። በመሆኑም በተለያየ ጊዜ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ የረብሻና የሰላም እጦት መናኸሪያ ሆነው ከርመዋል። በዚህም በርካታ ተማሪዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ የአካል ጉዳተኛ ሆነዋል፤ የተቋማት ሀብትና ንብረትም ወድሟል።
እነዚህና ሌሎችም ሀገራዊ ሁኔታዎች የትምህርት ስርዓቱን መከለስ አስፈላጊና ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አመላክተዋል። በመሆኑም ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በትምህርት ሚኒስቴር አማካኝነት ከፍተኛ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ችግሮችን የመለየት ጥናት ተካሂዷል። አዲስ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታም ተዘጋጅቷል። በዚህም ላይ ሁሉም መምህራን፣ የትምህርት ማህበረሰቡ እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲወያዩበት፣ አስተያየት እና ግብአት እንዲያክሉበት ተደርጎ ጸድቋል።
ይሄንን መሰረት በማድረግም ስርዓተ ትምህርቱ ከባህል ፣ ከብዝሀነት፣ ከታሪክ፣ከምክንያታዊነት ጋር ተያይዞ እና በአጠቃላይ በሳል አዕምሮ እንዲኖረው ከማድረግ አንፃር በመቃኘት ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ከታችኛው እስከ ከፍተኛው የትምህርት እርከን የትምህርት ስርዓቱን በመቃኘት እና በማስተካከል ከተማሪዎች ስነምግባርና ሞራል፣ ከባህል ከጋራ ታሪኮች እና ሀብቶቻችን እንዲሁም ከብዝሀነት እና ሌሎች ዜጎች እንደ ዜጋ ማወቅ፣ መረዳትና ማስተካከል የሚገባቸውን ጉዳዮች የማካተት ሥራ እየተሠራ ይገኛል።
በ2012 ዓ.ም ወደ መንግሥትም ሆነ ግል ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎችም ትምህርታቸውን የሚጀምሩት የጋራ በሆኑ የትምህርት ዓይነቶች እንደሚሆን የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ አስታውቋል። ትምህርቱም በዋነኛነት የሚያተኩረው ከሰብእና ግንባታ፣ ከሞራል፣ ከባህልና እምነት እንዲሁም የጋራ በሆኑ እሴቶች ፣ታሪክ እና ለሌሎች ተያያዥነት ያላቸው 15 ዓይነት የጋራ የትምህርት ዓይነቶች ናቸው። ይህ ኃላፊነት የሚሰማው የነገውን ሀገር ተረካቢ ዜጋን ከመፍጠር አንፃር እጅግ ጠቃሚና አስፈላጊ ነው። የተበላሹ ታሪኮችን አርሞና አስተካክሎ ለመሄድም እጅግ ጠቃሚ ነው። ተማሪውም ራሱን በዚህ መልኩ ለመቅረጽ መዘጋጀት ይኖርበታል።
ይሁን እንጂ አንድ ትልቅ ጉዳይ አብሮ መታሰብ እንዳለበት ደግሞ መዘንጋት የለበትም። የትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ለመቅረጽ የራሳቸው ድርሻ ቢኖራቸውም ትምህርት ቤቶች ብቻቸውን ዜጋን አስተካክሎ ይቀርጻሉ ብሎ ማሰበ የዋህነት ነው። የተስተካከለና ሰብዕናው የተሟላ ዜጋን በመቅረጽ ሂደት ወላጆች፣ አካባቢና ማህበረሰበ ትልቅ ድርሻ አላቸው። በመሆኑም ወላጆች ልጆቻቸውን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ የጋራ ባህልን፣ ታሪክን፣ እምነትን ፣ መተሳሰብንና መከባበር እንዲሁም ስነምግባር ያላቸው በአጠቃላይ የተሟላ ሰብዕና ተላብሰው እንዲያድጉ በማድረግ ሂደት ውስጥ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል። ማህበረሰቡም በተመሳሳይ ይሄንኑ ሥራ አጽንኦት ሰጥቶ መሥራት አለበት። ዛሬ በእያንዳንዱ ማህበረሰብ ውስጥ በፖለቲከኞች የሚቀነቀነው አክራሪ ብሄረተኝነት አስተሳሰብ ፣ ባለስልጣናትም የስልጣን ዘመናቸው ማራዘሚያነት የሚጠቀሙበት እንጂ ለዜጎች የሚበጅ አለመሆኑን ማስተማርና ማሳወቅ ያስፈልጋል።
ተማሪዎች ታሪክን አገላብጠው ፣ አዋቂዎች የሚናገሩትን አዳምጠውና እራሳቸውን በራሳቸው ሚዛን ላይ አስቀምጠው ጥሩውን ከመጥፎ መለየት ይጠበቅባቸዋል። በሁሉም መልኩ ሰብዕናው የተሟላ ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋን መፍጠር የሚቻለው ግን በትምህርት ተቋማት ብቻ አለመሆኑን ሁሉም ወገን ተገንዝቦ የራሱን ኃላፊነት መወጣት ይገባዋል፣
አዲስ ዘመን ነሀሴ 12/2011