በተወለደችባት ከተማ በፈጠራ የታ ገዘ የንግድ ሥራን ጀምራ ውጤታማ መሆን ችላለች። በአንድ በኩል ቤተሰብ ማስተዳደር፣ በሌላ በኩል ደግሞ በሥራ ቦታ ድርጅት መምራቱን በዕለት ተዕለት ህይወቷ አጣምራ ማስኬድን ተክናበታለች። አንዱም አዳግቷት አያውቅም። ይልቁንም የበለጠ ለመሥራት እየተነሳሳች መሆኑን በርቱዕ አንደበቷ ታስረዳለች። የሚያውቋት ደግሞ ዓላማ እና ጥረት ስላላት ለበለጠ ስኬት እንደምትበቃ ይመሰክሩላታል። በቀይ ደመግቡ ፊቷ ላይ አንድም የድካም ስሜት ከቶ እንደማይ ታይባትም ነው በርካቶች የሚናገሩላት።
በማስታወቂያ ባለሙያነት እና በጋዜጠኝነት ሙያ በተጀመረው የአዋቂነት ዘመኗ ብቻ ተወስና አልቀረችም። ወደ ንግዱ ዓለም በመቀላቀል ምርት እያዘጋጀች መሸጡን ተያይዛዋለች። ከትዳር አጋሯ ጋር በጥምረት በሚሠሩት የጤንነት መጠበቂያ እና የሰውነት እንክብካቤ መስጫ ምርት አማካኝነት ደግሞ በተለያዩ የዓለም ጫፎች ጭምር ታዋቂነትን አትርፎላታል። ወይዘሮ መሰረት አረፋይኔ ይባላል ሙሉ ስሟ፤ የህይወት ተሞክሮዋን እና የንግድ ህይወቷን ልታካፍለን የዛሬዋ እንግዳችን ሆናለች።
በአዲስ አበባ ከተማ የተወለደችው ወይዘሮ መሰረት ያደገችውም ኮልፌ ክፍለ ከተማ ዕንቁላል ፋብሪካ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። በወቅቱ ፀጥ ባለው እና የወፍ ጫጫታ ብቻ በሚሰማበት አካባቢ በልጅነቷ እንደማንኛውም ሕፃን ተጫውታ እና ቦርቃ ብታድግም ለሥዕል እና ለተረት ልዩ ፍቅር እንደነበራት አትዘነጋውም። የሰፈር ልጆችን ሰብስባ ተረት በዜማ መንገር ያስደስታት እንደነበር ታስታውሳለች። ለቤተሰቧ አራተኛ ልጅ ብትሆንም ከታላላቆቿ በላይ ቤት ውስጥ ኃላፊነት የመውሰድ ፍላጎት ነበራት። ሁልጊዜም ጠያቂ በመሆኗ አባቷ ስታድግ ለምን ፖሊስ አትሆኚም እያሉ ጠያቂነቷን በአግራሞት ይመለከቱ ነበር።
አንደኛ ደረጃ ትምህርቷን አዲስ አበባ የተሰኘው ትምህርት ቤት እየተከታተለች ማንበብ እና መጻፉን አቀላጥፋ ስትናገር ደግሞ ሁልጊዜም አዲስ ዘመን ጋዜጣን እንድታነብ ትጠየቃለች። ጠያቂው ደግሞ አባቷ ናቸው። እናም ጋዜጣውን ገልጣ እያንዳንዱን ዜና እስከ የአምድ ጽሑፎችን እያነበበች የምሽት የዕለት ተዕለት ተግባሯ አድርጋው ነበር። እናቷ ደግሞ ታታሪ እና ጠንካራ በመሆናቸው ለእርሷም አርአያ በመሆን ብርታት እንደሰጧት ትናገራለች። የመጀመሪያ ትምህርቷን ስትጨርስ መድኃኒያለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ተከታትላለች።
የልጅነት ሥዕል፣ ተረት እና ምንባቡ ሳታውቀውም ቢሆን ወደኪነጥበቡ ስቧት ነበርና የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ስታመጣ ምርጫዋ ያደረገችው ወደ ቋንቋና ስነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍል ነው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስነ ጽሑፍ እና ቋንቋ ክፍል እየተማረች ከአንድ ሴት ጓደኛዋ ጋር ትተዋወቃለች። ጓደኛዋ ከቀድሞው ዛሚ መልቲሚዲያ የአሁኑ ዛሚ ሬድዮ ባለቤቶች ጋር ዝምድና ነበራትና አልፎ አልፎ እርሷን ይዛት ወደ ቢሯቸው ታመራ ጀመር።
በዛሚም ወይዘሮ መሰረት ከሰዎች ጋር እየተዋወቀች እና እየተግባባች በመምጣቷ ተማሪ እያለች የማስታወቂያ ሥራ ላይ መሳተፍ ጀመረች። ከማስታወቂያ ሥራዎች ባለፈ የተለያዩ ጽሑፎችን ማዘጋጀት እና ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት ላይ መሳተፍ ችላለች።
የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን ስታጠናቅቅ ደግሞ እዚያው ዛሚ ላይ በመቀጠል ከመጀመሪያዎቹ የሬዲዮ ጣቢያው መስራች ጋዜጠኞች ተርታ ተሰላፊ ሆናለች። በሬዲዮ ጣቢያውም በርካታ ሥራዎችን በማቅረብ አድማጮች ዘንድ ድምጿን ታደርስ ነበር። የጋዜጠኝነቱ ሥራ ላይ እያለችም ትዳር መጣ።
በትዳር የተጣመረችው ባለቤቷ ደግሞ በሕፃናት እና እናቶች እንክብካቤ ላይ ጥናቶችን ያከናውን ነበር። እናም ወይዘሮ መሰረት ጽንስ ስትይዝ ባለቤቷ እርግዝናው ችግር እንዳይገጥመው በሚል አንድ የእናቶች ትራስ ማዘጋጀት ጀመረ። ትራሱ ተሠርቶ ሲጠናቀቅ ጋዜጠኛዋ ተመቻችታ እንድትተኛ እና እንድትቀመጥ አጋዥ በመሆኑ ባለትዳሮቹ ሌሎች እናቶችንም ለመርዳት በሚል ትራሱን ሠርቶ ማቅረብ እንደሚ ያስፈልግ ተስማሙበት።
ችግር መፍትሔን ያመጣል በሚለው ብሂል ተመርተው ከወሊድ በኋላም የትራሱን ጥቅም ያዩት ጥንዶች ሲኤም ሲ አካባቢ የሚገኝ አንድ አነስተኛ ቤት ተከራይተው ምርቱን ለማዘጋጀት ይነሳሳሉ። ቤቱንም በስምንት መቶ ብር ተከራይተው በአስር ሺ ብር መነሾ <<ሀ>> ብለው ሥራቸውን ጀመሩ።
ከውጭ አገር ከሚኖር ዘመድ አንድ የአጥንት እና ነርቭ ችግሮችን መከላከያ ክብ ትራስ በማስመጣት ስለአሠራሩ ጥናት ማድረግ ጀመሩ። የማይሞቅ እና መታጠብ የሚችል ጠንካራ ጨርቅ በመፈለግ እንዲሁም ለረጅም ጊዜ በምቾት የሚቆይ ስፖንጅ ፍለጋ ብዙ ጥናቶችን አድርገው የመጀመሪያዎቹን ሦስት ትራሶች በተከራዩት ቤት ማዘጋጀት ቻሉ። አውሮፓ እና አሜሪካ አገራት ታዋቂ የሆነው ነገር ግን ለኢትዮጵያውያን አዲስ የሆነው የነርቭና የአጥንት ችግሮችን መከላከያ የእናቶች እና የሕፃናት ትራስ ምርቱን ይዘው ወደ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት በማቅናት ምዝገባ እና የፈጠራ ሰርተፍኬት ይዘዋል።
ከዚህ በኋላ ትልቁ ሥራ ለተጠቃሚው እና ፋርማሲዎች አሳምኖ የመሸጡ ጉዳይ ነበር። በየሕፃናት ሱቆች ሲያመሩ ግን <<ይህ የቅንጦት ዕቃ ይመስላል ማን ይገዛናል?>> በሚል ምላሽ ምክንያት ሊቀበሏቸው ፍቃደኛ አልሆኑም ነበር። ነገር ግን ይቀመጥና ፈላጊ ሲመጣ ይሸጣል በሚል የገበያ አካሄድ ተጠቅመው 200 ብር የሚሸጡ ደንገል የሚል ስያሜ የተመረቱ ትራሶችን በሕፃናት ልብስ ቤት እና መጫወቻ መሸጫ ቤቶች በዱቤ ሂሳብ አስቀመጡ።
ሐኪሞች ምርቱ ለጤና ጠቃሚ መሆኑን ስላረጋገጡ በየሆስፒታሉ እና መድኃ`ኒት ቤቶች ይሸጥ ጀመር። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ወይዘሮ መሰረት የምትወደውን የጋዜጠኝነት ሥራዋን አልተወችም ነበር።
ምርቱን ለእያንዳንዱ ሻጭ እያስተዋወቁ መሸጥ አድካሚ ቢሆንም ኤግዚቢሽኖች ላይ ቢተዋወቅ ተመራጭ እንደሚሆን በማሰብ ጥንዶቹ አማራጩን ወሰዱ። ኤግዚቢሽን ላይ በቀረቡ ቀን ግን ስለ ምርቱ ዓይነት እና ጥቅሙ በማስረዳት በርካታ ደንበኞችን ማፍራት ችለዋል። በተለይ ደግሞ የደንገል ትራስን ፈጠራ እና ጥቅም የተረዱ በርካታ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን በመስጠታቸው የምርቱ ተቀባይነት በአጭር ጊዜ መናኘት ጀመረ። በርካታ ፈላጊዎችም ውጭ አገራት ድረስ ይዘው በመሄድ ለቤተሰባቸው አገልግሎት ማዋል ጀመሩ።
ወይዘሮ መሰረትም ውስጧ ያለውን የጋዜጠኝነት ሥራ በመተው ለስምንት ዓመት ከሠራችበት ዛሚ ሬድዮ ለቃ ሙሉ ትኩረቷን ወደ ደንገል ትራስ ማምረቻ አዞረች። 2001 ዓ.ም የተቋቋመው ድርጅቱም የማምረቻ ቦታው እና ሠራተኞች ቁጥር እየጨመረ ምርቱን በመላ አገሪቷ ማከፋፈሉን ቀጠለ። የእርግዝና ትራስ፣ የአራስ ሕፃናት መንከባከቢያ፣ የመቀመጫ አጥንት ስብራት ማከሚያ፣ ለወላድ እናት ቁስል ማገገሚያ የሚሆን እና የተለያዩ የአጥንት እና የነርቭ ህክምና የሚረዱ እንዲሁም የጉዞ ትራሶችን በማምረት ለበያ ያቀርባሉ።
አንድ ቀን የደንገል ትራሶችን ጥቅም የተረዱ ካይሮፕራክተር ዶክተር ሰላም ወደ ቢሯቸው ያስጠሯቸዋል። በዚያም የደንገልን አምራቾች የእስከአሁኑን ከሠራችሁ ለጀ ርባ ህመም ማከሚያ የሚሆኑ ሦስት ዓይነት ትራሶችን ማምረት አያቅታችሁም በሚል ያማክሯቸዋል። ወይዘሮ መሰረት ከባለቤታቸው ጋር ስለ ትራሶቹ አመራረት ጥናት ካደረጉ በኋላ አዘጋጅተው ለተጠ ቃሚው ማድረስ ቻሉ። አሁን ላይ በበርካታ የህክምና ተቋማት እና በተለያተዩ ግለሰቦች ቤት የተለያዩ ትራሶች ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጉዞ ትራሶችን እየተረከበ ለመንገደኞች ይሸጣል። በዚህ ዓይነት አካሄድ በወር እስከ አስር ሺ የሚደርሱ የተለያዩ ዓይነት ትራሶች እያመረቱ መሆኑን የሚገልጹት ወይዘሮ መሰረት በአዲስ አበባ ብቻ ስምንት የመሸጫ ሱቆችን እንደከፈቱ ያብራራሉ።
ከመዲናዋ ውጪ ያሉ ደንበኞችን ለማስተናገድ ደግሞ በሐዋሳ እና በመቀሌ ሁለት ሱቆች ተከፍተዋል። በቀጣይም በየክፍለ ሀገሩ በሚገኙ አምራቾችን በማሰልጠን እዚያው እያመረቱ እንዲሸጡ ለማድረግ በሆሳዕና እና ሌሎች ከተሞችም ሱቆች ለመክፈት ድርጅቱ ዕቅድ ይዟል። ሲኤምሲ አካባቢ በሚገኘው ሕንፃ ከ30 ሺ ብር በላይ ኪራይ በመክፈል በየዓመቱ የብዙዎችን ህመም እና ድካም የሚቀንሱ ከጤና ጋር የተያያዙ ትራሶችን እያመረተ ይገኛል። አሁን ላይ ወይዘሮ መሰረት ከባለቤቷ ጋር በትንሹ የጀመሩት ሥራ 40 ሠራተኞችን ቀጥሮ የሚያሠራ ትልቅ ማምረቻ ሆኗል።
በቀጣይ ደግሞ ወደተለያዩ የአፍሪካ አገራት ምርቶቹን በመላክ ድርጅቱ እንደሚስፋፋ ወይዘሮ መሰረት ውጥን ይዛ እየተንቀሳቀሰች ነው። ለዚህም የሚረዱ የማስፋፊያ ሥራዎችን እና ማሽነሪዎች ተገጥመው ድርጅቱ በቀጣይ ዓመት የበለጠ አድጎ እንደሚገኝ ተስፋ አድርጋለች። ይሁንና የማምረቻ ቦታ እጥረት ትልቁ ፈተና እንደሆነባት አትሸሽግም።
‹‹በርካቶች የማይሠሩበትን ቦታ ተረክ በው ሲሸጡ እንዳልነበር ለእኛ የሚሆን መስሪያ ቦታ ማግኘት አለመቻሉ ያሳዝናል›› ስትልም ትገልጻለች። በመሆኑም የሚመ ለከታቸው የመንግሥት አካላት የማምረቻ ቦታውን ቢያመቻቹ ድርጅቱ ለበርካቶች የሚያስፈልጉ ምርቶቹን በስፋት እያመረተ ማደግ ይችላል። አልፎ ተርፎም ምርቶቹን ወደውጭ በመላክ ለሀገር ምንዛሬ ማስገባት የሚችል አቅም እንዳለው ታስረዳለች። ሥራውን በእራስ ጥረት ተሠርቶ ውጤታማ ማድረግ ቢቻልም ለበለጠ ስኬት ግን የይፋናንስ ተቋማት እና የመሬት አስተዳደር አካላት እገዛ አስፈላጊ መሆኑን ትናገራለች።
‹‹ሥራ ልክ እንደ ልጅ ነው›› የምትለው ወይዘሮ መሰረት፤ በቅርብ እየተከታተሉ እና እየደገፉ ማሳደግን ይጠይቃል ባይ ነች። እንደ እርሷ አስተያየት፤ ትኩረት ካልተደረገበት ንግድ አዋጭ አይሆንም። በመሆኑም ሥራ ለመጀመር የሚያስቡ ሰዎች በተለይ ደግሞ ሴቶች ዋናው ጉዳይ ገንዘብ ሳይሆን ራዕይ እና ትኩረት መሆኑን መገንዘብ እንዳለባቸው ትመክራለች። ገንዘብ ከሥራ በኋላ የሚመጣ ጉዳይ መሆኑን በመረዳት ፈተናዎችን አልፎ በጥንካሬ የመሄድ ጥበብን መላበስ አስፈላጊ መሆኑንም ታሰምርበታለች።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 11/2011
ጌትነት ተስፋማርያም