
አዲስ አበባ፡- በሀገር አቀፍ ደረጃ የሂሳብ ትምህርት ውድድር ማካሄድ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ለሀገር የሚጠቅሙ፣ ለምርምር እና ለፈጠራ ቅርብ የሆኑ ተማሪዎችን ለማፍራት እንደሚያግዝ ተገለጸ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሂሳብ ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ጥላሁን አበባው እንደገለጹት፤ ሂሳብ ትምህርትን ብዙ ተማሪዎች ከባድ ነው ብለው ስለሚያምኑ ይፈሩታል፡፡ በዚህም ምክንያት ተወዳዳሪ ተማሪዎች እንዳይፈጠሩ አድርጓል፡፡ “ያለሂሳብ ትምህርት ሌሎችን መማር ከባድ ነው” ያሉት አቶ ጥላሁን በተለይ ደግሞ ሳይንስንና ቴክኖሎጂን ለሀገር ዕድገት መጠቀም ካስፈለገ በሂሳብ ትምህርት ሀገር አቀፍ ውድድሮች መዘውተር አለባቸው ብለዋል፡፡ ይህም ጎበዝ ተማሪዎች ሀገራቸውን በሚገባ እንዲጠቅሙ በር ከፋች ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት በሀገር ደረጃ ያለውን የትምህርት ጥራት ችግር በከፍተኛ ሁኔታ ያሻሽለዋል ብለው እንደሚያምኑ የሚናገሩት መምህሩ ውድድሩ በታዳጊ ተማሪዎች ላይ መሥራቱ በቀላሉ የበለፀገች ሀገር ለመፍጠር እንደሚረዳም ገልጸዋል፡፡ በሀገር ውስጥ እንዲህ ዓይነት ውድድሮች መለመዳቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የማትስ ኦሎምፒያ ላይ ለመወዳደር ይረዳል፡፡ ጥሩ ሳይንቲስቶችን ማፍለቂያ መንገድ ሊሆን ይችላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የደብረ ማርቆስ የትምህርት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ መኩሪያ የሂሳብ ትምህርት ውድድር ዋናው ዓላማ የሂሳብ ትምህርት በአስተሳሰብ፣ በአመለካከትና በተግባር ከባድ ነው የሚለውን አስተሳሰብ የሚያስቀር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ሕፃናቶች በዚህ ሂደት ማለፍ መቻላቸው ወደ ፊት ለምርምርና ለፈጠራ ቅርብ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ እንዲሁም የብሩህ አዕምሮ ባለቤት በመሆን በሁሉም የትምህርት ዘርፍ ፈላስፋና ለችግሮች ሁሉ መፍትሔ አፈላላጊ እንዲሆኑ የሚያግዛቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ተማሪዎችን በሂሳበ ትምህርት በማወዳደር የሚታ ወቀው የሰሮባንና የማይንድ ፕላስ ማትስ ማህበር ምክትል ሥራ አስኪያጁ አቶ ከበደ አጥናፉ እንደተናገሩት የሂሳብ ትምህርት ውድድር መካሄዱ በሀገር ደረጃ ከፍተኛ ጥቅም አለው፡፡ በሳይንስና በፈጠራ ዘርፍ ፈጣን ተማሪዎችን ለመፍጠር እንዲሁም ሀገራችን ያለባትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በመፍታት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንድትሆን ያስችላታል፡፡ ተማሪዎች በቀላሉ የሂሳብ ስሌቶችን ተጠቅመው ማንኛው ንም ጥያቄ ለመመለስ ይረዳቸዋል፡፡
ውድድሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን ከስምንት ከተሞች የተውጣጡ ተማሪዎች ተሳትፈውበታል፡፡
አዲስ ዘመን ነሀሴ 12/2011
ሞገስ ፀጋዬ