የተወለዱት በቀድሞ ወሎ ክፍለሃገር ቦረና አካባቢ ሲሆን እስከ 8ኛ ክፍል እዚያው ተምረዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ደሴ በሚገኘው ወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። ከዚያም ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በመምህርነት ዲፕሎማቸውን ካገኙ በኋላ በትግራይና በኮምቦልቻ ለሦስት ዓመታት በአስተማሪነት አገልግለዋል። በመቀጠልም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሲቪል ምህንድስና ዘርፍ አገኙ። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አየርላንድ ብሄራዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሃድሮሎጂ ትምህርት ፤ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ ሲዊዲን ስቶክሆልም ውስጥ የሮያል ኢንስቲዩት ኦፍ ቲክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በውሃ ምህንድስና ዘርፍ ማግኘት ችለዋል። ከረዳት መምህርነት ጀምሮ በተለያዩ ሥራዎች ለ13 ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አገልግለዋል። በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም በዲንነት ለአንድ ዓመት ከሠሩ በኋላ ተመልሰው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምጣት ማስተማራቸውን ቢቀጥሉም እርሳቸውን ጨምሮ 40 የሚሆኑ መምህራን ባልታወቀ ምክንያት እንዲሰናበቱ ተደርገዋል። ምንም እንኳ ከሚወዱት ሙያ ያለ አግባብ ቢሰናበቱም በዚህ ተስፋ ሳይቆርጡ በተለየዩ ድርጅቶች ከፕሮጀክት እስከ ተፋስስ ልማት ድረስ በአማካሪነት ሠርተዋል።
በአገሪቱ የፖለቲካ ስርዓት ኢ ዲሞክራሲያዊ ነው ብለው በመቃወም የኢዴአፓ መድህን ከሌሎች የትግል አጋሮቻቸው ጋር በመሆን መስርተዋል። ለአምስት ዓመታትም የፓርቲው ፕሬዚዳንት ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፤ በ1997 ዓ.ም በተደረገው ምርጫ ከዝግጅት እስከ ፍፃሜው ድረስ በወቅቱ በነበረው ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ/ቅንጅት/ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል። ከምርጫው በኋላ ግን በአገሪቱ በነበረው የፖለቲካ ሁኔታ ምክንያት ወደ ሲዊድን በመሄድ ለ12 ዓመታት በተማሩበት የውሃ ምህንድስና ዘርፍ በመምህርነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ደግሞ ዳግም ወደ አገራቸው ተመልሰው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ላይ ይገኛሉ። የዛሬው የዘመን እንግዳችን ዶክተር ኢንጅነር አድማሱ ገበየሁ ሲሆኑ ወደ አገራቸው የመጡበትን ምክንያት፥ ስለወቅታዊው ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገናል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- ከአገርዎ ተሰደው በቆዩባ ቸው 12 ዓመታት በምን ሁኔታ ላይ እንደነበሩ በማስታወስ ውይይታችን እንጀምር?
ዶክተር ኢንጅነር አድማሱ፡- ከአገሬ ከወጣሁ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ሲዊዲን ስቶክሆልም በምርምር ሥራ ላይ ነበር የቆየሁት። ከስድት ወር ቆይታ በኋላ የዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት ተቀጠርኩ። በዚያ ድርጅት አማካኝነትም በበርካታ የአፍሪካ አገራት ላይ የመሥራት ዕድሉን አግኝቻለው። ከእነዚህም መካከል ሩዋንዳ፥ ቡሩንዲ፥ ሞዛምቢክ፥ ደቡብ ሱዳንና ታንዛኒያ የሚገኙበት ሲሆን እነዚህ አገራት የሚጋሯቸውን ተፋሰሶች ላይ ጥናት አድርጌያለሁ። በአማካሪነት፣ በጥናት፣ በመጠጥና ውሃ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች፣ በስልጠና፥ በምርምርና በቡድን መሪነትም ተሳትፌያለሁ። በነገራችን ላይ ምንም እንኳን አገሬን በምፈልገው ደረጃ ያህል ባላገለግልም በዓለምአቀፍ ደረጃ የተሳተፍኩባቸው ጥናቶች ለእኔ ሌላ ትምህርት ቤት ነው የሆኑልኝ።
ወደ ሲዊዲን ስሄድም ሆነ በነበረኝ ቆይታ በኢትዮጵያ ከነበረው ጥሩ ያልሆነ የፖለቲካ ሁኔታ የተነሳ ዳግም ወደ አገሬ እመለሳለሁ የሚል ሃሳብ አልነበረኝም። ይሁንና ምስጋና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ይሁንና በህልምሜም በውኔም አስቤው የማላውቀውን ዳግም ወደ አገሬ መግባት ችያለሁ። ታስታውሽ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን እንደመጡ መምህራን ሰብሰበው ካነጋገሩ በኋላ በተለያየ ምክንያት ከአገራቸው የተሰደዱ መምህራን ወደ አገራቸው ተመልሰው ህዝባቸውን እንዲያገለግሉ ጥሪ አቅርበው ነበር። እኔም ይህንን ጥሪ እንደሰማሁ ምንም ሳላመነታ ከቤተሰቤ ጋር ከተማከርኩ በኋላ የሁልጊዜ መሻቴ የሆነውን አገሬን የማገልገል ህልም ለማሳካት በ2010 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ተመልሼያለሁ። እንደመጣሁ በቀጥታ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመሄድ ማገልገል እንደምፈልግ ነገርኳቸውና እነሱም ጥያቄን ተቀብለው ይኸው አሁን አምስት ኪሎ በሚገኘው የሳይንስና ቴክሎጂ ትምህርት ቤት በማስተማር ላይ እገኛለሁ።
በነገራችን ላይ እኔ ወደእዚህ ልመጣ ስል በሌሎች ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች እንዳስተምር ጥያቄ ቀርቦልኝ ነበር። ነገር ግን ከአገሬ በላይ የማስቀድመው ስለሌለ ጥያቄያቸውን ወደ ጎን ብዬ መላ ቤተሰቤን እዚያው ሲዊድን ውስጥ ትቼ ነው የመጣሁት። በተለይም መምህርነት በመጀመሪያ የሰለጠንኩበት ሙያ እንደመሆኑ ከልቤ እወደዋለሁ።አከብረዋለሁ። ደግሞም መምህርነት ዘር ማለት ነው፤ ልክ እንደ ዘር መሰለን ማፍራት የሚቻልበት ዘርፍ ነው። ይህ ዕድል በሌላ ሙያ ላይ የለም። ስለዚህ በዚህ ትውልድን የመቅረፅ ሥራ ላይ የበኩሌን አስተዋፅኦ ማድረግ በመቻሌ ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል። ከዚህ በተጨማሪም ከማስተምራቸው ዕጩ ዶክተሮች ጋር ልክ እንደ ቤተሰብ ሆነንና ተቀራርበን የምንሠራ በመሆኑ ድርብ እርካታን ፈጥሮልኛል። ሁልጊዜም ቢሆን ለተማሪዎቼ ቢሮዬ ክፍት ነው፤ በፈለጉበት ሰዓትና ሁኔታ ላይ ሆነው ስልክ ቢደውልሉኝ ቅር አልሰኝም፤ ይልቁንም የሚቻለኝን ሁሉ ድጋፍ አድጌላቸው ውጤታማ የምርምር ሥራ እንዲሠሩ ነው የእኔ የቀን ተቀን መሻቴ።
አዲስ ዘመን፡- የሞቀ ደመወዝና ኑሮ ትተው ወደ አገርዎ ተመልሰው ከመጡ አንድ ዓመት ገደማ እየሆነዎት ነው፤ በቆይታዎ ደስተኛ ነዎት? እስከአሁን ባለው ሁኔታስ ለምን መጣሁ የሚል ቁጭት ተፈጥሮብዎ ያውቃል? በተለይ በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ ሊፈቱ የይባሉ የሚሉትስ ችግር የለም?
ዶክተር ኢንጅነር አድማሱ፡- የአጠቃ ላዩን አላውቅም፤ ምክንያቱም ገና ራሴን ከሁኔታው አላደባለቅሁም። ነገር ግን ከማስተምራቸው 31 ተማሪዎች ጋር በመመካከር እየሠራሁ በመሆኔ በጣም እርካታ አለኝ። እንዳልኩሽ ከተማሪዎቼ ጋር ያለኝ ግንኙነት የመምህርና የአስተማሪ ሳይሆን የቤተሰብ ስለሆነ ውጤታማ እንዲሆኑ የበኩሌን እገዛ ነው እያደረኩ ያለሁት። በዚህ ደስተኛ ነኝ። ደግሞም እኔ ወደዚህ የመጣሁት በገዛ ፍላጎቴና ነገ ሲያልፍ ለአገሬ ማበርከት የሚገባኝን ነገር ሳላበረክት ባልፍ እንዳይቆጨኝ በማሰብ ነው። ለዚህ ዓለማዬ መሳካት ደግሞ ተማሪዎቼ የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ። ስለዚህ በዚህ በኩል ለምን መጣሁ ብዬ የምቆጭበት ነገር የለም። እኔ ስለኑሮዬ አላስብም፤ ልጆቼም ከእኔ የሚጠብቁት የለም። ስለዚህ ሥራዬ ለተማሪዎቼ ያለኝን ዕውቀትና ልምድ ማካፈል ብቻ ነው።
በሌላ በኩል ግን ዩኒቨርሲቲው የቀጠረኝ የዛሬ 30 ዓመት በነበረኝ ደረጃ ላይ ብቻ መሆኑ ትንሽ ቅር አሰኝቶኛል፤ ምንም እንኳ ስለሚከፈለኝ ገንዘብ ባልጨነቅም ያለኝ የሥራ ልምድና የትምህርት ደረጃ ከግምት ውስጥ በማስገባት በሚመጥነኝ ቦታ ላይ እንድቀመጥ በደብዳቤ ለዩኒቨርሲቲው ሴኔት አቅርቤያለሁ። ይሁንና እስከአሁን አጥጋቢ ምላሽ አላገኘሁም። ይህን ስል ግን ሁሉም ልብ እንዲልልኝ የምፈልገው ዳግም አገሬ ተመልሼ ህዝቤን ማገልገል መቻሌ ከምንም በላይ የሚያስደስተኝ መሆኑን ነው።
አዲስ ዘመን፡- እስቲ ወደ ኋላ ልመልስዎ እና እርሶ የውሃ ኢንጅነሪንግ ምሁር ሆነው ሳለ ወደ ፖለቲካው ዓለም የገቡበት ምክንያት ምን እንደነበር ያስታውሱን?
ዶክተር ኢንጅነር አድማሱ፡- በአ ጠቃላይ በትምህርት ባገኘነው ዕውቀት ብቻ ሳይሆን ዜጋ በመሆናችን በሁሉም ዘርፍ መሳተፍ አስፈላጊ እንደሆነ አምናለሁ። እኔ ወደ ፖለቲካው ከመግባቴም በፊት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለህብረተሰቡ የሲቪክ አገልግሎት መስጠት ያስደስተኝ ነበር። የማምንበትን አስተሳሰብ በሚቻለኝ ሁሉ የመግለጽና በኑሮዬ ውስጥ የመቀላቀልም ልምድ ነበረኝ። ከዚህ ቀደምም ቢሆን በዚሁ ዩኒቨርሺቲ ውስጥ እያለሁ «ይፍሩ» በሚባል ድርጅት በርሃብ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች በተለያየ መንገድ እንዲቋቋሙ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ላይ እሳተፍ ነበር። በበርካታ የሲቪል ማህበራት በአመራር ደረጃ ሠርቻለሁ። ከእነዚህም መካከል በሰብዓዊ መብት ጉባኤ ሰባት ዓመት በሥራ አስፈፃሚነት ሠርቻለሁ።
ከዚያ በኋላ ነው እንግዲህ በፖለቲካው መስክ የተሳተፍኩት። በፖለቲካ ዘርፍ ውስጥ ስሳተፍ ዋናው ትኩረቴ የነበረው በኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲኖር ማድረግ ነው። እኔ ተመረጥኩም፤ አልተመረጥኩም፤ በፖለቲካው ውስጥ ስልጣን ኖረኝም፤ አልኖረኝ የሚያስጨንቀኝ ዜጎች እውነተኛ ዲሞክራሲን ማጣጣም መቻላቸው ነበር። ህዝቡ ራሱ በፖለቲካው ስርዓት ውስጥ እንዲሳተፍ፥ እሱን በሚመለከት በሚደረጉ ውሳኔዎች ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ እንድሆን፤ ለዚያ ደግሞ ይወክሉኛል የሚላቸውን ሰዎች እንዲመርጥና በራሱ ሙሉ ባለስልጣንነት ያልፈላገቸውን መሻር የሚችልበትን መብት እንዲጎናፀፍ ማድረግ ነው።
በፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ ማለት ለእኔ በኑሮ ውስጥ መሳተፍ ማለት ነው። መጀመሪያም ስገባ በተለይ በመሪነት ደረጃ ከሁለት ተርም በላይ ለመሥራት ፍላጎት አልነበረኝም። ለነገሩ በማንኛውም ቦታ ላይ ብዙ ጊዜ መቆየት አስፈላጊ አይደለም። በማንኛውም ምክንያት አንቺ ልትሰጪ የምትችይው ነገር ሊያረጅ ይችላል። በአጠቃላይ ሁልጊዜ መታደስ በጣም ፈተና ነው። ሃሳብ ያላቸውና ሌላ ነገር መጨመር የሚችሉ ወገኖች እንዲተኩ የማድረግ ሥራ መሥራት አለበት። በተለይም በፖለቲካ ውስጥ ያለ ሰው ከአምስት ዓመት በላይ መቆየት አለበት ብዬ አላምንም። ምክንያቱም ጊዜው በጨመረ ቁጥር ህብረተሰቡም የተሻለ ነገር ይፈልጋል፤ የተሻለ ነገር ሊያመጣ የሚችለው ደግሞ አፍላው ወይም አዲሱ ኃይል ነው።
አዲስ ዘመን፡- በቅንጅት ውስጥ የነበርዎ ድርሻ ምን ነበር? የሚጠበቅብኝን ሚና ተጫውቻለሁ ብለውስ ያምናሉ?
ዶክተር ኢንጅነር፡- በቅንጅት ውስጥ የእኔ ድርሻ ምክትል ሊቀመንበርነት ነበር። ስለዚህ እንደማንኛው የፖለቲካ ፓርቲ ዋናው ሊቀመንበር በማይኖርበት ጊዜ ተክቶ መሥራት፤ ፅሕፈት ቤቱን መምራትም የኔ ኃላፊነት ነበር። ከዚህ በተጨማሪም በቅንጅት ውስጥ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ካደረግናቸው ጥረቶች አንዱ ማኑፌስቶ ማዘጋጀት ነበር። በዚህ ማኒፌስቶ ዝግጅት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ነበረኝ። ይህም ያኮራኛል። ሌላው የቅንጅቱን የምርጫ ምልክትም መጀመሪያ ያመጣሁት እኔ ነኝ። ይሄ ደግሞ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ባይ ነኝ። ምክንያቱም በዚያ ወቅት እኛ ሥራ አስፈፃሚው የወሰነው የምርጫ ምልክት ምርጫ ቦርድ ለማስመዝገብ ስንሞክር ሌሎች ወገኖች ቀድመው አስመዝግበውት ኖሮ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ። የነበረን ጊዜ ደግሞ በደቂቃዎች የሚቆጠር ስለነበር ሥራአስፈፃሚው አባል በሙሉ በጣም ተጨነቀ። ይሁንና አስቀድሞም በአዕምሮዬ ሲመላለስ የነበረውን የጣት ምልክት ለምን አንጠቀምም ስል ለዋናው ሊቀመንበር ለኢንጅነር ኃይሉ አጫወትኩት። እሱም ተስማማና አራት ኪሎ ከሚገኙት ፎቶ ቤቶች በአንዱ ገብቼ እጄን ፎቶ አስነሳሁና ወደ ምርጫ ቦርድ ሄድኩ። ምልክቱ ምን እንደሚወክልና ምን ዓላማ እንዳለው ዝርዝር ሃሳብ አስቀድሜ ስለነበረኝ አብራራሁላቸውና ተቀበሉት። ያ ምልክትም እስከመጨረሻው ድረስ የድርጅቱ መለያ ሆኖ የቆየ ከመሆኑም ባሻገር በብዙዎች አዕምሮ ውስጥ የድል ተምሳሌት ሆኖ ነው የኖረው። እንዳልኩሽ የእኔ የሥራ ድርሻ ምክትል ሊቀመንበርነት ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ የሥራ መደብሽ ላይ ያሉትን ሥራ ብቻ እንዳትሠሪ የምትገደጅበት ሁኔታ ያጋጥምሻል። እናም እኔ በፓርቲ ውስጥ በነበረኝ ቆይታ ክፍተቶችን ባየሁባቸው ቦታዎች ሁሉ እየሸፈንኩ ለፓርቲው ተልዕኮ መሳካት የበኩሌን ሚና ስጫወት ነበር። የማረሳው ግን ልክ እንደ ልጅነቴ የተወዳዳሪዎቻችን ፖስተሮች በምላጭ እየቀዳደኩኝ የመለጠፍና የዝግጅት ሥራ ላይ መሳተፌን ነው። ይህንን በማድረጌ ዛሬም ድረስ ያስደስተኛል።
አዲስ ዘመን፡- ህዝቡ ያን ያክል ከተከተላችሁ በኋላ አዲስ አበባን አንረከብም ማለታችሁ ተገቢ ነው ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ኢንጅነር አድማሱ፡- እንዳል ሽው ከፍተኛ የሚባል የህዝብ ድጋፍ ነበረን። ከገመትነው በላይ ነበር ተቀባይነት ያገኘነው። ለዚህ ደግሞ አንደኛው ምክንያት ነበር ብዬ የማምነው ህዝቡ ኢህአዴግ በሚሠራቸው ሥራዎች ደስተኛ ያለመሆኑ ነው። በመሆኑም አማራጭ እስከሚኖረው ድረስ ኢህአዴግን በዓይኔ አልየው ያለው ወገን ይከተለን ነበር። ኢህአዴግ ግን ብዙ ጊዜ አፈፃፀም ችግር እንጂ ፖሊሲዬ እንከን የለውም ይላል። ለእኔ ግን ፖሊሲ የሚባለው በተግባር የሚታየው ነገር ነው። ለነገሩ እሱም የተቀበለው ጥፋት ጭምር ህዝብ አልፈለገውም ነበር። እኛ ደግሞ ይህንን ሁኔታ በመጠቀም አመቺ ሁኔታ ኖሮ ራሳችን ማስተዋወቅ ባንችልም ባሉን ዕድሎች ሁሉ ህዝቡ የተሻለ አማራጭ እንዳለው ለመግለጽ ሞክረናል። ያም ሆኖ ግን የማፈኑ ሁኔታ የበረታ ስለነበር ህዝቡ ጋር ብዙ ልንደርስ አልቻልንም። የደረስንበት ቦታ ሁሉ ግን ህዝቡ እልል ብሎ ነው የተቀበለን። በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ በጣም ብዙ ህዝብ ተሳታፊ እንዲሆን አድርገናል።
ምርጫው ሲካሄድ ግን በገሃድ ከባድ የሚባል መጭበርበር ነበር በኢህአዴግ የተፈፀመብን። እነዚህ ነገሮች እንዲስተካከሉ በተደጋጋሚ ጥያቄ ስናቀርብ ነበር። ለነገሩ የምናቀርባቸው ቅሬታዎች ያለአግባብ አልነበሩም። በተጨባጭ የምናምንባቸውና ያጋጠሙን እንጂ። በዚያን ጊዜ ቅንጅት ከ440 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ተወዳድሯል። ከነበረው ሁኔታ አንፃር በእነዚህ ሁሉ መሳተፍ ቀላል አይደለም። ይህም የሚያሳየው በዚህ ሁሉ አፈና ውስጥ ቅንጅት ጠንካራ እንደነበር ነው። አሁንም ያሉ ተወዳዳሪዎች የሚገጥማቸው አንዱ ፈተና ይሄ ይመስለኛል። የተቻለውን ያህል በብዙ ቦታዎች ላይ መሳተፌ አስፈላጊ ነው። አማራጭ ሆኖ መቅረብ በራሱ ትልቅ ውጤት ነው። አንድ ብቻ አማራጭ ኖሮ መምረጥ ምርጫ አያሰኘውም። ምክንያቱም የመረጥሽው ሁኔታው አስገድዶሽ በመሆኑ ነው። በአማራጭነት ለመቅረብ ደግሞ ብዙ አመቺ ሁኔታዎች በሌሉበት መታገል ድል ነው። ቅንጅትም ያንን ማድረጉ በራሱ ለእኔ ትልቅ ድል ነው። እርግጥ ነው የውጤቱ ጉዳይ የተወሰነው በኢህአዴግ ፈቃድ ነው። ስለዚህ በቅንጅት ምክንያት ህዝብ ያጣው ነገር የለም። ይህንን ጥቅም የነፈገው ቅንጅት ሳይሆን ኢህአዴግ ነው።
አዲስ አበባን ካለመረከባችን ጋር ተያይዞ ያነሳሽውን ጥያቄ በሁለት መልኩ ነው የማየው። በወቅቱ አዲስ አበባን መረከብና ምክር ቤት መግባት የለብንም ያሉ ወገኖች የራሳቸው የሆነ ትክክለኛ ምክንያት ነበራቸው። መግባት አለብን ያሉትም የራሳቸው ምክንያት ይኖራቸዋል። ሁለቱም ግን በመግባትም ሆነ ባለመግባት በሚጠብቁት ነገር ላይ አልስማማም። ለእኔ ግን የሚታየኝና በተጨባጭ የሆነው ነገር ቢገባ የሚያጋጥሙ ችግሮች ነው። እንደ ተፈራውም ከምርጫው ማግስት ጀምሮ አፋኝ ህጎች መውጣት ጀመሩ። ልክ ቅንጅት አሸነፈ ሲባል የገቢ ምንጭ የሆኑ ተቋማት ሁሉ ወደ ፌዴራል መዞር ጀመረ። ከዚያም በላይ የአዲስ አበባ ምክር ቤትም ይሁን የተመራጮች ወገን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቁጥጥር ስር እንዲሆን ነው የተደረገው። ሁለቱ ወገኖች በደንብ ካልተግባቡ በደንብ ህዝብን ለማገልገል በቅንጅት ካልሠሩ የትም አይደርሱም። አዲስ አበባን ብቻውን ብንይዝም የትም አንደርስም ነበር። ደግሞም በምርጫ ጊዜ ብዙ ክፉና ደግ ተባብለናል። ከዚያም በፊት ብዙ ውጣ ውረድ ነበር። በዚያ ውጣ ውረድ ውስጥ ያሉት መቃቃሮችና መሻከሮች እያሉ ሥራ መሥራት አይቻልም ነበር። በዚያ ዓይነት ስሜት ውስጥ ሆኖ አገር ማስተዳደርም መምራትም የማይቻል ነበር። እናም ብንገባ ኖሮ የሚሉ ወገኖች ይሄኛውን ሐቅ ይመስለኛል የዘነጉት። ለእኔ ግን ወለል ብሎ ነው የሚታየኝ። ብዙ መቋሰሎች ባሉበት ቦታ ብሄራዊ እርቅ እየተባለ ቢነሳም ወደ አገር መምራት ሲመጣ ግን የማይቻል ነው የሚሆነው። ሁሉም በየተሰማራበት ዘርፍ በተጨባጭ ሊሳካለት የሚችለው አንዱ ሲገነባ ሌላው እያፈረሰ ሳይሆን በወቅቱ የነበረው የአገሪቱን ህግና ስርዓት ተከትሎ ህዝብን ማገልገል ሲቻል ነው። ያንን ለማድረግ ግን ሁኔታው በዚያ መልኩ የተመቸ አይደለም። እንኳን እንደ እኛ ገና በማደግ ላይ ያለን አገር ህዝቦች አሜሪካ እንኳ ዲሞክራቶችንና ሪፐብሊካኑ ተፋጠው ቁጭ ብለዋል ምንም መሥራት አልቻሉም። በመሆኑም መግባት ነበረባችሁ የሚሉ ወገኖች ይህንን ሐቅ ሊዘነጉት አይገባም ባይ ነኝ። ደግሞ የሆነው ነገር ከፓርቲው አቅም በላይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚሁ ጋር ተያይዞ አብዛኞቹ የቅንጅት አመራሮች ታስረ ዋል፤ እርስዎ እንዴት አመለጡ?
ዶክተር ኢንጅነር አድማሱ፡- እኔ እስር አላጋጠመኝም፤ እንግዲህ የዕድል ነገር ነው የሚሆነው። ምክንያቱም የቅንጅት መሪዎች ፍርድ ቤት እየቀረቡ በሚከራከሩ ጊዜ እዚህ ስለነበርኩ በየቀጠሮው እየተገኘሁ ክርክሩን እከታተል ነበር። በክርክሩ ወቅት እንደማስረጃ ብለው የሚያቀርቡት ፊልም ላይ እኔም እታይ ነበር። ያ ወንጀል ተብሎ በቀረበው መረጃ የሚያስጠይቅ ነገር አልነበረውም። ቢሆንም ግን እኔም በዚያ ማስረጃ ውስጥ ነበርኩበት። እነዚህ የተሰቃዩትና የተንገላቱት ሁሉ ይሄነው የሚባል ወንጀል ካለመሥራታቸውም ባሻገር የሚያስጠይቃቸው ነገር አልነበረም። ነገር ግን የፍርድ ሂደቱ ፍትሐዊ አልነበረም። ያ ግፍ አልደረሰብኝም። ከዚያ አንፃር እኔን ለምን እንደዚያ አላሰቃዩኝም አልልም። ዞሮ ዞሮ ግን የታሰሩት ሰዎች እኔ ካገኘሁት ዕድል ካልሽው የተለየ መሆን አልነበረበትም። ነገር ግን በእኔ ላይ ግፍ ስላልተሠራ ብቻ እውነታውን የተለየ አያደርገውም። እነሱ ላይ የተፈፀመው በአጠቃላይ አግባብም ህጋዊም አልነበረም።
አዲስ ዘመን፡- ከሌሎች የትግል አጋሮችዎ አብረው ችግሩን አለመጋፈ ጥዎ ቁጭት አይፈጥርበዎትም?
ዶክተር ኢንጅነር አድማሱ፡- እሱ ሁልጊዜም ቢሆን የሚቆጨኝ ነገር ነው። በዋናነት ግን የሚቆጨኝ ነገር መሰደዴ ነው። እዚህ ብሆን የምሠራው ነገር ነበር ብዬ ግን አላስብም። ምክንያቱም ለመሥራት የሚያስችል አመቺ ነገር አልነበረም። እዚያ ሆኜ እዚህ አገር እንዳሉት ሰዎች መሳተፍም እንደማልችል ይታወቃል። እዚህ መሆኔ ጠዋት ማታ በማህበራዊ ህይወት የመሳተፍ ዕድል ይኖረኛል። ግን ዝም ብሎ ከመቆየት ባለፈ ፈቅ የሚልና የምሠራው ነገር ይኖራል ብዬ አላምንም። እንግዲህ በውጭ በእኔ ዕድሜ ደረጃ ስትቆይ ክፉም ይሁን ደግ እዚሁ ሌላው ሰው እንደሆነው መሆንን ነው የምትፈልጊው። በሌላ በኩል ደግሞ ለእኔ ባይሆንም ለቤተሰቦቼ እዚህ ብቆይ የማያገኙትን ዕድል አግኝተዋል። በመጀመሪያ ደረጃ አንድ ላይ መሆናችን፤ ምንም ዓይነት ስጋት ሳይኖርና ለአንድ ቀንም ሳንነጣጠል መቆየት ትልቅ ነገር ነው። በተለይም ደግሞ የሄድንበት አገር ደግሞ ለልጆቼ በህልሜም በውኔም ያላሰብኩትን መልካም አጋጣሚ ሆኖ ጥሩ ደረጃ እየደረሱ ነው። እንዳልሽው ሌሎች ባልደረቦቼ ግን ታፍነውና ቤታቸውና ኑሯቸው እስር ቤት ሆኖ ነው የቆዩት። ከዋና እስር ቤት በተጨማሪ ሊሠሩ ያሰቡትን እንዳይሠሩ ተቀፍድደው ተይዘው መከራቸውን እያዩ ነው የኖሩት። በዚህ ምክንያት እኔ ያለኝን ዓይነት እዚህ ሆኜ ላደርግ ይገባል የሚል ቁጭት አይኖራቸውም። ይህም ማለት ማስተማር ላይ አለመቆየቴ በጣም ይቆጨኛል። ይህንን መቀልበስ ይቻል ነበር ወይ? ብለሽ ከጠየቅሽ አይቻልም ነው መልሴ። ምክንያቱም ጉዳዩ በእኔ እጅ አልነበረምና ነው። እኔ አማራጭ ኖሮኝ እያለ አስቤ ያደረጉት የወሰንኩት ጉዳይ ባለመሆኑ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በመጽሐፍዎ የአብ ላጫ ድምፅ ስርዓት ለኢትዮጵያ እንደ ማያስፈልጋት ገልጸዋል። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ሌላ የምርጫ ስርዓት ማምጣት ይቻላል ወይ?
ዶክተር ኢንጅነር አድማሱ፡- አሁን ባለው ሁኔታ አሁን ካለው ሌላ አያስፈልጋትም። ነገር ግን ወደፊት ለሚኖረው ምርጫ ግን ስርዓቱ መቀየር አለበት። በእኔ እምነት የአብላጫ ድምፅ ስርዓት የሚበጅ አይደለም። በዚህ ስርዓት የሚጠቀሙ አገሮች ሁሉ ሁልጊዜም ውስጣቸው ቁስል አለው። እናም ለኢትዮጵያ ትክክለኛው የምርጫ ስርዓት የምለው የተመጣጠነ የምርጫ ስርዓት ነው። ይሄ ደግሞ ዝም ብሎ የተፈጠረ ሳይሆን የአንዱ ድምፅና የሌላው ድምፅ እኩል ነው ከተባለ የአንቺ ድምፅ የእኔ ድምፅ እኩል ድምፅ ነው። የእኔ የሁለት ድምፅ ከሆነ የአንቺ የግማሽ ሰው ድምፅ ከሆነ (ለነገሩ ግማሽ ሰው የሚባል የለም) ይህ አስተሰሰብ ፍትሐዊ አይደለም። የተመጣጠነ ድምፅ ሲባል ለምሳሌ ሁለት ሺ ሰው ባለበት የምርጫ ጣቢያ ሁለት ተወካይ ቢኖራቸው አንድ ሺ ሰዎች ባሉበት ደግሞ አንድ ተወካይ ብቻ ይሆናል ማለት ነው። ይህ በመሆኑ የያዝነው ስርዓት ትክክለኛ ስርዓት አይደለም። የሚበጅም አይደለም። ይህ ማለት ግን ጨርሶ የአብላጫ ስርዓት አይጠቅምም ማለት አይደለም። እስኪቀየር ድረስ ልንጠቀምበት እንችላለን። እስከአሁን ባለው ሂደት ግን ከሁለቱም ውጪ የሆነ ሂደት ነበር ስንከተል የነበረው። ስለዚህ አሁን ያለውን ህግ ተጠቅመን ምርጫ ይካሄድ። ከውጤቱ በኋላ ግን መክረው፤ ዘክረው የተሻለውን ስርዓት ማበጀት ይገባቸዋል።
በአጠቃላይ በአገራችን ውስጥ የላቀ ዲሞክ ራሲ ስርዓት እንዲገነባ እንፈልጋለን። ጥራት ያለው የዲሞክራሲ ስርዓት መዳረሻው ምንድን ነው የሚለውን ነገር ከአሁኑ ብናውቀው ጥሩ ይሆናል። ምክንያቱም ባገኘነው ዕድል ሁሉ ወደዚያ አቅጣጫ እንሄዳለን ማለት ነው። ልክ አንድ ሃይማኖተኛ ፅድቅን አስቦ በምድር ላይ እያለ መልካም መልካም ነገሮችን እንደሚያደርገው ሁሉ አገርም ወደ ትክክለኛው የፖለቲካ ስርዓት እስከምትገባ ድረስ ጥርጊያ መንገዶችን ሁሉ ማስተካከል ይገባታል ባይ ነኝ። መዳረሻችንን ካላወቅን ግን ዝም ብለን መኳተን ነው የሚሆንብን። በነገራችን ላይ ትክክለኛውን የዲሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት የፖለቲካ ተቋማት ብቻ መስፋፋት አለባቸው እያልኩ አይደለም። ይህ እንዲሆን ከተፈለገ የፓርቲ ውግንና የሌላቸውን የሲቪክ ማህበራትን ማጠናከር ይገባናል። ለህዝብ የሚወግን ተቋም የሚፈጠረው ሲቪክ ማህበራት ሲደራጁ ነው። ብዙ ምሁራንን ማሳተፍ የሚችሉት ዲሞክራሲ እንዲዳብር የሚያደርጉት ሲቪክ ማህበራት ናቸው። እኔም ከዚህ በኋላ በፖለቲካ ፓርቲ ሳይሆን በሲቪክ ማህበራት ላይ ንቁ ተሳትፎ አደርጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- እንደ አገር ብዙ እሴቶቻችን የፀብና የመለየያት ምክን ያት በሆነበት ወቅት እርሶ «መግባባት» በሚል መጽሐፍ አሳትመዋል፤ እንዳው ለመሆኑ ይህንን መጽሐፍ ለመፃፍ ያነሳሳዎት አብይ ምክንያት ምንድን ነው? በዚሁ አጋጣሚም የመጽሐፉንስ ጥቅል ፍሬ ነገር ቢገልጹልን?
ዶክተር ኢንጅነር አድማሱ፡- እንግ ዲህ መግባባት የሚለው ቃል «consensus» ከሚለው የእንግሊዝኛ ቃል የተወሰደ ነው። የዚህ መጽሐፍ ዓላማ አንደኛው ዜጎች ሁሉ እኩል የፖለቲካ መብታቸውን ማረጋገጥ ነው። ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ በፖለቲካ ጉዳይ ማንም ከማንም ጋር መጣላት እንደሌለበት ያሳያል። ምክንያቱም አስቀድሜ እንዳልኩት በጋራ ጉዳይ ላይ ለመወሰን የሚመለከታቸው ሁሉ መሳተፍ ይገባቸዋል። የተገለለ ካለ ቁስል አለ፤ ስለዚህ ሁሉን አካታች መሆን አለበት። ሌላው ከዚሁ ከመግባባት ዲሞክራሲ ጋር በተያያዘ ሥራ አስፈፃሚውን የመንግሥት አካል ስናየው በአብላጫ የምርጫ ስርዓት 50 በመቶና አንድ ተጨማሪ ድምፅ ካገኙ ሙሉውን ስልጣን ይይዛሉ። 49 በመቶ ድምፅ ያገኘው ባዶውን ይቀራል። ያኛው አካል ግን ከሚገባው በላይ መቶ በመቶውን ይወስዳል። ይህ ሂደት ፍትሐዊ አይደለም። ለዚህም ነው የተመጣጠነ ስርዓት መዘርጋት አለበት የምንለው። የኢትዮጵያ ህዝብ ለፖለቲከኞች የሰጠው አደራ እኔ ከጎረቤቴ ጋር ተባብሬ፥ ተስማምቼ አቻችለን ሁሉም እንደፈለገው ሳይሆን ለሁላችን እንዲመች አድርገን አቀራርበን እንኖራለን።
በሌላ በኩል በእኛ አገር ርዕዩተ የሚባለው ነገር ልዩነት የለውም ባይ ነኝ። ያለው ልዩነት የአደረጃጀት ነው። ስለዚህ የሚያግባቡንና የሚያስማሙን ነገሮች በርካቶች በመሆናቸው በአጋጣሚ የተለያየ ፓርቲ አባል ብንሆንም በሚያስማሙን ጉዳዮች ላይ መክረን ወደ አንድ መምጣት እንችላለን የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ። ይህም ለመግባባት ዲሞክራሲ በር ይከፍታል። ይህም ሲባል ግን በመግባባት ዲሞክራሲ ሁሉም እጁን አንድ ላይ ያወጣል ማለት አይደለም። ለምሳሌ በአካሄድና በመስመር ልንመሳሰል እንችላለን። በአጠቃላይ በመግባባት ዲሞክራሲ በምንመርጣቸው ነገሮች አንዱ ወዳቂ አንዱ ተነሺ የሚሆንበት ሁኔታ የለም። እንደዚህ ዓይነት ድምፅ አሰጣጥ ሁልጊዜ ወደ መሃል ያመጣል፣ ወደ መግባባት ያመጣል። ይህ ደግሞ ለህዝብ ጥቅም ሲባል ሁሉም የግሉን ጥቅም በመተው ወደ አንድነትና ወደ መግባባት የሚመጣበትን ዕድል ይፈጥራል። ደግሞም በጋራ ጉዳይ ላይ የእኔ ብቻ የሚባል ነገር የለውም። ስለዚህ በምርጫ ስርዓቱ ላይ የመግባባት ዲሞክራሲ የተመጣጠነ የምርጫ ውክልናን ያመለክታል። እናም በጥቅሉ መጽሐፌን ለመፃፍ የተነሳሁት ከእዚህ እሳቤ ነው። የፅሑፉም አጠቃላይ ዓውድ ይህንን ጉዳይ ይዳስሳል።
አዲስ ዘመን፡- ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ምክንያት የሆንዎ የዶክተር አብይ ጥሪ እንደሆነ ነግረውናል። በአገር ውስጥ በነበርዎ የአንድ ዓመት ቆይታ የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት አዩት? በዶክተር አብይ የሚመራውስ መንግሥት ምን መልካም እና ምን ህፀፆች አሉበት ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ኢንጅነር አድማሱ፡- እንደእኔ እምነት እነ ዶክተር አብይ፥ ኦቦ ለማ፥ እነ ገዱና ሌሎች ቅን አሳቢዎች በመጀመሪያ ደረጃ በአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ ያለውን ችግር መረዳታቸው በራሱ የሚያስመሰግናቸው ነው። ወቅታዊውን ሁኔታ መመዘኑን እንደቀላል ነገር ማየት ስለማይገባ ማለቴ ነው። ከዚያ በመቀጠልም ከችግሩ ለመውጣት የሚደረገው እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው። ይህንን ለውጥ ለማምጣት የተጓዙበት መንገድ ሰላማዊ መሆኑም ሌላ ሊደነቁበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ያለ ጠበንጃና ያለ ደም መፋሰስ ለውጥ ማምጣታቸው ለሰላም ያላቸውን ፍላጎትም ያሳያል። ምክንያቱም ይሄ ይሆናል ብሎ ያሰበውም አልነበረምና ነው።ይህንን ማድረግ መቻላቸው ለእኔ እንደ ህልም ነው የሚታየኝ። አካላዊ ግጭት ሳይፈጠር ይህንን ለውጥ ከውጭ የሆነ አካል ሊያመጣው አይችልም ነበር። ምንአልባት አሁን ባለው ሁኔታ ቀድሞ የነበርንበትን ነገር ረስተነው ሊሆን ይችል ይሆናል። ግን እዚህ ለመድረስ ምን ያህል ዋጋ እንደተከፈለበት መረዳትና ማስታወስ ይገባናል ባይ ነኝ።
የእኔ የዲሞክራሲ መነፅር ሩቅ ነው የሚያየው። በቅርብም ይሳካል ብዬ አላምንም። ከእነዚህም መካከል የሲቪል መብቶች በአሁኑ ወቅት በጣም ተሻሽሏል። ችግሩን ሙሉ ለሙሉ ማስወገዱ ላይ ግን ገና ብዙ ዓመታት ይወስዳል። ሁለተኛው የፖለቲካዊ መብቶች መከበር ሲሆን ምናልባት ዋናው መለኪያው ምርጫ ቢሆንም በመሪዎች ደረጃ በጎ ፈቃድ አለ። በተግባር ተችሏል የሚለው ነገር ሌላ ጥያቄ ነው። ደግሞም ታች ያለው አካል ሊያስበው ይገባል። በተለይ ደግሞ «ይህ መሬት የእኛ ነው» እየተባለ እንቅስቃሴ የተገደበበት ሁኔታ ሊፈተሽ ይገባል ባይ ነኝ። የመንግሥት ዱላ፥ የመንግሥት ጥይት፥ የመንግሥት እስር ቤት የሚባሉ ነገሮች በአብዛኛው ቀርተዋል ማለት እችላለሁ። ይህም ሆኖ ፓርቲዎች እንደልባቸው መንቀሳቀስ ችለዋል ማለት አይደለም፤ ገና ብዙ ትግል ይጠይቃል። ይህንንም ስል ከላይ ካለው አመራር ይህንን አድረጉ ተብሎ ነው ብዬ አላምንም። ያው ተሸክመን የመጣነው ኮተት እንዲሁ በቀላሉ የሚለቀን ባለመሆኑ ነው። ሌላው ፍትሐዊ የምርጫ ስርዓትን ከመዘርጋት አኳያ ደግሞ በዝግጅት ሲታይ መድረሻው ገና የሚታይ ቢሆንም ህግ ለማሻሻል መሞከሩ፥ ቦርዱን እንደገና ለማቋቋም መሞከሩም የሚበረታታ ነው። የምርጫ ስርዓቱ ባይቀየርም አሁን ባለው ህግና ስርዓት ተጠቅሞ ማካሄዱ ጥቅም አለው። እዚህ ጋር ሁሉም ከልቡ ሊነሳሳ ይገባል። ምክንያቱም የዚህ ምርጫ መካሄድ በራሱ ሰላማችንን ለማስጠበቅ ያግዘናል። ተፎካካሪ ፓርቲዎች መድረኩ የጨዋ ዎች እንዲሆን ትግል ማድረግ አለባቸው።
መንግሥት ሰላማችንን የሚያውኩ አሉባል ታዎችና ሐሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካላትን መቆጣጠር ይገባዋል። እኛም ብንሆን የመንግሥትን ያህል ኃላፊነት ባንወስድም ባለንበት አካባቢ ከአፋችን በሚወጣውና በምናደርገው ነገር መጠንቀቅ አለብን ብዬ አምናለሁ። ይህንን ስናደርግ አገራችንን እንጠቅማለን፤ መጪው ትውልድ የሚኮራብን ዜጎች እንሆናለን። ሌላው የተመጣጠነ የጎንዮሽ ቁጥጥር ስርዓት ነው፤ የሦስት መንግሥት አካላት የሥራ ክፍፍል ስርዓት ሊበጅለት ይገባል። በአጠቃላይ አሁን ያለው ለውጥ ህልም ሆኖ እንዳይጠፋ ሁሉም መታገል አለበት። አሁን ያለው ሰላም በወሬኛ እንዳይፈታ መጠንቀቅ ይገባናል። በተጨማሪም የአስተዳደር አቅም ብቃትን ማሻሻልም ከመንግሥት የሚጠበቅ ነው። ይህንን ማድረግ በራሱ ወስላቶች አገርን ለማተራመስ በሚፈጥሩት ችግር እንዳንታወክ መሰረት ይጥልልናል። መፈናቀሉንና ስደቱን ለማስቀረት መንግሥት የህግ ማስከበር ሥራውን ማጠናከር አለበት። የሰብዓዊ መብት ጋር ሳይጋጭ ህግ ማስከበር ሥራ እንዴት መሠራት አለበት የሚለው ነገር አሳሳቢ ነው። ሌላው የፆታ እኩልነት መከበር ጉዳይ በከፍተኛ አደረጃጀት ላይ በእኩል ደረጃ መሳተፋቸው የሚያስደስት ቢሆንም በቀጣይነት ባለው መልኩ ስርዓት ተበጅቶለት ዋስትና የሚሰጥ አካሄድ መከተል ይገባል። ሰዎች ቢፈልጉም፤ ባይፈልጉም ስርዓቱ የሚቀጥሉበት ሁኔታ መበጀት አለበት። የሚቀጥለው ምርጫ ላይ ሁሉም ፓርቲ የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ እንዲችሉ ማሳሰብ እወዳለው።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ ከዚህ በኋላ በሲቪክ ማህበራት እንጂ በፖለቲካው ዘርፍ እንደማይሳተፉ ገልጸዋል፤ እስቲ ለሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ማስተካከል ይገባቸዋል የሚሉት ነገር የለም?
ዶክተር ኢንጅነር አድማሱ፡- እኔ ለፓርቲዎች የማስተላልፈው መልዕክት የለም። አግባብነት ያለው የመምከር የመመካከር የመወሰን ስርዓት አላቸው። ነገር ግን ካለፍኩበት ሁኔታ አንፃርና በምርምር ላይ ተሳትፌ ካዳበርኩት ልምድ በመነሳት ከአሁኑ ጀምሮ በየምርጫ ክልሉ የሚወዳደሩትን ሰዎች የመለየትና እነሱንም ለህዝቡ ይፋ ማድረግ ይገባቸዋል። ምክንያቱም በእኛ አገር ፖለቲካ ትልቁ ነገር ጨዋነት ነው። አደራ መሸከም የሚችልና የማይችለውን አንጥረው ማውጣት አለባቸው። ፖለቲካ ቆሻሸ ነው ብለው የተሸሸጉትንም ሳይቀር ከጓዳቸው እንዲወጡ ማድረግ ይገባቸዋል። ተፎካካሪ ፓርቲዎች የውድድር መድረኩ የጨዋዎች እንዲሆን ትግል ማድረግ አለባቸው። ጨዋ ሰው መረጃ ላይኖረው ይችላል፤ ነገር ግን ህዝብን በሚጎዳ ነገር ላይ አይሳተፍም፤ ለራሱ ጥቅም ብሎ አደራውን አይበላም። ሃሳቦች የሚወሰኑት በዓይነት ሚዛን ውስጥ የጨዋና የባለጌን ድርሻ ማጤን ይገባል። ምክንያቱም እንደአለመታደል ሆኖ ብዙ የተማረ ሰው የለንም፤ ስለዚህ ብርቱ ተፎካከሪ መሆን የሚችሉት ጨዋና የአገር ፍቅር ያላቸውን መምረጥ ሲችሉ ነው። እርግጥ አሁን ባለው ሁኔታ ለምሳሌ የእኔን እናት ብትጠይቂያት አብይን ክፉ እንዳይነካባት ትጸልያለች። ሌላ ጉዳይ ኖሯት አይደለም፤ ልጆቿን ዳግም በህይወት እያለች ስላሳያት እንጂ። ሌላውም እንደዚሁ የራሱ መልካም እሴት አለው። በመሆኑም በተቻለ መጠን የአብዛኛውን መራጭ ስሜት አጢነው አቀራረባቸውን ሊያስተካክሉ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎም እንዳነ ሱት አሁን ባለው ሁኔታ አብዛኛው የአገሪቱ ህዝብ ዶክተር አብይን ከልቡ የሚወድና የሚያምን ነው፤ ይህ በሆ ነበት ሁኔታ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሊገጥማቸው የሚችል ፈተና ይኖ ራል ብለው ያምናሉ? ሊኖራቸው የሚችለውስ የቤት ሥራ ምንድን ነው?
ዶክተር ኢንጅነር አድማሱ፡- በነገራ ችን ላይ ህዝቡ የሚወደው ኢህአዴግን ሳይሆን ዶክተር አብይን ነው። ስለዚህ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ኢህአዴግን መርታት የሚችሉበት ዕድል አለ ማለት ነው። ህዝቡ ጥንቁቅ ስለሆነ ነው እኮ የተሠራው በጎ ነገር ሁሉ በኢህአዴግ ሳይሆን በዶክተር አብይ መሆኑን ነው ደጋግሞ ሲገልጽ የነበረው። ይህች ጉዳይ አስፈላጊ ትመስለኛለች። ኢህአዴግም እንበለው ሌላው በዚያ ባህል በሚኖሩ ሰዎች ጋር መግባባት መቻል አለበት። ያንን ለማድረግ ደግሞ መንገዱን ጠንቅቆ ማወቅ ይገባዋል። ዶክተር አብይም ቢሆኑ ፓርቲያቸው እንዲመረጥ ብዙ ፈታና አለባቸው። ምክንያቱም ይሄ ለውጥ ሰው ነጥሏል። ከልባቸው ህዝብ ለማገልገል የሚፈልጉ ሰዎችን መፍጠር መቻል አለባቸው። ዞሮ ዞሮ በፓርቲ ደረጃ ያልተሞከረው ጨዋ ሰዎች መልምለው ካልያዙ ዶክተር አብይም ቢሆኑ ማሸነፍ አይችሉም። እርግጥ ከዶክተር አብይ ጋር ግብ ግብ ከመግባታቸው በፊት ራሳቸውን ማሸነፍ እና ውስጣቸውን እየፈተሹ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚመጥን ሥራ ሊሠሩ ይገባል። አደራዬ ይሄ ነው። በግሌ ግን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታን በተመለከተ ስልጠና መስጠት እፈልጋለሁ። ለምሳሌ በቅርቡ በውሃ ጉዳይ ላይ ኢዜማ ጥሪ አቅርቦልኝ ፅሑፍ አቅርቤለሁ። ስለዚህ ማንም ማንም ይሁን ለህዝብ የሚጠቅም ነገር እንዲሠሩ የበኩሌ ድጋፍ አደርጋለሁ። ይህንን የምለው ከህዝብ ወገን ሆኜ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ ባለቤትዎ ዶክተር ሙሉዓለም ፖለቲከኛ ነበሩ። አሁን በምን ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ለሚያውቋቸውና ለሚያደንቋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ቢገልጹልንና ብንሰ ነባበት? ይችላሉ?
ዶክተር ኢንጅነር አድማሱ፡- ዶክተር ሙሉዓለም በአሁኑ ወቅት ሲዊድን ውስጥ የራሷን ክኒሊክ ከፍታ የተሳካ ሥራ እየሠራች ነው የምትገኘው። ልጆቼም ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የእኔን ብቻ ሳይሆን የአገራቸውን ስም በማስጠራት ላይ ናቸው። ስለዚህ በቤተሰቤ ሁኔታ ደስተኛ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ኢንጅነር አድማሱ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 11/2011
ማህሌት አብዱል