አሜሪካ በሱዳን ላይ የኬሚካል ጦር መሣሪያ ተጠቅማለች በሚል ማዕቀብ ጣለችባት

በሱዳን በቀጠለው የእርስ በርስ ጦርነት ባለፈው ዓመት የሱዳን መንግሥት በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (አርኤስኤፍ) ላይ የኬሚካል ጦር መሣሪያ ተጠቅሟል በማለት በሱዳን ላይ አዲስ ማዕቀብ እንደምትጥል የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታወቀ።ከሰኔ 6 ጀምሮ አሜሪካ ወደ ሀገሪቱ የምትልካቸው ምርቶች እንደሚገደቡ እና የፋይናንስ ብድር ገደቦች ተግባራዊ ይሆናሉ ሲሉ ቃል አቀባዩ ታሚ ብሩስ ተናግረዋል።

ከእዚህ ቀደም የሱዳን ጦር እና የፈጥኖ ደራሽ አማፂያኑ በግጭቱ ወቅት የጦር ወንጀሎችን ፈጽመዋል በሚል ተከሰው ነበር።አሜሪካ ለወሰደችው ርምጃ ምላሽ ለማግኘት የሱዳንን ባለሥልጣናት ቢጠይቁም እስካሁን መግለጫ አለማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት የሱዳን ጦር እና አርኤስኤፍ መካከል በተፈጠር የሥልጣን ሽኩቻ በተቀሰቀሰው ግጭት ከ150 ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል።ባለፉት ወራት የሱዳን ጦር ዋና ከተማዋ ካርቱምን ቢቆጣጠርም ውጊያው አሁንም እንደቀጠለ ነው።አሜሪካ የትኛውን የኬሚካል ጦር መሣሪያ ጥቅም ላይ እንደዋለ የተገለጸ ነገር የለም።ሱዳን ብዙ ጉዳት፣ ስቃይ እና አለፍ ሲልም ሊገድል የሚችለውን ክሎሪን ጋዝ ለሁለት ጊዜያት ተጠቅማለች ሲል ኒውዮርክ ታይምስ በጥር ወር ዘግቧል።

“የሱዳን መንግሥት ሁሉንም የኬሚካል ጦር መሣሪያዎች አጠቃቀም እንዲያቆም እና የዓለም አቀፍ መርህ ስር ያሉትን ግዴታዎች እንዲወጣ ዩናይትድ ስቴትስ ትጠይቃለች” ብሏል በመግለጫው።በዓለም አቀፉ የኬሚካል ጦር ስምምነት መሠረት ፈራሚ ሀገራት የያዙትን የጦር መሳሪያ ክምችት ለማስወገድ ቃል ገብተዋል።በዩናይትድ ስቴትስ መቀመጫውን እንዳደረገው አርምስ ኮንትሮል አሶሴሽን ከሆነ፤ ስምምነቱን ከግብጽ፣ ከሰሜን ኮሪያ እና ከደቡብ ሱዳን በስተቀር ሱዳንን ጨምሮ ሁሉም ሀገራት ፈርመዋል።

እስራኤል ስምምነቱን ብትፈርምም ግን ፊርማዋን አላጸደቀችውም። ይህ ማለት በስምምነቱ ውስጥ መግባቷን በሕጋዊ መንገድ አላረጋገጠችም ሲል ተቋሙ ገልጿል።ብሩስ አክለውም “ዩናይትድ ስቴትስ ለኬሚካል ጦር መሳሪያ መስፋፋት አስተዋፅኦ የሚያደርጉትን ተጠያቂ ለማድረግ ሙሉ በሙሉ ቁርጠኛ ነች።”አሜሪካ በሱዳን ላይ ማዕቀብ ስትጥል ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም። በጥር ወር በግጭቱ ውስጥ በተሳተፉት የሁለቱም ወገን መሪዎች ላይ ማዕቀብ ጥላለች።

የሱዳኑ ወታደራዊ መሪ አብዱልፈታህ አል ቡርሃን “ሱዳንን በማተራመስ እና የዲሞክራሲ ሽግግር ግብን ማፍረስ” የሚል ክስ የቀርበባቸው ቢሆንም፤ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “እንግዳ እና አሳሳቢ” ሲል አውግዞታል።የአርኤስኤፍ መሪው መሃመድ ሃምዳን ዳግሎ (ሄሜቲ) በሀገሪቱ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲፈጸም ቆርጠዋል ሲሉ በቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ተከሰዋል።ሁለቱም ወገኖች ላለፉት ሁለት ዓመታት ሥልጣን ለመቆጣጠር ሲፋለሙ ቆይተዋል።በእዚህም የተነሳ ወደ 12 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ሲፈናቀሉ እና 25 ሚሊዮን ሕዝብ ደግሞ የምግብ ርዳታ ጠባቂ ሆኗል።

በቀደምት ርምጃዎች ምክንያት አዳዲስ ማዕቀቦች በሀገሪቱ ላይ ብዙም ተጽዕኖ አይኖራቸውም ሲል ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።የአሁኑ የአሜሪካ ርምጃ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በግጭቱ ውስጥ በመሳተፏ ዙሪያ ውጥረት እንዲፈጠር አድርጓል።የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ እና ሱዳን እስከእዚህ ወር መጀመሪያ ድረስ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የነበራቸው ቢሆንም፤ የሱዳን መንግሥት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለአርኤፍኤፍ የጦር መሣሪያ ሰጥታለች በማለት ከሷል። የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ውንጀላ አልተቀበለችውም።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሳምንት በባሕረ ሰላጤዋ ሀገር ያደረጉትን ደማቅ ጉብኝት ተከትሎ በኮንግረስ የሚገኙ ዲሞክራቶች፣ አሜሪካ ለተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ለመሸጥ ያቀደችውን የጦር መሳሪያ በከፊል ለማገድ ሞክረዋል።ምክንያት ያሉት ደግሞ የተባበሩት አረብ ኤሚሬት በግጭቱ ውስጥ እጇ አለበት በሚል ነው።የሱዳን የዲፕሎማቲክ ምንጭ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ከሆነ፤ አሜሪካ አዲሱን ማዕቀብ የጣለችው “በቅርቡ በኮንግረስ ውስጥ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ላይ የተካሄደውን ዘመቻ አቅጣጫ ለማስቀየር” ነው።

በእዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሱዳን በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ላይ ያቀረበችውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ ውድቅ አድርጎታል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።

አሜሪካ እኤአ በ1991 የኬሚካል ጦር መሳሪያ ተጠቅመዋል የተባሉ አገሮች ላይ ማዕቀብ የሚጥል ህግ ያወጣች ሲሆን፤ ሱዳን ዓለም አቀፉን የኬሚካል ጦር መሳሪያ ስምምነትም ፈርማለች።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You