ወርሐ ነሐሴ የአዲስ ዓመት ዋዜማ ስለሆነ ሽርጉድ ይበዛበታል። ከወሩ መጀመሪያ ቀን ጀምሮ እንደ አሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል የመሳሰሉ የልጃገረዶች ጨዋታዎች ይጀመራሉ። እነዚህ ጨዋታዎች ሰፊ የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን ስላላቸው ይታወቃሉ። በትግራይ ክልል አሸንዳ፣ በአማራ ክልል ደግሞ ሻደይ፣ በዋግህምራ አሸንድዬ፣ በላስታ ላሊበላ ሶለል በራያና ቆቦ ይከበራሉ። እነዚህ የልጃገረዶች በዓላት ስለሚታወቁ ስለሌሎች እናውራ።
ይህኛውም የልጃገረዶች ጨዋታ ሲሆን በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የሚከወን ነው። በሰሜን ሸዋ፣ በደቡብ ወሎ እና በምሥራቅ ጎጃም አካባቢዎች ይከበራል። በምሥራቅ ጎጃም እና ከምሥራቅ ጎጃም ጋር በሚዋሰነው የሰሜን ሸዋ አካባቢ ‹‹ከሴ አጨዳ›› ተብሎ ይጠራል። ከሴ ጥሩ መዓዛ ያለው የተክል ዓይነት ሲሆን ነሐሴ 16 ቀን ልጃገረዶች ይህን ተክል አጭደው በየመንደሩ እየዞሩ ይጥላሉ። ከሴ አጨዳ የተባለው በዕለቱ ልጃገረዶች ከሴ የተባለውን ተክል ስለሚያጭዱ ነው።
ስለሥርዓተ ክዋኔው በሌላ ማብራሪያ እንገናኛለን። በዚህ ጽሑፍ ትኩረት የሚደረገው የቃል ግጥሞች ላይ ነው። እነ አሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል የበዓላት ቀን ይቀመጥላቸው እንጂ ወርሐ ነሐሴ በሙሉ የልጃገረዶች የጨዋታ ወር ነው። የአዲስ ዓመት መምጣትን፣ የምድሩ በአበባ መፍካትን ለመቀበል ወሩን ሙሉ ይጫወታሉ።
በጨዋታቸው ውስጥ የሚተላለፈው መልዕክት ነው ቀልብን የሚገዛው። ተስፋን፣ ፍቅርን፣ አብሮነትን የሚናገሩ ዘፈኖችን ይዘፍናሉ። ዘፈኖቹ አብዛኛውን ጊዜ የቃል ግጥሞች ናቸው። ወደዘፈኖቹ ከመግባታችን በፊት እግረመንገድ ስለቃል ግጥም አንድ ጥናት ዋቢ አድርገን እንንገራችሁ!
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ የሂዩማኒቲስ፣ የቋንቋዎች ጥናት፣ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩ ኒኬሽን ኮሌጅ የአማርኛ ቋንቋ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ትምህርት ክፍል ለድህረ ምረቃ መርሐ ግብር ሀብታም ግዛት የተባሉ አጥኚ በሠሩት ጥናት፤ ‹‹ ስነ ቃል ከፎክሎር ዘውጎች አንዱ ነው። ቃል ግጥም ደግሞ ከስነ ቃል ዘርፎችአንዱ ነው።
ቃል ግጥም በመዜምና በመንጎርጎር በቃል የሚፈጠር ሲሆን የራሱ የሆነ የመከወኛ አጋጣሚ፣ ከዋኝና ታዳሚ አለው። በዚህ ፈጠራ ህዝብ አመለካከቱን፣ ስሜቱን፣ ፍላጎቱን፣ ድጋፍና ተቃውሞውን ይገልጽበታል›› ይላሉ።
እዚህ ላይ ስነቃል እና የቃል ግጥም ልዩነት እንዳለው እንረዳለን። ስነቃል ማለት ግጥም ባይሆንም ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲወራረድ የመጣ በቃል የሚነገር ሁሉ ነው። የቃል ግጥም ማለት ግን በእንጉርጉሮ የሚባለውና የግጥም ስንኝ ያለው ነው። ወደ ልጆቹ ጨዋታ እንግባ!
ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ይህ ጽሑፍ የሚያተኩረው በምሥራቅ ጎጃም፣ ሰሜን ሸዋና ደቡብ ወሎ አካባቢ በሚነገሩ የቃል ግጥሞች ላይ ነው (የቃል ግጥም ከአካባቢ አካባቢ ሊለያይ ስለሚችል)። ልጅአገረዶች በዚህ ወር ሲጫወቱ እርስበርስ ተጠራርተው ነው። ታዲያ በበጋ ወቅት ያገባች ጓደኛቸው ካለች አብራቸው አትሄድም፤ ምክንያቱም በዓሉ ላላገቡ ሴቶች ብቻ ነው። በጋብቻ የተለየቻቸው ጓደኛቸው ካለች እንደመታደል አይቆጥሩትም፤ ማግባቷን አይደግፉትም። በእነዚህ አካባቢዎች ደግሞ ያለዕድሜ ጋብቻ ይበዛል፤ እንዲህ ዓይነት ጨዋታ ብዙም ሳትጫወት ልታገባ ትችላለች። ይህን ድርጊት ለመቃወም ልጃገረዶቹ እንዲህ እያሉ ይዘፍናሉ።
ከሴ አጨዳ መጣ፤ አይምጣ ይመለስ
እንቁጣጣሽ መጣ፤ አይምጣ ይመለስ
መስቀልም መጣ፤ አይምጣ ይመለስ
ቆንጆቹ አልቀዋል ጨፌውም ይታረስ!
‹‹ቆንጆ›› ማለት በጎጃም አካባቢ ያላገባች(ልጃገረድ) ማለት ነው። የዚህ ቃል ግጥም መልዕክት፤ ቆንጆዎቹ በልጅነታቸው እየተዳሩ ተቸግረናል፤ እነ ከሴ አጨዳ፣ እንቁጣጣሽና መስቀል ሲመጡ ብዙ ቆንጆ በሌለበት ማክበር አይቻልም፤ ለጨዋታ የሚሆነው አበባና ጨፌ እየባከነ ነው፤ ስለዚህ ካልተጫወትንበት ‹‹ይታረስ›› የሚል እልህ የሚመስል መልዕክት ነው።
ከወርሐ ነሐሴ ቀጥሎ የሚገባው በአበባው የሚታወቀው መስከረም ነው። ይሁን እንጂ የአበባማ ተክሎች የሚበቅሉት ደግሞ በሐምሌና ነሐሴ ነው፤ አንዳንዶቹም ነሐሴ ውስጥ ይበቅላሉ። የአበባ ነገር ያው ሁላችንም የምናውቀው ነው፤ የውበት መገለጫ ነው። በአበባ ስም ፍቅረኛ ይወደሳል። በእንዲህ ዓይነት ጨዋታዎች ልጃገረዶች እንዲህ እያሉ ይዘፍናሉ።
አበባው አበበ ንቡም ገባልሽ
እንግዲህ የአገር ልጅ ማር ትበያለሽ
የሰምና ወርቅ ባህሪ አለው። በአበባ ወቅት ንብ በብዛት ይታያል። ንብ በዛ ማለት ያው ማር ይበላል ማለት ነው። በሌላ በኩል ግን እነዚህ ልጃገረዶች ከፍቅረኞቻቸው ጋር የሚገናኙት በእንዲህ ዓይነት ጨዋታዎች ነው። በሰኔ እና በሐምሌ ወራት ሥራ ስለሆነ አይገናኙም። በእነዚህ በዓላት ግን ነፃነት ይሰጣቸዋል። አበባ ማበብ ሲጀምር እነዚህ በዓላት የሚመጡበት ነውና ፈቅረኛቸውን ይናፍቃሉ። ‹‹ፍቅረኛ ተገኘ›› ማለት ማር ተበላ ማለት ነው።
እንዲህ ዓይነት በዓላት የግድ ፍቅረኛ(የከንፈር ወዳጅ) ላላቸው ብቻ አይደለም። የከንፈር ወዳጅ የሌላቸውም የሚያገኙበት ነው። በጨዋታው ዕለት የከንፈር ወዳጅ ያላቸው ሲጫወቱ የሌላቸውም አዲስ ይጀምራሉ። ይሄም ያልተሳካላቸው ደግሞ እንዲህ እያሉ ያንጎራጉራሉ።
አበባው ያብባል በየሁሉ ደጅ
ምነው እኔ የለኝ የከንፈር ወዳጅ
ይችኛዋን ዘፈን የሚጠቀሟት ወንዶች ናቸው። በጨዋታው ውስጥ ሴቶች ይፈራሉ፤ ያፍራሉ፤ ወንዶች ደፈር ይላሉ። ማታ ወደቤት ሲገቡም ቁጣው የሚጠነክረው ሴቶች ልጆች ላይ ነው። ለዚህም ነው በጨዋታው ላይ እንዲህ የሚሉት ። (ይህ የቃል ግጥም የእጅጋየሁ ሽባባው ዘፈን ውስጥ አለ)።
አንተ የከንፈር ወዳጅ በጊዜ ሳመኝ
ጤፍ አበጥራለሁ የሰዉ ግዙ ነኝ
የሰዉ ግዙ ሆኖ የሰዉ ግዙ መውደድ
እሳት በገለባ እፍ ብሎ ማንደድ!
ልጆቹ የሰው ቤት ሠራተኛ ባይሆኑም ወላጆቻቸው እንደልብ አይፈቅዱላቸውም። በዚያ ላይ ደግሞ የሰው ቤት ሠራተኛ መሆንም አለ፤ ያ ደግሞ የባሰ ይከብዳል። በዚህ ሁኔታ ፍቅር ከያዘ እሳት እንደማንደድ ነው፤ ምክንያቱም ከወደዱት ሰው ጋር መገናኘት አይቻልማ!
በዚህ ጨዋታ ውስጥ መወዳደስ ብቻ ሳይሆን በነገር መጎሻሸምም አለ። በተለይም በተቃራኒ ጾታዎች ላይ ይጠነክራል። ሴቶች ለወንዶች፤ ወንዶችም ለሴቶች የንቀት መልዕክት ያስተላልፋሉ። ሴቶች ወንዶችን ሲንቁ በአካላዊ ገጽታውና በስነ ልቦናው(ፍርሐትና ጀግንነት) ላይ በመመስረት ነው። ለምሳሌ በአካላዊ ገጽታው ከሆነ እንዲህ ብለው ጎሸም ያደርጉታል።
ልሳምሽ አለኝ አለማፈሩ
የበጋ ኩበት መስሎ ከንፈሩ!
የከንፈር ወዳጅ ከሌለውም የንቀት መልዕክት ይተላለፍለታል። ወዳጅ ያላቸው ወንዶች ከፍቅረኛቸው ጋር ለመገናኘት ሲያንዣብቡ የሌለው ደግሞ ከርቀት ሆኖ ያያል፤ ወይም ፈራ ተባ እያለ ይጠጋል። ለእንዲህ ዓይነቱ ደግሞ እንዲህ ብለው ይዘፍናሉ።
ምን ታደርጋለህ ከቁልቋሉ ሥር
የቆንጆ ወዳጅ ያለህ ይመስል!
የከሴ አጨዳ ዕለት ብቻ ሳይሆን በሌሎች ቀናትም ይጫወታሉ። የሚጫወቱት በእንጨት ሰበራ እና ኩበት ለቀማ አካባቢ ነው። በደጋማ አካባቢዎች ኩበት ለቀማ የሚባል ሲሆን በቆላማ አካባቢዎች እንጨት ሰበራ ነው የሚባለው። ልጃገረዶቹም ሆኑ ጎረምሶች የሚሄዱት ከእንጨት ሰበራው ይልቅ እርስበርሳቸው ለመገናኘት ነው። ወላጆች በእንጨት ሰበራ ስም ቢልኳቸውም ከከንፈር ወዳጆቻቸው ጋር እንደሚጫወቱ ያውቃሉ፤ እንዲያውም አንዳንድ ወላጆች የእገሌ ልጅ የእገሊት ወዳጅ ነው ሁሉ ይባባላሉ። ወደ እንጨት ሰበራ ሲሄዱም ተኳኩለውና ተቆነጃጅተው ነው። ለዚህም የዘፈናቸው መልዕክት ይመሰክራል።
ራሴን ስሪኝ ጭራ በጭራ
ቆላ እወርዳለሁ እንጨት ሰበራ!
እንጨት ሰበራ ለእነዚህ ልጆች የፍቅር ጊዜ ማሳለፊያ ነው፤ እንዲያ ባይሆን ኖሮ ለእንጨት ሰበራ ፀጉርን በአዲስ መልክ መሠራት አይገባም ነበር። ‹‹ጭራ በጭራ›› የሚለው በቀጭኑ ለማለት ነው። በልጃገረዶችም ሆነ በጎረምሶች ቀጭን ሹሩባ ይወደዳል።
በእንጨት ሰበራ ጊዜም ሆነ በከሴ አጨዳ ጨዋታ ጎረምሶች ሊጣሉ ይችላሉ። በጠቡ ውስጥ ድብድብ ይኖራል። የሚጣሉት ደግሞ የአንዱን የከንፈር ወዳጅ አንዱ ከነካት ነው። የከንፈር ወዳጁም ባትሆን አንዱ የሚፈልጋትን ሌላው ከነካት ሊደባደቡ ይችላሉ። በጨዋታው ልጃገረዶች በስጋት ውስጥ ነው የሚቆዩት። ጥርጣሬ ካላቸው እንዲህ እያሉ ይዘፍናሉ።
ቦለል ቦለል በይ እንደምንሽር
ይሄ ጨዋታ ሳይል ምንሽርሽር
ከጠብና ከድብድብ በኋላ ሰላማዊ ጨዋታ ስለማይኖር ቶሎ እንጫወት ማለታቸው ነው። ወይ ከድብድቡ ወይ ከጨዋታው ሳይሆን አንድ ቦታ ቆሞ ወይም ተቀምጦ የሚያስተውለውን ደግሞ በነገር ወጋ ያደርጉታል።
ዛርጤው ዝርጥርጥ
ዛርጤው ምንጣፉ
የተደገፈው ደረቀ ዛፉ!
‹‹አራዳ›› እና ‹‹ፋራ›› የሚሉ ቃላት ባይጠቀሙም ነገሮችን በቀላሉ የሚረዳ እና ቶሎ የማይረዳ እኩል አይደሉም። በአራድኛው ‹‹ሙድ›› የሚባለውን ነገር እነርሱም ይጠቀሙታል። ለምሳሌ ይህን ዘፈናቸውን እንየው!
ይሄ ምን ይላል እግረ ወልቻማ
ያቺን ልጅ ጠቅሶ አላት ‹‹ነይማ››
የመጀመሪያው ስንኝ አካላዊ ገጽታን የሚያመለክት ቢሆንም ሁለተኛው ስንኝ ግን መልዕክቱ ስነ ልቦናዊ ነው። መንገር የተፈለገውም ‹‹ፋራ›› መሆኑን ነው። እንደሚታወቀው በባህላችን ወንድ ነው የሚጠይቅ። ሲጠይቅ ደግሞ ‹‹ነይ›› በማለት ሳይሆን እሷ ወዳለችበት ራሱ በመሄድ ነው።
በወርሐ ነሐሴ የሚጀመረው የልጃገረዶች ጨዋታ ሌሎች በእንቁጣጣሽና መስቀልም ይቀጥላል። ጊዜው ሲደርስ እንደየወቅታቸው እናያቸዋለን። መልካም በዓል!
ልጃገረዶች በጨዋታ ጊዜ የሚጠቀሙት ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ፤ (አታሞ)
ቃል ግጥም በመዜምና በመንጎርጎር በቃል የሚፈጠር ሲሆን የራሱ የሆነ የመከወኛ አጋጣሚ፣ ከዋኝና ታዳሚ አለው። በዚህ ፈጠራ ህዝብ አመለካከቱን፣ ስሜቱን፣ ፍላጎቱን፣ ድጋፍና ተቃውሞውን ይገልጽበታል››
አዲስ ዘመን ነሀሴ 11/2011
ዋለልኝ አየለ